በገደል አፋፍ ላይ የሚታይ የአክሮባት ትርዒት
በሙት ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ በኩል ጥንታዊቷ ከተማና በአካባቢዋ ያለው ዓይንጋዲ በመባል የሚታወቅ ምድረ በዳ ይገኛል። ገደላማው አካባቢና በትላልቆቹ ቋጥኞች መካከል ያሉት መሽሎክሎኪያዎች በሥዕሉ ላይ ከሚታዩት ዋልያዎች ጋር ተመሳሳይ ለሆነው በተስፋይቱ ምድር ለነበረው የዋልያ ዝርያ ተስማሚ መኖሪያ ሆኖለት ነበር።
ይህ እግሩ የማያዳልጠው እንስሳ አስገራሚ ከሆኑት የፍጥረት ሥራዎች አንዱ ነው። እስቲ መጽሐፍ ቅዱሳችንን እናውጣና ስለዚህ አስገራሚ እንስሳ ተጨማሪ ነገር እንመልከት።
“ዋልያዎች በከፍተኛ ተራሮች ላይ ይገኛሉ”
ይህንን ያዜመው መዝሙራዊው ነበር። (መዝሙር 104:18 የ1980 ትርጉም) ዋልያዎች በረጅም ተራራዎች ላይ ለመኖር የተመቻቹ ፍጥረታት ናቸው! ከፍተኛ የአካል ቅልጥፍና ያላቸው ሲሆን ከአንዱ ወጣገባ ቦታ ወደ ሌላው በከፍተኛ ትምክህትና ፍጥነት ዘለው ይሄዳሉ። ለዚህ ችሎታቸው በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገው የሸኾናቸው አሠራር ነው። እንደ ዋልያው ክብደት የሸኾናው ክፍተት ስለሚሰፋ እንስሳው ጠባብ በሆነው ዓለት ጠርዝ ላይ ሲቆምም ሆነ ሲንቀሳቀስ ቆንጥጦ ለመያዝ ያስችለዋል።
ዋልያዎች እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ ሚዛናቸውን የመጠበቅ ችሎታ አላቸው። ረጅም ርቀት ዘለው አራት እግራቸውን እንኳ በቅጡ ማቆም በማይችል ጠባብ ቦታ ላይ ማረፍ ይችላሉ። የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ዳግላስ ቻድዊክ በአንድ ወቅት ሌላ ዓይነት ዝርያ ያለው ዋልያ ወደኋላ ዞሮ ለመመለስ በማያስችል ጠባብ ገደል አፋፍ ላይ ሲደርስ እንዴት ሚዛኑን እንደጠበቀ ተመልክተዋል። እንዲህ ይላሉ:- “ከበታቹ 120 ሜትር ዝቅ ብሎ የሚገኘውን አፋፍ ቁልቁል አየት ካደረገ በኋላ ሁለቱን የፊት እግሮቹን ተክሎ የአክሮባት ትርዒት የሚሠራ ይመስል የኋላ እግሮቹን ወደ ላይ በማንሳት ከጎኑ ከፍ ብሎ በሚገኘው አለት ላይ አሳረፈና በቀስታ መዞር ጀመረ። ምን ያደርግ ይሆን ብዬ ልቤ ተንጠልጥሎ ስመለከት ዋልያው ፊቱን ወደመጣበት አቅጣጫ መልሶ የኋላ እግሮቹን አሳረፈ።” (ናሽናል ጂኦግራፊክ ) ዋልያዎች ‘በገደል አፋፍ ላይ የአክሮባት ትርዒት የሚያሳዩ እንስሳት’ ተብለው መጠራታቸው ምንም አያስገርምም!
‘ዋልያ የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን?’
ዋልያዎች በጣም ድንጉጥ እንስሳት ናቸው። ከሰዎች ርቀው መኖርን ይመርጣሉ። በመሆኑም ሰዎች የእነዚህ እንስሳት የዱር ኑሮ ምን እንደሚመስል ቀረብ ብለው ለመመልከት ይቸገራሉ። ከዚህ የተነሣ “በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶች” ባለቤት የሆነው አምላክ ኢዮብ የተባለውን ሰው ‘ዋልያ የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን?’ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነበር።—መዝሙር 50:10፤ ኢዮብ 39:1
እንስቷ ዋልያ አምላክ በሰጣት ተፈጥሮአዊ ጥበብ በመጠቀም የምትወልድበት ትክክለኛ ጊዜ መቼ መሆን እንዳለበት ታውቃለች። አስተማማኝ የሆነ ቦታ ትመርጥና አንድ ወይም ሁለት ግልገሎች ትወልዳለች፤ ብዙውን ጊዜ የምትወልደው በግንቦት መጨረሻ ወይም በሰኔ ወር ውስጥ ነው። አዲስ የተወለዱት ግልገሎች ከጥቂት ቀናት በኋላ እነርሱም በእግራቸው እየቆነጠጡ መቆምን ይማራሉ።
‘የተወደደች ዋልያ የተዋበችም ሚዳቋ’
ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ባሎችን እንዲህ ሲል መክሯል:- “ከጉብዝናህ ሚስት ጋር ደስ ይበልህ። እንደ ተወደደች ዋላ [“ዋልያ፣” የ1980 ትርጉም] እንደ ተዋበችም ሚዳቋ።” (ምሳሌ 5:18, 19) ይህ ሴቶችን ለማቃለል የተነገረ ቃል አይደለም። እዚህ ላይ ሰሎሞን ስለ እነዚህ እንስሳት ውበት፣ ግርማና ስላሏቸው ሌሎች ግሩም ባሕርያት እየጠቀሰ ያለ ይመስላል።
ዋልያ የፈጣሪን ጥበብ ከሚመሠክሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ‘ሕያዋን ፍጥረታት’ መካከል አንዱ ነው። (ዘፍጥረት 1:24, 25) አምላክ እንደነዚህ ያሉ ብዙ አስገራሚ ፍጥረታት በዙሪያችን እንዲኖሩ በማድረጉ ደስ አይለንምን?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of Athens University