የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 2/1 ገጽ 20-23
  • በይሖዋ ላይ ያለኝ ትምክህት ደግፎ አቁሞኛል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በይሖዋ ላይ ያለኝ ትምክህት ደግፎ አቁሞኛል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በይሖዋ ላይ ትምክህት ማሳደር
  • ከመንፈሳዊ ሥራ ብርታት ማግኘት
  • እየተስፋፋ የሄደው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
  • ቤቴል ውስጥ የተሰጡኝ ሥራዎች
  • የቤቴል ሕንፃዎቻችን
  • ውድ መብቶች
  • ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ይምጡና ይጎብኙ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ይሖዋን የሚያገለግል አንድነት ያለው ቤተሰብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 2/1 ገጽ 20-23

በይሖዋ ላይ ያለኝ ትምክህት ደግፎ አቁሞኛል

አዤኖር ዳ ፒሻው እንደተናገረው

ፓውሎ የተባለው አንድ ልጃችን ገና የ11 ወር ሕፃን ሳለ ብሮንካይት ይዞት ሞተ። ከሦስት ወራት በኋላ ነሐሴ 15, 1945 ውዷ ባለቤቴ በሳንባ ምች ሞተች። የዚያን ጊዜ 28 ዓመቴ ነበር፤ እነዚህ መከራዎች መደራረባቸው ሐዘንና ጭንቀት ውስጥ ከተተኝ። ሆኖም በይሖዋና እሱ በሰጠን ተስፋዎች ላይ ያለኝ ትምክህት ደግፎ አቁሞኛል። እንዲህ ዓይነቱን ትምክህት እንዴት ላገኝ እንደቻልኩ ልንገራችሁ።

ጥር 5, 1917 በብራዚል ባሃይ ግዛት ሳልቫዶር ውስጥ ከተወለድኩበት ጊዜ አንስቶ እናቴ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ቅዱሳንን” እንዳመልክ ታስተምረኝ ነበር። እንዲያውም እኔንና ወንድሞቼን ሌሊት ከቀሰቀሰችን በኋላ አብረን እንድንጸልይ ታደርግ ነበር። ሆኖም ወላጆቼ ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ-ብራዚላውያን የቩዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በሚከናወኑበት በካንዶምብሌ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ነበር። ምንም እንኳ ለእነዚህ እምነቶች አክብሮት የነበረኝ ቢሆንም በካቶሊክ እምነት ቅዱሳን ተደርገው በሚታዩት ሰዎችም ሆነ በካንዶምብሌ ላይ ምንም ትምክህት አልነበረኝም። በተለይ በጣም ያበሳጨኝ በእነዚህ ሃይማኖቶች ውስጥ በግልጽ የሚታየው የዘር መድልዎ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ሁለት ታላላቅ ወንድሞቼ ሥራ ለመፈለግ ከቤት ወጡ። ከዚያም አባቴ ቤተሰቡን ጥሎ ሄደ። ስለዚህ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴንና ታናሽ እህቴን ለመርዳት ሥራ መፈለግ ነበረብኝ። ይህ ከሆነ ከ16 ዓመት በኋላ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ የሥራ ባልደረባዬ ከነበረ ሰው ጋር ያደረግኋቸው ውይይቶች በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አስከትለዋል።

በይሖዋ ላይ ትምክህት ማሳደር

በ1942 ከፈርናንዶ ቴሌዝ ጋር ተዋወቅሁ። ፈርናንዶ “ቅዱሳንን” ማምለክ ስሕተት እንደሆነ ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:​14፤ 1 ዮሐንስ 5:​21) በመጀመሪያ ምንም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። ይሁን እንጂ ቅንነቱና የተለያዩ ዘሮች ላላቸው ሰዎች የሚሰጠው ትኩረት ሳበኝ፤ በተለይ ስለ አምላክ መንግሥትና ምድራዊ ገነት ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማድነቅ ጀመርኩ። (ኢሳይያስ 9:​6, 7፤ ዳንኤል 2:​44፤ ራእይ 21:​3, 4) እሱም የነበረኝን ፍላጎት ስለ ተረዳ መጽሐፍ ቅዱስና አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ሰጠኝ።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እንድገኝ ያቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። ቡድኑ የሚያጠናው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ያሳተመውን ሃይማኖት የተባለ (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ነበር። በጥናቱ ስለ ተደሰትኩ በሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በተለይ እኔን የማረከኝ የዘር መድልዎ አለመኖሩና ወዲያውኑ ተቀባይነት ማግኘቴ ነበር። በዚያን ወቅት ከሌንዱራ ጋር መጠናናት ጀመርኩ። እየተማርኩ ስላለሁት ነገር ስነግራት ከእኔ ጋር ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች መሄድ ጀመረች።

