የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 9/1 ገጽ 8-13
  • ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረው ሕግ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረው ሕግ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሙሴ ሕግና ዓላማው
  • ምሕረትና ርኅራኄ በግልጽ የተንጸባረቀበት ሕግ
  • ሕጉን አለአግባብ መጠቀም
  • ፈሪሳውያን የፈጸሙት ብክለት
  • ከፈሪሳውያን ስሕተቶች መማር
  • “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • የክርስቶስ ሕግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የሙሴ ሕግ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
    እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
  • በአሥሩ ትእዛዛት ሥር ነንን?
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 9/1 ገጽ 8-13

ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረው ሕግ

“አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።”—መዝሙር 119:97

1. የሰማይ አካላትን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው ምንድን ነው?

ኢዮብ ከልጅነቱ ጀምሮ ከዋክብትን በአድናቆት ይመለከት የነበረ ይመስላል። ወላጆቹ የታላላቅ ኅብረ ከዋክብትን ስምና ኅብረ ከዋክብቱ በሰማይ ላይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ስለሚቆጣጠሩት ሕጎች የሚያውቁትን ነገር ሳያስተምሩት አይቀሩም። እንዲያውም በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ግዙፍና በጣም ድንቅ የሆኑትን የእነዚህን ሥርዓተ ከዋክብት ቋሚ እንቅስቃሴ የወቅቶችን መፈራረቅ ለይተው ለማወቅ ይጠቀሙበት ነበር። ኢዮብ ብዙ ጊዜ ሰማይን በአንክሮ ቢመለከትም እነዚህን የከዋክብት ክምችቶች አንድ ላይ የሚያስተሳስራቸው ብርቱ ኃይል ምን እንደሆነ ግን አያውቅም ነበር። በመሆኑም ይሖዋ አምላክ “የሰማይ አካላትን የሚቆጣጠሩትን ሕጎች ታውቃለህን?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብለት ኢዮብ መልስ አልነበረውም። (ኢዮብ 38:31-33፣ ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል) አዎን፣ ከዋክብት የሚመሩት በሕግ ነው። እነዚህ ሕጎች ፍጹም ትክክለኛና ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሳይንቲስቶች ሙሉ በሙሉ ሊረዷቸው አልቻሉም።

2. ፍጥረታት በሙሉ በሕግ ይመራሉ ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው?

2 በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻው ከፍተኛ ሕግ አውጪ ይሖዋ ነው። ሥራዎቹ በሙሉ የሚመሩት በሕግ ነው። “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” የሆነው ውድ ልጁ ግዑዙ አጽናፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የአባቱን ሕጎች በታማኝነት ይታዘዝ ነበር! (ቆላስይስ 1:15) መላእክቱም የሚመሩት በሕግ ነው። (መዝሙር 103:20) እንስሳትም ቢሆኑ ፈጣሪያቸው በውስጣቸው ለቀረጻቸው ተፈጥሮአዊ ትእዛዞች ስለሚገዙ በሕግ ይመራሉ ማለት ይቻላል።—ምሳሌ 30:24-28፤ ኤርምያስ 8:7

3. (ሀ) የሰው ልጅ ሕግ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር ያስተዳደረው በምን አማካኝነት ነበር?

3 ስለ ሰው ልጆችስ ምን ማለት ይቻላል? ምንም እንኳ የማሰብ ችሎታ፣ ግብረገብነትና መንፈሳዊነትን በመሳሰሉት ስጦታዎች የተባረክን ብንሆንም እነዚህን ችሎታዎች በመጠቀም ረገድ የሚመራን የተወሰነ መለኮታዊ ሕግ ያስፈልገናል። የመጀመሪያ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ፍጹማን ስለነበሩ እነሱን ለመምራት ያስፈለጉት ጥቂት ሕጎች ብቻ ነበሩ። ለሰማያዊ አባታቸው የነበራቸው ፍቅር እሱን በደስታ ለመታዘዝ በቂ ምክንያት ሊሆናቸው ይገባ ነበር። ሆኖም ሳይታዘዙት ቀሩ። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:15-17፤ 3:6-19) በዚህ ምክንያት ዘሮቻቸው መመሪያ የሚሆኑ ሌሎች ብዙ ተጨማሪ ሕጎች የሚያስፈልጓቸው ኃጢአተኛ ሰዎች ሆኑ። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ በፍቅር ተነሣስቶ ይህን አስፈላጊ ነገር አሟልቷል። ኖኅም ለቤተሰቡ ሊያስተላልፋቸው የሚገቡ ሕጎችን ይሖዋ ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 9:1-7) ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ አምላክ በሙሴ አማካኝነት ዝርዝር ሐሳቦችን ያካተተ በጽሑፍ የሠፈረ ሕግ ለአዲሱ የእስራኤል ብሔር ሰጥቷል። ይሖዋ አንድን ብሔር ሙሉ በሙሉ በመለኮታዊ ሕግ ሲያስተዳድር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ይህን ሕግ መመርመራችን ይህ መለኮታዊ ሕግ በዛሬው ጊዜ በሚገኙ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ምን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ለመረዳት ያስችለናል።

