የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 3/1 ገጽ 14-19
  • ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት ማሳየት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት ማሳየት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሚያንጹ ስብሰባዎች
  • በደንብ ተዘጋጅ
  • በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጹ ምሳሌዎች
  • ከሁሉ የሚበልጠው ምሳሌ
  • ዘመናዊ ምሳሌዎች
  • ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን አክብሮት ማሳየት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 3/1 ገጽ 14-19

ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት ማሳየት

“ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . መሰብሰባችንን አንተው።”​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

1, 2. (ሀ) በእውነተኛ ክርስቲያኖች ስብሰባ ላይ መገኘት ትልቅ መብት የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ተከታዮቹ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ የሚገኘው በምን መንገድ ነው?

ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና” ስላለ ከአሥር የማይበልጡም ሆነ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ አምላኪዎች በተገኙበት ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (ማቴዎስ 18:​20) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ይህን የተናገረው ጉባኤውን በግንባር ቀደምትነት የሚመሩ ወንድሞች ስለሚመለከቷቸው የፍርድ ጉዳዮች ሲናገር ነው። (ማቴዎስ 18:​15-19) ይሁን እንጂ ይኸው የኢየሱስ ቃል በስሙ በሚቀርብ ጸሎት በሚጀመሩና በሚደመደሙ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሙሉ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ተፈጻሚነት ይኖረዋልን? አዎን። ኢየሱስ ተከታዮቹን ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እንዲያካሂዱ ባዘዘ ጊዜ “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሎ እንደነበረ አስታውስ።​—⁠ማቴዎስ 28:​20

2 የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ተከታዮቹ ስለሚያደርጓቸው ስብሰባዎች አጥብቆ እንደሚያስብ ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት በእነርሱ መካከል እንደሚገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሥራ 2:​33፤ ራእይ 5:​6) ይሖዋ አምላክም ቢሆን ስለምናደርጋቸው ስብሰባዎች ያስባል። የእነዚህ ስብሰባዎች ተቀዳሚ ዓላማ “በማኅበር” የሚቀርብ ውዳሴ ወደ አምላክ እንዲያርግ ማድረግ ነው። (መዝሙር 26:​12) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ለአምላክ ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ነው።

3. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን የምናደንቀው በምን አስፈላጊ ምክንያቶች የተነሣ ነው?

3 ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት የምናሳይባቸው ሌሎች ተገቢ ምክንያቶችም አሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርን ለቅቆ ከመሄዱ በፊት ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱን ለእምነት ቤተሰቦች ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው እንዲያገለግሉ ሾሞአል። (ማቴዎስ 24:​45) ይህ መንፈሳዊ ምግብ ከሚቀርብባቸው ዋነኛ መንገዶች መካከል የጉባኤ ስብሰባዎችና ታላላቅ ስብሰባዎች ይገኛሉ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ታማኝ ባሪያ አመራር በመስጠት ከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ድነው በአምላክ የጽድቅ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እንዲቀርብ ያደርጋል።

4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትኛው አደገኛ የሆነ “ልማድ” ተጠቅሷል? ይህንንስ ለማስወገድ የሚረዳን ምንድን ነው?

4 ስለዚህ ማንኛውም ክርስቲያን ሐዋርያው ጳውሎስ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ” ብሎ በጻፈ ጊዜ የገለጸው ዓይነት አደገኛ ልማድ እንዲጠናወተው ቢፈቅድ በጣም መጥፎ ይሆንበታል። (ዕብራውያን 10:​24, 25) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚያስገኛቸውን መብቶችና ጥቅሞች ብናሰላስል እነዚህን ስብሰባዎች በታማኝነትና በሙሉ ልብ እንድንደግፍ ይረዳናል።

የሚያንጹ ስብሰባዎች

5. (ሀ)በስብሰባዎች ላይ ንግግራችን እንዴት ያለ ውጤት ማስገኘት ይኖርበታል? (ለ) ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሳንዘገይ በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ መጋበዝ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

