የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 7/15 ገጽ 20-23
  • የልጃችሁን ሕይወት አድኑ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የልጃችሁን ሕይወት አድኑ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የቅርብ ወዳጆች ሁኑ
  • የአምላክ ፍቅር
  • አምላክን መፍራት
  • አስደሳች ወሮታ
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ እርዷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ መገንባት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 7/15 ገጽ 20-23

የልጃችሁን ሕይወት አድኑ!

ማይክልና አልፊን በደቡብ አፍሪካ፣ ክዋዙሉ-​ናታል ግዛት አረንጓዴ በተላበሱ ኮረብታዎች መካከል በምትገኝ አንዲት ገጠራማ ሸለቆ ውስጥ ይኖራሉ። ሰባት ልጆች ለማሳደግ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመዋል። ማይክል ሚስቱ በምትሰጠው ሙሉ ድጋፍ በመታገዝ “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች የሚሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። (ኤፌሶን 6:​4) ሆኖም ችግሮች አንዳንድ ጊዜ ብቅ ይላሉ።

ለምሳሌ ያህል ከብት የሚያግዱ አፍሪካውያን ልጆች ረዘም ያለ ጊዜ አግኝተው አንድ ላይ መጫወት እንዲችሉ ከብቶቻቸውን አንድ ላይ ቀላቅለው ማገዳቸው የተለመደ ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ችግር ውስጥ ይገባሉ፤ እንዲሁም መነጋገር ስለማይገቧቸው ነገሮች ይነጋገራሉ። የማይክል ልጆች የቤተሰባቸውን ከብቶች ለማገድ በሚሄዱበት ጊዜ ከአንዳንድ ልጆች ጋር እንዳይገጥሙ ጠንከር ያለ ትእዛዝ ይሰጣቸዋል። (ያዕቆብ 4:​4) ሆኖም ማይክል ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ አንዳንድ ጊዜ ከእነዚያ መጥፎ ልጆች ጋር ገጥመው ያገኛቸው ነበር። ስለዚህም እነርሱን መቅጣት ነበረበት።​—⁠ምሳሌ 23:​13, 14

ማይክል ልጆቹን ከመጠን በላይ ይቆጣጠራቸው ነበር ብለህ ታስባለህን? አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ “የጥበብ ትክክለኛነት በሥራዋ ይገለጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:​19 የ1980 ትርጉም) ማይክልና አልፊን ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ በማሳለፋቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንና እውነቶችን በማስተማራቸው በቤታቸው ውስጥ አስደሳች መንፈስ እንዲሰፍን አድርገዋል።

ማይክልና አልፊን ቲምብኪል፣ ስፊው፣ ቶልኪሊ እና ቲምብካኒ የሚባሉ አራት ሴት ልጆች አሏቸው። ሁሉም የአምላክ መንግሥት ምሥራች የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ናቸው። ሁለቱ ወንድ ልጆቻቸው በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆነው ያገለግላሉ። የሙሉ ጊዜ ወንጌል ሰባኪ ሚስት ያለችው ሦስተኛው ወንድ ልጃቸው ደግሞ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።

ብዙ ልጆች ያሏቸው በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በማሳደግ በኩል ስኬታማ በመሆን ተባርከዋል። ይሁን እንጂ ጥሩ የወላጅ እንክብካቤ አግኝተው ያደጉ አንዳንድ ልጆች እውነትን ትተዋል። ወላጆቻቸው ኢየሱስ ስለ ኮብላዩ ልጅ የተናገረውን ምሳሌ በአእምሯቸው እንደሚይዙና ወንድ ልጃቸው ወይም ሴት ልጃቸው ንስሐ ገብተው ውሎ አድሮ ደግሞ ደህንነት እንደሚያገኙ ተስፋ እንደሚያደርጉ የተረጋገጠ ነው።​—⁠ሉቃስ 15:​21-24

የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው በሙሉ ወደ ዓለም ይኮበልላሉ። ይህ በተለይ ልጆች አሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ጥሩ መስለው በሚታዩበት በአንዳንድ አፍሪካ አገሮች አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። ከዚያ ከፍ ሲሉና ወደ አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ሥነ ምግባር በጎደለው የሰይጣን ዓለም አካሄድ ይታለላሉ። (1 ዮሐንስ 5:​19) በዚህም የተነሳ ብዙ አባቶች የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል ብቁ ሳይሆኑ ይቀራሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1, 4, 5) አንድ ክርስቲያን አባት ለራሱ ቤተሰብ መዳን ትልቅ ቦታ መስጠት እንዳለበት የታወቀ ነው። ታዲያ ወላጆች የልጆቻቸውን ሕይወት ለማዳን ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

