የአንባብያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በሰጠው ምሳሌ ላይ ያደረግነው ጥናት በጣም አስደስቶናል። በጥቅምት 15, 1995 “መጠበቂያ ግንብ” ከወጣው አዲስ እውቀት አንፃር ሲታይ የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ በጎችንና ፍየሎችን በመለየቱ ሥራ እየተካፈሉ ነው ለማለት እንችላለንን?
አዎን። ማቴዎስ 25:31, 32 “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል” ስለሚል ብዙዎች በዚህ ረገድ ግራ መጋባታቸው ምክንያታዊ ነው። የጥቅምት 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ እነዚህ ቁጥሮች ተፈጻሚ የሚሆኑት ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ለምን እንደሚሆን ያሳያል። ኢየሱስ ከመላእክቱ ጋር በክብሩ ይመጣና በፍርድ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። ከዚያም ሰዎችን ይለያል። በምን ሁኔታ? ሰዎች ቀደም ሲል በነበሩት ዘመናት ያደረጉትን ወይም ሳያደርጉ የቀሩትን ነገር መሠረት በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይሰጣል።
ይህን ሁኔታ ለፍርድ የቀረበ አንድ ጉዳይ ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት ከሚያልፍባቸው የሕግ ሂደቶች ጋር ማመሳሰል ይቻላል። ችሎቱ የሕግ ብይን ወይም ፍርድ ከመስጠቱ በፊት ረዘም ላለ ጊዜ ማስረጃ ሲሰበስብ ይቆያል። በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉት ሰዎች በግ ይሁኑ ወይም ፍየል የሚረጋገጠው ወደፊት ሲሆን እነዚህን ሰዎች በተመለከተ ረዘም ላለ ጊዜ ማስረጃ ሲሰበሰብ ቆይቷል። አሁንም በመሰብሰብ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በፍርድ ዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ የፍርድ ጉዳዩ ይሟላል። ፍርድ ለመስጠት ዝግጁ ይሆናል። በዚያ ጊዜ ሰዎች ለዘላለም ሕይወት ወይም ለዘላለም ጥፋት ፍርድ ይለያሉ።
ይሁን እንጂ በማቴዎስ 25:32 ላይ የተገለጸው ሰዎችን ለሕይወት ወይም ለሞት መለየት ገና ወደፊት የሚከናወን መሆኑ ከዚያን ጊዜ በፊት ምንም ዓይነት የመለየት ወይም የመክፈል ሥራ አይከናወንም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 13 ላይ ቀደም ብሎ ስለሚከናወን አንድ የመለያየት ሥራ ይጠቅሳል። የሚያስደንቀው እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት የተባለው መጽሐፍ ገጽ 179-80 ላይ “ሰዎችን በየወገኑ መለያየት” በሚል ርዕስ ሥር ይህን ጉዳይ በዝርዝር አስፍሯል።a መጽሐፉ እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስ ከሥርዓቱ መደምደሚያ ዘመን ጋር በከፍተኛ ደረጃ ያዛመዳቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ “የመንግሥቱን ልጆች” “ከክፉው ልጆች” በየወገናቸው የመለያየቱ ሥራ ነው። ኢየሱስ ይህንን ሲገልጽ ስንዴ በተዘራበት እርሻ ላይ ጠላት እንክርዳድ እንደዘራ የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል።”
መጽሐፉ ኢየሱስ ማቴዎስ 13:24-30 ላይ የተናገረውን ምሳሌና ከቁጥር 36-43 ትርጉሙን የገለጸበትን ቦታ ማመልከቱ ነበር። መልካሙ የስንዴ ዘር የመንግሥትን ልጆች፣ እንክርዳዱ ደግሞ ክፉ ሰዎችን የሚያመለክት እንደሆነ የሚገልጸውን ቁጥር 38ን ልብ በሉ። ቁጥር 39 እና 40 ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ወቅት’ ማለትም አሁን በምንኖርበት ዘመን እንክርዳዶቹ ተሰብስበዋል። አሁን ስለተለዩ የመጨረሻ እጣቸው መቃጠልና መጥፋት ይሆናል።
