በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ውስጥ አንድነታችሁን ጠብቁ
“ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፣ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ . . . ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።”—ፊልጵስዩስ 1:27
1. በይሖዋ ምሥክሮችና በዓለም መካከል ምን ልዩነት አለ?
የምንኖረው “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ ነው። ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ እንዳለን ምንም አያጠያይቅም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ያልተረጋጋ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ባለበት በዚህ የ“ፍጻሜ ዘመን” የይሖዋ ምሥክሮች በመካከላቸው ያለው ሰላምና አንድነት በጣም ለየት ብለው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። (ዳንኤል 12:4) ይሁን እንጂ የዓለም አቀፉ የይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ አባል የሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ ይህን አንድነት ለመጠበቅ ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል።
2. ጳውሎስ አንድነትን በተመለከተ ምን ብሏል? የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ አንድነታቸውን እንዲጠብቁ መሰል ክርስቲያኖችን አጥብቆ መክሯቸዋል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፣ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፣ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፣ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፣ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፣ ይህም ከእግዚአብሔር ነው።” (ፊልጵስዩስ 1:27, 28) የጳውሎስ ቃላት ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን አንድ ላይ መሥራት እንዳለብን በግልጽ ያሳያሉ። እንግዲያው በዚህ ፈታኝ ዘመን ውስጥ ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ጠብቀን ለመኖር እንድንችል የሚረዳን ነገር ምንድን ነው?
ለመለኮታዊ ፈቃድ ተገዙ
3. የመጀመሪያዎቹ ያልተገረዙ አሕዛብ የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑት መቼና እንዴት ነው?
3 አንድነታችንን ለመጠበቅ የሚረዳን አንዱ መንገድ ዘወትር ለመለኮታዊ ፈቃድ ተገዢ መሆን ነው። ይህ አስተሳሰባችንን እንድናስተካክል ሊጠይቅብን ይችላል። የጥንቶቹን የኢየሱስ ክርስቶስ አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት ተመልከት። ሐዋርያው ጴጥሮስ በ36 እዘአ ለመጀመሪያ ጊዜ ላልተገረዙ አሕዛብ ሲሰብክ አምላክ በእነዚህ የሌሎች ብሔራት ሰዎች ላይ ቅዱስ መንፈሱን አፈሰሰና ተጠመቁ። (ሥራ ምዕራፍ 10) እስከዚያ ጊዜ ድረስ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች የነበሩት አይሁዳውያን፣ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎችና ሳምራውያን ብቻ ነበሩ።—ሥራ 8:4-8, 26-38
4. ጴጥሮስ ቆርኔሌዎስን በተመለከተ የተፈጸመውን ሁኔታ ከገለጸ በኋላ ምን አለ? ይህስ አይሁዳውያን በሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ምን ፈተና አስከትሎ ነበር?
4 ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የነበሩ ሌሎች ወንድሞች ቆርኔሌዎስና ሌሎች አሕዛብ እንደተለወጡ ሲሰሙ የጴጥሮስን ሪፖርት ለመስማት ጓጉተው ነበር። ሐዋርያው ቆርኔሌዎስንና ሌሎች አማኞች የሆኑ አሕዛብን በተመለከተ የተፈጸመውን ሁኔታ ከገለጸ በኋላ ንግግሩን በሚከተሉት ቃላት ደመደመ፦ “እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመ[ን]ነው ለእኛ [ለአይሁዶች] ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ [አማኞች ለሆኑት አሕዛብ] ከሰጠ፣ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?” (ሥራ 11:1-17) ይህ አይሁዳውያን ለሆኑት የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ፈተና ሆኖባቸው ነበር። ለአምላክ ፈቃድ በመገዛት አማኞች የሆኑትን አሕዛብ መሰል የይሖዋ አምላኪዎች አድርገው ይቀበሏቸዋል? ወይስ የይሖዋ ምድራዊ አገልጋዮች አንድነት አደጋ ላይ ይወድቃል?
