በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች አፋጣኝ እርዳታ ማድረግ
ሰዎች በተፈጥሮ አደጋዎች ማግስት እርዳታ ለመስጠት የሚያሳዩት ጥረት በእርግጥ የሚያስመሰግን ነው። ብዙ የእርዳታ ፕሮግራሞች የፈረሱ ቤቶች እንደገና እንዲገነቡ፣ የተበታተኑ ቤተሰቦች እንዲገናኙና ከሁሉ በላይ ደግሞ የሰዎች ሕይወት እንዲተርፍ ረድተዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ሌሎች የእርዳታ ፕሮግራሞች በሚያደርጓቸው ዝግጅቶች ሁሉ የሚጠቀሙ ሲሆን ለሚደረግላቸው ነገር ሁሉ አመስጋኞች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ‘በተለይ በእምነት ለሚዛመዷቸው’ በጎ የማድረግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አለባቸው። (ገላትያ 6:10) አዎን፣ ምሥክሮቹ በዝምድና እንደተሳሰሩ ሆኖ ይሰማቸዋል፤ እርስ በርሳቸው እንደ “ቤተሰብ” ይተያያሉ። “ወንድም” እና “እህት” እየተባባሉ የሚጠራሩትም ለዚህ ነው።—ከማርቆስ 3:31-35 እና ከፊልሞና 1, 2 ጋር አወዳድር።
በመሆኑም በአንድ አካባቢ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያሉት ሽማግሌዎች እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ያለበትን ቦታና የደረሰበትን ችግር ለመረዳት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ አስፈላጊውን እገዛ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታ በጋና አክራ፣ በ ዩ ኤስ ኤ ሳን አንጄሎ እና በጃፓን ኮቤ ውስጥ እንዴት እንደተፈጸመ ተመልከት።
አክራ—“ትንሹ የኖኅ ዘመን”
ዝናቡ መጣል የጀመረው ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ ሲሆን ለረጅም ሰዓታት ያለ አንዳች ፋታ ዘነበ። በአክራ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ የሆነው ጆን ቱውማሲ “ዝናቡ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሣ መላው ቤተሰቤ መተኛት አልቻለም” ይላል። ዴይሊ ግራፊክ “ትንሹ የኖኅ ዘመን” ሲል ጠርቶታል። ጆን በመቀጠል “አንዳንድ ውድ ዕቃዎቻችንን ወደ ላይኛው ፎቅ ለመውሰድ ሞከርን፤ ይሁን እንጂ ወደ ደረጃው የሚወስደውን በር ስንከፍት ጎርፉ ቤት ውስጥ ግልብጥ ብሎ ገባ።”
የአካባቢው ባለ ሥልጣኖች ነዋሪው ሕዝብ ቤቱን ለቆ እንዲወጣ ቢያሳስቡም ብዙዎቹ ቤታቸው በውኃ ቢሞላም እንኳ ባዶውን ትቶ መሄዱ ዘራፊዎችን እንደሚጋብዝ በማሰብ ለመውጣት አመነቱ። አንዳንዶች ለመውጣት ቢፈልጉም እንኳ አልቻሉም። ፖሊና የተባለች አንዲት ልጃገረድ እንዲህ ትላለች፦ “እናቴና እኔ በሩን መክፈት አልቻልንም ነበር። ውኃው እየጨመረ ሲመጣ ከእንጨት በተሠራ በርሜል ላይ ወጥተን የጣሪያውን ወራጅ እንጨት ይዘን ቆምን። በመጨረሻ ከጠዋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ጎረቤቶቻችን መጥተው አዳኑን።”
ወዲያው ጋብ እንዳለ የይሖዋ ምሥክሮች ለሥራ ታጥቀው ተነሡ። ቤአትሪስ የተባለች አንዲት ክርስቲያን እህት እንዲህ በማለት ስለ ሁኔታው ትናገራለች፦ “በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ሲፈልጉን ቆይተው በመጨረሻ ተጠግተንበት በነበረው የአንድ ምሥክር ቤት አገኙን። የጎርፍ መጥለቅለቁ ከደረሰ ከሦስት ቀናት በኋላ በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎችና ወጣቶች ሁሉ እኛን ለመርዳት ቤታችን መጡ፤ በቤቱ ውስጥና ውጭ የተከመረውን ደለል በሙሉ አፀዱልን። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለማጠቢያ የሚያገለግሉ ኬሚካሎች፣ የጀርም መግደያ መርዞች፣ ቀለም፣ ፍራሾች፣ ብርድ ልብሶች፣ እንዲሁም ጨርቆችና የሕፃናት ልብሶች ላከልን። ወንድሞች ለበርካታ ቀናት የሚሆን ምግብ ላኩልን። ይህ ልቤን በጣም ነክቶታል!”