የሙሴ ሕግና ዓላማው

4. የተመረጡት የአብርሃም ዝርያዎች የተስፋውን ዘር የማስገኘታቸው ሁኔታ አስቸጋሪ የነበረው ለምንድን ነው?

4 ሕጉን ጠንቅቆ የተማረው ሐዋርያው ጳውሎስ “ታዲያ ሕግ የተሰጠው ለምንድን ነው?” በማለት ጠይቆ ነበር። (ገላትያ 3:19 የ1980 ትርጉም) ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይሖዋ ለወዳጁ ለአብርሃም፣ ለአሕዛብ ሁሉ ታላላቅ በረከቶችን የሚያስገኝ አንድ ዘር በእርሱ የቤተሰብ ሐረግ በኩል እንደሚመጣ ቃል መግባቱን ማስታወስ ያስፈልገናል። (ዘፍጥረት 22:18) ይሁን እንጂ አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። ከተመረጡት የአብርሃም ዝርያዎች ማለትም ከእስራኤላውያን መካከል ይሖዋን የማይወዱ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ አብዛኞቹ እስራኤላውያን አንገተ ደንዳኖችና ዓመፀኞች ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶቹ ጨርሶ የማይታዘዙ ሆነዋል! (ዘጸአት 32:9፤ ዘዳግም 9:7) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በአምላክ ሕዝብ መካከል ሊገኙ የቻሉት በሕዝቡ ውስጥ ስለተወለዱ ብቻ እንጂ በፍላጎታቸው ያደረጉት አይደለም።

5. (ሀ) ይሖዋ በሙሴ ሕግ አማካኝነት እስራኤላውያንን ምን አስተማራቸው? (ለ) ሕጉ በሥሩ ያሉትን ሰዎች አኗኗር በሚነካ መንገድ የተዘጋጀው እንዴት ነው?

5 እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የተስፋውን ዘር ሊያስገኙና እሱ ከሚያመጣቸው በረከቶች ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ እነሱን እንደ ሮቦት ከመቆጣጠር ይልቅ በሕጉ አማካኝነት አስተማራቸው። (መዝሙር 119:33-35፤ ኢሳይያስ 48:17) እንዲያውም “ሕግ” ተብሎ የተተረጎመው ቶህራህ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል “ትምህርት” ማለት ነው። ሕጉ ያስተማራቸው ምን ነበር? በመጀመሪያ ደረጃ እስራኤላውያን ከኃጢአተኛ ሁኔታቸው የሚቤዣቸው መሲሕ እንደሚያስፈልጋቸው አስተምሯቸዋል። (ገላትያ 3:24) በተጨማሪም ሕጉ አምላካዊ ፍርሃትንና ታዛዥነትን አስተምሯቸዋል። እስራኤላውያን ለአብርሃም በተሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ለሌሎች ብሔራት በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ማገልገል ነበረባቸው። በመሆኑም ሕጉ ይሖዋን የሚያስመሰግን የላቀ የሥነ ምግባር ሥርዓት ሊያስተምራቸው ይገባ ነበር፤ ይህም የእስራኤል ብሔር በዙሪያው ያሉት ሕዝቦች ከሚፈጽሟቸው ወራዳ ልማዶች የተለየ እንዲሆን የሚያደርገው ነበር።—ዘሌዋውያን 18:24, 25፤ ኢሳይያስ 43:10-12

6. (ሀ) የሙሴ ሕግ ምን ያህል ደንቦችን ይዟል? ከመጠን በላይ ብዙ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የሌለበትስ ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ስለ ሙሴ ሕግ በማጥናት ምን ጥልቅ ማስተዋል ልናገኝ እንችላለን?

