ሃይማኖታዊ ነፃነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሃይማኖት ነፃነት እንደ አንድ መሠረታዊ መብት የሚቆጠር ቢሆንም በ1940ዎቹ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚቃወም ከፍተኛ ሕዝባዊ ዓመፅ አገሪቱን አጥለቅልቆ ነበር
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተዋግተውለታል። እንዲያውም አንዳንዶች ሕይወታቸውን ሰውተውለታል። በእርግጥም የሰው ልጅ ካሉት በጣም ውድ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ለመሆኑ ይህ ነገር ምንድን ነው? ነፃነት ነው! ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ነፃነትን “የመምረጥና የመረጡትን ነገር የማድረግ ችሎታ” በማለት ይፈታዋል። በመቀጠልም የሚከተለውን ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል:- “ከሕግ አንፃር ሲታይ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ ያልሆነ፣ አላስፈላጊ ወይም ምክንያታዊነት የጎደለው ገደብ እስካልጣለባቸው ድረስ ሰዎች ነፃ ናቸው። ኅብረተሰቡ መብታቸውን ማለትም መሠረታዊ የሆነ ነፃነታቸውን፣ የፈጠራ ችሎታቸውንና ጥቅማቸውን ሊያስጠብቅላቸው ይገባል።”
ጽንሰ ሐሳቡ ሲታይ እንዲያው ቀላል ይመስላል። ሆኖም የነፃነት ገደቦች የት ላይ መጣል እንዳለባቸው ሰዎች በአንድ ሐሳብ እንዲስማሙ ማድረግ ጨርሶ የሚቻል አይመስልም። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች መንግሥት የዜጎቹን መብት የሚያስጠብቁ ሕጎች ማውጣት አለበት ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች ደግሞ እስከ ጭራሹ እነዚህ ሕጎች ነፃነት የሚነፍጉ ማነቆዎች ስለሆኑ ዜጎች ከእነዚህ ሕጎች ነፃ መውጣት ያስፈልጋቸዋል ብለው ይከራከራሉ! በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ነፃነት ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም አለው።
ስለ ሃይማኖታዊ ነፃነት ምን ማለት ይቻላል?
ከሁሉም ይበልጥ የጦፈ ክርክር የሚደረግበት ነፃነት “የፈለጉትን የማመንና የመረጡትን እምነት የማራመድ መብት” የሚል ፍቺ የተሰጠው የሃይማኖት ነፃነት ሳይሆን አይቀርም። በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ መሠረት “ማንም ሰው የአመለካከት፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት አለው።” ይህም “ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን” የመለወጥ መብቱንና “በትምህርት፣ በድርጊት፣ በአምልኮ ሥርዓትና በበዓል መልክ በማክበር ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የመግለጽ” ነፃነቱን ጭምር የሚያጠቃልል ነው።— አንቀጽ 18
ለዜጎቹ ከልብ የሚቆረቆር ማንኛውም መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት ይሰጣል ብለን እንደምንጠብቅ የታወቀ ነው። የሚያሳዝነው ግን ሁሌ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ አይገኝም። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ በማለት ይዘግባል:- “ሃይማኖት የብዙ ሰዎችን ጥልቅ ስሜት ይነካል። አንዳንድ መንግሥታት ከአንድ ሃይማኖት ጋር የጠበቀ ትስስር ይመሰርቱና የሌላ እምነት ተከታዮችን ለፖለቲካዊ ሥልጣናቸው እንደሚያሰጉ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሃይማኖቶች ከፖለቲካዊ መንግሥት ይልቅ ለአምላክ ታማኝ መሆንን ሊያስበልጡ ስለሚችሉ አንድ መንግሥት አንድን ሃይማኖት ለፖለቲካ አደገኛ እንደሆነ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል።”
ከዚህ የተነሳ አንዳንድ መንግሥታት በሃይማኖት ላይ እገዳዎችን ይጥላሉ። ጥቂት መንግሥታት ደግሞ ማንኛውንም እምነት ማራመድን እስከ ጭራሹ ይከለክላሉ። ሌሎች ደግሞ የአምልኮ ነፃነትን እንደሚደግፉ ይናገሩ እንጂ ማንኛውንም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በጥብቅ ይቆጣጠራሉ።
ለምሳሌ ያህል በሜክሲኮ ለብዙ ዓመታት ሰፍኖ የቆየውን ሁኔታ ተመልከት። ሕገ መንግሥቱ ምንም እንኳ የሃይማኖት ነፃነት ቢሰጥም የሚከተለውን ገደብ አስቀምጧል:- “ለአምልኮ የሚያገለግሉ አብያተ ክርስቲያናት በፌደራላዊ አስተዳደር የተወከለው መንግሥት ንብረቶች ናቸው፤ የትኛው በአገልግሎቱ መቀጠል እንደሚችልና እንደማይችል የሚወስነው ፌደራላዊው መንግሥት ነው።” ይህን እገዳ ለማንሳት በ1991 በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። የሆነ ሆኖ ይህ ምሳሌ የሃይማኖት ነፃነት በተለያዩ አገሮች የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ያሳያል።
ሌላ ዓይነት ሃይማኖታዊ ነፃነት
አንተ በምትኖርበት አገር የሃይማኖት ነፃነት አለን? ካለ በምን መልክ ተቀምጧል? አምላክን በመረጥከው መንገድ ማምለክ ትችላለህ ወይስ የመንግሥትን ሃይማኖት እንድትከተል ትገደዳለህ? ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ማንበብም ሆነ ማሰራጨት ተፈቅዶልሃል ወይስ እንደዚህ ዓይነት ጽሑፎች ፈጽሞ በመንግሥት የታገዱ ናቸው? ስለ እምነትህ ለሌሎች መናገር ትችላለህ ወይስ ይህ ድርጊት የሌሎችን ሃይማኖታዊ መብት እንደመጋፋት ይቆጠራል?
ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ እንደየምትኖርበት አገር ይለያያል። ደስ የሚለው ግን የምትኖርበት አካባቢ የማይወስነው ሃይማኖታዊ ነፃነት አለ። ኢየሱስ በ32 እዘአ በኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት ለተከታዮቹ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ትሆናላችሁ፤ እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏቸው ነበር።— ዮሐንስ 8:31, 32 የ1980 ትርጉም
ኢየሱስ ይህን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? አይሁዳውያን አድማጮቹ ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ የሚወጡበትን ጊዜ ይናፍቁ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከፖለቲካዊ ጭቆና ነፃ ስለመውጣት እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቀጥሎ በሚቀርበው ርዕስ እንደምንመለከተው ለደቀ መዛሙርቱ ከዚህ በጣም የተሻለ ነገር ቃል እየገባላቸው ነበር።