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆን ቱውማሲ እንዲህ ይላል፦ “አካባቢያችን ላሉት ተከራዮች ማኅበራችን ጠቅላላውን ቤት ለማጽዳት የሚያስችሉ የማጠቢያ ኬሚካሎችና የጀርም መግደያ መርዞች እንደላከልን ነገርኳቸው። በአካባቢው ተከራይተው የሚኖሩ 40 የሚያክሉ ሰዎች በጽዳቱ ሥራ ተባበሩን። ለማጠቢያ ከሚያገለግሉት ኬሚካሎች መካከል የተወሰኑትን ለአንድ በአካባቢው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚሠራ ቄስና ለጎረቤቶቼ ሰጠኋቸው። የሥራ ባልደረቦቼ የይሖዋ ምሥክሮች ፍቅራቸውን የሚገልጹት ለእነርሱ ሰዎች ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው።”
ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የተደረገላቸውን ፍቅራዊ እርዳታ ከልብ አድንቀዋል። ወንድም ቱውማሲ ሲያጠቃልል እንዲህ ብሏል፦ “በጎርፉ ምክንያት ያጣሁት ንብረት በገንዘብ ሲተመን በእርዳታ ካገኘኋቸው ቁሳቁሶች የበለጠ ዋጋ የነበረው ቢሆንም ቤተሰቤና እኔ ማኅበሩ ያደረገልን ይህ ልብ የሚነካ ዝግጅት ካጣነው እጅግ የሚልቅ ነገር እንዳገኘን እንዲሰማን አድርጓል።”
ሳን አንጄሎ—“የዓለም መጨረሻ የመጣ ይመስል ነበር”
ግንቦት 28, 1995 ሳን አንጄሎን እንዳልነበረች ያደረጋት ዓውሎ ነፋስ ዛፎችን ነቃቅሏል፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ገነዳድሷል እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ያላቸውን ገመዶች በጣጥሶ በየመንገዱ ላይ ጥሏቸዋል። ንፋሱ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን እያወደመ በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር ይጋልብ ነበር። ከ20,000 በላይ ቤቶች ጨለማ ውጧቸዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በረዶ መዝነብ ጀመረ። ብሔራዊው የአየር ሁኔታ አገልግሎት ድርጅት፦ “በመጀመሪያ “ጥንግ ጥንግ የሚያክል በረዶ” ከዚያም “የሸራ ኳስ የሚያክል በረዶና” በመጨረሻም “ትላልቅ ግሬፕ” የሚያክል በረዶ ይወርድ ጀመር” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ድምፁ ጆሮ ያደነቁራል። አንድ ነዋሪ እንዳሉት፦ “የዓለም መጨረሻ የመጣ ይመስል ነበር።”
ከዓውሎ ነፋሱ በኋላ የሰፈነው ፀጥታ ስጋት የሚፈጥር ነበር። ሁሉም የደረሰውን ጥፋት ለመመልከት ከፈራረሱት ቤቶቻቸው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ከመገንደስ የተረፉት ዛፎች ቅጠላቸው በሙሉ ረግፏል። ቆመው የሚታዩት ቤቶችም የተራቆቱ ይመስሉ ነበር። በአንዳንድ አካባቢዎች በረዶው እስከ አንድ ሜትር በሚደርስ ከፍታ መሬቱ ላይ ተከምሯል። በሺህ የሚቆጠሩ የመስኮት መስተዋቶች ከቤቶችና ከመኪናዎች ላይ ረግፈው ስለነበር የብርጭቆ ስብርባሪዎች መሬቱን እንደ ብርድ ልብስ ከሸፈነው በረዶ ግራና ቀኝ ሲያንጸባርቁ ይታያል። አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “እቤቴ ስደርስ መኪናዬን መንገዱ መሀል አቁሜ እዚያው መኪናዬ ውስጥ ቁጭ እንዳልኩ አለቀስሁ። የደረሰው ጥፋት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ከመጠን በላይ ተረብሼ ነበር።”