የቅርብ ወዳጆች ሁኑ

ኢየሱስ በፍጽምና ደረጃ ብቻ ሳይሆን በእውቀትና በተሞክሮም ከማንኛውም ሰብዓዊ ሰው የላቀ ነበር። ሆኖም ፍጹም ያልነበሩ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ቅርብ ወዳጆቹ አድርጎ ይዟቸዋል። (ዮሐንስ 15:​15) ከእርሱ ጋር አብረው ለመሆን ይጓጉ የነበረውና በመካከላቸው ሲሆን ደግሞ ይደሰቱ የነበረው በዚህ የተነሳ ነው። (ዮሐንስ 1:​14, 16, 39-42፤ 21:​7, 15-17) ወላጆችም ከዚህ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ቅጠሎቻቸውን ሙቀት ወደሚሰጥ የፀሐይ ጨረር እንደሚዘረጉ ትንንሽ ተክሎች ልጆችም የፍቅርና የወዳጅነት መንፈስ በቤት ውስጥ በሚሰፍንበት ጊዜ በደስታ ይፈነድቃሉ።

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የሚያስጨንቋቸውን ነገሮች ሁሉ ይዘው ወደ እናንተ ለመቅረብ ነፃነት ይሰማቸዋል? ታዳምጧቸዋላችሁ? ቸኩላችሁ መደምደሚያ ላይ ከመድረሳችሁ በፊት የተሟላ መረጃ ለማግኘት እንድትችሉ አሳባቸውንና ስሜታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ታደርጓቸዋላችሁ? አብራችኋቸው ሆናችሁ መጽሐፍ ቅዱስን በሚያብራሩ ጽሑፎች ላይ ምርምር በማድረግ ለአንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በትዕግሥት ትረዷቸዋላችሁ?

አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት እናት እንዲህ ብላለች:- “ልጃችን ትምህርት ቤት ከገባችበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በዕለቱ ውስጥ የገጠሟትን ነገሮች እንድትነግረን እናበረታታት ነበር። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብዬ እጠይቃት ነበር:- ‘የምሳ ሰዓትሽን ከማን ጋር አሳለፍሽ? ስለ አዲሷ አስተማሪሽ እስቲ ንገሪኝ። ምን ዓይነት ናት? በሳምንቱ ውስጥ ምን ለማድረግ እቅድ አውጥተሻል?’ አንድ ቀን ልጃችን እቤት መጣችና ፊልሙን ከተመለከቱ በኋላ ግምገማ እንዲጽፉ ለማድረግ የእንግሊዝኛ አስተማሪያቸው የክፍሉን ልጆች ሁሉ ወደ ፊልም ቤት ይዛቸው ልትሄድ እንደሆነ ነገረችን። የፊልሙ ርዕስ አጠያያቂ ነበር። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ምርመራ ስናደርግ ፊልሙ ለአንድ ክርስቲያን የማይስማማ ሆኖ አገኘነው። መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ተወያየንበት። በቀጣዩ ቀን ልጃችን ወደ አስተማሪዋ ዘንድ ሄዳ በፊልሙ ውስጥ ከክርስቲያናዊ እምነቷ ጋር የማይስማማ ሥነ ምግባር ስለሚተላለፍ ለማየት እንደማትፈልግ ነገረቻት። አስተማሪዋም ጉዳዩን በጥሞና አሰበችበትና ጸጸት ውስጥ ሊከታት የሚችል ነገር እንዲመለከቱ ተማሪዎቹን መውሰድ እንደማትፈልግ በመናገር ልጃችንን አመሰገነቻት።” እነዚህ ወላጆች ለልጃቸው መዳን ያሳዩት ያልተቋረጠ ፍቅራዊ ስሜት ጥሩ ፍሬ አፍርቷል። ልጅቷ ደስተኛና ብሩህ ተስፋ ያላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆና ታገለግላለች።

