ወንጌሎች በሃይማኖት ምሁራን ዓይን
“ሕዝቡ እኔ ማን እንደሆንሁ ይላሉ?” (ሉቃስ 9:18) ኢየሱስ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ይህን ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። በዚያን ወቅት ጉዳዩ አከራካሪ ነበር። ስለ ኢየሱስ ትኩረት በሚደረግበት በተለይ በገና ሰሞን ከዚያ ዘመን ይበልጥ ጉዳዩ አሁን አከራካሪ የሆነ ይመስላል። ኢየሱስ የሰውን ዘር ለማዳን ከሰማይ እንደተላከ ብዙዎች ያምናሉ። የአንተም አመለካከት ይህ ነውን? አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን ከዚህ የተለየ አመለካከት ያቀርባሉ። የሃይማኖትና የባሕል ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክስ ጄ ቦርግ “ኢየሱስ ለዓለም ኃጢአት ሊሞት የመጣ የአምላክ ልጅ መሆኑን ያስተማረ ግለሰብ ነው የሚለው በሰዎች አእምሮ ውስጥ የተቀረጸው አመለካከት ከታሪክ አንፃር እውነት አይደለም” ብለዋል።
ሌሎች የሃይማኖት ምሁራን እውነተኛው ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ከምናገኘው ኢየሱስ የተለየ ነው ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሁሉም ወንጌሎች የተጻፉት ኢየሱስ ከሞተ ከአራት አሥርተ ዓመታት በኋላ ወይም ከዚያ ጊዜ በላይ ቆይቶ ነው፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢየሱስ እውነተኛ ማንነት ብዙ ነገር ተጨማምሮበታል የሚል አመለካከት አላቸው። ችግሩ የወንጌል ጸሐፊዎች የማስታወስ አለማስታወስ ጉዳይ ሳይሆን ለወንጌሉ የሰጡት ትርጓሜ ነው በማለት ምሁራኑ ይከራከራሉ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን በተለየ መንገድ ማለትም እንደ አምላክ ልጅ፣ እንደ አዳኝና መሲህ አድርገው መመልከት የጀመሩት ከሞተ በኋላ ነው ተብሎ ይነገራል። አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን ኢየሱስ ከቦታ ቦታ ይዞር የነበረ ፈላስፋና የማኅበራዊ አብዮት አራማጅ ነበር በማለት በድፍረት አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል። እንግዲህ በሃይማኖት ምሁራን አመለካከት ወንጌሎች የያዙት እውነት ይህ ነው።
የሃይማኖት ምሁራን ስለ ኢየሱስ ያላቸው “ምሁራዊ” አመለካከት
የሃይማኖት ምሁራን “ምሁራዊ” አመለካከታቸው ትክክለኛ እንደሆነ አድርገው ለመከራከር እንዲያመቻቸው ሲሉ ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ከሰብዓዊ ባሕርይ ውጭ የሚመስል ማንኛውንም ነገር ላለመቀበል በጉጉት ሰበብ የሚፈላልጉ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ከድንግል ተወለደ የሚባለው ዲቃላነቱን ለመሸፋፈን ነው የሚሉ አሉ። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት የተናገራቸውን ትንቢቶች አይቀበሉም፤ ትንቢቶቹ በወንጌሎች ውስጥ የተጨመሩት “ከተፈጸሙ” በኋላ ነው በማለት ይከራከራሉ። አንዳንዶች ኢየሱስ የፈወሰው በሥነ ልቦናዊ ዘዴዎች አማካኝነት መሆኑ አንዳችም ጥርጥር የለውም ይላሉ። እነዚህ አባባሎች ምክንያታዊ ሆነው ይታዩሃል ወይስ ጨርሶ የማይመስሉ?
