የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 1/15 ገጽ 18-22
  • አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም”
  • ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም
  • አምላክ ያወጣቸውን መስፈርቶች ማሟላት
  • ለሕይወትና ለደም አክብሮት ማሳየት
  • ከተደራጁት የይሖዋ ሕዝቦች ጋር ማገልገል
  • “አምላክን መውደድ” ሲባል ምን ማለት ነው?
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • የአምላክ ፍቅር ለዘላለም ይኖራል
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • አምላክ ለሕይወት ያለው ዓይነት አመለካከት አለህ?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ለሕይወት የአምላክ ዓይነት አመለካከት አለህ?
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 1/15 ገጽ 18-22

አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

“ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።”​— 1 ዮሐንስ 5:​3

1, 2. አምላክ እርሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን ማውጣቱ የማያስገርመን ለምንድን ነው?

ብዙ ጊዜ ሰዎች “የራሴ ሃይማኖት ምን አለኝ?” ይላሉ። ይሁን እንጂ “ሃይማኖቴ አምላክን ያስደስታልን?” ብሎ መጠየቅ ይገባ ነበር። አዎን፣ አምላክ ተቀባይነት ባለው መንገድ ሊያመልኩት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲያሟሉ የሚፈልጋቸው ብቃቶች አሉ። ይህ እንግዳ ነገር ሊሆንብን ይገባልን? በፍጹም አይገባም። በቅርቡ ብዙ ገንዘብ አውጥታችሁ ያደሳችሁት አንድ ቆንጆ ቤት አላችሁ እንበል። ማንም ሰው እንዲኖርበት ትፈቅዳላችሁ? እንደማትፈቅዱ የታወቀ ነው። በቤታችሁ ሊኖር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው እናንተ ያወጣችሁትን ብቃት ማሟላት ይኖርበታል።

2 በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክ ይህችን ምድራዊ መኖሪያ ለሰው ልጆች አዘጋጅቶ ሰጥቷል። በቅርቡ ደግሞ በመንግሥታዊ ግዛቱ አማካኝነት ምድር ሙሉ በሙሉ “ትታደሳለች”፤ ወይም በሌላ አባባል ውብ ገነት ትሆናለች። ይሖዋ ይህን ይፈጽመዋል። ይህን ማድረግ አንድያ ልጁን አሳልፎ መስጠትን የሚያህል ትልቅ ዋጋ መክፈል ጠይቆበታል። በእርግጥም አምላክ በዚህች የታደሰች ምድር ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ የተወሰኑ ብቃቶችን እንዲያሟሉ መጠየቁ ተገቢ ነው!​— መዝሙር 115:​16፤ ማቴዎስ 6:​9, 10፤ ዮሐንስ 3:​16

3. ሰሎሞን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምን እንደሆነ ጠቅለል አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

3 የአምላክ ብቃቶች ምን እንደሆኑ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ጠቢቡን ንጉሥ ሰሎሞን በመንፈሱ አነሳስቶ ከእኛ የሚፈልገውን ነገር ጠቅለል ባለ አነጋገር እንዲጽፍ አድርጎታል። ሰሎሞን በከፍተኛ ጥረት ያከናወናቸውን ነገሮች በሙሉ፣ ማለትም ሀብቱን፣ የግንባታ ሥራዎቹን፣ የሙዚቃ ፍቅሩን፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያሳፈለውን የፍቅር ሕይወት መለስ ብሎ ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።”​— መክብብ 12:​13 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

“ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም”

4-6. (ሀ) ‘ከባድ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥሬ ፍቺ ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ትእዛዞች ከባዶች አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?

4 “ትእዛዙንም ጠብቅ።” አምላክ ከእኛ የሚፈልገው መሠረታዊ ነገር ይህ ነው። ታዲያ ይህን ከእኛ መጠየቁ የሚበዛበት ነውን? በፍጹም አይደለም። ሐዋርያው ዮሐንስ የአምላክን ትእዛዞች ወይም ብቃቶች በተመለከተ መንፈሳችንን የሚያሳርፍ ነገር ይነግረናል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።”​— 1 ዮሐንስ 5:​3 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

