እንዳሰቡት ስማቸውን አላስጠሩም
መጥፎ ታሪክ ያለውን የባቤልን ግንብ የገነቡትን ሰዎች የግል ስም መጽሐፍ ቅዱስ አይጠቅስም። እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።”—ዘፍጥረት 11:4
ይህን ያሉት ሰዎች እነማን ነበሩ? ይህ ሁኔታ የተፈጸመው የጥፋት ውኃ ከደረሰ ከ200 ዓመት ገደማ በኋላ ነበር። በዚህ ጊዜ ዕድሜው ወደ 800 ዓመት ይጠጋ የነበረው ኖኅ በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩት ዘሮቹ ጋር አብሮ ይኖር ነበር። ኖኅም ሆነ ዘሮቹ አንድ ዓይነት ቋንቋ ይናገሩ የነበረ ሲሆን እሱም ሆነ ወንዶች ልጆቹ ከጥፋት ውኃ በኋላ በሰፈሩበት አካባቢ አንድ ላይ ይኖሩ ነበር። (ዘፍጥረት 11:1) በዚሁ ጊዜ ከዚህ ብዙ ሺህ ሕዝብ መሀል የተወሰነው ክፍል ወደ ምሥራቅ በመጓዝ “በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ።”—ዘፍጥረት 11:2
ሙሉ በሙሉ ከሸፈ
ይህ ቡድን በአምላክ ላይ ለማመፅ የተማከረው በዚህ ቦታ ነበር። እንዴት? ይሖዋ አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት” በማለት ትእዛዝ ሲሰጣቸው ዓላማውን ገልጾ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ከጥፋት ውኃ በኋላ ይኸው ትእዛዝ ለኖኅና ለወንዶች ልጆቹ በድጋሚ ተሰጥቷል። አምላክ “እናንተም ብዙ፣ ተባዙ በምድር ላይ ተዋለዱ፣ እርቡባትም” ሲል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 9:7) ይሁን እንጂ ይህ ሕዝብ፣ ከይሖዋ መመሪያ በተቃራኒ ‘በምድር ላይ እንዳይበተኑ’ ከተማ ገነቡ።
በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ‘ስማቸውን ለማስጠራት’ ግንብ መገንባት ጀመሩ። ይሁን እንጂ እንዳሰቡት የግንባታ ሥራውን ሊያጠናቅቁ አልቻሉም። እርስ በርስ እንዳይግባቡ ይሖዋ ቋንቋቸውን እንደ ደባለቀባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይገልጻል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ታሪክ “እግዚአብሔር ከዚያም በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው ከተማይቱንም መሥራት ተዉ” ይላል።—ዘፍጥረት 11:7, 8
ህንፃውን የገነቡት ሰዎች እንዳሰቡት ስማቸውን ‘ማስጠራት’ ወይም ዝና ማትረፍ አለመቻላቸው ሙከራው ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ያሳያል። እንዲያውም ስማቸው ፈጽሞ የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ ከሰው ልጅ የታሪክ ማኅደር ጨርሶ ተፍቋል። የኖኅ የልጅ ልጅ ስለሆነው ስለናምሩድስ ምን ለማለት ይቻላል? በአምላክ ላይ ለተነሳው ለዚህ ዓመፅ መሪ አልነበረምን? ስሙስ የታወቀ አይደለምን?