እንዲያውም አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የክርስትና እምነት እንዳይጠፋ ለማድረግ ሲሉ ኢየሱስ ትንሣኤ አግኝቷል የሚል የፈጠራ ታሪክ ጽፈዋል ይላሉ። የሃይማኖት ምሁራኑ የኢየሱስ ተከታዮች ኢየሱስ የለም ከተባለ ሃይማኖታቸው ስለሚሽመደመድ መምህራቸውን በተመለከተ የፈጠራ ታሪክ ለመጻፍ ተገደዱ የሚል ምክንያት ያቀርባሉ። በሌላ አነጋገር ትንሣኤ ያገኘው ክርስቶስ ሳይሆን ክርስትና ነው ማለታቸው ነው። ይህ ምሁራዊ ውስልትና እንደሆነ ተደርጎ የሚታይ ከሆነ እስከነጭራሹ ኢየሱስ አልተገደለም የሚለው የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት የባርባራ ሴሪንግ ሐሳብ ምን ሊባል ነው? እኚህ ምሁር ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ከመሞት የተረፈ ከመሆኑም በላይ ሁለት ጊዜ አግብቶ ሦስት ልጆች ወልዷል ብለው ያምናሉ።
እነዚህ አነጋገሮች በሙሉ ኢየሱስ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ’ የመጣ የአምላክ ልጅ ሳይሆን እንደ አንድ ፈላስፋ፣ ተራ አይሁዳዊ ወይም እንደ አንድ የለውጥ አራማጅ አድርገው ያስቀምጡታል፤ ይህ ደግሞ ብዙዎቹ የሃይማኖት ምሁራን ወደሚስማሙበት ደረጃ ወረደ ማለት ነው።—ማቴዎስ 20:28
በዓመቱ ውስጥ በዚህ ወቅት ምናልባት የወንጌሎችን የተወሰኑ ክፍሎች፣ ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በከብት በረት ውስጥ እንደተወለደ የሚናገረውን ክፍል አንብበህ ይሆናል። ወይም ደግሞ እነዚህ ታሪኮች በቤተ ክርስቲያን ሲነገሩ አድምጠህ ሊሆን ይችላል። ወንጌሎች የያዙትን ታሪክ ጠቃሚና የሚታመን እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህን? እንግዲያው ይህን ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ነገር ልብ በል። አንድ የሃይማኖት ምሁራን ቡድን ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት ለማረጋገጥ በሚል ከ1985 ጀምሮ በዓመት ሁለት ጊዜ ስብሰባ ሲያደርግ ቆይቷል። ይህ ስብሰባ የኢየሱስ ሴሚናር የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ኢየሱስ እንደተናገረው ተደርጎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ በእርግጥ እሱ ተናግሮታልን? የጉባኤው ተሳታፊዎች ኢየሱስ በተናገረው በእያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ላይ የተለያየ ቀለም ባላቸው ጨሌዎች አማካኝነት ድምፅ ሰጥተዋል። ቀይ ቀለም ያለው ጨሌ ዓረፍተ ነገሩን በእርግጥ ኢየሱስ የተናገረው መሆኑን ለማመልከት የሚያገለግል ሲሆን ሐምራዊ ቀለም ያለው ጨሌ ተናግሮ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ የሚያመለክት ነው፤ ግራጫ ቀለም ያለው ጨሌ ጥርጣሬን ያመለክታል፤ ጥቁር ቀለም ያለው ጨሌ ደግሞ ዓረፍተ ነገሩን ኢየሱስ ያልተናገረው መሆኑን ለማመልከት ያገለግላል።
ኢየሱስ የተናገራቸው ዓረፍተ ነገሮች ናቸው ከሚባሉት መካከል 82 በመቶ የሚሆኑት እሱ ያልተናገራቸው እንደሆኑ የኢየሱስ ሴሚናር የተባለው ጉባኤ ማስታወቁን ስትሰማ በጣም ትገረም ይሆናል። ከማርቆስ ወንጌል ውስጥ ትክክለኛ ነው ተብሎ የታመነበት አንድ ጥቅስ ብቻ ነው። የሉቃስ ወንጌል “ሥረ መሠረቱ ምን እንደሆነ ሊታወቅ በማይችል” ፕሮፓጋንዳ የተሞላ ነው ተብሏል። ከዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ከሦስት ዓረፍተ ነገሮች በስተቀር ሌላው በሙሉ ሐሰትነትን ለማመልከት የሚያገለግለውን ጥቁር ጨሌ ነው ያገኘው። የቀሩት ሦስት ዓረፍተ ነገሮች ጥርጣሬን ለማመልከት የሚያገለግለውን ግራጫ ቀለም ያለው ጨሌ አግኝተዋል።
ለጭንቅላት እውቀት ያህል ብቻ አይደለም
የሃይማኖት ምሁራኑ በወሰዱት አቋም ትስማማለህን? የሃይማኖት ምሁራን ኢየሱስን በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ ትክክለኛ ማስረጃ በማቅረብ ላይ ናቸውን? እነዚህን ጥያቄዎች የምንመረምረው እንዲያው ለጭንቅላት እውቀት ያህል ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አምላክ ኢየሱስን የላከው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” መሆኑን በዓመቱ ውስጥ በዚህ ወቅት ላይ ትዝ ይልህ ይሆናል። አምላክ ኢየሱስን እንደላከ በዚህ የዓመቱ ወቅት በተለያዩ መንገዶች ታስታውስ ይሆናል።—ዮሐንስ 3:16
ኢየሱስ ማለት ብዙም የማይታወቅ ከቦታ ወደ ቦታ የሚዞር አንድ አይሁዳዊ ፈላስፋ ቢሆን ኖሮ ‘በእሱ ማመን’ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረው ነገር እውነት ከሆነ ጉዳዩ ዘላለማዊ መዳን ማግኘት ወይም አለማግኘታችንን የሚመለከት ይሆናል። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረው ነገር እውነት መሆኑንና አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልገናል።