ውድ ለሆነው ክርስቲያናዊ ቅርስ አመስጋኝ ነኝ
ግዌን ጉች እንደተናገረችው
በትምህርት ቤት እያለሁ ‘ታላቁ ይሖዋ በክብር ዙፋኑ ላይ ተቀምጧል ’ የሚሉትን ቃላት የያዘ መዝሙር እዘምር ነበር። ብዙ ጊዜ ‘ይህ ይሖዋ የሚባለው ማን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር።
አያቶቼ አምላክን የሚፈሩ ነበሩ። በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ከሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አንድ ላይ መሰብሰብ ጀመሩ። አባቴ በንግዱ ሥራ ተሳክቶለት ነበር። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ላይ የወረሰውን ክርስቲያናዊ ቅርስ ለሦስት ልጆቹ አላስተላለፈም ነበር።
አባቴ ለወንድሜ ለዳግላስ፣ ለእህቴ ለአንና ለእኔ የእርሱ ሥራዎች እና አምላክ ማን ነው? የተባሉትን (የእንግሊዝኛ) ቡክሌቶች በሰጠን ጊዜ ይሖዋ የእውነተኛው አምላክ ስም መሆኑን ተገነዘብኩ። (መዝሙር 83:18 NW) እጅግ ተደስቼ ነበር! ይሁን እንጂ የአባቴ ፍላጎት እንዲቀሰቀስ ያደረገው ምን ነበር?
አባቴ በ1938 ብሔራት ለጦርነት እየተዘጋጁ እንዳሉ ሲመለከት የሰው ልጆች የዓለምን ችግሮች ለመፍታት እንደማይችሉ ተገነዘበ። ሴት አያቴ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሙትን ጠላቶች (የእንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ ሰጠችው። መጽሐፉን ካነበበ በኋላ የሰው ልጅ ቀንደኛ ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑንና ለዓለም ሰላም የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን አወቀ።a—ዳንኤል 2:44፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4
ጦርነቱ እየተቃረበ ሲመጣ ቤተሰባችን በሰሜን ለንደን በዉድ ግሪን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። በሰኔ 1939 በአቅራቢያችን ወደሚገኘው አሌክሳንድራ ቤተ መንግሥት ሄደን “መንግሥት እና ሰላም” የሚለውን በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የቀረበውን የሕዝብ ንግግር አዳመጥን። ራዘርፎርድ በኒው ዮርክ ከተማ በሜዲሰን ስኩዌር ያደረገው ንግግር ወደ ለንደንና ወደ ሌሎች ትላልቅ ከተሞች በራዲዮ ተላልፎ ነበር። ድምፁ በጥራት ይሰማ ስለ ነበር በኒው ዮርክ ከተማ የሚገኙ ጋጠወጥ አድመኞች ረብሻ ሲፈጥሩ እኛ ባለንበት አዳራሽ ውስጥ የተፈጸመ መስሎኝ ዙሪያዬን ቃኘሁ።
አባቴ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረው ቅንዓት
አባቴ በእያንዳንዱ ቅዳሜ ምሽት ቤተሰቡ በጠቅላላ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና አደረገ። ጥናታችን በሚቀጥለው ቀን በሚጠናው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕስ ላይ ያተኮረ ነበር። በግንቦት 1, 1939 መጠበቂያ ግንብ ላይ ስለ ኢያሱና ስለ አይ ከተማ ከበባ የተሰጠው መግለጫ እስከ አሁን ድረስ ከአእምሮዬ አለመጥፋታቸው እነዚህ ጥናቶች በእኔ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ያሳያል። በታሪኩ መግለጫ ከመመሰጤ የተነሣ ጥቅሶቹን በሙሉ ከራሴ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቼ አነበብኳቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንዲህ የመሰለውን ምርምር ማድረግ በጣም ያስደስተኛል።
የምንማራቸውን ነገሮች ለሌሎች ማካፈሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ወደ ልቤ ጠልቀው እንዲገቡ አድርጓል። አንድ ቀን አባቴ የሸክላ ማጫወቻና የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር የተቀዳበት ሸክላ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት እንጠቀምበት የነበረ አንድ ቡክሌት እና የአንዲት በዕድሜ የገፋች ሴት አድራሻ ሰጠኝ። ከዚያም ይህችን ሴት ሄደሽ አነጋግሪያት አለኝ።
“ምንድን ነው የምለው? ደግሞስ ምን ማድረግ አለብኝ?” ስል ጠየቅሁት።
አባቴ “ሁሉም ነገር አለልሽ። ሸክላውን አሰሚያት፣ ጥያቄዎቹን አንብቢ፣ የቤቱ ባለቤት መልሶቹን እንድታነብ አድርጊ። ከዚያም ጥቅሶቹን አንብቢ” አለኝ።
እንዳለኝ አደርግሁ። በዚህ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ተማርኩ። ቅዱሳን ጽሑፎችን በዚህ መልኩ በአገልግሎት ላይ በመጠቀሜ ስለ እነሱ ያለኝ ግንዛቤ ሊያድግ ችሏል።