5 እዚህ ላይ ‘ከባድ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥሬ ፍቺው “ለመሸከም የሚከብድ” ማለት ነው። ለመቋቋም ወይም ለማሟላት አስቸጋሪ የሆነን ነገር ሊያመለክት ይችላል። ቃሉ በማቴዎስ 23:​4 ላይ ጻፎችና ፈሪሳውያን በሕዝቡ ላይ ጥለዋቸው የነበሩት ሰው ሠራሽ ሕጎችና ወጎች ‘ከባድ ሸክም’ መሆናቸውን ለመግለጽ ተሠርቶበታል። በዕድሜ ገፍቶ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ለመናገር የፈለገው ነገር ምን እንደሆነ አስተዋላችሁ? የአምላክ ትእዛዛት ከባድ ሸክሞች አይደሉም። ልንጠብቃቸው የማይቻሉ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮችም አይደሉም። (ከዘዳግም 30:​11 ጋር አወዳድር።) በተቃራኒው ደግሞ አምላክን የምንወድ ከሆነ ብቃቶቹን ማሟላት ያስደስተናል። ለይሖዋ ያለንን ፍቅር በተግባር ለመግለጽ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይሰጠናል።

6 ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለማሳየት አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። አሁን አምላክ ከእኛ የሚፈልጋቸውን አምስት ብቃቶች እንመርምር። እነዚህን ብቃቶች በምንመረምርበት ጊዜ ሁሉ ዮሐንስ ‘የእግዚአብሔር ትእዛዛት ከባዶች አይደሉም’ በማለት የተናገረውን አስታውሱ።

ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም

7. መዳናችን የተመካው በምን ላይ ነው?

7 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው አንደኛው ብቃት ስለ እርሱ እውቀት መቅሰም ነው። በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ የሚገኙትን ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ተመልከቱ። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፋት የመጨረሻ ምሽት ነበር። ይህን ምሽት በአብዛኛው ያሳለፈው ሐዋርያቱን ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ በማዘጋጀት ነበር። የወደፊት ሕይወታቸው፣ አዎን፣ የዘላለም ተስፋቸው አሳስቦት ነበር። ራሱን ወደ ሰማይ አሻቅቦ እየተመለከተ ጸለየላቸው። በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መሠረት በቁጥር 3 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ብቻህን እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸው ይህ የዘላለም ሕይወት ማለት ነው።” አዎን፣ መዳናቸው ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እውቀት በመቅሰማቸው’ ላይ የተመካ ነበር። ለእኛም ቢሆን እንዲሁ ነው። መዳንን ለማግኘት ከፈለግን ይህን ዓይነቱን እውቀት ማግኘት ይኖርብናል።

8. ስለ አምላክ ‘እውቀት መቅሰም’ ማለት ምን ማለት ነው?

8 ስለ አምላክ ‘እውቀት መቅሰም’ ሲባል ምን ማለት ነው? እዚህ ላይ ‘እውቀት መቅሰም’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማወቅን፣ ማንነቱን መገንዘብን” ወይም “ሙሉ በሙሉ መረዳትን” ያመለክታል። በተጨማሪም ‘እውቀት መቅሰም’ የሚለው አባባል ቀጣይነት ያለውን ሂደት እንደሚያመለክት ማስተዋል ይገባል። ስለዚህ የአምላክን እውቀት መቅሰም ማለት ስለ አምላክ ላይ ላዩን ሳይሆን ጠለቅ ብሎ ማወቅ፣ ከእርሱ ጋር እርስ በርስ በመተዋወቅ የቅርብ ዝምድና መመስረት ማለት ነው። ከአምላክ ጋር ቀጣይነት ያለው ዝምድና ካለን ስለ እርሱ ያለን እውቀት ዕለት ከዕለት እየጨመረ ይሄዳል። ስለ ይሖዋ ሁሉን አውቀን መጨረስ ስለማንችል ይህ ሂደት ለዘላለም የሚቀጥል ይሆናል።​— ሮሜ 11:​33

9. ከፍጥረት መጽሐፍ ስለ ይሖዋ ምን መማር እንችላለን?