5 ክርስቲያኖች የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ስለሚጸልዩ በስብሰባ የሚገኝ እያንዳንዱ ግለሰብ ከመንፈሱ ጋር የሚስማማ ሥራ ለመሥራትና ‘የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንዳያሳዝን’ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። (ኤፌሶን 4:​30) ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት በጻፈ ጊዜ ትክክለኛ ስለሆነ የአንደበት አጠቃቀም መናገሩ ነበር። ምንጊዜም ቢሆን የምንናገረው ነገር “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም” መሆን ይኖርበታል። (ኤፌሶን 4:​29) በተለይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክት ላይ ስብሰባዎች የሚያንጹ፣ ትምህርት የሚሰጡና የሚያበረታቱ መሆን እንደሚገባቸው አጥብቆ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 14:​5, 12, 19, 26, 31) እንዲህ ካለው ስብሰባ በዚያ የተገኙ በሙሉ፣ “እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው” ከሚል መደምደሚያ ሊደርሱ የሚችሉ አዳዲስ ሰዎች ጭምር ጥቅም ያገኛሉ። (1 ቆሮንቶስ 14:​25) በዚህ ምክንያት ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች አብረውን እንዲሰበሰቡ ሳንዘገይ መጋበዝ ይኖርብናል። አብረ​ውን መሰብሰባቸው መንፈሳዊ እድገታቸውን ያፋጥን​ላቸዋል።

6. አንድ ስብሰባ የሚያንጽ እንዲሆን ከሚያደርጉት ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

6 በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ንግግር፣ ቃለ መጠይቅ ወይም ሠርቶ ማሳያ እንዲያቀርቡ የሚመደቡ ሁሉ የሚናገሩት ነገር የሚያንጽና የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ መሆኑን ለማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ትክክለኛ ነገር ከመናገር በተጨማሪ ከአምላክና ከክርስቶስ የፍቅር ባሕርይ ጋር የሚስማማ ስሜትና ዝንባሌ ማሳየት ይኖርብናል። በስብሰባው ፕሮግራም ላይ ክፍል ያላቸው በሙሉ እንደ ደስታ፣ ትዕግሥትና እምነት የመሳሰሉትን ‘የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች’ የሚያንጸባርቁ ከሆነ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ ታንጸው እንደሚመለሱ የተረጋገጠ ነው።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

7. በስብሰባ ላይ የሚገኙ ሁሉ ስብሰባው የሚያንጽ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት እንዴት ነው?

7 በጉባኤ የስብሰባ ፕሮግራሞች ላይ ክፍል የሚኖራቸው ጥቂቶች ቢሆኑም ሁሉም ሰው ስብሰባው የሚያንጽ እንዲሆን አስተዋጸኦ ሊያደርግ ይችላል። አድማጮች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡባቸው አጋጣሚዎች አሉ። እነዚህ አጋጣሚዎች እምነታችንን በሕዝብ ፊት እንድንገልጽ ያስችሉናል። (ሮሜ 10:​9) እነዚህን አጋጣሚዎች የግል አስተሳሰባችንን ለማስፋፋት፣ በግላችን ስላገኘናቸው መልካም ውጤቶች በጉራ ለመናገር ወይም የእምነት ባልደረባችንን ለመተቸት መጠቀም አይገባንም። እንዲህ ብናደርግ የአምላክን መንፈስ ማሳዘን አይሆንብንምን? ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር አለመግባባት ቢፈጠር ብቻችንን በፍቅር መንፈስ ብንፈታው በጣም የተሻለ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ” ይላል። (ኤፌሶን 4:​32) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይህን ግሩም ምክር ሥራ ላይ እንድናውል የሚያስችሉ እንዴት ያሉ ግሩም አጋጣሚዎች ናቸው! ለዚህም ሲሉ ብዙዎች ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ቀደም ብለው መሰብሰቢያው ቦታ ይደርሳሉ፣ ካለቀም በኋላ ቆይተው ይሄዳሉ። እንዲህ ማድረግ ባይተዋርነት ሊሰማቸው የሚችሉትን አዳዲስ ሰዎች በጣም ይረዳል። በዚህ መንገድ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ ‘እርስ በርሳቸው ለፍቅርና ለመልካም ሥራ በመነቃቃት’ ስብሰባቸውን የሚያንጽ በማድረግ ረገድ የየበኩላቸውን ድርሻ ያበረክታሉ።

በደንብ ተዘጋጅ

8. (ሀ) አንዳንዶች በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንዴት ያለ የሚያስመሰግን መሥዋዕትነት ይከፍላሉ? (ለ) ይሖዋ በእረኝነት ረገድ ምን ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል?