በስብሰባዎቹ ላይ በጣም የነካኝ ሌላው ነገር ለስብከቱ ሥራ ጉልህ ስፍራ መሰጠቱ ነበር። (ማቴዎስ 24:​14፤ ሥራ 20:​20) አቅኚዎች ተብለው የሚጠሩት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ስላበረታቱኝ ከሥራ መልስና ወደ ሥራ ስሄድ በባቡር ውስጥ ለተሳፈሩ ሌሎች መንገደኞች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መስበክ ጀመርኩ። ፍላጎት ያለው ሰው ሳገኝ አድራሻውን ወስጄ ተመላልሼ በመጠየቅ ፍላጎቱን ለማሳደግ ጥረት አደርግ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በይሖዋና እሱ እየተጠቀመበት ባለው ድርጅት ላይ ያለኝ ትምክህት እያደገ ሄደ። ስለዚህ ስለ ክርስቲያናዊ ጥምቀት የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ካዳመጥኩ በኋላ ሚያዝያ 19, 1943 በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ተጠመቅሁ። በዚያው ቀን በመደበኛው ከቤት ወደ ቤት አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ተካፈልኩ።

ከሁለት ሳምንት በኋላ ግንቦት 5 እኔና ሌንዱራ ተጋባን። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች በሳልቫዶር ከተማ ውስጥ ነሐሴ 1943 ባደረጉት የመጀመሪያ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሌንዱራ ተጠመቀች። የ1973 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ይህን ስብሰባ አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ምንም እንኳ ቀሳውስት በሳልቫዶር የሕዝብ ንግግሩን ለማስቆም ቢሳካላቸውም ቀደም ሲል ንግግሩ በሰፊው ለሕዝብ ተዋውቆ ነበር።” ከባድ ስደት ባለበት ወቅት እንኳ የይሖዋ አመራር እንዳልተለየን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማየቴ በእሱ ላይ ያለኝ ትምክህት ከፍ ብሏል።

መጀመሪያ ላይ እንደተናገርኩት ውዷ ባለቤቴ ሌንዱራ ከተጠቀመች ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም ልጃችን ከሞተ ከሦስት ወራት በኋላ ሞተች። ሌንዱራ ገና 22 ዓመቷ ነበር። ይሁን እንጂ በይሖዋ ላይ ያለኝ ትምክህት በእነዚያ አስቸጋሪ ወራት ወቅት ደግፎ አቁሞኛል።

ከመንፈሳዊ ሥራ ብርታት ማግኘት

በ1946 ማለትም ባለቤቴንና ልጄን ካጣሁ ከአንድ ዓመት በኋላ በዚያን ወቅት በሳልቫዶር ይገኝ በነበረ አንድ ጉባኤ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። በዚያው ዓመት በብራዚል በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በመጀመሩ በባሃይ ግዛት ውስጥ የመጀመሪያው የትምህርት ቤቱ መሪ ሆንኩ። ከዚያ በኋላ በጥቅምት 1946 በሳኦ ፓውሎ ከተማ ውስጥ “ደስተኛ ሕዝቦች” የተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ተካሄደ። ለአሥር ዓመት ያህል ቀጥሮ ሲያሠራኝ የቆየው የፋብሪካው ባለቤት ለሥራው በጣም ስለማስፈልግ መሄድ እንደሌለብኝ ነገረኝ። ሆኖም በዚህ ትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘት ለእኔ ምን ትርጉም እንዳለው ስነግረው ስጦታ ሰጠኝና መልካም ምኞቱን ገልጾ አሰናበተኝ።