6 እንግዲያውስ የሙሴ ሕግ ከ600 በላይ የሚሆኑ ብዙ ደንቦችን መያዙ ምንም አያስደንቅም።a ይህ በጽሑፍ የተደነገገው ሕግ አምልኮን፣ አስተዳደርን፣ ሥነ ምግባርን፣ ፍትሕን፣ አመጋገብንና ንጽሕናን ሳይቀር የሚቆጣጠር ነበር። ታዲያ ይህ ሲባል ሕጉ ችክ ያሉ ደንቦችና የማያፈናፍኑ ትእዛዞች ጥርቅም ነበር ማለት ነውን? ፈጽሞ አይደለም! ይህን ሕግ ማጥናት ስለ ይሖዋ ፍቅር የተላበሰ ሁለንተና ጥልቅ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዳናል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

ምሕረትና ርኅራኄ በግልጽ የተንጸባረቀበት ሕግ

7, 8. (ሀ) ሕጉ ምሕረትንና ርኅራኄን ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ከዳዊት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ሕጉን ምሕረት በተሞላበት መንገድ ያስፈጸመው እንዴት ነው?

7 ሕጉ በተለይ ለችግረኞች ወይም ለአቅመ ደካሞች ምሕረትና ርኅራኄ ማሳየትን ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። መበለቶችና ወላጆች የሌሏቸው ልጆች ለየት ያለ ጥበቃ ይደረግላቸው ነበር። (ዘጸአት 22:22-24) ሕጉ ለሥራ የሚያገለግሉት እንስሳት በጭቃኔ እንዳይያዙ ይከላከል ነበር። መሠረታዊ የሆኑ የንብረት ባለቤትነት መብቶች ይከበሩ ነበር። (ዘዳግም 24:10፤ 25:4) ሕጉ ነፍሰ ገዳይ በሞት እንዲቀጣ የሚያዝዝ ቢሆንም በስሕተት ነፍስ የገደለ ሰው ምሕረት የሚያገኝበትም ዝግጅት ተደርጎ ነበር። (ዘኁልቁ 35:11) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው እስራኤላዊ ዳኞች ለአንዳንድ ጥፋቶች በክፉ አድራጊው ግለሰብ ዝንባሌ ላይ ተመሥርተው ፍርድ የመስጠት መብት ነበራቸው።—ከዘጸአት 22:7 እና ከዘሌዋውያን 6:1-7 ጋር አወዳድር።

8 ይሖዋ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ጥብቅ በመሆን፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ደግሞ ምሕረት እያደረገ ሕጉን በማስፈጸም ለእስራኤል ዳኞች ምሳሌ ሆኖላቸዋል። ምንዝር ፈጽሞና ነፍስ አጥፍቶ የነበረው ንጉሥ ዳዊት ምሕረት አግኝቷል። ሆኖም ከቅጣት አላመለጠም፤ ምክንያቱም የፈጸመው ኃጢአት ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ እንዳይቀምስ ይሖዋ ከለላ አልሆነውም። ይሁንና በመንግሥቱ ቃል ኪዳን ምክንያት እንዲሁም ዳዊት ራሱ በተፈጥሮው መሐሪ ሰው በመሆኑና ከልቡ ንስሐ በመግባቱ ከሞት አምልጧል።—1 ሳሙኤል 24:4-7፤ 2 ሳሙኤል 7:16፤ መዝሙር 51:1-4፤ ያዕቆብ 2:13

9. ፍቅር በሙሴ ሕግ ውስጥ ምን ድርሻ ነበረው?

9 ከዚህም በተጨማሪ የሙሴ ሕግ ፍቅር በጉልህ ተንጸባርቆበታል። እስቲ አስበው ዛሬ ካሉት ብሔራት መካከል ፍቅር ማሳየትን የሚያዝ ሕግ የደነገገ የትኛው መንግሥት ነው! በመሆኑም የሙሴ ሕግ ነፍስ መግደልን ከመከልከልም አልፎ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በማለት ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:18) መጻተኛው ፍትሕ በጎደለው መንገድ እንዳይያዝ በመከልከል ብቻ ሳይወሰን “እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና . . . እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ” በማለት ያዝዛል። (ዘሌዋውያን 19:34) ምንዝር ሕገ ወጥ እንደሆነ ከመናገርም አልፎ ባል ሚስቱን ደስ እንዲያሰኛት ያዝዝ ነበር! (ዘዳግም 24:5) በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ብቻ 20 ጊዜ ያህል የፍቅርን ባሕርይ የሚያመለክቱ የዕብራይስጥ ቃላት ይገኛሉ። ይሖዋ ለእስራኤላውያን ቀድሞ ይወዳቸው እንደነበር፣ አሁንም እንደሚወዳቸውና ወደፊትም ፍቅሩን እንደማይነፍጋቸው አረጋግጦላቸዋል። (ዘዳግም 4:37፤ 7:12-14) በእርግጥም ከሙሴ ሕግ መካከል የላቀ ቦታ ያለው “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህ ውደድ” የሚለው ሕግ ነው። (ዘዳግም 6:5) ኢየሱስ ሕግ ሁሉ የተመሠረተው በዚህኛውና ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ በሚለው ትእዛዝ ላይ መሆኑን ተናግሯል። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ማቴዎስ 22:37-40) መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” በማለት መጻፉ አያስደንቅም።—መዝሙር 119:97

ሕጉን አለአግባብ መጠቀም

10. አይሁዳውያን በአመዛኙ ለሙሴ ሕግ የነበራቸው አመለካከት ምን ነበር?