8 ለአንዳንዶች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ብዙም ከባድ ባይሆንባቸውም ለሌሎች ግን የማይቋረጥ መሥዋዕትነት ይጠይቅባቸዋል። ለምሳሌ አንዲት ክርስቲያን እናት ለቤተሰብዋ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ሰብዓዊ ሥራ ስትሠራ ከዋለች በኋላ ደክሟት እቤትዋ ትደርሳለች። ከዚያም ምግብ መሥራትና ልጆችዋን ለስብሰባ ማዘጋጀት ይኖርባት ይሆናል። ሌሎች ክርስቲያኖች ወደ ስብሰባዎች ለመድረስ ብዙ መጓዝ ያስፈልጋቸው ይሆናል፣ ከእርጅና ወይም ከአካል ጉዳተኝነት የተነሳ ችግር ይኖርባቸዋል። ይሖዋ አምላክ በመንጋው ውስጥ ያለውን የእያንዳንዱን በግ ሁኔታ አሳምሮ እንደሚያውቅ አፍቃሪ እረኛ የእያንዳንዱን ታማኝ ተሰብሳቢ ሁኔታ እንደሚረዳ የተረጋገጠ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “[“ይሖዋ፣” NW] መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል” ይላል።​—⁠ኢሳይያስ 40:​11

9, 10. ከስብሰባዎች የተሟላ ጥቅም ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?

9 ሁልጊዜ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከፍተኛ መሥዋዕትነት የሚጠይቅባቸው ወንድሞችና እህቶች የሚጠናውን ጽሑፍ ለመዘጋጀት የሚያውሉት ጊዜ በጣም መጠነኛ ሊሆንባቸው ይችላል። የየሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ተከታትሎ ማንበብ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ብዙ ጥቅም ለማግኘት ያስችላል። በተመሳሳይም እንደ መጠበቂያ ግንብ እና መጽሐፍ ጥናት ላሉት ሌሎች ስብሰባዎች ቀደም ብሎ መዘጋጀት ከስብሰባዎቹ ብዙ ጥቅም ለማግኘት ይረዳል። የጊዜ እጥረት ያለባቸው የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች የሚጠናውን ጽሑፍ አስቀድመው ቢያነቡና ቢያንስ በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሱትን አንዳንድ ጥቅሶች ቢያነቡ በጣም አስፈላጊ በሆኑት በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል።

10 ሰፊ ጊዜ ያላቸው ደግሞ ለስብሰባዎች ዝግጅት የሚያሳልፉትን ጊዜ ረዘም ሊያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ በተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ምርምር ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህ መንገድ በስብሰባ ላይ የሚገኙት በሙሉ ከስብሰባዎች ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም በሙሉ ለማግኘትና በንግግራቸውና በሚሰጡት ሐሳብ ጉባኤውን በማነጽ ሊሳተፉ ይችላሉ። ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮችም ጥሩ ዝግጅት በማድረግ እጥር ምጥን ያለና ግልጽ መልስ በመስጠት ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። በስብሰባ ላይ የሚገኙ ሁሉ ለይሖዋ ዝግጅቶች ካላቸው አክብሮት በመነሳሳት ስብሰባው እየተካሄደ ባለበት ጊዜ ማንኛውንም የሚረብሽ ነገር ከማድረግ ይቆጠባሉ።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​3

11. ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት ራስን መገሰጽ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ለመንፈሳዊ ጤናችን አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዳዮችና መዝናኛዎች አብዛኛውን ጊዜያችንን ይሻሙብን ይሆናል። ከሆነ ራሳችንን መመርመርና በጊዜ አጠቃቀማችን ረገድ ‘ሞኞች መሆናችንን’ ማቆም ይኖርብናል። (ኤፌሶን 5:​17) ዓላማችን ጊዜያችንን በጣም አስፈላጊ ካልሆኑ ጉዳዮች ‘ዋጅተን’ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ለስብሰባ ዝግጅት፣ እንዲሁም ለመንግሥቱ አገልግሎት ማዋል ነው። (ኤፌሶን 5:​16) እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆንና ራስን መገሰጽ እንደሚጠይቅ አይካድም። ለዚህ ነገር ትኩረት የሚሰጡ ወጣቶች ለወደፊት እድገታቸው ጥሩ መሠረት ይጥላሉ። ጳውሎስ ለወጣቱ ባልደረባው ለጢሞቴዎስ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር” ሲል ጽፏል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​15

በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጹ ምሳሌዎች

12. የሳሙኤል ቤተሰብ ምን ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል?