በሳኦ ፓውሎ ማዘጋጃ ቤት የቲያትር አዳራሽ የተደረገው ስብሰባ የተካሄደው የብራዚል ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውን የፖርቱጊዝ ቋንቋን ጨምሮ በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛ፣ በሃንጋሪ ቋንቋ፣ በፖላንድ ቋንቋና በሩስያኛ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ንቁ! መጽሔት ለመጀመሪያ ጊዜ በፖርቱጊዝ ቋንቋ ታትሞ ወጣ። በዚህ 1,700 የሚያህሉ ሰዎች የሕዝብ ንግግሩን ባዳመጡበት ስብሰባ በጣም በመነካቴ ኅዳር 1, 1946 የአቅኚነት አገልግሎት ለመጀመር ማመልከቻ ሞላሁ።

በዚያን ጊዜ በአቅኚነት ሥራችን በፎኖግራፍ በሰፊው እንጠቀም ነበር። ብዙውን ጊዜ ለምናነጋግራቸው ሰዎች “ጥበቃ” የተባለውን ንግግር እናጫውትላቸው ነበር። ከዚያ በኋላ እንዲህ እንላለን:- “በዓይን ከማይታይ ጠላታችን ራሳችንን ለመከላከል በዓይን ከማይታይ አንድ ወዳጅ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ያስፈልገናል። ይሖዋ ከሁሉ የበለጠ ወዳጃችን ከመሆኑም በተጨማሪ ከጠላታችን ከሰይጣን የበለጠ ኃይል አለው። ስለዚህ ከሰይጣን ራሳችንን ለመከላከል ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት አለብን።” ከዚያ በኋላ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሰጠውን ጥበቃ የተባለውን (የእንግሊዝኛ) ቡክሌት እናበረክት ነበር።

በሪዮ ዴ ጃኔሮ በሚገኘው የካሬኦካ ጉባኤ ውስጥ በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል ግብዣ ሲቀርብልኝ በአቅኚነት ማገልገል ከጀመርኩ ገና አንድ ዓመት አልሞላኝም ነበር። አንዳንድ ጊዜ በካሬኦካ ውስጥ ከባድ ተቃውሞ ያጋጥመን ነበር። በአንድ ወቅት የአገልግሎት ጓደኛዬ የነበረው ኢቫን ብሬነርን የቤቱ ባለቤት ደበደበው። ጎረቤቶቹ ፖሊስ ጠርተው ሁላችንም ወደ ፖሊስ ጣቢያው ተወሰድን።

ምርመራ በሚካሄድበት ወቅት በጣም ተናድዶ የነበረው የቤቱ ባለቤት የአካባቢውን ሰላም ይበጠብጣሉ ሲል ከሰሰን። የፖሊስ አዛዡ ዝም እንዲል አዘዘው። ከዚያ በኋላ የፖሊስ አዛዡ ወደ እኛ ዞር አለና በለዘበ ድምፅ መሄድ ትችላላችሁ አለን። ከሳሻችንን ያዘውና ሰው በመደብደብ ወንጀል ከሰሰው። እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች በይሖዋ ላይ ያለኝን ትምክህት ከፍ እንዲል አድርገዋል።

እየተስፋፋ የሄደው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት

ሐምሌ 1, 1949 በቤቴል እንዳገለግል ስጋበዝ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ። ቤቴል በየአገሩ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚጠሩበት ስም ነው። በዚያን ጊዜ የብራዚል ቤቴል በሪዮ ዴ ጃኔሮ 330 ሊሲኒዮ ካርዶሱ ጎዳና ይገኝ ነበር። በዚያን ወቅት የቤቴል ቤተሰብ አባላት 17 ብቻ ነበሩ። ለጥቂት ጊዜ በአካባቢው በሚገኘው በኢንዤኒዮ ደ ዴንትሩ ጉባኤ ስሰበሰብ ከቆየሁ በኋላ ከሪዮ ዴ ጃኔሮ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ ቤልፎር ሮሹ ውስጥ በሚገኘው ብቸኛ ጉባኤ ውስጥ በሰብሳቢ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ።

ቅዳሜና እሑድ በጣም ሥራ ይበዛብን ነበር። ቅዳሜ ቅዳሜ ወደ ቤልፎር ሮሹ በባቡር እሄድና ከሰዓት መስክ አገልግሎት እካፈላለሁ። ከዚያም በዚያው ምሽት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ እገኝ ነበር። ቅዳሜ ማታ ወንድሞች ቤት ካደርኩ በኋላ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት በመስክ አገልግሎት እካፈላለሁ። እሑድ ከሰዓት በሕዝብ ስብሰባና መጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ከተገኘሁ በኋላ ማታ በሦስት ሰዓት ተኩል ወደ ቤቴል እመለሳለሁ። ዛሬ በቤልፎር ሮሹ ውስጥ 18 ጉባኤዎች ይገኛሉ።