የእርዳታ ፕሮግራሞችና ሆስፒታሎች ወዲያው የገንዘብ እርዳታ፣ የግንባታ ቁሳቁሶች፣ ሕክምናና ምክር መስጠት ጀመሩ። ራሳቸው የዓውሎ ነፋሱ ሰለባ የነበሩ ብዙ ሰዎች ሌሎችን ለመርዳት የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸው የሚያስመሰግን ነበር።
የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችም እንዲሁ ለሥራ ተንቀሳቅሰዋል። በሳን አንጄሎ የሚገኝ ኦብሪ ኮነር የተባለ ሽማግሌ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል፦ “ወዲያው አውሎ ነፋሱ እንዳበቃ አንዳችን የሌላውን ደህንነት ለማረጋገጥ ስልክ ተደዋወልን። የራሳችንንም ሆነ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑት ጎረቤቶቻችንን ቤቶች መስኮት ለመሸፈን፣ ጣሪያዎችን ፕላስቲክ ለማልበስና የተቻለውን ያህል ቤቶቹን ከነፋሱ ለመከላከል እርስ በርስ ተረዳድተናል። ከዚያም በጉባኤ ውስጥ ያለውንና ቤቱ የተጎዳበትን የእያንዳንዱን ሰው ስም መዘገብን። አንድ መቶ የሚያክሉ ቤቶች ጥገና ያስፈልጋቸው የነበረ ሲሆን ከሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች የተገኘው እርዳታ በቂ አልነበረም። በመሆኑም ተጨማሪ ቁሳቁሶችን ገዛንና ለሥራው ራሳችንን አዘጋጀን። በድምሩ ወደ 1,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች በሥራው ለመርዳት ፈቃደኛ ሆነው የተገኙ ሲሆን በእያንዳንዱ ሳምንት የመጨረሻ ቀኖች ላይ 250 የሚያክሉ ሰዎች ይሠሩ ነበር። 740 ኪሎ ሜትር ርቀት ካለው ቦታ ሁሉ የመጡ ነበሩ። ሁሉም ያላንዳች መታከት አብዛኛውን ጊዜ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሚደርስ ሙቀት ሠርተዋል። አንዲት የ70 ዓመት አረጋዊት እህት እንኳ ከአንድ ቅዳሜና እሁድ በስተቀር በየሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት አብረውን ሲሠሩ ሰንብተዋል፤ ያኔም ቢሆን የቀሩት የሳቸው ቤት ሲጠገን ስለ ነበር ነው። በዚያ ሳምንት ደግሞ ቤታቸው ጣሪያ ላይ ወጥተው በጥገናው ሥራ ሲያግዙ ነበር!
“ብዙውን ጊዜ በሩቅ የሚታዘቡ ሰዎች ‘ሌሎች ሃይማኖቶችም ለአባሎቻቸው እንዲህ ቢያደርጉ ምን ነበረበት?’ የሚሉትን የመሰሉ ቃላት ሲሰነዘሩ እንሰማ ነበር። (እህቶችን ጨምሮ) ከ10 እስከ 12 የሚያክሉ ፈቃደኛ ሰዎች የአንዱን የይሖዋ ምሥክር ቤት ጣሪያ ያለ አንዳች ክፍያ ለመጠገን አልፎ ተርፎም እንደ አዲስ ለመሥራት ተዘጋጅተው ዓርብ ዕለት ማለዳ ወደ ቤቱ ሲመጡ ሲያዩ ጎረቤቶቻችን በጣም ተነክተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሥራው በአንድ ቅዳሜና እሁድ ይጠናቀቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የእኛ ቡድን ወደ ሌላኛው ቤት ሲሻገር ኮንትራት ወስዶ የሚሠራ አንድ ኮንትራክተርና ሠራተኞቹ ግን ገና ጣሪያውን ሲሠሩ ይታዩ ነበር። እነርሱ ሳይጨርሱ በፊት እኛ ጣሪያውን አንሥተንና እንደ አዲስ ሠርተን ግቢውን እናጸዳ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሥራቸውን አቁመው እኛን ይመለከታሉ!”