12 የአምላክ መገናኛ ድንኳን በሴሎ ይገኝ በነበረበት ጊዜ ከአምልኮ ባልደረቦች ጋር ለመሰብሰብ በሚያስችሉ ዝግጅቶች ላይ ዘወትር ይገኝ የነበረውን የሳሙኤል ቤተሰብ እንውሰድ። በዓመታዊ በዓላት ላይ የመገኘት ግዴታ የነበረባቸው ወንዶች ብቻ ነበሩ። የሳሙኤል አባት ሕልቃና ግን መላ ቤተሰቡን ይዞ “ይሰግድ ዘንድ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው በየዓመቱ ይወጣ ነበር።” (1 ሳሙኤል 1:​3-5) የሳሙኤል ትውልድ ከተማ የሆነችው አርማቴም መሴፋ በዘመናዊቱ ረንቲስ አቅራቢያ በሚገኘው የባሕር ጠረፍ፣ “በተራራማው የኤፍሬም አገር” ግርጌ የምትገኝ ሳትሆን አትቀርም። (1 ሳሙኤል 1:​1) ስለዚህ ወደ ሴሎ የሚያደርገው ጉዞ የ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን በዚያ ዘመን በጣም የሚያደክም መንገድ ነበር። የሕልቃና ቤተሰብ ግን ‘በየዓመቱ እንዲህ ያደርግና ወደ ይሖዋ ቤት ይወጣ ነበር።’​—⁠1 ሳሙኤል 1:​7

13. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ታማኝ አይሁዶች ምን ምሳሌ ትተውልናል?

13 ኢየሱስም ያደገው ብዙ አባላት ባሉት ቤተሰብ ውስጥ ነው። ይህ ቤተሰብ በኢየሩሳሌም በሚከበረው የማለፍ በዓል ላይ ለመገኘት ከናዝሬት ተነስቶ 100 ኪሎ ሜትር የሚያክል መንገድ ወደ ደቡብ ይጓዝ ነበር። ሊጓዙባቸው የሚችሉ ሁለት አማራጭ መንገዶች ነበሯቸው። ይበልጥ ቀጥተኛ የሆነው መንገድ ወደ መጊዶ ሸለቆ ካሽቆለቆለ በኋላ 600 ሜትር ያህል ሽቅብ ወጥቶ የሳምራውያንን ግዛት አቋርጦ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርሰው ነው። ይበልጥ ተመራጭ የሆነው ሌላ መንገድ ኢየሱስ በ33 እዘአ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ የተከተለው ነው። ይህም ከባሕር ወለል በታች ወደሚገኘው የዮርዳኖስ ሸለቆ ከተጓዙ በኋላ “በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር” መምጣትን የሚጠይቅ ነበር። (ማርቆስ 10:​1) ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርሰው መንገድ የ30 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከ1,100 ሜትር የሚበልጥ አቀበት መውጣት ይጠይቃል። (ማርቆስ 10:​32) በጣም ብዙ የሆኑ ታማኝ በዓል አክባሪዎች ከገሊላ እስከ ኢየሩሳሌም የሚገኘውን አድካሚ ጉዞ ያደርጉ ነበር። (ሉቃስ 2:​44) ለዘመናዊ መጓጓዣ ምስጋና ይድረሰውና ብዙ ውጣ ውረድ ሳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ለሚችሉ ባደጉ አገሮች ለሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች እንዴት ያለ ጥሩ አርዓያ ነው!

14, 15. (ሀ) ሐናስ ምን ምሳሌ ትታልናለች? (ለ) በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ አዳዲስ ሰዎች ከሚያሳዩት ጥሩ ዝንባሌ ምን እንማራለን?