9 ስለ አምላክ እውቀት የምንቀስመው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ ሁለት መጻሕፍት አሉ። አንዱ የፍጥረት መጽሐፍ ነው። ይሖዋ የፈጠራቸው ሕይወት ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው ነገሮች፣ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው እንድናስተውል ይረዱናል። (ሮሜ 1:​20) ጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት። በከፍተኛ ድምፅ እያስገመገመ የሚወርድ ትልቅ ፏፏቴ፣ ከውቅያኖስ ዳርቻዎች ጋር የሚላተሙትን የባሕር ሞገዶችና በጠራ ሌሊት በሰማይ ላይ የሚታዩትን ከዋክብት ስንመለከት ይሖዋ ‘ታላቅ ኃይል’ ያለው መሆኑን አንማርም? (ኢሳይያስ 40:​26) አንድ ሕፃን ልጅ አንዲት የውሻ ቡችላ የገዛ ጅራትዋን ስታባርር ወይም አንዲት የድመት ግልገል በክር ኳስ ስትጫወት እያየ ሲስቅ ብንመለከት “ደስተኛው አምላክ” ይሖዋ የሚስቅና የሚጫወት እንደሆነ እንድናስብ አያደርገንም? (1 ጢሞቴዎስ 1:​11 አዓት ) ጣፋጭ የሆነ ምግብ ስንቀምስ፣ የሜዳ አበቦችን አስደሳች መዓዛ ስናሸት፣ የሚያማምሩ ቢራቢሮዎችን ደማቅ ቀለም ስንመለከት፣ በጸደይ ወራት የሚሰማውን የወፎች ዝማሬ ስናዳምጥ፣ የምንወደው ሰው ሞቅ ባለ ስሜት እቅፍ አድርጎ ሲስመን ፈጣሪያችን በሕይወታችን እንድንደሰት የሚፈልግ የፍቅር አምላክ መሆኑን አናስተውልም?​— 1 ዮሐንስ 4:​8

10, 11. (ሀ) ከፍጥረት መጽሐፍ ስለ ይሖዋ እና ስለ ዓላማዎቹ ልንማር የማንችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የየትኞቹ ጥያቄዎች መልሶች ናቸው?

10 ይሁን እንጂ ከፍጥረት መጽሐፍ ብቻ ስለ ይሖዋ ልንማር የምንችለው ነገር ውስን ነው። ለምሳሌ ያህል የአምላክ ስም ማን ነው? ምድርን የፈጠረውና ሰዎችን በምድር ላይ ያኖረው ለምንድን ነው? አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልናል? እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ስለ አምላክ እውቀት ወደምንቀስምበት ወደ ሌላው መጽሐፍ ይኸውም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መሄድ ይኖርብናል። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ ስለ ራሱ፣ ማለትም ስለ ስሙ፣ ስለ ባሕሪውና ስለ ዓላማው ይገልጽልናል። ይህን ዓይነቱን እውቀት ከሌላ ከየትም ምንጭ ልናገኘው አንችልም።​— ዘጸአት 34:​6, 7፤ መዝሙር 83:​18፤ አሞጽ 3:​7

11 በተጨማሪም ይሖዋ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ልናውቃቸው ስለሚገቡ ሌሎች አካላት ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነ እውቀት ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? በይሖዋ ዓላማዎች አፈጻጸም ረገድስ ምን ሚና ይጫወታል? (ሥራ 4:​12) ሰይጣን ዲያብሎስ ማን ነው? ሰዎችን የሚያስተው በምን መንገዶች ነው? በሰይጣን ከመታለል ልንጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 5:​8) ሕይወት አድን የሆኑት የእነዚህ ጥያቄዎች መልሶች የሚገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው።

12. ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እውቀት መቅሰም ሸክም እንዳልሆነ እንዴት ማስረዳት ትችላለህ?

12 ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን እንዲህ ያለው እውቀት መቅሰም ከባድ ሸክም ነውን? በፍጹም አይደለም! የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ፣ የአምላክ መንግሥት ገነትን በምድር ላይ መልሶ እንደሚያቋቁም፣ የሚወደውን ልጁን ለኃጢአታችን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠና ሌሎች በጣም ውድ የሆኑ እውነቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታውቅ እንዴት እንደተሰማህ ታስታውሳለህ? ዓይንህን የሸፈነው ግርዶሽ እንደተነሳና ነገሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥርት አድርገህ ማየት እንደጀመርክ ያህል አልነበረምን? ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም የሚያስደስት ነገር ነው እንጂ ከባድ ሸክም አይደለም!​— መዝሙር 1:​1-3፤ 119:​97

አምላክ ያወጣቸውን መስፈርቶች ማሟላት

13, 14. (ሀ) የአምላክን እውቀት እያገኘን ስንሄድ በሕይወታችን ውስጥ ምን ለውጦችን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) አምላክ ከየትኞቹ ርኩስ ድርጊቶች እንድንርቅ ይፈልግብናል?