10 እስራኤላውያን በአመዛኙ ለሙሴ ሕግ አድናቆት ማጣታቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነበር! ሕዝቡ ሕጉን ተላልፈዋል፣ ችላ ብለውታል ወይም ከነመኖሩም ረስተውት ነበር። ንጹሑን አምልኮ በሌሎች ብሔራት አጸያፊ ሃይማኖታዊ ልማዶች በክለዋል። (2 ነገሥት 17:16, 17፤ መዝሙር 106:13, 35-38) በሌሎች መንገዶችም ሕጉን ተላልፈዋል።

11, 12. (ሀ) ከዕዝራ ዘመን በኋላ በአይሁዳውያን መካከል የተነሡት የሃይማኖት መሪዎች ጥፋት የፈጸሙት እንዴት ነው? (ሣጥኑን ተመልከት።) (ለ) የጥንቶቹ ረቢዎች “በሕጉ ዙሪያ አጥር ማበጀት” አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማቸው ለምን ነበር?

11 አንዳንዶቹን በጣም አስከፊ ነገሮች በሕጉ ላይ የፈጸሙት ሕጉን እናስተምራለን እንዲሁም እንጠብቃለን የሚሉት ሰዎች ራሳቸው ነበሩ። ይህ የሆነው በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከኖረው ከታመነው ጸሐፊ ከዕዝራ ዘመን በኋላ ነበር። ዕዝራ ሕዝቡን ከሌሎች ብሔራት የሚበክል ተጽዕኖ ለመከላከል ከፍተኛ ተጋድሎ ከማድረጉም በላይ ሕጉን የማንበብንና የማስተማርን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ዕዝራ 7:10፤ ነህምያ 8:5-8) አንዳንድ የሕጉ አስተማሪዎች የዕዝራን ፈለግ እንከተላለን በማለት “ታላቅ ምኩራብ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ማኅበር መሠረቱ። ከማኅበሩ መፈክሮች መካከል “በሕጉ ዙሪያ አጥር ማበጀት” የሚለው መመሪያ ይገኝበት ነበር። እነዚህ አስተማሪዎች ሕጉ እንደ ውድ የአትክልት ቦታ ነው ብለው ያስቡ ነበር። ማንም ሰው የአትክልት ሥፍራውን ሕግጋት በመተላለፍ እንዳይበድል ሲሉ ሕዝቡን እንደዚህ ወዳለው ስህተት ጨርሶ እንዳይቃረብ የሚከለክሉ ብዙ ሕጎችን ማለትም “የቃል ሕግ” አወጡ።

12 የአይሁድ መሪዎች እንደዚህ ማሰባቸው ትክክል ነበር ብለው የሚከራከሩ አይጠፉ ይሆናል። ከዕዝራ ዘመን በኋላ አይሁዳውያን በውጪ ኃይሎች በተለይ ደግሞ በግሪካውያን እጅ ወድቀው ነበር። የግሪክ ፍልስፍናና ባህል የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመዋጋት የሃይማኖት መሪዎችን ያቀፉ ቡድኖች በአይሁድ ሕዝብ መካከል አቆጠቆጡ። (በገጽ 10 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ውሎ አድሮ ከእነዚህ ቡድኖች አንዳንዶቹ ሕጉን በማስተማር ረገድ ሌዋውያን ካህናትን የሚፎካከሩና አልፎ ተርፎም ከእነርሱ የሚያስንቁ ሆነዋል። (ከሚልክያስ 2:7 ጋር አወዳድር።) በ200 ከዘአበ የቃል ሕጉ በአይሁዳውያን ሕይወት ውስጥ ሚና መጫወት ጀመረ። መጀመሪያ አካባቢ እነዚህ ሕጎች በጽሑፍ ከሰፈረው ሕግ ጋር በእኩል ዓይን ሊታዩ ይችላሉ በሚል ፍራቻ በጽሑፍ መልክ አልተቀመጡም ነበር። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ከመለኮታዊው አስተሳሰብ ይልቅ ሰብዓዊው አስተሳሰብ በማየሉ ይህ “አጥር” ይከላከልለታል የተባለለትን “የአትክልት ቦታ” ራሱ አበላሽቷል።

ፈሪሳውያን የፈጸሙት ብክለት

13. አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ብዙ ደንቦች ያወጡት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት የሚያቀርቡት ምክንያት ምን ነበር?