ምሳሌው የሚናገረው ስለ ቅቡዓን ክርስቲያኖች (ስለ በጎችና ፍየሎች በሚናገረው ምሳሌ ውስጥ የኢየሱስ ወንድሞች ተብለው ስለ ተጠሩት ሰዎች) ነው። ዋናው የመለየት ሥራ የሚከናወነው ቅቡዓኖች ራሳቸውን ክርስቲያን ነን ብለው ከሚጠሩት ነገር ግን “የክፉ ልጆች” ከሆኑት የሐሰት ክርስቲያኖች በሚለዩበት አሁን ባለንበት ጊዜ ውስጥ ነው።
ኢየሱስ እየተከፈሉ ወይም እየተለዩ ስላሉ ሰዎች የሚገልጽ ሌላ ምሳሌ ተናግሯል። ወደ ጥፋት የሚወስደውን ሰፊ መንገድ አስመልክቶ ኢየሱስ “ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው” በማለት የተናገረውን እናስታውሳለን። (ማቴዎስ 7:13) ይህ በመጨረሻ ላይ ውጤቱ ስለሚታይ ነገር የተነገረ አይደለም። ጥቂት ሰዎች ወደ ሕይወት የሚወስደውን ጠባብ መንገድ ይፈልጉ እንደነበሩ ሁሉ ይህም ቀጣይነት ያለው እድገት እንዳለው የሚያሳይ አስተያየት ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ሐዋርያቱን በሰደደ ጊዜ የሚገባቸውን አንዳንድ ሰዎች ያገኛሉ ብሎ ተናግሮ እንደነበር አስታውሱ። ሌሎች ደግሞ የሚገባቸው ስላይደሉ ሐዋርያቱ “ምስክር እንዲሆንባቸው” የእግሮቻቸውን ትቢያ ማራገፍ ነበረባቸው። (ሉቃስ 9:5) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአደባባይ የሚያደርጉትን አገልግሎት በሚያከናውኑበት ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ ነገር እየተከናወነ እንዳለ እውነት አይደለም? አንዳንዶች ይዘነው ለምንሄደው መለኮታዊ መልእክት ጥሩ ምላሽ ሲሰጡ ሌሎች ደግሞ አሻፈረኝ ይላሉ።
ስለ በጎችና ፍየሎች የሚናገረው መጠበቂያ ግንብ ርዕሰ ትምህርት እንዲህ ብሎ ነበር:- “በምሳሌው ውስጥ የተገለጸው ፍርድ ወደፊት በቅርብ ጊዜ የሚፈጸም ቢሆንም እንኳ አሁን አንድ በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር እየተከናወነ ነው። እኛ ክርስቲያኖች፣ ሰዎች እንዲለዩ የሚያደርገውን ሕይወት አድን መልእክት በማወጅ ላይ ነን። (ማቴዎስ 10:32-39)” ማቴዎስ 10 ላይ ያለው ዘገባ እርሱን መከተል አባትን ከልጅ፣ ሴት ልጅን ከእናት እንደሚለይ ኢየሱስ ተናግሯል።
በመጨረሻም የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች የመንግሥቱን መልእክት የመስበኩን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ሰዎች ይህን መልእክት የመስማት አጋጣሚ አግኝተው ሲቀበሉ ወይም ለመቀበል እምቢተኛ ሲሆኑ ማንነታቸውን ያሳውቃሉ። እኛ የሰው ልጆች ለማቴዎስ ምዕራፍ 25 በተሰጠው ትርጉም መሠረት ይህ ሰው በግ ነው፣ ያ ደግሞ ፍየል ነው ማለት አንችልም፤ ማለትም አይገባንም። ይሁን እንጂ ሰዎች የአምላክን መልእክት የማዳመጥ አጋጣሚ እንዲያገኙ ማድረጋችን በአሁኑ ጊዜ ምን ዓይነት አቋም እንዳላቸው፣ ምን እንደሆኑና ለኢየሱስ ወንድሞች ምን ዓይነት አቀባበል እንደሚያደርጉ እንዲያሳዩ ያስችላቸዋል። ስለዚህ ይህ የመለያየት ሥራ በፍርድ ችሎት ሲጣራ እንደቆየ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ እየሆነ ሄዷል። (ሚልክያስ 3:18) መጠበቂያ ግንቡ እንዳመለከተው ኢየሱስ በቅርቡ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ ይሰጣል፤ በመጨረሻም ሰዎች ለሕይወት ወይም ለጥፋት ይለያሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1983 የታተመ።