ኢየሱስ ከሌሎች ሰዎች ልጆች ጋር ባለው ግንኙነት ጥሩ ምሳሌ ትቷል። አብረውት ሲሆኑ ደስ ይለው ነበር። (ማርቆስ 10:​13-16) ከልጆቻቸው ጋር ነገሮችን በአንድ ላይ የሚያከናውኑ ወላጆች ምንኛ ደስተኞች ናቸው! በአንዳንድ አፍሪካ አገሮች አንድ አባት ከልጆቹ ጋር ኳስ ወይም ሌሎች ጨዋታዎችን ሲጫወት በሰዎች ዘንድ መታየቱ ያሳፍረዋል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን አባት ከልጆቹ ጋር አንዳንድ ነገሮች ሲያከናውን መታየት እንደሌለበት ሆኖ ፈጽሞ ሊሰማው አይገባም። ወጣቶች አብረዋቸው ጊዜ የሚያሳልፉ ወላጆች ያስፈልጓቸዋል። ይህም ልጆች የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ሁሉ ለመናገር ቀላል ያደርግላቸዋል። እንደዚህ ያለው ስሜታዊ ፍላጎት ችላ ከተባለ በተለይ ደግሞ ዘወትር እርማት የሚሰጣቸው ከሆነ ልጆች ሊበሳጩ ወይም ራሳቸውን ሊያገሉ ይችላሉ።

ጳውሎስ በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “አባቶች ሆይ፣ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” ብሏል። (ቆላስይስ 3:​21) ይህም አንዳንድ ጊዜ ሚዛኑን የሳተ ከልክ ያለፈ ተግሳጽ መስጠትንና ልጆችን አለማቅረብን ሊያመለክት ይችላል። በአሥራዎቹ እድሜ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ፍቅርና አድናቆት የሚያገኙ ልጆች ለሚሰጣቸው ተገቢ ተግሳጽ ጥሩ ምላሽ መስጠታቸው የማይቀር ነው።

የአምላክ ፍቅር

ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያስተላልፉ የሚችሉት በጣም ውድ የሆነ ውርስ ፍቅር የማሳየት ምሳሌነት ነው። ልጆች ወላጆቻቸው ለአምላክ ያላቸውን እውነተኛ ፍቅር ሲገልጹና ሲያሳዩ ማየትና መስማት ይኖርባቸዋል። ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግል አንድ ወጣት “ልጅ በነበርኩበት ጊዜ አባቴ ቤት ውስጥ አንዳንድ ነገሮች ሲያከናውን አብሬው እሠራ ነበር። አባባ ለማከናውናቸው ጥቃቅን ነገሮች አድናቆቱን ስለሚገልጽ እርሱን መርዳት ያስደስተኝ ነበር። ስለ ይሖዋ ብዙ ነገሮችን ለኔ ለመንገር ይህን ወቅት ይጠቀም ነበር። ለምሳሌ ያህል የግቢያችንን ሣር ስናጭድ ደክሞን የነበረበት አንድ ቅዳሜ ዕለት ትዝ ይለኛል። በጣም ሞቃታማ ቀን ነበር። አባባ ያልበው ስለነበር ሮጥ ብዬ ሁለት ብርጭቆ ውኃ አመጣሁና በረዶ ጨመርኩባቸው። አባባም እንዲህ አለ:- ‘ልጄ፣ ይሖዋ ምን ያህል ጥበበኛ እንደሆነ ታያለህ? በረዶ በውኃ ላይ ይንሳፈፋል። የሚሰምጥ ቢሆን ኖር በሐይቆችና በኩሬዎች ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ይሞቱ ነበር። ከዚያ ይልቅ በረዶው እንደ ብርድ ልብስ ሆኖ ይከላከልላቸዋል! ታዲያ ይህ ይሖዋን የበለጠ እንድናውቀው አይረዳንም?’a ከጊዜ በኋላ የገለልተኝነት አቋም መጠበቅን በሚመለከት እስር ቤት ስገባ ለማሰላሰል ጊዜ አገኘሁ። አንድ ቀን ሌሊት ታስሬ በነበርኩበት ክፍል ውስጥ የመንፈስ ጭንቀት ሲሰማኝ እነዚያን አባባ የተናገራቸውን ቃላት አስታወስኩ። እንዴት ያሉ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ናቸው! የምችል ከሆነ ይሖዋን ለዘላለም አመልከዋለሁ።”