13 ረቢዎች ቶራህ ወይም የሙሴ ሕግ ፍጹም ­ስለሆነ ሊነሣ ለሚችል ማንኛውም ጥያቄ መልስ መስጠት አለበት ብለው ያስቡ ነበር። ይህ ሐሳብ ለሕጉ ከነበራቸው አክብሮት የመነጨ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ረቢዎች ለትንሹም ለትልቁም ነገር ሁሉ የሚያወጧቸው ደንቦች በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ መስለው እንዲታዩ ለማድረግ አታላይ የሆነ ሰብአዊ አስተሳሰብ እንዲጠቀሙ በር ከፍቶላቸዋል።

14. (ሀ) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ከአሕዛብ የተለዩ ስለመሆን የሚናገረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ከመጠን በላይ በማስፋት ከቅዱስ ጽሑፉ ውጭ የሆነ አመለካከት የፈጠሩት እንዴት ነው? (ለ) ረቢዎች ያወጧቸው ደንቦች የአይሁድን ሕዝብ ከአረማዊ ተጽዕኖ መጠበቅ እንደተሳናቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?

14 ሃይማኖታዊ መሪዎቹ በየጊዜው ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎቸን ከመጠን በላይ በማስፋት የተንዛዛ ሥርዓት ያወጡ ነበር። ለምሳሌ ያህል የሙሴ ሕግ ከአሕዛብ የተለዩ ስለመሆን ይናገራል፤ ይሁን እንጂ ረቢዎች ይሰብኩ የነበረው ሕዝቡ የአይሁድ ላልሆኑ ነገሮች ሁሉ ጭፍን ጥላቻ እንዲያሳድሩ ነበር። አሕዛብ “ከእንስሳት ጋር የጾታ ግንኙነት በማድረግ ስለሚጠረጠሩ” አንድ አይሁዳዊ ከአሕዛብ ወገን በሆነ ሰው የእንግዶች ማረፊያ ግቢ ውስጥ ከብቱን ትቶ መሄድ የለበትም ብለው ያስተምሩ ነበር። አንዲት አይሁዳዊት ሴት ከአሕዛብ ወገን የሆነችን ሴት ማዋለድ አይፈቀድላትም፤ እንዲህ ብታደርግ “ጣዖት አምላኪ የሚሆን አንድ ልጅ እንዲወለድ አስተዋጽኦ እንዳደረገች ይቆጠራል።” ረቢዎች በግሪካውያን የስፖርት ማዕከሎች ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ ያደረጓቸው በቂ ምክንያቶች ስለነበሯቸው ማንኛውም የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ የተከለከለ ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሮች አይሁዳውያንን ከአሕዛብ እምነቶች ለመጠበቅ አንዳችም የፈየዱት ነገር እንደሌለ ታሪክ ይመሠክራል። እንዲያውም ፈሪሳውያን ራሳቸው ነፍስ አትሞትም የሚለውን ከአረማውያን የመጣ የግሪክ መሠረተ ትምህርት ማስተማር ጀመሩ!—ሕዝቅኤል 18:4

15. የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች የመንጻትን ሕግና በሥጋ ዘመዶች መካከል ስለሚፈጸም የጾታ ግንኙነት የተሰጡትን ሕጎች ያዛቡት እንዴት ነው?

15 ከዚህም በተጨማሪ ፈሪሳውያን የመንጻትን ሕግ አዛብተዋል። ፈሪሳውያን አጋጣሚው ቢሰጣቸው ፀሐይን ሳይቀር ያጠራሉ እየተባለ ይነገር ነበር። “እዳሪ ከመውጣት መዘግየት አንድን ሰው እንደሚያረክስ” ሕጋቸው ይደነግግ ነበር! እጅ መታጠብ አንድ ራሱን የቻለ አስቸጋሪ ሥርዓት ነበር፤ የትኛው እጅ በቅድሚያ መታጠብ እንዳለበትና እንዴት መታጠብ እንደሚገባ የመሳሰሉትን የሚደነግጉ ደንቦች ነበሩት። በተለይ ሴቶች ንጹሕ እንዳልሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። ረቢዎች ማንኛውም ሰው ወደ ሥጋ ዘመዱ “አይቅረብ” ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ በመነሣት ባል ከሚስቱ ኋላ ኋላ መሄድም ሆነ በገበያ ስፍራ ከእሷ ጋር መነጋገር የለበትም የሚል ድንጋጌ አውጥተው ነበር። (እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ የሚከለክለው በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን ነው)—ዘሌዋውያን 18:6

16, 17. የቃል ሕግ ሳምንታዊ ሰንበትን ስለ ማክበር የተሰጠውን ትእዛዝ ያስፋፋው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?