በእንዲህ ዓይነት ፕሮግራም ለሦስት ዓመት ተኩል ከቆየሁ በኋላ በ1954 ወደ ሪዮ ዴ ጃኔሮ ተመልሼ በሳኦ ክርስታቫው ጉባኤ ውስጥ በሰብሳቢ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ። ለቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከዚህ ጉባኤ ጋር አገልግያለሁ።

ቤቴል ውስጥ የተሰጡኝ ሥራዎች

ቤቴል ውስጥ የተሰጠኝ የመጀመሪያ ሥራ ማኅበሩ ለነበረችው አንዲት መኪና የሚሆን ጋራዥ መሥራት ነበር። ይህች መኪና የ1949 ሞዴል ዕቃ መጫኛ ዶጅ ስትሆን ቡና ዓይነት ቀለም ስለነበራት ቸኮሌት የሚል ቅጽል ስም አውጥተንላት ነበር። ጋራዡ ተሠርቶ ሲያልቅ ማዕድ ቤት ውስጥ ተመድቤ ለሦስት ዓመት አገለገልኩ። ከዚያ በኋላ ወደ ኅትመት ክፍል ተዛውሬ መሥራት ጀመርኩ። በኅትመት ክፍሉ ውስጥ እንደ ደብዳቤዎችና የመንግሥት አገልግሎታችን ያሉት አነስተኛ ጽሑፎች ይታተሙ ነበር። እዚህ ክፍል ውስጥ ማገልገል ከጀመርኩ አሁን ከ40 ዓመታት በላይ ሆኖኛል።

አብዛኞቹ የኅትመት መሣሪያዎቻችን ያገለገሉ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ለብዙ ዓመታት እንጠቀምባት የነበረችውና በአብርሃም ሚስት ስም ሣራ ብለን በፍቅር የምንጠራት ያረጀች ማሽን ነበረችን። ይህች ማሽን በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ፋብሪካ ውስጥ ለብዙ ዓመታት አገልግላለች። ከዚያ በኋላ በ1950ዎቹ ወደ ብራዚል ተላከች። እዚህ ብራዚል ውስጥ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በማተም የአብርሃም ሚስት እንደነበረችው እንደ ሣራ በስተርጅናዋ ፍሬ አፍርታለች።

በብራዚል በሚገኘው ፋብሪካ ውስጥ የሚታተሙትን ጽሑፎች ብዛት ስመለከት ሁልጊዜ ይገርመኛል። በ1953 ዓመቱን ሙሉ ያተምነው 324,400 መጽሔቶች ቢሆንም አሁን በየወሩ ከሦስት ሚልዮን በላይ መጽሔቶች ይመረታሉ!

የቤቴል ሕንፃዎቻችን

ብራዚል ውስጥ ለብዙ ዓመታት በየጊዜው የቤቴል ሕንፃዎች እየጨመሩ ሲሄዱ መመልከት በጣም የሚያስደስት ነበር። በ1952 በሪዮ ዴ ጃኔሮ ከሚገኘው የቤቴል መኖሪያችን በስተጀርባ ሁለት ፎቅ ያለው የፋብሪካ ሕንፃ ሠራን። ከዚያ በ1968 ቤቴል በሳኦ ፖሎ ከተማ ውስጥ ወደ ተሠራ አዲስ ሕንፃ ተዛወረ። ወደዚያ ስንዛወር 42 አባላት ብቻ ለነበሩት የቤቴል ቤተሰባችን ሁሉም ነገር በጣም የሚሰፋን መስሎን ነበር። ይህ ሕንፃ ወደፊት ለምናደርገው ጭማሪ ሁሉ ያገለግለናል ብለን አስበን ነበር። ሆኖም በ1971 ሁለት ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃዎች የተሠሩ ከመሆናቸውም በላይ አጠገባችን የሚገኝ አንድ የፋብሪካ ሕንፃ ተገዝቶ በአዲስ መልክ ከተሠራ በኋላ ከዚህ ሕንፃ ጋር እንዲያያዝ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1975 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር አድጎ ከ100,000 በላይ ስለሆነ ተጨማሪ ቦታ አስፈለገ።