አዎን፣ ልጆች ወላጆቻቸው በሚያከናውኑት በማንኛውም ነገር ላይ የአምላክ ፍቅር ሲንጸባረቅ ማየት ይኖርባቸዋል። የአምላክ ፍቅርና እርሱን ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት ለመካፈልና የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ጥናት ለማድረግ የሚገፋፋ ኃይል ሆኖ መታየት ይኖርበታል። (1 ቆሮንቶስ 13:​3) ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምላክ ፍቅር በሙሉ ልብ በሚቀርቡ የቤተሰብ ጸሎቶች መንጸባረቅ ይኖርበታል። እንዲህ ያለውን ውርስ ለልጆች የመስጠቱ አስፈላጊነት ከመጠን በላይ ተጋኗል ሊባል አይችልም። እስራኤላውያን “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው” ተብለው የታዘዙት በዚህ የተነሳ ነው።​—⁠ዘዳግም 6:​5-7፤ ከማቴዎስ 22:​37-40 ጋር አወዳድር።

አምላክን ለማፍቀርና ለመታዘዝ አስቸጋሪ የሚያደርገው ትልቁ እንቅፋት የወረስነው የኃጢአት ባሕርያችን ነው። (ሮሜ 5:​12) እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ” በማለት ያዝዘናል። (መዝሙር 97:​10) ክፉ አስተሳሰብ ብዙውን ጊዜ ወደ መጥፎ ድርጊት ይመራል። ይህንን ለማስወገድ አንድ ልጅ ሌላ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ጠባይ ማዳበር አለበት።

አምላክን መፍራት

ይሖዋን ላለማሳዘን ከሚደረግ አክብሮታዊ ፍርሃት ጋር ፍቅር መታከሉ በጣም የሚፈለግ ነገር ይሆናል። “በእግዚአብሔር ፍርሃት” ደስታውን የሚያየው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። (ኢሳይያስ 11:​1-3) አንድ ልጅ አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚደርስበትና ኃይለኛ የጾታ ግፊት መሰማት በሚጀምረው ጊዜ እንዲህ ያለው ፍርሃት እጅግ ጠቃሚ ነው። አምላክን መፍራት አንድ ወጣት ወደ ሥነ ምግባር ብልግና ሊመሩት የሚችሉትን ዓለማዊ ግፊቶች መቋቋም እንዲችል ሊረዳው ይችላል። (ምሳሌ 8:​13) በአንዳንድ ማኅበረሰብ የሚኖሩ ወላጆች የጾታ ፈተናዎችን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ ለልጆቻቸው ማስተማር ያሳፍራቸዋል። እንዲያውም ስለነዚህ ነገሮች ውይይት ማድረግ ስህተት እንደሆነ የሚሰማቸው ብዙዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ወላጆች በዚህ መንገድ ቸልተኞች መሆናቸው ያስከተለው ነገር ምንድን ነው?

ቡጋ፣ አሞኮና ጻዬያን የተባሉ ሦስት የሕክምና ስፔሻሊስቶች በደቡብ አፍሪካ በትራንስካ ግዛት በገጠር ለሚኖሩ ለ1,702 ልጃገረዶችና ለ903 ወንዶች ቃለ መጠይቅ አደረጉ። ሳውዝ አፍሪካን ሜዲካል ጆርናል “በዚህ ጥናት መሠረት 76% ልጃገረዶችና 90.1% ወንዶች ቀደም ሲል የጾታ ግንኙነት እንደፈጸሙ” ዘግቧል። የልጃገረዶቹ አማካይ ዕድሜ 15 ሲሆን ብዙዎቹም የጾታ ግንኙነት የፈጸሙት ተገደው ነው። ከ250 የሚበልጡት አንድ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ አርግዘዋል። ሌላው መዘዝ ደግሞ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች መበራከታቸው ነው።

ብዙ ወላጆች ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም መራቅ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለልጆቻቸው የማስተማሩ አስፈላጊነት አይታያቸውም። ከዚህ ይልቅ ከላይ የተጠቀሰው መጽሔት “በገጠሬው የትራንስካ ኅብረተሰብ ዘንድ ልጅን ማሳደግና እናት መሆን ከፍ ተደርጎ የሚታይ የሴትነት ጠባይ ሲሆን ልጃገረዶች ለአቅመ ሔዋን እንደደረሱ ወዲያው የሚታያቸው ነገር ነው” በማለት ያብራራል። እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ችግር በሌሎች የዓለም ክፍሎችም እንዳለ በጥናት ተደርሶበታል።