ወንድም ኮነር እንዲህ በማለት ያጠቃልላል፦ “አብረን በመሥራት ያሳለፍናቸው እነዚያ አስደሳች ቀናት የሚያበቁበት ጊዜ ደረሰ። ፍቅር በማሳየትና የሌሎችን ፍቅር በማግኘት እርስ በርሳችን ከአሁን ቀደም ከምንተዋወቀው የበለጠ ተዋውቀናል። ይህም ወንድሞችና እህቶች ከልባቸው ተነሣስተው እርስ በርስ በሚረዳዱበት አዲስ ዓለም ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር የሚጠቁም ቅምሻ እንደሆነ ተሰምቶናል።”—2 ጴጥሮስ 3:13
ኮቤ—“የተሰባበረ እንጨት፣ የግድግዳ ፍርስራሽና የሰው አስከሬን ክምር”
የኮቤ ነዋሪዎች ዝግጁ እንደሆኑ ይታሰብ ነበር። በእርግጥም ደግሞ በየዓመቱ መስከረም 1ን የአደጋ መከላከል ቀን ብለው ያከብሩታል። በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች በርዕደ መሬት ወቅት ምን እንደሚያደርጉ ይለማመዳሉ፣ ወታደሮች በሄሊኮፕተር ተጠቅመው ሰዎችን እንዴት ማዳን እንደሚችሉ ይለማመዳሉ። የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍሎችም ርዕደ መሬት ሲከሰት ራስን እንዴት ማዳን እንደሚቻል ሥልጠና የሚሰጥበትን አንድ ክፍል የሚያክል ስፋት ያለውን ማሽናቸውን ያወጣሉ፤ ይህ ማሽን ልክ እንደ እውነተኛው የምድር መንቀጥቀጥ የሚናወጥ ሲሆን ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ማዳን የሚችሉበትን ሥልጠና ለማግኘት ገብተው ይለማመዱበታል። ይሁን እንጂ ጥር 17, 1995 እውነተኛው ርዕደ መሬት ሲከሰት ያ ሁሉ ዝግጅታቸው ምንም አልፈየደም። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጣራዎች ተደረመሱ፤ እንዲህ ያለው ነገር ደግሞ በማሽኖቹ አማካኝነት እንደሚደረገው የልምምድ ወቅት አልነበረም። ባቡሮች በጎናቸው ተጋደሙ፣ አውራ ጎዳናዎች ግማሽ ጎናቸው ተደረመሰ፣ የጋዝና የውኃ መተላለፊያ ቧንቧዎች ተሰባበሩ። መኖሪያ ቤቶቹ ከካርቶን እንደተሠራ ቤት ፈራረሱ። ታይም መጽሔት “የተሰባበረ እንጨት፣ የግድግዳ ፍርስራሽና የሰው አስከሬን ክምር” በማለት ሁኔታውን ገልጾታል።
ከዚያም እሳት ተነሣ። መንገዶቹ በመዘጋታቸው ምክንያት የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌዶች ገና በኪሎ ሜትሮች በሚገመት ርቀት ላይ ቆመው ሳሉ ሕንጻዎቹ በእሳት ጋዩ። ወደ ቦታው የደረሱትም ቢሆኑ የከተማዋ የውኃ መስመር በመውደሙ ምክንያት ውኃ ማግኘት አልቻሉም። አንድ ባለ ሥልጣን እንደሚከተለው ብለዋል፦ “የመጀመሪያው ቀን ፈጽሞ ሽብር ነበር። በእሳት በሚጋዩት ቤቶች ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች እንደተቀበሩ እያወቅሁ ምንም ማድረግ እንደማልችል ስገነዘብ የከንቱነት ስሜት ተሰማኝ፤ በሕይወቴ እንደዚህ ተሰምቶኝ አያውቅም።”
በጠቅላላው 5,000 ሰዎች ሲሞቱ ወደ 50,000 የሚገመቱ ቤቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል። በወቅቱ ኮቤ ውስጥ የነበረው ምግብ ከሚያስፈልገው መጠን አንድ ሦስተኛው ብቻ ነበር። አንዳንዶች ውኃ ለማግኘት ሲሉ ከፈነዱት የቧንቧ መስመሮች በታች ያለውን ቆሻሻ ውኃ ይጨልፉ ነበር። ቤት አልባ ከሆኑት መካከል ብዙዎቹ ወደ መጠለያ ጣቢያዎች ይጎርፉ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ጣቢያዎች መካከል አንዳንዶቹ በቀን ለእያንዳንዱ ሰው ጥቂት ሩዝ ብቻ የሚታደልባቸው ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ሰዉ በሁኔታው ማማረር ጀመረ። አንድ ሰው እንዲህ ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፦ “ባለ ሥልጣኖቹ አንዳች ነገር አላደረጉልንም። በእነርሱ ተማምነን ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ ራብ ይጨርሰን ነበር።”