ስለዚህ ከሳኦ ፓውሎ 140 ኪሎ ሜትር ያህል በምትርቀው ሲዛርዮ ላንዤ በተባለች ትንሽ ከተማ አቅራቢያ አዳዲስ ሕንፃዎች ተሠሩ። በ1980 መቶ ሰባ አባላት ያሉት የቤቴል ቤተሰባችን ወደ እነዚህ አዳዲስ ሕንፃዎች ተዛወረ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የመንግሥቱ ሥራ በአስደናቂ ሁኔታ አድጓል። በአሁኑ ጊዜ በብራዚል ውስጥ ከ410,000 በላይ የሚሆኑ አስፋፊዎች ዘወትር በስብከቱ ሥራ ይካፈላሉ! የእነዚህን ሁሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚታተምባቸው አዳዲስ ፋብሪካዎችንና የቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚኖሩባቸው አዳዲስ ሕንፃዎችን መሥራታችንን መቀጠል አስፈልጎናል። በአሁኑ ጊዜ 1,100 ያህል የቤቴል ቤተሰብ አባላት አሉን!

ውድ መብቶች

የቤቴል አገልግሎትን እንደ ውድ መብት አድርጌ እመለከተዋለሁ። ስለዚህ በወጣትነቴ እንደገና ማግባት አስቤ የነበረ ቢሆንም በቤቴል ውስጥ ባገኘኋቸው መብቶችና በስብከቱ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ ማተኮር መረጥኩ። እዚህ በኅትመት ክፍሉ ውስጥ ከብዙ ወጣቶች ጋር ለማገልገልና በተመደቡበት ሥራ ማሠልጠን በመቻሌ ተደስቻለሁ። እነሱን እንደ ልጆቼ አድርጌ ለመያዝ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ። ቅንዓታቸውና ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅራቸው ለእኔ ትልቅ የማበረታቻ ምንጭ ሆኖልኛል።

ሌላው ያገኘሁት መብት ለብዙ ዓመታት ከተለያዩ ጥሩ ወንድሞች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ አብሮ መኖር ነው። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ የባሕርይ ልዩነቶች ፈታኝ ሆነው ይገኛለሁ። ሆኖም ከሌሎች ፍጽምና መጠበቅ እንደማይገባኝ ተምሬአለሁ። አነስተኛ ችግሮችን እንደ ትላልቅ ተራራዎች አድርጌ ከመመልከት ወይም ለራሴ ከፍተኛ ግምት ከመስጠት ለመቆጠብ ጥረት አደርጋለሁ። የራሴን ስሕተቶች መገንዘቤ የሌሎችን ስሕተቶች እንድታገሥ ረድቶኛል።

ሌላው ያገኘሁት ውድ መብት በዩናይትድ ስቴትስ በተደረጉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት መቻሌ ነው። ከእነዚህ ትልልቅ ስብሰባዎች አንዱ በ1963 በያንኪ ስታዲዮም የተደረገው “የዘላለም ምሥራች” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ ሲሆን ሌላው ደግሞ በ1969 በዚያው ቦታ የተደረገው “ሰላም በምድር” የተባለው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ነበር። እዚያ በነበርኩበት ወቅት በአቅራቢያው ማለትም በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት ለመጎብኘት በመቻሌ ተደስቻለሁ።

በተጨማሪም ለአሥር ዓመታት ያህል ከሌሎች ሽማግሌዎች ጋር በየተራ የቤቴል ቤተሰብ የጠዋት አምልኮን የመምራት መብት አግኝቼአለሁ። ሆኖም ለእኔ ከፍተኛ ደስታና ማበረታቻ ያስገኘልኝ ከሁሉ የበለጠው መብት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ቅን ልቦና ላላቸው ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ማድረስ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነርቭ በሽታ ያስከተለብኝን ችግር መቋቋም አስፈልጎኛል። በቤቴል ማስታመሚያ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች የሚያደርጉልኝ ፍቅራዊ እንክብካቤ የማያቋርጥ የእርዳታና የመጽናናት ምንጭ ሆኖልኛል። ለእውነተኛ አምልኮው የተቻለኝን ያህል መሥራቴን እንድቀጥል ብርታት እንዲሰጠኝ በሙሉ ትምክህት ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሁን የምኖርበት የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በ1945 ከሞተችው ባለቤቴ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