የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 5/15 ገጽ 30-31
  • ኤጳፍራ—“ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኤጳፍራ—“ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሌከስ ሸለቆ ወንጌላዊ
  • የኤጳፍራ ሪፖርት
  • ለጸሎት ከፍተኛ ግምት የሰጠ ሰው
  • ለይሖዋ እንደሚገባ እንዲመላለሱ ሌሎችን እርዱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ጽኑ እምነት በመያዝ ምሉዓን ሆናችሁ ቁሙ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • “እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • ይሖዋ ብርቱ ሊያደርጋችሁ ይችላል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 5/15 ገጽ 30-31

ኤጳፍራ—“ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ”

በቆሮንቶስ፣ በኤፌሶንና በፊልጵስዩስ የሚገኙትን ጉባኤዎች የቆረቆረው ማን ነው? ምንም ሳታመነታ “የአሕዛብ ሐዋርያ” የተባለው ጳውሎስ ነው ብለህ ትመልስ ይሆናል። (ሮሜ 11:​13) ትክክል ነህ።

ይሁን እንጂ በቆላስይስ፣ በኢያራና በሎዶቅያ የሚገኙትንስ ጉባኤዎች ያቋቋመው ማን ነው? እርግጠኛ መሆን ባንችልም ኤጳፍራ የተባለ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆነ ይህ ኤጳፍራ “ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ” ተብሎ የተጠራ በመሆኑ ስለዚህ ወንጌላዊ ተጨማሪ ነገር ለማወቅ ሳትፈልግ አትቀርም።​— ቆላስይስ 1:​7

የሌከስ ሸለቆ ወንጌላዊ

ኤጳፍራ አፍሮዲጡ የሚለው ስም አኅጽሮታዊ አጠራር ነው። ይሁን እንጂ ኤጳፍራንና የፊልጵስዩሱን አፍሮዲጡ ልናምታታ አይገባም። ኤጳፍራ በትንሿ እስያ በሌከስ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤ ከሚገኝባቸው ሦስት ቦታዎች መካከል አንዷ የሆነችው የቆላስይስ ሰው ነው። ቆላስይስ በጥንቷ የፍርግያ ግዛት ከሎዶቅያ 18 ከኢያራ ደግሞ 19 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ከተማ ነበረች።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት ምስራች ወደ ፍርግያ እንዴት እንደደረሰ ይሄ ነው ብሎ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁን እንጂ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት የፍርግያ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተገኝተው ነበር፤ ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ የቆላስይስ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። (ሥራ 2:​1, 5, 10) ጳውሎስ በኤፌሶን ባከናወነው አገልግሎት አማካኝነት (በ52-55 እዘአ ገደማ) በዚያ አካባቢ የተሰጠው ምሥክርነት በጣም ከፍተኛና ውጤታማ ከመሆኑ የተነሣ በኤፌሶን ያሉት ብቻ ሳይሆኑ “እስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል” ሰምተዋል። (ሥራ 19:​10) በዚያ አካባቢ ወደ ክርስትና ከመጡት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ጳውሎስን አይተውት ስለማያውቁ ጳውሎስ በሌከስ ሸለቆ በሙሉ እየተዘዋወረ የሰበከ አይመስልም።​— ቆላስይስ 2:​1

እንደ ጳውሎስ አባባል ከሆነ ለቆላስይስ ሰዎች ‘በእውነት ስላለው ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት’ ያሳወቃቸው ኤጳፍራ ነው። ጳውሎስ እርሱን ‘ከእኛ ጋር አብሮ የሚያገለግል ባሪያ’ ብሎ መጥራቱ ኤጳፍራ በዚያ አካባቢ ወንጌል ሰባኪ ሆኖ ይሠራ እንደነበር ያሳያል።​— ቆላስይስ 1:​6, 7

ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ወንጌላዊው ኤጳፍራ በሌከስ ሸለቆ ለሚገኙት የእምነት አጋሮቻቸው መንፈሳዊ ደህንነት በጣም ይጨነቁ ነበር። ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ” እንደመሆኑ መጠን ስላደረጉት ዕድገት ሲሰማ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት። የቆላስይስ ሰዎች ስለሚገኙበት መንፈሳዊ ሁኔታ ለጳውሎስ የነገረው ከኤጳፍራ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።​— ቆላስይስ 1:​4, 8

የኤጳፍራ ሪፖርት

የቆላስይስ ሰዎች የገጠማቸው ችግር በጣም ከባድ ስለነበር ኤጳፍራ ስለዚሁ ጉዳይ ከጳውሎስ ጋር ለመወያየት ብቻ ሲል ወደ ሮም ረጅም ጉዞ ማድረጉን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። ጳውሎስ በአካል ለማያውቃቸው ለእነዚያ ወንድሞች ሁለት ደብዳቤዎች እንዲጽፍ ያነሳሳው ኤጳፍራ ያቀረበለት ዝርዝር ሪፖርት እንደነበር ግልጽ ነው። አንዱ ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈው ደብዳቤ ነው። ሌላኛው ደግሞ ለሎዶቅያ የተላከው ሲሆን ይህ ደብዳቤ እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ እንዲቆይ አልተደረገም። (ቆላስይስ 4:​16) እነዚህ ደብዳቤዎች ኤጳፍራ የተገነዘበውን የእነዚያን ክርስቲያኖች ችግር ለመፍታት ሲባል የተጻፉ ናቸው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። ምን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቧል? ይህስ ስለ እርሱ ባሕርይ ምን ይጠቁመናል?

ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈው ደብዳቤ ኤጳፍራ በዚያ ያሉት ክርስቲያኖች ምናኔን፣ መናፍስታዊ ድርጊቶችንና ከጣዖት አምልኮ ጋር የተያያዙ አጉል እምነቶችን ላቀፈው አረመኔያዊ ፍልስፍና ተጋልጠዋል የሚል ስጋት አድሮበት እንደነበር የሚጠቁም ይመስላል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹ የጉባኤው አባላት ከምግብ መታቀብንና አንዳንድ ቀናትን ማክበርን በሚያዘው የአይሁዳውያን ትምህርት ሳይነኩ አይቀሩም።​— ቆላስይስ 2:​4, 8, 16, 20-23

ጳውሎስ ስለ እነዚህ ጉዳዮች መጻፉ ኤጳፍራ መሰል ክርስቲያኖች ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ ምን ያህል ንቁና ጠንቃቃ እንደነበር የሚያሳይ ነው። የሚኖሩበት አካባቢ ያለውን አደገኛነት በመገንዘብ ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይቷል። ኤጳፍራ የጳውሎስን ምክር ለማግኘት መጣሩ ትሑት እንደነበረ የሚያሳይ ነው። ምናልባትም ይበልጥ ተሞክሮ ካለው ሰው ምክር ማግኘት እንደሚያስፈልገው ሳይሰማው አይቀርም። ያም ሆነ ይህ ኤጳፍራ የጥበብ እርምጃ ወስዷል።​— ምሳሌ 15:​22

ለጸሎት ከፍተኛ ግምት የሰጠ ሰው

ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ መደመደሚያ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፣ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል። ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና።”​— ቆላስይስ 4:​12, 13

አዎን፣ ኤጳፍራ በሮም ከጳውሎስ ጋር ‘አብሮ ታስሮ’ እንኳ ያስብ የነበረው በቆላስይስ፣ በሎዶቅያና በኢያራ ስላሉት የተወደዱ ወንድሞቹ ነበር። (ፊልሞና 23) ቃል በቃል በጸሎት ስለ እነርሱ ‘ይጋደል’ ነበር። ዲ ኤድመንድ ሂበርት የተባሉት ምሁር እንዳሉት ከሆነ እዚህ ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በነበረበት ጊዜ ከተሰማው ዓይነት የአእምሮ ‘ጣር’ ጋር የሚመሳሰልን “አድካሚና ትንቅንቅ የሚጠይቅ” ነገር ያመለከታል። (ሉቃስ 22:​44) ኤጳፍራ መንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ጽናትና የተሟላ ክርስቲያናዊ ጉልምስና እንዲያገኙ ከልቡ ይመኝ ነበር። ይህ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው ወንድም ለጉባኤዎቹ ምን ያህል በረከት ሆኖላቸው ይሆን!

ኤጳፍራ ‘የተወደደ ባሪያ’ ተብሎ በመጠራቱ በሌሎች ክርስቲያኖች ዘንድ የተወደደ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። (ቆላስይስ 1:​7) የጉባኤ አባላት በሙሉ እንደሁኔታቸው ልባዊ በሆነ ስሜትና በፍቅር ራሳቸውን ማቅረብ ይገባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የታመሙትንና፣ አረጋውያንን ወይም ለየት ያለ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ወንድሞች ለመርዳቱ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይችላል። በጉባኤ ውስጥ ልንይዛቸው የምንችላቸው የተለያዩ ኃላፊነቶች ይኖሩ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ለቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጄክቶች አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን።

ኤጳፍራ እንዳደረገው ስለ ሌሎች መጸለይ ሁላችንም ልናከናውነው የምንችለው የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ ነው። እንዲህ ያሉት ጸሎቶች መንፈሳዊም ሆነ አካላዊ አደጋና ችግር ስለ ገጠማቸው የይሖዋ አምላኪዎች ያለንን አሳቢነት የምንገልጽባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ረገድ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ኤጳፍራን ልንመስለው እንችላለን። ሁላችንም የታመኑ የይሖዋ አገልጋዮች በሚገኙበት ቤተሰብ ውስጥ ‘የተወደድን ባሪያ’ የመሆን መብትና ደስታ ልናገኝ እንችላለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