14 ሌላዋ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነን ሴት የ84 ዓመትዋ መበለት ሐና ናት። መጽሐፍ ቅዱስ “ከመቅደስ አትለይም ነበር” ይላል። (ሉቃስ 2:​37) ከዚህም በላይ ሐና ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት ታሳይ ነበር። ሕፃኑን ኢየሱስን በተመለከተችና ተስፋ የተደረገው መሲሕ መሆኑን ባወቀች ጊዜ ምን አደረገች? አምላክን አመሰገነች፤ በተጨማሪም “የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።” (ሉቃስ 2:​38) ለዛሬዎቹ ክርስቲያኖች አርዓያ የሚሆን እንዴት ያለ ድንቅ ዝንባሌ ነው!

15 አዎን፣ በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘትና መካፈል ልክ እንደ ሐና የሚያስደስተን መሆን አለበት እንጂ የመቅረት ፍላጎት ፈጽሞ ወደ አእምሯችን ሊመጣ አይገባውም። ብዙ አዳዲስ ሰዎች በስብሰባዎች መገኘት ያስደስታቸዋል። ከነበሩበት ጨለማ ወጥተው አስደናቂ ወደሆነው የአምላክ ብርሃን ስለመጡ የተቻላቸውን ያህል ብዙ ለመማር ይፈልጋሉ። ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። በሌላው በኩል ደግሞ በእውነት ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩት ‘የቀድሞ ፍቅራቸውን እንዳይተዉ’ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (ራእይ 2:​4) ከባድ የጤና እክል ወይም ሌላ ችግር አንድን ሰው ከስብሰባ ሊያስቀር የሚችልበት ጊዜ ይኖራል። ይሁን እንጂ ፍቅረ ንዋይ፣ መዝናኛ ወይም ፍላጎት ማጣት ሳንዘጋጅ እንድንሄድ፣ ተመልካቾች ብቻ ወይም የማናዘወትር ተሰብሳቢዎች እንዳያደርገን መጠንቀቅ ይኖርብናል።​—⁠ሉቃስ 8:​14

ከሁሉ የሚበልጠው ምሳሌ

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ለመንፈሳዊ ስብሰባዎች ምን ዓይነት ዝንባሌ ነበረው? (ለ) ሁሉም ክርስቲያኖች የትኛውን ጥሩ ልማድ ለመከተል መሞከር ይገባቸዋል?

16 ለመንፈሳዊ ስብሰባዎች አድናቆት በማሳየት ረገድ ግንባር ቀደም ምሳሌ የተወልን ኢየሱስ ነው። ገና በ12 ዓመት የወጣትነት ዕድሜው በኢየሩሳሌም ለነበረው የአምላክ ቤት ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው አስመስክሯል። ወላጆቹ የደረሰበት ጠፍቷቸው ከቆዩ በኋላ በቤተ መቅደስ ውስጥ ከመምህራን ጋር የአምላክን ቃል ሲወያይ አገኙት። ኢየሱስ ወላጆቹ ለተሰማቸው ጭንቀት መልስ ሲሰጥ በአክብሮት “በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። (ሉቃስ 2:​49) ወጣቱ ኢየሱስ በታዛዥነት ከወላጆቹ ጋር ወደ ናዝሬት ተመለሰ። በዚያም አዘውትሮ በምኩራብ በመገኘት ለአምልኮ ስብሰባዎች ያለውን ፍቅር አሳይቷል። በዚህም ምክንያት አገልግሎቱን ሲጀምር ያደረገውን መጽሐፍ ቅዱስ ይተርክልናል:- “ወዳደገበቱም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፣ ሊያነብም ተነሣ።” ኢየሱስ ኢሳይያስ 61:​1, 2ን ካነበበና ካብራራ በኋላ አድማጮቹ “ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ” ተደነቁ።​—⁠ሉቃስ 4:​16, 22፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

17 በዛሬው ጊዜ የሚደረጉ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም የሚከተሉት ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት ነው። ስብሰባው በውዳሴ መዝሙርና በጸሎት ከተጀመረ በኋላ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተውጣጡ ጥቅሶች (ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱ ጥቅሶች) እየተነበቡ ይብራራሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ጥሩ ልማድ የመከተል ግዳጅ ተጥሎባቸዋል። ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት በጣም ያስደስታቸዋል።

ዘመናዊ ምሳሌዎች

18, 19. በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ረገድ ባልበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች ምን አስደናቂ ምሳሌነት አሳይተዋል?