በጦርነቱ ዓመታት የነበሩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 በፈነዳ በዓመቱ ይሖዋን ለማገልገል ራሴን ወስኜ ተጠመቅሁ። ገና 13 ዓመቴ ነበር። አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን የወሰንኩት ያኔ ነበር። በ1941 ትምህርቴን አቋረጥኩና በሌስተር በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከዳግላስ ጋር በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ መሳተፍ ጀመርኩ።
በቀጣዩ ዓመት አባቴ በጦርነቱ ለመካፈል ሕሊናው ስላልፈቀደለት ታሰረ። እኛ ልጆች በዚያ አስቸጋሪ የጦርነት ወቅት እናታችን ለቤተሰቡ በምታደርገው እንክብካቤ አግዘናታል። ከዚያም አባቴ ከእስር ከተለቀቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዳግላስ ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ተጠራ። በአንድ የከተማው ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “ልጅየው እንደ አባቱ መታሰርን የመረጠበት ምክንያት” ይል ነበር። ይህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን የማይገድሉት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ ስለነበር ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል።—ዮሐንስ 13:35፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12
በእነዚያ የጦርነት ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይካፈሉ የነበሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ሁልጊዜ ወደ ቤታችን እየመጡ ይጠይቁን ነበር። ገንቢ የነበሩት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይቶቻቸው ከአእምሯችን የማይጠፋ ትዝታን ትተው አልፈዋል። ከእነዚህ የታመኑ ክርስቲያን ወንድሞች መካከል ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት የሆኑት ጆን ባርና አልበርት ሽሮደር ይገኙበታል። ወላጆቼ እንግዳ ተቀባዮች የነበሩ ሲሆን እኛም እንደ እነሱ እንድንሆን አስተምረውናል።—ዕብራውያን 13:2
መልስ ለመስጠት የተዘጋጁ መሆን
የአቅኚነት አገልግሎት እንደ ጀመርኩ ብዙም ሳልቆይ ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ሂልዳን አገኘኋት። እሷም “ባለቤቴ እንደ አንቺ ላሉ ሰዎች ሲል እየተዋጋ ነው! አንቺስ ለጦርነቱ የበኩልሽን አስተዋጽኦ የማታደርጊው ለምንድን ነው?” ስትል በቁጣ ጮኸችብኝ።
“እያደረግሁት ስላለው ነገር የምታውቂው ምን ያህል ነው? ወደ አንቺ የመጣሁትስ ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?” ስል ጠይቅኋት።
“እስቲ ግቢና ንገሪኝ” ስትል መለሰች።
ብዙውን ጊዜ በአምላክ ስም በሚደረጉ አሰቃቂ ነገሮች ምክንያት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እውነተኛ ተስፋ መኖሩን እየተናገርን መሆኑን አስረዳኋት። ሂልዳ በአድናቆት አዳመጠችኝ፤ እንዲሁም የመጀመሪያዋ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ሆነች። ሂልዳ ንቁ ምሥክር በመሆን ከ55 የሚበልጡ ዓመታት አገልግላለች።
በጦርነቱ ማብቂያ ላይ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ በምትገኘው ዶርቸስተር በምትባል መንደር አዲስ የአቅኚነት ምድብ ተቀበልኩ። ከቤቴ ርቄ ስኖር ይህ የመጀመሪያዬ ነበር። ትንሹ ጉባኤያችን ይሰበሰብ የነበረው በ16ኛው መቶ ዘመን በተገነባ “ዚ ኦልድ ቲ ሃውስ” በሚባል ሕንፃ ውስጥ ነበር። ለእያንዳንዱ ስብሰባችን ጠረጴዛዎችንና ወንበሮችን እንደገና ማስተካከል ነበረብን። ቀደም ሲል እሰበሰብበት ከነበረው የመንግሥት አዳራሽ በጣም የተለየ ነበር። ቢሆንም በዚያ ከነበረው ጋር የሚመሳሰል መንፈሳዊ ምግብና የክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ፍቅራዊ ኅብረት እዚህም ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወላጆቼ በደቡብ ለንደን ወደሚገኘው ተንብሪጅ ዌልስ ተዛወሩ። ከአባቴና ከአን ጋር አንድ ላይ በአቅኚነት ለማገልገል እንድንችል ወደ ቤት ተመለስኩ። ብዙም ሳይቆይ ጉባኤያችን ከ12 ወደ 70 ምሥክሮች በማደጉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት በደቡብ ጠረፍ ወደሚገኘው ወደ ብሪቶን እንዲሄድ ቤተሰባችን ተጠየቀ። ብዙዎች ከእኛ የአቅኚዎች ቤተሰብ ጋር በመስበኩ ሥራ በቅንዓት የተካፈሉ ሲሆን ይሖዋም ሥራችንን አብዝቶ ሲባርከው ተመልክተናል። ብዙም ሳይቆይ አንድ የነበረው ጉባኤ ሦስት ሆነ!