5. አምላክ አሕዛብ ንስሐ እንዲገቡ በመፍቀዱ ሐዋርያትና ሌሎች ወንድሞች ምን ተሰማቸው? ከዚህ ዝንባሌ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
5 ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “[ሐዋርያትና ሌሎቹ ወንድሞች] ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና፦ እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።” (ሥራ 11:18) ይህ ዝንባሌ የኢየሱስ ተከታዮች አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይና እንዲጠናከር አድርጓል። የስብከቱ ሥራ በአሕዛብ ወይም በሌሎች ብሔራት ሰዎች መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋፋ፤ ይሖዋ ሥራውን ባርኮት ነበር። እኛም አንድ አዲስ ጉባኤ ሲቋቋም ወይም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሪነት አንድ ቲኦክራሲያዊ ማስተካከያ በሚደረግበት ጊዜ ትብብራችን ሲጠየቅ መስማማት ይኖርብናል። በሙሉ ልባችን ትብብር ማሳየታችን ይሖዋን ያስደስተዋል፤ በዚህ መጨረሻ ቀንም አንድነታችንን መጠበቅ እንድንችል ይረዳናል።
እውነትን አጥብቃችሁ ያዙ
6. እውነት በይሖዋ አምላኪዎች አንድነት ላይ ምን ተፅእኖ አለው?
6 የይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ አባሎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ‘ከይሖዋ የተማርን’ በመሆናችንና እሱ የገለጠውን እውነት አጥብቀን በመያዛችን አንድነታችንን እንጠብቃለን። (ዮሐንስ 6:45፤ መዝሙር 43:3) ትምህርቶቻችን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ሁላችንም የምንናገረው አንድ ነው። ይሖዋ በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል የሚሰጠንን መንፈሳዊ ምግብ በደስታ እንቀበላለን። (ማቴዎስ 24:45-47) ይህ አንድ ወጥ የሆነ ትምህርት በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድነታችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል።
7. በግለሰብ ደረጃ አንድን ነጥብ ለመረዳት ብንቸገር ምን ማድረግ ይኖርብናል? ምንስ ማድረግ የለብንም?
7 ሆኖም በግለሰብ ደረጃ አንድን የሆነ ትምህርት ለመረዳት ወይም ለመቀበል ብንቸገርስ? ጥበብ ለማግኘት መጸለይና ቅዱሳን ጽሑፎችንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን መመርመር ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:4, 5፤ ያዕቆብ 1:5-8) ሽማግሌ ማማከርም ሊረዳ ይችላል። ይህንንም ካደረግን በኋላ ነጥቡ ግልጽ ሊሆንልን ካልቻለ ጉዳዩን መተዉ ይመረጣል። ምናልባት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ይወጣና እውቀታችን ይሰፋ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች የእኛን የተለየ አመለካከት እንዲቀበሉ ለማሳመን መጣር ስህተት ነው። ይህ አንድነትን የሚጠብቅ ሳይሆን መከፋፈልን የሚዘራ ነው። ‘በእውነት መንገድ በመሄድ’ ሌሎችን ማበረታታቱ ምንኛ የተሻለ ነው!—3 ዮሐንስ 4
8. ለእውነት ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከት ምንድን ነው?
8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ በትክክል የምታወቀውን ያህል በትክክል አውቃለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:12 አዓት) ምንም እንኳ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉንም ዝርዝር ጉዳዮች ተረድተው የነበረ ባይሆንም አንድነታቸውን ጠብቀው ኖረዋል። እኛ በአሁኑ ጊዜ ስለ ይሖዋ ዓላማና ስለ እውነት ቃሉ ይበልጥ ግልጽ የሆነ እውቀት አለን። እንግዲያው ‘በታማኙ ባሪያ’ በኩል ላገኘነው እውነት አመስጋኞች እንሁን። በተጨማሪም ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ስለሚመራን አመስጋኞች መሆን አለብን። ሁልጊዜ እኩል የሆነ እውቀት ባይኖረንም እንኳ በመንፈሳዊ አልተራብንም ወይም አልተጠማንም። ከዚህ ይልቅ እረኛችን ይሖዋ አንድነታችን እንዲጠበቅ ከማድረጉም በላይ ጥሩ እንክብካቤ አድርጎልናል።—መዝሙር 23:1-3
አንደበታችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት!
