የአንባብያን ጥያቄዎች
የነሐሴ 15, 1996 “መጠበቂያ ግንብ” “በመከራው የመጨረሻ ክፍል ወደ ይሖዋ የሸሸ ‘ሥጋ ለባሽ’ ሁሉ ይድናል” ይላል። ይህ አባባል ከታላቁ መከራ የመጀመሪያ ክፍል በኋላ ከአምላክ ጎን የሚሰለፉ ብዙ አዳዲስ ሰዎች እንደሚኖሩ የሚያመለክት ነውን?
ለመግለጽ የተፈለገው ሐሳብ ይህ አይደለም።
በማቴዎስ 24:22 ላይ ያሉት የኢየሱስ ቃላት በከፍተኛ ደረጃ የሚፈጸሙት በመጪው ታላቅ መከራ የመጀመሪያ ክፍል በሃይማኖት ላይ ከሚደርሰው ጥቃት በሕይወት በሚተርፉ ሰዎች ላይ ነው። ርዕሰ ትምህርቱ እንዲህ ብሎ ነበር:- “‘ሥጋ ለባሽ’ የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎችም ሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመጀመሪያው የመከራው ክፍል ታላቂቱ ባቢሎን በአንድ ጊዜ ስትደመሰስ ከጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የሚድኑ መሆኑን አስታውስ።”
እነዚህ የታመኑ ሰዎች በመጨረሻው የመከራው ክፍል ኢየሱስና ሰማያዊ ሠራዊቱ እርምጃ በሚወስዱበት ወቅት ምንም ዓይነት ጉዳት አይደርስባቸውም። ይሁን እንጂ ከዚህ የመከራ ክፍል በሕይወት የሚተርፉት እነማን ናቸው? ራእይ 7:9, 14 ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች በሕይወት እንደሚተርፉ ይገልጻል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችስ? በመጠበቂያ ግንብ 16/111 ላይ የወጣው “የአንባብያን ጥያቄዎች” ቅቡዓን ቀሪዎች ወደ ሰማይ ስለሚወሰዱበት ጊዜ ቁርጥ ያለ ሐሳብ መስጠት የማንችልበትን ምክንያት አብራርቷል። ስለዚህ በቅርቡ የወጣው ርዕሰ ትምህርት (ነሐሴ 15, 1996) በጉዳዩ ላይ ቁርጥ ያለ ሐሳብ ሳይሰጥ “በተመሳሳይም በመከራው የመጨረሻ ክፍል ወደ ይሖዋ የሸሸ ‘ሥጋ ለባሽ’ ሁሉ ይድናል” የሚል አጠቃላይ አስተያየት ሰንዝሯል።
ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ አዳዲስ ሰዎች እውነትን አውቀው ከአምላክ ጎን ይሰለፉ ወይም አይሰለፉ እንደሆነ ለማወቅ በማቴዎስ 24:29-31 ላይ የተመዘገቡትን የኢየሱስ ቃላት ልብ በል። ታላቁ መከራ ከፈነዳ በኋላ የሰው ልጅ ምልክት ይታያል። ኢየሱስ የምድር ወገኖች ዋይ ዋይ ይላሉ ብሏል። ሁኔታው አንቅቷቸው ንስሐ ስለገቡ፣ በአምላክ ጎን ስለ ተሰለፉና እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ስለሆኑ ሰዎች ምንም ነገር አልተናገረም።
በተመሳሳይም የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሰው ልጅ ከመጣ በኋላ ቀደም ሲል ባደረጉት ወይም ሳያደርጉ በቀሩት ነገር መሠረት ፍርድ በመስጠት ሰዎችን እንደሚለያያቸው ይገልጻል። ኢየሱስ ፍየል መሰል ጠባይ ያሳዩ ሰዎች በድንገት ተለውጠው በግ መሰል ስለ መሆናቸው የተናገረው ነገር የለም። ሰዎች ቀደም ሲል ባደረጓቸው ነገሮች መሠረት ለመፍረድ ይመጣል።— ማቴዎስ 25:31-46
ሆኖም አሁንም ቢሆን በዚህ ረገድ ቁርጥ ያለ ሐሳብ የምንሰጥበት ምክንያት የለም። የአምላክ ሕዝቦች ቅቡዓንም ሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች፣ አሁን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማለትም መስበክና ደቀ መዛሙርት ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ማርቆስ 13:10) ከዚህ በታች የሚገኘውን ማሳሰቢያ ልብ የምንልበት ጊዜ አሁን ነው:- “አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፣ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።”— 2 ቆሮንቶስ 6:1, 2