ያልተጠበቀ ግብዣ
በኒው ዮርክ ከተማ በያንኪ ስታዲየም በ1950 የበጋ ወቅት የተካሄደውን የቲኦክራሲው ጭማሪ የተባለውን ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለመካፈል ከብሪታንያ ከሄዱት 850 ልዑካን መካከል ቤተሰባችንም ይገኝበት ነበር። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከሌሎች አገሮች የመጡ ብዙ አቅኚዎች በኒው ዮርክ ሳውዝ ላንሲንግ አቅራቢያ በሚገኘው በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የሚያስችል ማመልከቻ ተልኮላቸው ነበር። ከእነዚህ መካከል ዳግላስ፣ አንና እኔ እንገኝበት ነበር! ማመልከቻውን ሞልቼ ፖስታ ቤት ስከት ‘አሁን ቃል ገብቻለሁ! ሕይወቴ ምን አቅጣጫ ይይዝ ይሆን?’ እያልኩ አስብ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ሆኖም ቁርጥ ውሳኔዬ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” የሚል ነበር። (ኢሳይያስ 6:8) የአውራጃ ስብሰባው ካበቃ በኋላ በዚያው ቆይቼ ከዳግላስና ከአን ጋር በመሆን የጊልያድ 16ኛው ክፍል ተማሪ እንድሆን ስጠራ እጅግ ተደሰትኩ። ሁላችንም ሚስዮናውያን በመሆን ወደ የትኛውም የዓለም ክፍል ልንላክ እንደምንችል ተገንዝበን ነበር።
ቤተሰባችን አንድ ላይ ሆኖ የአውራጃ ስብሰባውን ከተካፈለ በኋላ ወላጆቻችን ለብቻቸው ወደ እንግሊዝ የሚመለሱበት ጊዜ ደረሰ። ወላጆቻችን ሞሪቴኒያ በተባለችው መርከብ ተሳፍረው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ሦስት ልጆቻቸው እጃችንን እያውለበለብን ተሰናበትናቸው። እንዴት ያለ ስሜትን የሚነካ የመሰናበቻ ጊዜ ነበር!
ሚስዮናዊ ምድቦች
የጊልያድ ትምህርት ቤት 16ኛው ክፍል በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ሥቃይ የደረሰባቸውን አንዳንድ ወንድሞች ጨምሮ ከሁሉም የዓለም ክፍል የተውጣጡ 120 ተማሪዎችን ያቀፈ ነበር። በክፍል ውስጥ ስፓንኛ ተምረን ስለነበር ስፓንኛ ተናጋሪ በሆነ በደቡብ አሜሪካ በሚገኝ አንድ አገር ውስጥ እንመደባለን ብለን ጠብቀን ነበር። በምረቃችን ቀን ዳግላስ በጃፓን፣ አንና እኔ ደግሞ በሶሪያ እንድናገለግል የተመደብን መሆናችንን ስንሰማ ምን ያህል እንደተገረምን ልትገምቱ ትችላላችሁ። ስለዚህ እኔና አን አረብኛ መማር ነበረብን። ምድባችን ወደ ሊባኖስ ሲቀየርም ቋንቋውን መማራችን ያንኑ ያህል አስፈላጊ ነበር። ቪዛ እስክናገኝ ድረስ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአረብኛ መጠበቂያ ግንብ ታይፕሴተር የሆነው ጆርጅ ሻካሺሪ በሳምንት ሁለት ጊዜ አረብኛ ያስተምረን ነበር።
በክፍል ውስጥ ባጠናነውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰ ምድር ለማገልገል መሄድ ምንኛ የሚያስደስት ነበር! ኬዝ እና ጆይስ ቹ፣ ኤድና ስታክሃውስ፣ ኦሊቭ ተርነር፣ ዶሪን ዎርበርተን እና ዶሪስ ዉድ አብረውን ተጉዘዋል። እጅግ ደስተኛ የሚስዮናውያን ቤተሰብ ሆነን ነበር! በከተማው የሚገኝ አንድ ወንድም ወደ ሚስዮናዊ ቤታችን እየመጣ ቋንቋውን በደንብ እንድንችል ያስተምረን ነበር። በየቀኑ አረብኛ በምንማርበት ወቅት ቀላል የሆነ አቀራረብ እንለማመድ ነበር። ከዚያም መስክ ወጥተን የተለማመድነውን አቀራረብ በስብከት ሥራችን ላይ እንጠቀምበት ነበር።
የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓመታት ያሳለፍነው ቀደም ሲል ጉባኤ ተመሥርቶባት በነበረችው በትሪፖሊ ነበር። ጆይስ፣ ኤድና፣ ኦሊቭ፣ ዶሪን፣ ዶሪስ፣ አንና እኔ ሆነን በከተማው ውስጥ የሚገኙ ምሥክሮችን ሚስቶችና ሴት ልጆች በጉባኤና ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት ተካፋይ እንዲሆኑ ረድተናቸዋል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የአካባቢውን ወግ በመከተል በስብሰባዎች ላይ አንድ ላይ አይቀመጡም ነበር፤ እንዲሁም እነዚህ ክርስቲያን እህቶች ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አይካፈሉም ነበር ለማለት ይቻላል። ለሕዝብ በምንሰጠው አገልግሎት በቋንቋቸው እንዲረዱን ስለፈለግን በዚህ ሥራ እንዲካፈሉ አበረታታናቸው።
ቀጥሎ አንና እኔ በጥንታዊቷ ከተማ በሲዶን የሚገኙ አነስተኛ የምሥክሮችን ቡድን እንድንረዳ ተመደብን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋና ከተማው ወደ ቤይሩት እንድንመለስ ተጠየቅን። በዚያም አርመንኛ ተናጋሪዎች በሚኖሩበት አካባቢ የእውነት ዘር ተዘርቶ ስለነበር እነሱን ለመርዳት እንድንችል ቋንቋውን ተማርን።
የምድብ ሥራችን መለዋወጥ
እንግሊዝን ለቅቄ ከመሄዴ በፊት ከዊልፍሬድ ጉች ጋር ተገናኝቼ ነበር። በለንደን ቤቴል ያገለግል የነበረ ቀናተኛና አሳቢ ወንድም ነበር። ዊልፍ በ1950 በያንኪ ስታዲየም በተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ወቅት ከተመረቁት የጊልያድ 15ኛው ክፍል አባላት መካከል አንዱ ነበር። ሚስዮናዊ ሆኖ እንዲያገለግል የተመደበው ናይጄርያ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ሲሆን በዚያ እያለ እንጻጻፍ ነበር። በ1955 ሁለታችንም “ድል አድራጊው መንግሥት” የተሰኘውን የአውራጃ ስብሰባ በለንደን አብረን ከተካፈልን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተጫጨን። በሚቀጥለው ዓመት በጋና ተጋባንና በሌጎስ ናይጄርያ ከዊልፍ ጋር በሚስዮናዊነት ማገልገል ጀመርኩ።
አንን በሊባኖስ ትቻት ከሄድኩ በኋላ በኢየሩሳሌም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን የተማረ አንድ ጥሩ ክርስቲያን ወንድም አገባች። ዳግላስ፣ አንና እኔ ያገባነው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስለሆነ ወላጆቻችን በሠርጋችን ላይ ሊገኙ አልቻሉም። ቢሆንም ሁላችንም አምላካችን ይሖዋን በደስታ እያገለገልን መሆናችንን በማወቃቸው ተደስተዋል።
በናይጄርያ ያለው ሥራ
በሌጎስ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚገኙትን ስምንት የቅርንጫፍ ቤተሰባችንን አባላት ክፍሎች እንዳጸዳ፣ ምግብ እንዳዘጋጅላቸውና ልብሳቸውን እንዳጥብ ተመደብኩ። ባል ብቻ ሳይሆን በአንድ ጊዜ ቤተሰብም እንዳገኘሁ ተሰማኝ!