9. አንደበታችንን አንድነትን ሊያጠናክር በሚችል መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
9 አንደበትን ሌሎችን ለማበረታታት መጠቀም አንድነትና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲኖር ለማድረግ የሚቻልበት አንዱ ዐቢይ መንገድ ነው። በግርዘት ጉዳይ ላይ የተነሳውን ጥያቄ የፈታው ከመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል የተላከው ደብዳቤ የማበረታቻ ምንጭ ሆኖ ነበር። በአንጾኪያ የነበሩት አሕዛብ ደቀ መዛሙርት ደብዳቤውን ካነበቡ በኋላ “በማበረታቻው ተደሰቱ። [አዓት]” ደብዳቤውን ይዘው እንዲሄዱ ከኢየሩሳሌም የተላኩት ይሁዳና ሲላስ “ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው [“አበረታትተው፣” አዓት] አጸኑአቸው።” የጳውሎስና የበርናባስ መኖርም በአንጾኪያ የነበሩትን መሰል አማኞች እንዳበረታታቸውና እንዳጠነከራቸው ጥርጥር የለውም። (ሥራ 15:1-3, 23-32) እኛም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት አንድ ላይ በምንሆንበት ጊዜ ልክ እንደዚሁ ማድረግ እንችላለን፤ በስብሰባው ላይ በመገኘትና የሚያንጹ ሐሳቦችን በመስጠት ‘እርስ በርሳችን ልንበረታታ’ እንችላለን።—ዕብራውያን 10:24, 25
10. ተሳዳቢ የሆነ የጉባኤ አባል ቢኖር አንድነት ለመጠበቅ ሲባል ምን ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል?
10 ሆኖም አንደበታችንን በተሳሳተ መንገድ ከተጠቀምንበት አንድነታችንን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። “አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል” በማለት ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ጽፏል። “እነሆ፣ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።” (ያዕቆብ 3:5) ይሖዋ ጠብ የሚዘሩ ሰዎችን ይጠላል። (ምሳሌ 6:16-19) እንዲህ ዓይነቱ ወሬ መከፋፈል ሊፈጥር ይችላል። እንግዲያው በአንድ ሰው ላይ የስድብ መዓት ቢከመር ወይም ደግሞ ሰውየውን የሚያንቋሽሹ ቃላት ቢሰነዘሩ ምን ይደረጋል? ሽማግሌዎቹ ኃጢአተኛውን ለመርዳት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ተሳዳቢው ንስሐ የማይገባ ከሆነ የጉባኤው ሰላም፣ ሥርዓትና አንድነት ሊጠበቅ እንዲችል መወገድ ይኖርበታል። ጳውሎስ “ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ . . . ተሳዳቢ . . . ቢሆን ከእርሱ ጋር መብል እንኳን አትብሉ” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 5:11
11. የተናገርነው ነገር በእኛና በአንድ መሰል አማኝ መካከል አለመግባባት ፈጥሮ ከሆነ ትሕትና በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ለአንደበታችን ልጓም ማበጀታችን አንድነታችንን ለመጠበቅ እንድንችል ይረዳናል። (ያዕቆብ 3:10-18) ይሁን እንጂ አንድ የተናገርነው ነገር በእኛና በአንድ መሰል ክርስቲያን መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ እንበል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ይቅርታ በመጠየቅ ቅድሚያውን ወስደን ከወንድማችን ጋር ሰላም መፍጠር አይገባንምን? (ማቴዎስ 5:23, 24) ይህ ትሕትናን ወይም ራስን ዝቅ የማድረግን ባሕርይ የሚጠይቅ መሆኑ አይካድም፤ ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (1 ጴጥሮስ 5:5) ትሕትና ስህተታችንን አምነን እንድንቀበልና ተገቢውን ይቅርታ ጠይቀን ከወንድሞቻችን ጋር ‘ሰላምን እንድንከተል’ ይገፋፋናል። ይህ የይሖዋን ቤተሰብ አንድነት ለመጠበቅ ይረዳል።—1 ጴጥሮስ 3:10, 11
12. አንደበታችንን የይሖዋን ሕዝብ አንድነት ለመጠበቅና ለማጠንከር ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