13 ስለ አምላክ እውቀት እየቀሰምን ስንሄድ በአኗኗራችን ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብን እንገነዘባለን። ይህም አምላክ ከእኛ ወደሚፈልገው ሁለተኛ ነገር ይመራናል:- አምላክ ለትክክለኛ ሥነ ምግባር ያወጣቸውን መስፈርቶች ማሟላትና የአምላክን እውነት መቀበል አለብን። እውነት ምንድን ነው? የፈለግነውን ብናምን ወይም የፈለግነውን ብናደርግ አምላክ የሚገደው ነገር ይኖራልን? በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ምንም የሚገደው አይመስላቸውም። የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በ1995 አሳትማ ባወጣችው ሪፖርት ላይ በሕጋዊ ጋብቻ ሳይተሳሰሩ አብሮ መኖር እንደ ኃጢአት ሆኖ መታየት የለበትም የሚል ሐሳብ አቅርባለች። አንድ የቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲህ ዓይነቱ ኑሮ “‘የኃጢአት ኑሮ’ መባሉ የሚያሳፍራቸው ስለሆነ አይጠቅማቸውም” ብለዋል።

14 ታዲያ ‘ሳይጋቡ አብሮ መኖር’ ኃጢአት መሆኑ ቀርቷል ማለት ነውን? ይሖዋ እንዲህ ስላለው ድርጊት ምን እንደሚሰማው በማያሻማ ሁኔታ ገልጾልናል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።” (ዕብራውያን 13:​4) ከጋብቻ በፊት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ልቅ አመለካከት ባላቸው ቀሳውስትና የአብያተ ክርስቲያናት አባላት እንደ ኃጢአት ላይቆጠር ይችላል፤ በአምላክ ዓይን ግን ከባድ ኃጢአት ነው! ምንዝር፣ ከቅርብ ዘመድ ጋር ሩካቤ ሥጋ መፈጸምና ግብረ ሰዶምም እንደዚሁ ከባድ ኃጢአቶች ናቸው። (ዘሌዋውያን 18:​6፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10) አምላክ ርኩስ አድርጎ ከሚመለከታቸው እንደነዚህ ካሉ ድርጊቶች እንድንርቅ ይፈልግብናል።

15. አምላክ እንድናሟላ የሚፈልግብን ብቃቶች ሌሎችን የምንይዝበትን መንገድና የምንከተለውን እምነት ጭምር የሚመለከቱት እንዴት ነው?

15 ይሁን እንጂ አምላክ ኃጢአት ናቸው ከሚላቸው ድርጊቶች መራቅ ብቻውን በቂ አይሆንም። አምላክ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድም እንድናሟላቸው የሚፈልግብን ብቃቶች አሉ። በቤተሰብ ውስጥ ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱና እንዲከባበሩ ይፈልጋል። ወላጆች ለልጆቻቸው ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎቶች እንዲያስቡ ይፈልጋል። ልጆች ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ ተናግሯል። (ምሳሌ 22:​6፤ ቆላስይስ 3:​18-21) እምነታችንን በተመለከተስ? ይሖዋ አምላክ ከሐሰት አምልኮ የመጡ ወይም ግልጽ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የሚጻረሩት እምነቶችንና ልማዶችን እንድናስወግድ ይፈልግብናል።​— ዘዳግም 18:​9-13፤ 2 ቆሮንቶስ 6:​14-17

16. አምላክ ለትክክለኛ ሥነ መግባር ካወጣቸው መስፈርቶች ጋር በሚጣጣም መንገድ መኖርና የአምላክን እውነት መቀበል ሸክም የማይሆነው ለምን እንደሆነ አስረዳ።