16 በተለይ የሰንበትን ሕግ በሚመለከት በቃል ሕግ አማካኝነት የተጨመረው አላስፈላጊ ነገር በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው በሳምንቱ ሰባተኛ ቀን ማናቸውንም ሥራ አትሥሩ የሚል ቀላል ትእዛዝ ነበር። (ዘጸአት 20:8-11) ሆኖም የቃል ሕጉ 39 የሚያህሉ ልዩ ልዩ የተከለከሉ የሥራ ዓይነቶችን በመጨመር ሕጉን ተንትኗል፤ ይህም መቋጠርን ወይም የተቋጠረውን መፍታትን፣ ልብስን ሦስት ጊዜ በመርፌ ወግቶ በክር ማያያዝን፣ ሁለት የዕብራይስጥ ፊደላት መጻፍንና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። ከዚያም እያንዳንዳቸው የተከለከሉ የሥራ ዓይነቶች ደግሞ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ተጨማሪ ደንቦች አሏቸው። የሚፈቀዱት ምን ዓይነት ቋጠሮዎች ናቸው የማይፈቀዱትስ? የቃል ሕግ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ ጨቋኝ ደንቦች አሉት። ማከም የተከለከለ ሥራ ነበር። ለምሳሌ ያህል የተሰበረን አካል በሰንበት መጠገን ክልክል ነበር። የጥርስ ሕመም ያለበት ሰው ምግቡን ለማጣፈጥ ኮምጣጤ መጨመር የሚችል ቢሆንም ኮምጣጤውን በአፉ መያዝ ግን አይፈቀድለትም ነበር። ምክንያቱም ይህ ጥርሱን ሊፈውሰው ይችላል!

17 የሰንበት ሕግ በዚህ መንገድ በብዙ መቶዎች በሚቆጠሩ ሰው ሠራሽ ሕጎች በመዋጡ በአብዛኞቹ አይሁዳውያን ዘንድ መንፈሳዊ ትርጉሙን አጣ። “የሰንበት ጌታ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን በጣም አስገራሚና ልብ የሚነኩ ተአምራትን ባደረገበት ወቅት ጻፎችና ፈሪሳውያን ምንም ስሜት አልሰጣቸውም ነበር። እነርሱን ያሳሰባቸው ያወጧቸውን ደንቦች ችላ ማለቱ ነበር።—ማቴዎስ 12:8, 10-14

ከፈሪሳውያን ስሕተቶች መማር

18. በሙሴ ሕግ ላይ የቃል ሕጎችንና ወጎችን መጨመር ምን ውጤት አስከትሏል? በምሳሌ አስረዳ።

18 በጠቅላላው እነዚህ ጭማሪ ሕጎችና ወጎች ለሙሴ ሕግ በመርከብ አካል ላይ እንደሚለጠፉ ሙጭጭ አድርገው የሚይዙ ባርናክል የሚባሉ የባሕር ፍጥረታት ሆነውበት ነበር ለማለት እንችላለን። እነዚህ አስቸጋሪ ፍጥረታት የመርከቡን ፍጥነት ከመቀነሳቸውም በላይ የዝገት መከላከያውን ቅብ ስለሚያስለቅቁ አንድ የመርከብ ባለቤት እነዚህን ፍጥረታት ፈቅፍቆ ለማስለቀቅ የሚጠይቅበት ድካም እንዲህ የዋዛ አይደለም። በተመሳሳይም የቃል ሕጎቹና ወጎቹ ሕጉን በጣም ስላከበዱት እየተዳከመ እንዲሄድ ምክንያት ሆነዋል። ሆኖም ረቢዎች ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን እነዚህን ሕጎች አውጥተው ከመጣል ይልቅ ሌሎች ሕጎችን መጨመራቸውን ቀጠሉ። መሲሑ ሕጉን ለመፈጸም በመጣበት ወቅት “መርከቡ” “በባርናክል” ተሸፍኖ ስለነበር መንሳፈፍ እንኳ አቅቶት ነበር ማለት ይቻላል። (ከምሳሌ 16:25 ጋር አወዳድር።) እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የሕጉን ቃል ኪዳን ከችግር ከመጠበቅ ይልቅ ሕጉን በመተላለፍ ስሕተት ፈጽመዋል። ታዲያ የእነርሱ የደንብ “አጥር” ከንቱ ሆኖ የቀረው ለምንድን ነው?