ዊልፍና እኔ በዮሩባ ቋንቋ ቀላል የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያዎችን ተለማመድን። ባደረግነው ጥረትም ተክሰንበታል። ወጣት በነበረበት ጊዜ ያነጋገርነው አንድ ተማሪ ዛሬ በናይጄርያ በሚገኘው 400 የሚያክሉ አባላት ባሉበት ትልቅ የቤቴል ቤተሰብ ውስጥ የሚያገለግሉ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጆች አሉት።
በ1963 ዊልፍ በብሩክሊን ኒው ዮርክ አሥር ወራት የሚፈጅ ልዩ ስልጠና እንዲወስድ ተጋበዘ። ስልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ በእንግሊዝ እንዲያገለግል ተመደበ። እኔ በናይጄርያ ቆይቼ ስለነበር በ14 ቀናት ውስጥ ወደ ለንደን ሄጄ ከዊልፍ ጋር እንድገናኝ ተነገረኝ። የናይጄርያ ምድባችን አስደሳች ስለነበር አገሪቱን ለቅቄ የሄድኩት ደስታና ሐዘን በተቀላቀለበት ስሜት ነበር። ከአገሬ ውጪ ለ14 ዓመታት ያህል ካገለገልሁ በኋላ በእንግሊዝ ካለው ሕይወት ጋር እንደገና ለመላመድ ብዙ ጊዜ ወስዶብኛል። ይሁን እንጂ እድሜያቸው ከገፋው ወላጆቻችን ጎን በመሆን ልንረዳቸው በመቻላችን አመስጋኞች ነበርን።
በተስፋችን መጽናናት
ዊልፍ ከ1980 ጀምሮ የዞን የበላይ ተመልካች በመሆን በተዘዋወረባቸው በርካታ አገሮች አብሬው የመጓዝ መብት አግኝቻለሁ። በተለይ ወደ ናይጄርያ እየተመላለስን እናደርጋቸው የነበሩ ጉብኝቶች በጣም ያስደስቱኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ወደ ስካንዲኔቪያ፣ ዌስት ኢንዲስና ሊባኖስን ጨምሮ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተጉዘናል። አስደሳች የሆኑ ትዝታዎችን እንደገና የሚያስታውሱ አጋጣሚዎችን ማግኘት እንዲሁም ወጣት እያሉ የማውቃቸው ልጆች ዛሬ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውን መመልከት ልዩ ደስታ የሚፈጥር ነበር።
ውዱ ባለቤቴ በ1992 የጸደይ ወራት በመሞቱ በጣም አዝኛለሁ። ገና 69 ዓመቱ ነበር። በተለይ ደግሞ ሞቱ ድንገተኛ መሆኑ ከብዶኝ ነበር። በትዳር ሕይወት 35 ዓመታት ካሳለፍኩ በኋላ እንደገና ነጠላ ሆኜ መኖርን ለመልመድ ጊዜ ወስዶብኛል። ይሁን እንጂ ከዓለም አቀፉ ክርስቲያን ቤተሰብ ከፍተኛ እርዳታና ፍቅር አግኝቻለሁ። መለስ ብዬ የማሰላስልባቸው ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች አሉኝ።
ሁለቱም ወላጆቼ ንጹህ ክርስቲያናዊ አቋምን በመጠበቅ ግሩም ምሳሌ ሆነዋል። እናቴ በ1981 እንዲሁም አባቴ በ1986 ሞቱ። ዳግላስና አን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ዳግላስና ባለቤቱ ካም ለአባቴ እንክብካቤ ለማድረግ ወደ ለንደን ተመልሰው የነበረ ሲሆን አሁንም እዚያው ናቸው። አንና ቤተሰቧ በዩናይትድ ስቴትስ ይገኛሉ። ሁላችንም አምላክ የሰጠንን ተስፋና ውርሻ በእጅጉ እናደንቃለን። በሕይወት ያሉት በትንሣኤ ከተነሡት የሚወዷቸው ሰዎች ጋር የይሖዋ ምድራዊ ቤተሰብ አባላት በመሆን አንድ ላይ ለዘላለም የሚያገለግሉበትን ጊዜ ‘በተስፋ መጠባበቃችንን’ እንቀጥላለን።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአባቴ የኧርነስት ቢቨር የሕይወት ታሪክ በመጋቢት 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከግራ ወደ ቀኝ:-
ግዌን በ13 ዓመቷ በኢንፊልድ የመንግሥት አዳራሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ የሚያሳይ ሠርቶ ማሳያ
የሚስዮናውያን ቤተሰብ በትሪፖሊ፣ ሊባኖስ፣ 1951
ግዌን ከሟቹ ባሏ ከዊልፍ ጋር