16 አምላክ ለትክክለኛ ሥነ ምግባር ያወጣቸውን መስፈርቶች ማሟላትና የአምላክን እውነት መቀበል ከባድ ሸክም ይሆንብናልን? የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ካሰብን ከባድ ሸክም አይሆንብንም። ትዳራችን አንዳችን ለሌላው ታማኝ ባለመሆናችን ምክንያት ከመፍረስ ይልቅ ባልና ሚስት የሚዋደዱበትና እርስ በርስ የሚተማመኑበት ትዳር ይሆናል፣ ቤታችን ልጆች ያልተፈለጉ ሸክሞች ሆነው የሚታዩበት፣ ችላ የሚባሉበትና የማይወደዱበት ከመሆን ይልቅ በወላጆቻቸው እንደሚወደዱና እንደሚፈለጉ ተሰምቷቸው የሚኖሩበት ይሆናል፤ ሰውነታችን በኤድስና በሌሎች የአባለ ዘር በሽታዎች የተጎሳቆለና የበደለኛነት ስሜት የሚሰማን ከመሆን ይልቅ ንጹሕ ሕሊናና ጥሩ ጤንነት ይኖረናል። በእርግጥም ይሖዋ እንድናሟላቸው የሚፈልጋቸው ብቃቶች በሕይወት ለመደሰት የሚያስፈልገንን አንድም ነገር እንድናጣ አያደርጉንም!​— ዘዳግም 10:​12, 13

ለሕይወትና ለደም አክብሮት ማሳየት

17. ይሖዋ ለሕይወትና ለደም ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

17 ሕይወታችሁን ከአምላክ የጽድቅ መስፈርቶች ጋር ባስማማችሁ መጠን ሕይወት ምን ያህል ክቡር ነገር እንደሆነ ትገነዘባላችሁ። አሁን ደግሞ አምላክ እንድናሟላቸው ከሚፈልጋቸው ብቃቶች ሦስተኛውን እንመልከት። ለሕይወትና ለደም አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። ሕይወት በይሖዋ ዘንድ ቅዱስ ነው። መሆንም ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የሕይወት ምንጭ እርሱ ነው። (መዝሙር 36:​9) ገና በእናቱ ማኅፀን ያለ ያልተወለደ ሕፃን ሕይወት እንኳን በይሖዋ ዘንድ በጣም ክቡር ነው! (ዘጸአት 21:​22, 23) ደም ሕይወትን ይወክላል። ስለዚህ ደም በአምላክ ዘንድ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው። (ዘሌዋውያን 17:​14) እንግዲያው አምላክ ሕይወትንና ደምን በሚመለከት የእርሱ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን መፈለጉ እንግዳ ነገር ሊሆንብን አይገባም።

18. ይሖዋ ለሕይወትና ለደም ያለው አመለካከት ምን እንድናድርግ ይጠይቅብናል?

18 ታዲያ ለሕይወትና ለደም የሚኖረን አክብሮት ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ልብ የሚያንጠለጥል ስሜት እንዲሰማን ለማድረግ ስንል ብቻ ሳያስፈልግ ሕይወታችንን ለአደጋ አናጋልጥም። አደጋ እንዳይደርስብን ወይም እንዳናደርስ ስለምንጠነቀቅ መኪናችንና ቤታችን ለአደጋ የተጋለጡ አለመሆናቸውን እናረጋግጣለን። (ዘዳግም 22:​8) ትንባሆ አናጨስም፣ ጫት አንቅምም ወይም ለደስታ ስንል ሱስ የሚያስይዙ ወይም አእምሮን የሚያደነዝዙ ዕፆችን አንወስድም። (2 ቆሮንቶስ 7:​1) ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የአምላክ ትእዛዝ ስለምናከብር የሌሎች ሰዎችን ደም በማንኛውም መንገድ ወደ ሰውነታችን አናስገባም። (ሥራ 15:​28, 29) ሕይወታችንን የምንወድ ብንሆንም የአሁኑን ሕይወታችን ለማቆየት ስንል የአምላክን ሕግ በመጣስ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችንን ለማጣት አንፈልግም!​— ማቴዎስ 16:​25