19. (ሀ) “በሕጉ ዙሪያ ያለው አጥር” ከንቱ ሆኖ የቀረው ለምንድን ነው? (ለ) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች እውነተኛ እምነት እንደጎደላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?

19 የአይሁድ እምነት መሪዎች ከመጥፎ ዝንባሌዎች ጋር ውጊያ የሚደረገው በሕግ መጻሕፍት ገጾች ላይ ሳይሆን በልብ ውስጥ እንደሆነ መገንዘብ ተስኗቸው ነበር። (ኤርምያስ 4:14) በዚህ ትግል ድል ለማድረግ ቁልፉ ፍቅር ነው። ይኸውም ለይሖዋ፣ ለሕጎቹና ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያለን ፍቅር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በአንፃሩ ደግሞ ይሖዋ ለሚጠላው ነገር ጥላቻ እንድናሳድር ያደርገናል። (መዝሙር 97:10፤ 119:104) በዚህ መንገድ ልባቸው በፍቅር የተሞላ ሰዎች በዚህ ምግባረ ብልሹ ዓለም ውስጥ ለይሖዋ ሕጎች የታመኑ ሆነው ይኖራሉ። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ለማስፈን ሕዝቡን የማስተማር ታላቅ መብት ነበራቸው። ይህን ማድረግ የተሳናቸው ለምንድን ነው? ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው እምነት አልነበራቸውም። (ማቴዎስ 23:23 አዓት የግርጌ ማስታወሻ) የይሖዋ መንፈስ በታማኝ ሰዎች ልብ ውስጥ ለመሥራት ኃይል እንዳለው ቢያምኑ ኖሮ የሌሎችን ሕይወት አንድ ባንድ መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ሆኖ ባልተሰማቸው ነበር። (ኢሳይያስ 59:1፤ ሕዝቅኤል 34:4) እምነት ስላልነበራቸው ሌሎች እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ አልቻሉም፤ በሕዝቡ ላይ ሰው ሠራሽ ትእዛዞችን ተብትበው ጭነው ነበር።—ማቴዎስ 15:3, 9፤ 23:4

20, 21. (ሀ) በአጠቃላይ ሲታይ ወግ የተጠናወተው አስተሳሰብ በአይሁድ እምነት ላይ ምን ውጤት አስከትሏል? (ለ) በአይሁድ እምነት ላይ ከደረሰው ነገር ምን እንማራለን?

20 እነዚያ የአይሁድ መሪዎች ፍቅር እንዲሰፍን አላደረጉም። ወጎቻቸው ያፈሩት ነገር ቢኖር እንዲያው ለታይታ ብቻ የሚደረግ ልባዊ ያልሆነ ታዛዥነት ለማሳየት የሚጥር የግብዞች ዋሻ የሆነ ሃይማኖት ነው። (ማቴዎስ 23:25-28) ያወጧቸው ደንቦች በሌሎች ላይ ለመፍረድ የሚያስችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ምክንያቶችን ፈጥረውላቸዋል። በመሆኑም ኩራተኛና ፈላጭ ቆራጭ የነበሩት ፈሪሳውያን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይቀር መንቀፍ እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበር። ሕጉ የተሰጠበትን ዋነኛ ዓላማ በመሳታቸው እውነተኛውን መሲሕ ሳይቀበሉ ቀሩ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ “እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ለማለት ተገዶ ነበር።—ማቴዎስ 23:38፤ ገላትያ 3:23, 24

21 ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ግትርና ወግ የተጠናወተው አስተሳሰብ የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ ለማራመድ አይበጅም! ይሁን እንጂ ይህ ማለት በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በግልጽ ከሰፈሩት ውጭ ሌሎች ደንቦች አይኖሯቸውም ማለት ነውን? አይደለም። ለዚህ ጥያቄ የተሟላ መልስ ለማግኘት ኢየሱስ ክርስቶስ የሙሴን ሕግ በአዲስና የተሻለ ሕግ እንዴት እንደተካው ቀጥሎ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እርግጥ ይህም ቢሆን ዛሬ ካሉት መንግሥታት የሕግ መዋቅር ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ቁጥር ነው። ለምሳሌ ያህል በየዓመቱ ብዙ ሺህ አዳዲስ ሕጎች የሚታከሉበት የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራሉ መንግሥት ሕግ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከ125,000 የሚበልጡ ገጾች አስፈልገውት ነበር።

ልታብራራ ትችላለህን?

◻ ፍጥረት ሁሉ በመለኮታዊ ሕግ ይመራል ለማለት የምንችለው እንዴት ነው?

◻ የሙሴ ሕግ ዓይነተኛ ዓላማ ምን ነበር?