12 አንደበታችንን በአግባቡ የምንጠቀምበት ከሆነ የቤተሰብነት መንፈስ በይሖዋ ድርጅት አባላት መካከል እንዲስፋፋ ማድረግ እንችላለን። ጳውሎስ እንደዚህ አድርጎ ስለነበር የተሰሎንቄን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል፦ “ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፣ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና።” (1 ተሰሎንቄ 2:11, 12) ጳውሎስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ በመተው መሰል ክርስቲያኖችን “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” በማለት አጥብቆ ሊመክራቸው ችሏል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት) አንደበታችንን ለማጽናናት፣ ለማበረታታትና ሌሎችን ለማነጽ በመጠቀም ምን ያህል መልካም ነገር ማከናወን እንደምንችል አስብ። አዎን፣ “ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!” (ምሳሌ 15:23) በተጨማሪም በዚህ መንገድ መናገራችን የይሖዋ ሕዝብ አንድነት እንዲጠበቅና እንዲጠናከር ይረዳል።
ይቅር ባዮች ሁኑ!
13. ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
13 ክርስቲያናዊ አንድነታችን እንዲጠበቅ ከተፈለገ አንድን ይቅርታ የጠየቀ በደለኛ ይቅር ማለት በጣም አስፈላጊ ነው። ይቅር ማለት ያለብን ምን ያህል ጊዜ ነው? ኢየሱስ ጴጥሮስን “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም” ብሎታል። (ማቴዎስ 18:22) ይቅር የማንል ከሆነ ራሳችንን እንጎዳለን። እንዴት? ጥላቻና ቂም መያዝ የአእምሮ ሰላም ያሳጣናል። ጨካኝና ይቅር የማይል ሰው ነው የሚል ስም ካተረፍን ደግሞ በራሳችን ላይ ችግር እንፈጥራለን። (ምሳሌ 11:17) ቂም መያዝ አምላክ የማይደሰትበት ድርጊት ከመሆኑም በላይ ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም ሊመራ ይችላል። (ዘሌዋውያን 19:18) አጥማቂው ዮሐንስ ራሱ የተቆረጠው በእሱ ላይ ‘ቂም ይዛ’ የነበረችው ክፉዋ ሄሮድያዳ በሸረበችው ሴራ እንደነበር አስታውስ።—ማርቆስ 6:19-28
14. (ሀ) ማቴዎስ 6:14, 15 ስለ ይቅር ባይነት የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው? (ለ) ሁልጊዜ አንድን ሰው ይቅር ከማለታችን በፊት ይቅርታ እስኪጠይቀን ድረስ መጠበቅ አለብን?
14 የኢየሱስ የናሙና ጸሎት “ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፣ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና” የሚሉትን ቃላት ያካተተ ነው። (ሉቃስ 11:4) ይቅር ባዮች ካልሆንን ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ይሖዋ አምላክ እኛ የሠራናቸውን ኃጢአቶች ይቅር ማለቱን ሊያቆም ይችላል፦ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፣ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴዎስ 6:14, 15) ስለዚህ በይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ ውስጥ ያለውን አንድነት በመጠበቅ ረገድ የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት የምንፈልግ ከሆነ ይቅር ባዮች እንሆናለን። ምናልባትም ይህን የምናደርገው ሆን ተብሎ ሳይሆን ባለማወቅ የተፈጸመን አንድ በደል እንዲሁ በመርሳት ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ [“ይሖዋ በነጻ፣” አዓት] ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላስይስ 3:13) ይቅር ባዮች ስንሆን የይሖዋን ድርጅት ውድ አንድነት ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እናደርጋለን።
አንድነትና የግል ውሳኔዎች
15. የይሖዋ ሕዝቦች የግል ውሳኔዎች ሲያደርጉ አንድነታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ የሚረዳቸው ነገር ምንድን ነው?