በአፍሪካ የሚኖሩ ብዙ ወጣት ልጆች ጾታቸውን አስመልክቶ ግንዛቤ እንዲያገኙ ወላጆቻቸው ምንም እንደማይረዷቸው በማማረር ይናገራሉ። አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት በተባለው መጽሐፍ መጠቀም በጣም ያሳፍራቸዋል።b ከገጽ 20-3 የጾታ ብልቶችን ክብር ባለው መንገድ ስለመጠቀምና በጉርምስና ወቅት ስለሚከሰተው ለውጥ ማብራሪያ ይሰጣል።

አምላክ ለጾታ ያለውን አመለካከት ከልጆቻቸው ጋር ለመወያየት ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያን ወላጆች ሊመሰገኑ ይገባል። ይህም ልጁ ነገሮች ሊገቡት በሚችሉበት መጠን ቀስ በቀስ ቢደረግ የተሻለ ነው። የልጁን ዕድሜ የመሰሉ ሌሎች ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ወላጆች የሰውነት ክፍሎችንና ተግባሮቻቸውን ሲገልጹ ግልጥልጥ አድርገው መናገር ይኖርባቸው ይሆናል። አለበለዚያ ተሞክሮ የሌለው አንድ ወጣት እየተነገረ ያለውን ቁም ነገር ላይረዳ ይችላል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 14:​8, 9

ሁለት ሴት ልጆችና አንድ ወንድ ልጅ ያለው በደቡብ አፍሪካ የሚኖር አንድ አባት ሲያብራራ “በተደጋጋሚ ጊዜያት ከልጃገረዶቹ ጋር እንኳን ሳይቀር ጾታን የሚመለከቱ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች አንስቶ ለመወያየት አጋጣሚዎች ነበሩኝ። እርግጥ ነው ባለቤቴ ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ለሴት ልጆቻችን ልዩ ትኩረት ትሰጥ ነበር። [ከገጽ 26-31 ተመልከት።] ልጄ 12 ዓመት ሲሞላው በተራራ ላይ ረዥም ጉዞ ለማድረግ ይዤው ለመሄድ ወሰንኩ። በዚያ አጋጣሚ የወንድን ልጅ የአካል እድገትና ወደፊት በጋብቻ ውስጥ ስለሚኖራቸው ልዩ ዓላማ በዝርዝር ተወያየን። በተጨማሪም ርካሽ ከሆነው ከማስተርቤሽን ልማድ የመራቅን አስፈላጊነትና ሴቶችን፣ እናቱንና እህቶቹን በሚመለከትበት መንገድ በክብርና በጥንቃቄ እንዲመለከታቸው አወያየሁት።”

አስደሳች ወሮታ

ከላይ የተጠቀሱት አባትና እናት ጥረው ግረው ሦስት ልጆቻቸውን በማሳደግ ባገኙት ጥሩ ውጤት ደስተኞች ናቸው። ሦስቱም አድገው አሁን ታማኝ ክርስቲያኖችን አግብተው ይኖራሉ። ወንዱ ልጃቸውና የሴት ልጆቻቸው ባሎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆነው ያገለግላሉ። እንዲሁም ሁለቱ ባልና ሚስቶች ለብዙ ዓመታት በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ ሲካፈሉ ቆይተዋል።

አዎን፣ ለቤተሰባቸው መዳን ጠንክረው የሚሠሩ ወላጆች በምሳሌ 23:​24, 25 ላይ “የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፣ አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው” እንደሚሉት ላሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጥሩ ምላሽ ለመስጠት በመረጡ ልጆቻቸው የሚያስደስት ካሳ ሊጠባበቁ ይችላሉ። በዚህ ርዕሰ ትምህርት መግቢያ ላይ የተጠቀሰውን ትልቅ ቤተሰብ አስታውስ። “ልጆቼ በመንፈሳዊ ያደረጉትን መሻሻል መለስ ብዬ ሳስብ” ትላለች አልፊን “ልቤ በደስታ ይፈነድቃል።” እንዲህ ያለውን አስደሳች ወሮታ ለማግኘት እንዲችሉ ሁሉም ክርስቲያን ወላጆች ጠንክረው የሚሠሩ ይሁኑ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ውኃ ወደ ጠጣርነት ሲለወጥ ክብደቱ ይቀንስና ወደ ላይ ይወጣል። በመጠበቂያ ግንብ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለውን መጽሐፍ ገጽ ከ137-8 ተመልከት።

b በተጨማሪም ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አባት የሕይወትን እውነታዎች ለማብራራት ተስማሚ ጊዜና ቦታ ሊያዘጋጅ ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