የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በኩባ ‘ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቷል’
ሐዋርያው ጳውሎስ በጉልህ የሚጠቀስ የአምላክ መንግሥት ምሥራች ሰባኪ ነበር። ፈጣሪ ለታዛዥ የሰው ልጆች ስላዘጋጀው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለሌሎች ለማካፈል ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀም ነበር። ጳውሎስ ጥንታዊቷን የኤፌሶን ከተማ በሚጎበኝበት ጊዜ ብዙ ተጨማሪ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችለው አዲስ ሁኔታ እንደተፈጠረ ተገንዝቧል። “በኤፌሶን . . . እሰነብታለሁ። ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና” በማለት ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 16:8, 9
በኩባ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም አዲስ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። ምሥክሮቹ ገና ይፋ የሆነ ሕጋዊ እውቅና አግኝተው አይመዝገቡ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ተስፋቸውን ለአገራቸው ሰዎች በግልጽ ማካፈል ችለዋል። በቅርቡ የኩባ መንግሥት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ለመፍቀድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። ፕሬዚዳንት ካስትሮ የኩባ መንግሥት ከይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ቡድን ጋር ያለው ግንኙነት በጣም ጥሩ እንደሆነ በይፋ ተናግረዋል።
ይህ አዲስ ሁኔታ ለምሥክሮቹ “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” ከፍቶላቸዋል። ለምሳሌ በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች በኩባ ቢሮ ከፍተዋል። ይህ ቢሮ በዚያ አገር የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ ለማስተባበር ይረዳቸዋል። ከ65,000 የሚበልጡት የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑና በውስጡ የያዘውንም እውቀት እንዲቀስሙ በመርዳት ላይ ናቸው። እንደ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይጠቀማሉ። የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ብዙ ኩባውያን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው እየተጠቀሙ ነው።
በተጨማሪም ምሥክሮቹ በደሴቲቷ ዙሪያ በትናንሽ ቡድኖች ቋሚ ስብሰባዎች ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜም እስከ 150 ሆነው ተለቅ ያሉ ስብሰባዎችን የማድረግ መብት አግኝተዋል። ከመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር አንድ ላይ ለመሰብሰብ፣ አምላክን በመዝሙር ለማወደስና አንድ ላይ ለመጸለይ እንዲችሉ ከኩባ ባለ ሥልጣናት ፈቃድ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል።
በቅርቡም በሦስት ቅዳሜና እሁድ ውስጥ ከ1,000 የሚበልጡ የ“አምላካዊ ፍርሃት” የአውራጃ ስብሰባዎች ተከናውነዋል። አንድ ሪፖርት እንደጠቆመው ሁሉም ስብሰባዎች ‘ሥርዓታማና ሰላም የሰፈነባቸው’ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ባለ ሥልጣኖቹ የተሰማቸውን ደስታ ለምሥክሮቹ ገልጸውላቸዋል።
እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም ዙሪያ ከአምላክ የተሰጣቸውን የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ትእዛዝ ለመፈጸም ይጥራሉ። እንዲሁም ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ያላቸውን ሰላማዊ ግንኙነት ለመጠበቅ ይጥራሉ። (ቲቶ 3:1) የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚከተለው ሲል የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ይከተላሉ፦ “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፣ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።”—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2