18 በኢኮኖሚ ብዙ ባልዳበሩ የምድር ክፍሎች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት በማሳየት ረገድ በጣም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በሞዛምቢክ ኦርላንዶ የተባለ የአውራጃ የበላይ ተመልካችና ሚስቱ አሜልያ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለማገልገል በተራራማ አካባቢ 90 ኪሎ ሜትር ለ45 ሰዓት በእግር ተጉዘዋል። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ደግሞ በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ ለማገልገል ያንኑ መንገድ እንደገና መጓዝ ነበረባቸው። ኦርላንዶ የራሱን ድካም አሳንሶ በመመልከት “ከባዋ ጉባኤ የመጡትን ወንድሞች ስንመለከት እኛ ያደረግነው ከምንም እንደማይቆጠር ተሰማን። እነዚህ ወንድሞች በስብሰባው ላይ ለመገኘትና ወደ ቤታቸው ለመመለስ ስድስት ቀን የሚፈጅ የ400 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ማድረግ ነበረባቸው። ከመካከላቸው የ60 ዓመት አረጋዊ ወንድም ይገኝ ነበር” ብሏል።

19 ለሳምንታዊ ስብሰባዎች አድናቆት በማሳየት ረገድስ? ካሽዋሽዋ ንጃምባ 70 ዓመት የሆናት አቅመ ደካማ እህት ናት። የምትኖረው በናሚብያ ሩንዱ ከሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ 5 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ካይሶሶሲ በሚባል አነስተኛ መንደር ነው። በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጫካ አቋርጣ የ10 ኪሎ ሜትር ደርሶ መልስ ጉዞ ታደርጋለች። በዚህ መንገድ ላይ ብዙ ሰዎች በወንበዴዎች የተዘረፉ ቢሆንም ካሽዋሽዋ አዘውትራ በስብሰባዎች መገኘትዋን አላቆመችም። አብዛኞቹ ስብሰባዎች የሚመሩት በማታውቀው ቋንቋ ነው። ታዲያ ከስብሰባዎቹ የምትጠቀመው እንዴት ነው? ካሽዋሽዋ “ጥቅሶቹን እየተከታተልኩ ንግግሩ ስለ ምን ነገር እንደሆነ ለመገመት እሞክራለሁ” ትላለች። ይሁን እንጂ መጻፍና ማንበብ ሳትችል እንዴት ጥቅሶቹን ትከታተላለች? “በቃል የማውቃቸውን ጥቅሶች እያዳመጥሁ እከታተላለሁ” በማለት ትመልሳለች። ባሳለፈቻቸው ዓመታት ብዙ ጥቅሶችን በቃል ለመያዝ ችላለች። የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ችሎታዋን ለማሻሻል ስትል ጉባኤው ባዘጋጀው የመሠረተ ትምህርት ክፍል ትገኛለች። “በስብሰባዎች መገኘት በጣም ያስደስተኛል” ትላለች። “ሁልጊዜ ልንማራቸው የሚገቡ አዳዲስ ነገሮች ይኖራሉ። ከወንድሞችና እህቶች ጋር ተገናኝቶ መጫወት ያስደስተኛል። ከሁሉም ጋር ለመጫወት ባልችልም ሁልጊዜ እየመጡ ሰላም ይሉኛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በስብሰባዎች ላይ በመገኘቴ የይሖዋን ልብ እንደማስደስት አውቃለሁ።”

20. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችንን መተው የማይገባን ለምንድን ነው?

20 እንደ ካሽዋሽዋ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ በመላው ዓለም የሚኖሩ የይሖዋ አምላኪዎች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ተመሳሳይ የሆነ የሚያስመሰግን አድናቆት ያሳያሉ። የሰይጣን ዓለም ወደ ጥፋት እየገሰገሰ በሚገኝበት በአሁኑ ጊዜ አንድ ላይ መሰብሰባችንን መተው አንችልም። ከዚህ ይልቅ በመንፈሳዊ ንቁዎች ሆነን በመኖር ለጉባኤና ለትላልቅ ስብሰባዎች የጠለቀ አክብሮት እንዳለን እናሳይ። እንዲህ ማድረጋችን የይሖዋን ልብ ከማስደሰት አልፎ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን መለኮታዊ ትምህርት እንድናገኝ ስለሚያስችለን ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልናል።​—⁠ምሳሌ 27:​11፤ ኢሳይያስ 48:​17, 18፤ ማርቆስ 13:​35-37

የክለሳ ጥያቄዎች

◻ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ትልቅ መብት የሆነው ለምንድን ነው?