19. ለሕይወትና ለደም አክብሮት በማሳየታችን እንዴት እንደምንጠቀም ግለጽ።

19 ሕይወትንና ደምን በቅድስና መያዝ ከባድ ሸክም ይሆንብናልን? በጭራሽ አይሆንብንም! እስቲ አስቡት። ትንባሆ ከማጨስ ከሚመጣው የሳንባ ካንሰር ነጻ ሆኖ መኖር ሸክም ነው? በአደገኛ ዕፆች ሱስ የአእምሮና የአካል እስረኛ ከመሆን መገላገል ሸክም ነው? በኤድስ፣ በሄፓታይተስ ወይም ደም በመውሰድ በሚመጡ ሌሎች በሽታዎች ከመለከፍ መዳን ሸክም ነው? እንደነዚህ ያሉትን ጎጂ ልማዶችና ድርጊቶች ማስወገዳችን ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝልን መሆኑ ጥርጥር የለውም።​— ኢሳይያስ 48:​17

20. አንድ ቤተሰብ አምላክ ለሕይወት ያለውን አመለካከት በመያዙ የተጠቀመው እንዴት ነው?

20 አንድ ተሞክሮ እንመልከት። ከጥቂት ዓመታት በፊት የሦስት ወር ተኩል ነፍሰ ጡር የነበረች አንዲት የይሖዋ ምሥክር አንድ ቀን ምሽት ደም ይፈሳት ጀመር። ወዲያው ወደ ሆስፒታል ትወሰዳለች። ሐኪሙ ከመረመራት በኋላ ከነርሶቹ ለአንዷ ጽንሱን ማውጣት እንደሚኖርባቸው ሲነግራት ሰማች። ይሖዋ ያልተወለደውን ሕፃን ሕይወት እንዴት እንደሚመለከት ታውቅ ስለነበረ “ጽንሱ ገና አልሞተ ከሆነ እንዳታወጡት” ብላ ለዶክተሩ በመናገር ጽንሱን ለማስወረድ የቀረበውን ሐሳብ አጥብቃ ተቃወመች። ከዚያ በኋላም አልፎ አልፎ ደም ይፈሳት የነበረ ቢሆንም ከወራት በኋላ ጤነኛ የሆነ ወንድ ልጅ ከቀኗ በፊት ተገላገለች። ይህ ሕፃን በአሁኑ ጊዜ የ17 ዓመት ወጣት ሆኗል። እንዲህ ስትል ትናገራለች:- “ለልጃችን ይህን ሁሉ ነግረነዋል። ወደ ቆሻሻ መጣያ ባለመወርወሩ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል። በሕይወት ሊኖር የቻለበት ብቸኛ ምክንያት እኛ ይሖዋን የምናገለግል መሆናችን እንደሆነ ያውቃል!” በእርግጥም ይህ ቤተሰብ አምላክ ለሕይወት ያለውን አመለካከት ማክበሩ ከባድ ሸክም አልሆነበትም!

ከተደራጁት የይሖዋ ሕዝቦች ጋር ማገልገል

21, 22. (ሀ) ይሖዋ ከእነማን ጋር ሆነን እንድናገለግለው ይጠብቅብናል? (ለ) የተደራጁት የአምላክ ሕዝቦች ተለይተው ሊታወቁ የሚችሉት እንዴት ነው?

21 ሕይወታችንን አምላክ ካወጣቸው መስፈርቶች ጋር ለማስተካከል በምናደርገው ጥረት ብቻችንን አይደለንም። ይሖዋ በዚህች ምድር ላይ የራሱ ሕዝቦች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ሆነን እንድናገለግለው ይጠብቅብናል። ይህም አምላክ ከእኛ ወደሚፈልገው አራተኛ ነገር ይመራናል። ይሖዋን በመንፈስ ከሚመራው ድርጅቱ ጋር ሆነን ማገልገል አለብን።

22 ይሁን እንጂ የአምላክን የተደራጁ ሕዝቦች እንዴት ለይተን ለማወቅ እንችላለን? በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገኙት መስፈርቶች መሠረት እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይዋደዳሉ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት አላቸው፣ የአምላክን ስም ከፍ አድርገው ይመለከቱታል፣ ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብካሉ፣ የዚህ ክፉ ዓለም ክፍል አይደሉም። (ማቴዎስ 6:​9፤ 24:​14፤ ዮሐንስ 13:​34, 35፤ 17:​16, 17) በምድር ላይ እነዚህ የእውነተኛ ክርስትና መለያ ምልክቶች በሙሉ ያሉት ሃይማኖታዊ ድርጅት አንድ ብቻ ነው። ይህም የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት ነው!