15 አምላክ ሲፈጥረን የግል ውሳኔዎች የማድረግ መብትና ኃላፊነት እንዲሁም ልንከተለው የምንፈልገውን ጎዳና የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። (ዘዳግም 30:19, 20፤ ገላትያ 6:5) ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለምንከተል አንድነታችንን መጠበቅ እንችላለን። የግል ውሳኔዎች ስናደርግ ግምት ውስጥ እናስገባቸዋለን። (ሥራ 5:29፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ለምሳሌ ገለልተኝነትን የሚመለከት ጥያቄ ተነሳ እንበል። ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆንን’ እና ‘ሰይፋችንን ማረሻ አድርገን እንደቀጠቀጥን’ በማስታወስ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የግል ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። (ዮሐንስ 17:16፤ ኢሳይያስ 2:2-4) በተመሳሳይም ከመንግሥት ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ የግል ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን ምንም እንኳ በሰብዓዊ ጉዳዮች ረገድ “በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች” የምንገዛ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር’ ማስረከብን በተመለከተ የሚሰጠውን ሐሳብ አንዘነጋም። (ሉቃስ 20:25፤ ሮሜ 13:1-7፤ ቲቶ 3:1, 2) አዎን፣ የግል ውሳኔዎች በምናደርግበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ግምት ውስጥ ማስገባት ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ ይረዳናል።
16. ከቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ውሳኔዎች በምናደርግበት ጊዜ አንድነትን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
16 ራሳችንን ብቻ የሚመለከት ከቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓት ጋር ግንኙነት የሌለው የግል ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜም እንኳ ክርስቲያናዊ አንድነታችን እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። እንዴት? በውሳኔያችን ሊነኩ ለሚችሉ ሌሎች ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት በማሳየት ነው። ለምሳሌ ያህል በጥንቷ የቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ለጣዖት የሚሠዋ ሥጋን በተመለከተ አንድ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። እርግጥ፣ አንድ ክርስቲያን ለጣዖት አምልኮ በሚካሄድ ክብረ በዓል ላይ አይሳተፍም ነበር። ይሁን እንጂ የተረፈውን ሥጋ ደሙ በደንብ የፈሰሰ እስከሆነ ድረስ ከገበያ ገዝቶ መብላት ኃጢአት አልነበረም። (ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 10:25) ሆኖም ይህን ሥጋ የመብላቱ ጉዳይ የአንዳንድ ክርስቲያኖች ሕሊና እንዲረበሽ አድርጎ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ሌሎቹ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው ስሜት ያላቸውን ክርስቲያኖች እንዳያሰናክሉ አጥብቆ መክሯቸዋል። እንዲያውም “መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 8:13) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ወይም ሥርዓት ባይጣስም እንኳ የአምላክን ቤተሰብ አንድነት ሊነኩ የሚችሉ የግል ውሳኔዎችን ስናደርግ ሌሎችን ግምት ውስጥ ማስገባት እንዴት ያለ የፍቅር መግለጫ ነው!
17. የግል ውሳኔዎችን የግድ መውሰድ በሚያስፈልገን ጊዜ ምን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው?
17 ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ግራ ከገባን ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን የሚያደርግ ውሳኔ ብንወስድ ጥሩ ነው፤ ሌሎችም ውሳኔያችንን ማክበር ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 14:10-12) እርግጥ የግል ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። ልክ እንደ መዝሙራዊው ሙሉ እምነት አድሮብን እንዲህ ብለን ልንጸልይ እንችላለን፦ “ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፣ . . . አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም።”—መዝሙር 31:2, 3
ክርስቲያናዊ አንድነታችሁን ዘወትር ጠብቁ
18. ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን አንድነት በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?