በኮቤና በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ወዲያው ራሳቸውን አደራጁ። ሥራቸውን የተመለከተ አንድ የሄሊኮፕተር አብራሪ እንዲህ ብሏል፦ “አደጋው ወደደረሰበት ቦታ የሄድኩት ርዕደ መሬቱ በተከሰተበት ዕለት ነበር፤ ከዚያ በኋላ ለአንድ ሳምንት ያህል እዚያው ቆይቻለሁ። ወደ አንደኛው መጠለያ ስሄድ ሁሉም ነገር ምስቅልቅል ያለ ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የተጀመረ ምንም የዕርዳታ ሥራ አልነበረም። ወደ አካባቢው በፍጥነት ደርሰው ሲሯሯጡ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።”
በእርግጥ ብዙ ሥራ ነበር። አሥር የመንግሥት አዳራሾች ከጥቅም ውጭ ሲሆኑ ከ430 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ያለ መጠለያ ቀርተው ነበር። በተጨማሪም 1,206 ጥገና የሚያስፈልጋቸው ቤቶች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአደጋው የሞቱት የ15 ምሥክሮች ቤተሰቦች ትልቅ ማጽናኛ ያስፈልጋቸው ነበር።
ከመላው አገሪቷ 1,000 የሚያክሉ ምሥክሮች በጥገናው ሥራ ለመሳተፍ ራሳቸውን በፈቃደኛነት አቀረቡ። አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ያልተጠመቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቤት ስንሠራ ብዙ ጊዜ ‘ለዚህ ሁሉ የምንከፍለው ምን ያህል ነው?’ የሚል ጥያቄ ይገጥመን ነበር። ሥራውን የሚያሠሩት ጉባኤዎች እንደሆኑ ስንነግራቸው ‘ያጠናነው ነገር አሁን እውን ሆነልን’ በማለት ምስጋናቸውን ይገልጹ ነበር!”
ምሥክሮቹ ለአደጋው የሰጡት ፈጣንና የታሰበበት ምላሽ ብዙዎቹን አስገርሟቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የሄሊኮፕተር አብራሪ “በጣም ነው የተገረምሁት። እርስ በርሳችሁ ‘ወንድም’ እና ‘እህት’ ትባባላላችሁ። እንዴት እንደምትረዳዱ አይቻለሁ፣ በእርግጥም እንደ አንድ ቤተሰብ ናችሁ” ብሏል።
ይህ ርዕደ መሬት ራሳቸው ምሥክሮቹም ሳይቀሩ ትልቅ ትምህርት ያገኙበት ነበር። አንዲት እህት “ሁልጊዜ አንድ ድርጅት በሰፋ ቁጥር ለእያንዳንዱ ሰው በግል አሳቢነት ማሳየት ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ ይሄዳል ብዬ አስብ ነበር” በማለት ተናግራለች። ይሁን እንጂ የተደረገላት ፍቅራዊ እንክብካቤ አመለካከቷን ቀይሮላታል። “አሁን ግን ይሖዋ በድርጅት መልኩ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም እንደሚንከባከበን ተረድቻለሁ።” ይሁን እንጂ ከአደጋዎች ለዘለቄታው እፎይ የምንልበትን ጊዜ ከፊታችን እንጠብቃለን።
በቅርቡ ዘላቂ እፎይታ እናገኛለን!
የይሖዋ ምሥክሮች የሰው ልጅ ሕይወትና ኑሮ በአደጋዎች ምክንያት በአጭር የማይቀጭበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ ከምድር ተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር የሚችልበትን መንገድ ይማራል። ሰዎች ከራስ ወዳድነት ልማዶቻቸው ሲላቀቁ የተፈጥሮ አደጋዎች ለሚያስከትሉት ጥፋት የሚጋለጡበት አጋጣሚ ይቀንሳል።
ከዚህም በተጨማሪ የተፈጥሮ ኃይሎችን የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ሰብዓዊ ፍጥረታቱና ምድራዊ ሥራዎቹ ዳግም በተፈጥሮ ኃይሎች ስጋት ላይ እንዳይወድቁ ያደርጋል። ያን ጊዜ በእርግጥም ምድር ገነት ትሆናለች። (ኢሳይያስ 65:17, 21, 23፤ ሉቃስ 23:43) በራእይ 21:4 ላይ የሚገኘው ትንቢት ክብራማ ፍጻሜውን ያገኛል፦ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤአትሪስ ጆንስ (በግራ በኩል) እርሷና ሌሎች ሠንሰለት ሠርተው በጎርፉ ውስጥ እንዴት እንዳለፉ ስታሳይ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከዓውሎ ነፋሱ በኋላ የተካሄደው የእርዳታ ሥራ