በአምላክ ለማመን—የግድ ተዓምር ማየት ያስፈልጋል ?
አልበርት አምላክን መፈለግ የጀመረው በ20ዎቹ ዕድሜው መጀመሪያ ላይ ሳለ ነበር። በርካታ ሃይማኖቶችን ቢመረምርም ምንም የሚያረካ ነገር አላገኘም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ሲያነብ አምላክ እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ እና ሙሴ ከመሳሰሉት ግለሰቦች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደነበረው ተማረ። አልበርት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለትን አምላክ እየወደደው መጣ። ይሁን እንጂ አምላክ በእርግጥ እንዳለ እርግጠኛ መሆን ይችላልን?
አልበርት አንድ ምሽት ላይ መኪናውን አስነስቶ ገለል ወዳለ ቦታ በመሄድ “አምላክ ሆይ፣ እባክህ መኖርህን የሚያረጋግጥ አንድ ምልክት አሳየኝ” ሲል ጸለየ። አልበርት ምልክት ለማየት ብዙ ጠበቀ። ምንም ምልክት ባለማግኘቱ ተስፋው ሁሉ ወደ “ብስጭት፣ የባዶነት ስሜትና ቁጣ” እንደተለወጠ ይናገራል።
እንደ አልበርት አምላክን ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ ፍሬ ቢስ እንደሆነ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች አሉ። የቀሳውስት ስብከት ወይም ደግሞ የቴሌቪዥን ወንጌላውያን የሚያንጸባርቁት ገንዘብ የማግበስበስ መንፈስ ግራ ያጋባቸው ይሆናል። አንዳንዶቹም በብዙዎቹ ጎረቤቶቻቸው ላይ የሚታየው ግብዝነት ስለሚነካቸው በምን እንደሚያምኑ ግራ ይገባቸዋል። ይሁንና የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን “[አምላክን] ብትፈልገው ታገኘዋለህ” ሲል አረጋግጦለታል።— 1 ዜና መዋዕል 28:9
ታዲያ አምላክ መኖሩን የሚያሳውቀው እንዴት ነው? አምላክ እንዳለ የሚያረጋግጥልህ አንድ ዓይነት መለኮታዊ ተዓምር መጠበቅ ይገባሃልን? በታይም መጽሔት ላይ የወጣ በቅርቡ የተሰበሰበ አንድ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው ከአሜሪካ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው በተዓምራት ያምናል። ይኸው ርዕስ እንዳመለከተው “በአሜሪካ ውስጥ በፍጥነት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው አምልኮታቸውን ‘በምልክቶችና በድንቆች’ ዙሪያ የመሠረቱት የቻሪስሜቲክና የጰንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።”
ይሁን እንጂ በአምላክ ለማመን የግድ “ምልክትና ድንቅ” ማየት ያስፈልጋልን? አምላክ ጥንት በተዓምራት ተጠቅሟል። ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የአምላክ ልጅ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድ የነበረው የጠርሴሱ ሳውል ከኢየሩሳሌም ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ሲጓዝ አንድ እንግዳ ነገር አጋጥሞት ነበር። ሳውል ከሞት ከተነሣው ከኢየሱስ ጋር በተዓምራዊ መንገድ መገናኘቱ ወደ ክርስትና እንዲለወጥ ምክንያት ሆኗል። (ሥራ 9:1-22) በዚህ መንገድ ቀድሞ አሳዳጅ የነበረው ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ በሚል ስም የክርስትና ግንባር ቀደም ጠበቃ ሆነ!
ይሁን እንጂ ተዓምራት ሁልጊዜ እንደዚህ የመሰለ መልካም ውጤት ያስገኛሉን? አንድ ሰው በአምላክ ላይ ልባዊ እምነት እንዲያሳድር የግድ አንድ ዓይነት ተዓምር ማየት አለበትን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ልጅ በተዓምር የጠርሴሱን ሳውል አነጋግሮታል። አንተስ ተዓምር ልትጠብቅ ይገባሃልን ?