18 ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 ላይ የክርስቲያን ጉባኤን አንድነት ለማስረዳት የሰውን አካል እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። አንዱ የሌላው ጥገኛ መሆኑንና እያንዳንዱ ብልት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። “ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ?” ሲል ጳውሎስ ጠይቋል። “ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው። ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፣ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም።” (1 ቆሮንቶስ 12:19-21) በተመሳሳይም በይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ ውስጥ ያለነው ሁላችንም አንድ ዓይነት ሥራ አንሠራም። ሆኖም አንድ ነን፤ አንዱ ለሌላው ያስፈልገዋል።
19. ከአምላክ መንፈሳዊ ዝግጅት መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? አንድ በዕድሜ የገፋ ወንድም ይህን አስመልክቶ ምን ሐሳብ ሰጥቷል?
19 ሰውነት ምግብ፣ እንክብካቤና መመሪያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም አምላክ በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ በኩል ያደረገልን መንፈሳዊ ዝግጅት ያስፈልገናል። ከዚህ ዝግጅት ለመጠቀም የይሖዋ ምድራዊ ቤተሰብ አባል መሆን አለብን። አንድ ወንድም አምላክን ለብዙ ዓመታት ካገለገለ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁሉ ነገር የአሁኑን ያህል ግልጽ ካልነበረበት ከ1914 በፊት ከነበረው ቀደምት ዘመን አንስቶ . . . እውነት ልክ እንደ ቀትር ጸሐይ ቦግ ብሎ እስከበራበት እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ስለ ይሖዋ ዓላማዎች ከሚገልጸው እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር ተቀራርቦ የመኖሩን ጉዳይ ከሁሉ የላቀ ቦታ ሰጥቼው ቆይቻለሁ። ቀደም ሲል ያገኘሁት ተሞክሮ በሰብዓዊ አስተሳሰብ መመካት ትልቅ ስህተት እንደሆነ አስተምሮኛል። አእምሮዬ እዚህ መደምደሚያ ላይ ከደረሰ በኋላ ወዲያውኑ በታማኙ ድርጅት ውስጥ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። አንድ ሰው የይሖዋን ሞገስና በረከት ከዚህ ቦታ ሌላ የት ሊያገኝ ይችላል?”
20. የይሖዋ ሕዝቦች እንደ መሆናችን መጠን አንድነታችንን በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ለማድረግ መሆን ይኖርበታል?
20 ይሖዋ ሕዝቡን በዓለም ውስጥ ካለው መከፋፈልና ጨለማ አውጥቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:9) ከእሱ ጋርም ሆነ ከመሰል አማኞች ጋር የተባረከ አንድነት እንዲኖረን አድርጎናል። ይህ አንድነት በጣም በቀረበው አዲስ ሥርዓት ውስጥ ይኖራል። እንግዲያው በእነዚህ አስጨናቂ ቀኖች ውስጥ ‘ፍቅርን መልበሳችንን’ እንቀጥል፤ በተጨማሪም ውድ የሆነውን አንድነታችንን ለመጠበቅና ለማጠንከር የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።—ቆላስይስ 3:14
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችንና እውነትን አጥብቀን መያዛችን አንድነታችንን ለመጠበቅ ሊረዳን የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ አንድነት አንደበትን በአግባቡ ከመጠቀም ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?
◻ ይቅር ባይ መሆን ምንን ይጠይቃል?
◻ የግል ውሳኔዎች ስናደርግ አንድነትን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ክርስቲያናዊ አንድነትን መጠበቅ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ እረኛ መንጋው እንዳይበተን እንደሚጠብቅ ሁሉ ይሖዋም የሕዝቡን አንድነት ይጠብቃል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አንድን ሰው ካስቀየምን በትሕትና ይቅርታ በመጠየቅ አንድነታችን እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እናደርጋለን