◻ የሙሴ ሕግ ምሕረትንና ርኅራኄን ጎላ አድርጎ እንደሚገልጽ የሚያሳየው ምንድን ነው?

◻ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሙሴ ሕግ ላይ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ደንቦች የጨመሩት ለምን ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች

ጻፎች፦ የዕዝራ ተተኪዎቸ እንደሆኑና ስለ ሕጉ ማብራሪያ መስጠት የሚገባቸው ሰዎች እነርሱ እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ጅዩስ የተባለው መጽሐፍ ባሠፈረው መሠረት “ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ሁሉም ጻፎች አይደሉም፤ የተሠወረውን የሕጉን ትርጉም ፈልፍለን እናወጣለን የሚለው ጥረታቸው አጓጉል ደንቦችንና ትርጉም የለሽ እገዳዎችን እንዲያወጡ አድርጓቸዋል። እነዚህ እገዳዎች በባሕሉ ውስጥ ተቀባይነት ስላገኙ የማያፈናፍኑ ማነቆዎች ሆነው ነበር።”

ሔሲዲም፦ የዚህ ስም ትርጉም “ጻድቃን” ወይም “ቅዱሳን” ማለት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በቡድን መልክ የታወቁት በ200 ከዘአበ ገደማ ሲሆን በፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውና ሕጉን ከግሪካውያን መጥፎ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ለሕጉ ንጽሕና ጥብቅና የቆሙ ሰዎች ነበሩ። ሔሲዲም በሦስት ቡድን ተከፍሏል፦ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያን እና የአይሁድ መነኮሳት ማኅበር።

ፈሪሳውያን፦ አንዳንድ ምሁራን ይህ ስም የመጣው “ገለልተኞች” ወይም “ተገንጣዮች” የሚል ትርጉም ካለው ቃል እንደሆነ ያምናሉ። በእርግጥም ከአሕዛብ የተለዩ በመሆን ረገድ ከፍተኛ ግፊት የሚያሳድሩ አክራሪዎች ነበሩ፤ ሆኖም እርስ በርሳቸው ያላቸውም ኅብረት ውስብስብ ስለሆነው የቃል ሕግ አንዳችም እውቀት ከሌላቸው ከተራዎቹ አይሁዳውያን የተለየና የሚበልጥ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር። አንድ ታሪክ ጸሐፊ ስለ ፈሪሳውያን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “በጥቅሉ ሲታዩ ሰዎችን እንደ ሕፃን የሚመለከቱ እንዲሁም ጥቃቅን በሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ሳይቀር ችክ የሚሉና ትንታኔ የሚያበዙ ሰዎች ናቸው።” ሌላ ምሁርም እንዲሁ፦ “የፈሪሳውያን እምነት እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ የሚመለከት የሕግ ቁልል አውጥተዋል፤ ይህም ትናንሹን ነገር እያጋነኑ ትልቁን ነገር እንዲያቃልሉ አድርጓቸዋል (ማቴ. 23:23)” ብለዋል።

ሰዱቃውያን፦ ከመኳንንትና ከካህናት ቡድን ጋር በቅርብ የተሣሠረ ቡድን ነው። የቃል ሕግ በጽሑፍ የሠፈረውን ሕግ ያክል ዋጋ የለውም በማለት ጻፎችና ፈሪሳውያንን በጽኑ ይቃወሙ ነበር። በዚህ ትግል ግን እንደተሸነፉ ሚሽና ራሱ ይመሠክራል። እንዲህ ይላል፦ “የሕጉን [የተጻፈውን ሕግ] ቃል [ከማክበር] ይልቅ የፈሪሳውያንን ቃል [ማክበር] የላቀ ግምት የሚሰጠው ነገር ነው።” በቃል ሕግ ላይ ብዙ አስተያየቶችን ያከለ ታልሙድ “ጻፎች የተናገሯቸው ቃላት . . . ቶራህ ካሰፈራቸው ቃላት ይልቅ እጅግ የተወደዱ ናቸው” እስከ ማለት ደርሷል።

የአይሁድ መነኮሳት ማኅበር፦ ተገልለው በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚገኝ የመናኞች ቡድን። ዘ ኢንተርፕሪተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንደሚለው የአይሁድ መነኮሳት ማኅበር አባላት ከፈሪሳውያንም ይበልጥ ለእምነታቸው ያደሩ ሲሆኑ “አንዳንዴ የፈሪሳውያንም ፈሪሳዊ ሆነው ይገኛሉ።”

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢዮብ ወላጆች ኅብረ ከዋክብትን ስለሚቆጣጠሩት ሕጎች ልጃቸውን ሳያስተምሩት አይቀርም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