ናምሩድ—አምላክን የተሳደበ ዓመፀኛ
ናምሩድ ቀንደኛው መሪ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 “[“ይሖዋን በመጻረር፣” NW] ኃያል አዳኝ” በማለት ናምሩድን ያስተዋውቀናል። (ዘፍጥረት 10:9) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች “እርሱም በምድር ላይ ኃያል መሆንን ጀመረ” በማለት ይገልጻሉ። (ዘፍጥረት 10:8) ናምሩድ ዓመፀኛና ጦረኛ ሰው ነበር። ከጥፋት ውኃ በኋላ ራሱን ንጉሥ አድርጎ የሾመ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ገዥ ነበር። በተጨማሪም ናምሩድ ሕንፃ የሚገነባ ነበር። ባቤልን ጨምሮ ስምንት ከተሞችን እንደገነባ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል።—ዘፍጥረት 10:10-12
የአምላክ ተቃዋሚ፣ የባቤል ንጉሥና የብዙ ከተሞች ቆርቋሪ የነበረው ናምሩድ በባቤል ግንብ ግንባታ እጁ እንደነበረበት ምንም አያጠራጥርም። ታዲያ ስሙን አላስጠራምን? ስለ ምሥራቃውያን ሰዎች የሚያጠኑት ኢ ኤፍ ሲ ሮዚንሚዩለር የተባሉ ሰው ናምሩድ የተባለውን ስም አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለናምሩድ ይህ ስም የወጣለት በዕብራይስጥ ‘ዓመፀ፣’ ‘ከዳ’ የሚል ትርጉም ካለው [ማራድህ] ከተባለው ቃል ነው።” ሮዚንሚዩለር ሲያብራሩ “በምሥራቃውያን ሕዝቦች ዘንድ ብዙውን ጊዜ የታወቁ ሰዎችን ከሞቱ በኋላ በሚወጣላቸው ስም መጥራት የተለመደ ነው። ሰውየው ከሞተ በኋላ የሚወጣለት ስም ከሥራው ጋር የሚስማማ ነበር።”
ብዙ ሊቃውንት ናምሩድ የሚለው ስም ሲወለድ የወጣለት እንዳልሆነ ይስማማሉ። ከዚህ ይልቅ ዓመፀኛ ባሕሪው ከታወቀ በኋላ ከሥራው ጋር የሚስማማ ስም እንደተሰጠው አስተውለዋል። ለምሳሌ ሲ ኤፍ ኪል እንዲህ ብለዋል:- “[ማራድህ] ከተባለው ቃል የመጣው ናምሩድ የሚለው ስም ‘እናምፃለን’ የሚል ትርጉም ሲኖረው አምላክን የሚፃረር እንደነበረ ይጠቁመናል። ናምሩድ ይኖር በነበረበት ዘመን የተሰጠው ይህ ስም ከጊዜ በኋላ የግል መጠሪያ ስሙ ሆኗል።” ኪል በግርጌ ማስታወሻቸው ላይ ታሪክ ጸሐፊው ጃኮፕ ፔሪዞኒየስ እንደሚከተለው ብለው መጻፋቸውን ጠቅሰዋል:- “ናምሩድ አስፈሪ አዳኝ የነበረ ሲሆን በብዙ ጓዶችም ታጅቦ ይሄድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሰዎችን ለዓመፅ ለማነሳሳት ‘እናምፅ!’ የሚል ትርጉም ያለው ‘ናምሩድ’ የሚለው ቃል ከአፉ የማይጠፋ ሰው እንደነበር አምናለሁ። ከጊዜ በኋላ ሌሎች ሰዎች ሙሴም እንኳ ሳይቀር ናምሩድ የሚለውን ስም እንደ ግል መጠሪያው አድርገው ተጠቅመውበታል።”
ስለዚህ ናምሩድ ስሙን እንዳላስጠራ ግልጽ ነው። ሲወለድ የወጣለት ስም አይታወቅም። የተከተሉት ሰዎች ስም ከታሪክ ማህደር እንደጠፋ ሁሉ የእሱም ስም ጠፍቷል። ስሙን ሊያስጠራለት የሚችል አንድ ዘር እንኳ አላፈራም። ከክብርና ከዝና ይልቅ መጥፎ ስም አትርፎ አልፏል። ናምሩድ የሚለው ስም ይሖዋን የተሳደበ ዓመፀኛ እና አምላክን በሞኝነት የተገዳደረ ሰው በሚል ዘወትር እንዲታወስ አድርጎታል።