23, 24. ይሖዋን ከተደራጁት ሕዝቦቹ ጋር ሆኖ ማገልገል ከባድ ሸክም እንዳልሆነ እንዴት በምሳሌ ማስረዳት እንችላለን?

23 ከእነዚህ የተደራጁ ሕዝቦች ጋር ሆኖ ይሖዋን ማገልገል ከባድ ሸክም ነው? በፍጹም አይደለም! እንዲያውም ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የሚገኙበትን ዓለም አቀፋዊ የሆነ ቤተሰብ ፍቅርና ድጋፍ ማግኘት መቻል በጣም ውድ የሆነ መብት ነው። (1 ጴጥሮስ 2:​17) ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አደጋ ከደረሰበት መርከብ በሕይወት ተርፋችሁ ሳትሰጥሙ ለመቆየት በመጣጣር ላይ ናችሁ እንበል። በጣም ዝላችሁ ‘በቃ አለቀልኝ’ ብላችሁ ስታስቡ ለድንገተኛ አደጋ በተዘጋጀ ጀልባ ውስጥ ያለ ሰው እጁን ሰድዶ ጎትቶ ያወጣችኋል። አዎን፣ በሕይወት የተረፉ ሌሎች ሰዎችም አሉ! ለድንገተኛ አደጋ በተዘጋጀው ጀልባ ውስጥ ሆናችሁ እንዳይሰጥሙ በመታገል ላይ የሚገኙ ሌሎች ሰዎችን እግረ መንገዳችሁን አየጎተታችሁ በማውጣትና ተራ በተራ በመፈራረቅ ጀልባዋን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለማውጣት ትቀዝፋላችሁ እንበል።

24 የእኛስ ሁኔታ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ አይደለምን? በጣም አደገኛ ከሆነው ከዚህ ክፉ ዓለም “ባሕር” ተጎትተን ወጥተን ወደ ይሖዋ ምድራዊ ድርጅት “ጀልባ” ገብተናል። በዚህ ጀልባ ውስጥ ሆነን ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ጎን ለጎን እያገለገልን ጽድቅ ወደሚሰፍንበት አዲስ ዓለም የባሕር “ዳርቻ” በመቅዘፍ ላይ ነን። በዚህ መንገድ ላይ እያለን የኑሮ ጫናዎች ደክመን እንድንዝል ቢያደርጉን ባልደረቦቻችን የሆኑት እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሚሰጡን እርዳታና ማጽናኛ ምንኛ አመስጋኞች ነን!​— ምሳሌ 17:​17

25. (ሀ) አሁንም ገና በዚህ ክፉ ዓለም “ባሕር” ውስጥ ላሉት ሰዎች ምን ግዴታ አለብን? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንወያይበት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የትኛው ብቃት ነው?

25 ገና “ከባሕሩ” ውስጥ ያልወጡት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችስ? ወደ ይሖዋ ድርጅት እንዲመጡ እነርሱን የመርዳት ግዴታ አለብን፤ አይደለም እንዴ? (1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 4) አምላክ ምን እንደሚፈልግባቸው እንዲያውቁ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ይህም አምላክ ወደሚፈልግብን አምስተኛ ነገር ይመራናል። ታማኝ የአምላክ መንግሥት ሰባኪዎች መሆን ይገባናል። ይህ ብቃት ምን ማድረግን እንደሚጠይቅ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

ታስታውሳለህን?

◻ የአምላክ ትእዛዞች ከባዶች አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?

◻ ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም የምንችለው እንዴት ነው?

◻ አምላክ ለትክክለኛ ሥነ ምግባር ካወጣቸው መስፈርቶች ጋር በሚጣጣም መንገድ መኖር እና የአምላክን እውነት መቀበል ሸክም ያልሆነው ለምንድን ነው?

◻ አምላክ ለሕይወትና ለደም ያለው አመለካከት ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል?

◻ አምላክ ከእነማን ጋር ሆነን እንድናገለግለው ይጠብቅብናል? እነርሱንስ ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከፍጥረት መጽሐፍና ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ እንማራለን

[ምንጮች]

አዞ:- By courtesy of Australian International Public Relations; ድብ:- Safari-Zoo of Ramat-Gan, Tel Aviv

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