“በአምላክ ቃል ማመን” ወደተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ኑ!
በዓለም ዙሪያ በመቶ በሚቆጠሩ ቦታዎች በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 193 ስብሰባዎች ለማድረግ ፕሮግራም ወጥቷል። የመጀመሪያው ከግንቦት 23-25 ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ ከመስከረም 12-14 ይደረጋል። ከዓርብ እስከ እሁድ ከሚቆዩት ከእነዚህ የሦስት ቀን ስብሰባዎች መካከል አንዱ አንተ በምትኖርበት አቅራቢያ መደረጉ የማይቀር ነው።
ተግባራዊ ሊሆኑ ከሚችሉት ብዛት ካላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጥቅም ታገኛለህ። በአብዛኞቹ ቦታዎች እያንዳንዱ ቀን ጠዋት 3:30 ላይ በሚጀምረው ሙዚቃ ፕሮግራሙ ይከፈታል። ዓርብ ጠዋት በአምላክ ቃል ላይ እምነት በማሳደራቸው አኗኗራቸው በጥልቅ ከተነኩ ሰዎች ጋር 25 ደቂቃ የሚፈጅ ቃለ ምልልስ ይደረጋል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ “በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ” በሚለው የጭብጡ ቁልፍ ንግግር ይደመደማል።
ዓርብ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የመጀመሪያ ንግግር ወጣቶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ጉልህ ድርሻ የሚዳስስ ይሆናል። ቀጥሎ የሚቀርበው ሦስት ክፍል ያለው ሲምፖዚየም በክርስቲያናዊ አኗኗር፣ አነጋገር፣ ባሕርይና አጋጌጥ ላይ በማተኮር የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃ ያብራራል። ከዚያም “ከእምነት ማነስ ተጠበቁ” እና “የአምላክ ቃል ሕያው ነው” የሚሉት ንግግሮች በዕብራውያን ምዕራፍ 3 እና ምዕራፍ 4 ውስጥ ባሉት ጥብቅ ምክሮች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። የዓርቡ ፕሮግራም የሚደመደመው “ለሁሉም ሰዎች የሚሆን መጽሐፍ” በሚለው ንግግር ይሆናል።
ቅዳሜ ጠዋት የሚቀርበው የመጀመሪያው ንግግር “እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው” የሚለው ይሆናል። በዚሁ ዕለት ጠዋት የሚቀርበው “በእውነት ሥር ሰዳችሁና ጽኑ ሆናችሁ ኑሩ” የሚለው ጠቃሚ ንግግር በመንፈሳዊ ለማደግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የሚጠናቀቀው “በአምላክ ቃል ላይ እምነት ማሳደር ወደ ጥምቀት ይመራል” በሚለው ዘወትር በአውራጃ ስብሰባ ላይ በሚቀርበው ንግግር ይሆናል። ከዚያም የአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ጥምቀት ይከተላል።
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የመክፈቻ ንግግር “ለእምነት ተጋደሉ” የሚል ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የይሁዳ መጽሐፍ የያዘውን ማስጠንቀቂያ ያብራራል። “ወደ ይሖዋ ቤት እንሂድ” በሚል ርዕስ ለአንድ ሰዓት የሚቆየው ሲምፖዚየም የክርስቲያን ስብሰባዎችን ጠቃሚነት ይመረምራል። የዕለቱ ፕሮግራም የሚደመደመው “የእምነታችሁ ጥራት—አሁን ተፈተነ” በተሰኘው ንግግር ይሆናል።
በእሁድ ጠዋቱ ፕሮግራም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የኢዩኤልን መጽሐፍ የሚያብራራና ለጊዜያችን የሚያስተላልፈውን ትምህርት የሚገልጽ ሦስት ክፍል ያለው ሲምፖዚየም ይቀርባል። ከዚያም “ዓይናችሁ ቀና ይሁን” የተባለ ርዕስ ያለው ድራማ ይከተላል። የስብሰባው ጎላ ያለ ክፍል ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው “እምነትና የወደፊት ተስፋህ” የተሰኘው የሕዝብ ንግግር ይሆናል።
በስብሰባው ላይ በመገኘት መንፈሳዊ ብልጽግና ልታገኝ ትችላለህ። በሁሉም የስብሰባው ክፍለ ጊዜ ላይ እንድትገኝ በአክብሮት ተጋብዘሃል። በስብሰባው ላይ ለመገኘት አሁኑኑ እቅድ አውጣ። በመኖሪያ አቅራቢያህ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ጋር ተገናኝ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች ጻፍ። በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳ፣ በብሪታንያና በአየርላንድ ስብሰባዎቹ የሚደረጉባቸውን ቦታዎች አድራሻ በሰኔ 8 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትም ላይ ማግኘት ትችላለህ።