◻ በስብሰባ ላይ የሚገኙ ሁሉ ስብሰባው የሚያንጽ እንዲሆን የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል?

◻ ባልበለጸጉ አገሮች ከሚኖሩ ወንድሞች ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሳምንታዊ ስብሰባዎችን ያደንቃሉ

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነትና በወንጀል በተጥለቀለቁ ከተሞች ይኖራሉ። እንደነዚህ ባሉት ከተሞች የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን እነዚህን ሁኔታዎች በመቋቋም ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያስመሰግን አድናቆት እንዳላቸው አሳይተዋል። በደቡብ አፍሪካ፣ በጋውቴ ክፍለ ሐገር በሶዌቶ ከተማ ከሚገኙት ጉባኤዎች በአንዱ የሚያገለግል አንድ ሽማግሌ የሚከተለውን ሪፖርት ልኳል:- “60 ምሥክሮችና ያልተጠመቁ አስፋፊዎች በሚገኙበት ጉባኤ ውስጥ 70 እና 80 አንዳንዴም ከዚህ የሚበልጡ ሰዎች በስብሰባዎቻችን ላይ ይገኛሉ። ወንድሞችና እህቶች ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ሩቅ መንገድ መሄድ ባያስፈልጋቸውም በዚህ የሶዌቶ ክፍለ ከተማ ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ ነው። አንድ ወንድም ወደ ስብሰባ በሚሄድበት ጊዜ ጀርባው ላይ በጩቤ ተወግቷል። ቢያንስ ሁለት እህቶች የዘረፋ ሙከራ ተደርጎባቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ወደ ስብሰባ ከመምጣት አያግዳቸውም። ቅዳሜ፣ ቅዳሜ ስብሰባችንን በጸሎት ከዘጋን በኋላ አጭር የመዝሙር ልምምድ እናደርጋለን። ከስብሰባው በኋላም ቢያንስ 95 በመቶ የሚሆኑት ቆይተው በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ የሚዘመሩትን መዝሙሮች በሙሉ ይዘምራሉ። ይህም አዳዲስ ተሰብሳቢዎች መዝሙሮቹን እንዲለማመዱና አብረውን እንዲዘምሩ አስችሏል።”

በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ደግሞ ሌሎች እንቅፋቶችን ለመወጣት ተገደዋል። በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በሳምንት ሦስት ጊዜ ረዥም መንገድ መጓዝ አለባቸው። ፍላጎት ያላቸው አንድ ባልና ሚስት የሚኖሩት በቦትስዋና፣ ሎባትሰ ከሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ 15 ኪሎ ሜትር ርቀው ነው። ባለፈው ዓመት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ሆነው በስብሰባዎች አዘውትረው ይገኙ ነበር። ባልዬው ቤተሰቡን ለማስተዳደር ጫማ ይጠግናል። ሚስቲቱ ደግሞ ወደ ስብሰባዎች ለመመላለስ የሚያስፈልጋቸውን የመጓጓዣ ወጪ ለመሸፈን እንዲችሉ ትናንሽ ዕቃዎች እየሸጠች የቤተሰቡን ገቢ ትደጉማለች።

በቅርቡ በአንድ ምሽት የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የተገኘበትን ስብሰባ ከጨረሱ በኋላ አውቶቡስ ጣቢያ ሲደርሱ መኪና ያጣሉ። ከምሽቱ 3 ሰዓት ሆኗል። አውቶቡሶቹ መጥፎ የአየር ሁኔታ በመኖሩ ምክንያት ቀደም ብለው ሥራቸውን አቁመዋል። አንድ የፖሊስ መኮንን መኪናውን ያቆምና ምን እንደሚያደርጉ ይጠይቃቸዋል። ችግራቸውን ከሰማ በኋላ አዘነላቸውና 15ቱን ኪሎ ሜትር ተጉዞ እቤታቸው አደረሳቸው። ያልተጠመቀች አስፋፊ የሆነችው ሚስት ለባልዋ “አየህ፣ ስብሰባዎችን እስካስቀደምን ድረስ ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልገንን ያዘጋጅልናል” አለች። በአሁኑ ጊዜ ባልዬውም የምሥራቹ ሰባኪ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እነዚህን በሩማንያ የሚኖሩትን የመሰሉ ምሥክሮች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