የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፓርት
“ሕዝብህ በፈቃዳቸው ራሳቸውን ያቀርባሉ”
የኃያሉ የሶርያ ሠራዊት አለቃ ንዕማን የሥጋ ደዌ በሽታ ይዞት ነበር። ይህ መጥፎ በሽታ በቶሎ ካልታከመ በአካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስና አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርግ ይችላል። ንዕማን ምን ማድረግ ይኖርበት ይሆን? ‘ከእስራኤል ምድር የተማረከች’ አንዲት ብላቴና ከንዕማን አገልጋዮች አንዷ ነበረች። ይህች ብላቴና ኤልሳዕ የተባለው ነቢይ በሽታውን ሊፈውስለት እንደሚችል በድፍረት ተናገረች።—2 ነገሥት 5:1-3
ይህች ብላቴና ባሳየችው የድፍረት አቋም ንዕማን ኤልሳዕን ፈልጎ በማግኘት ከህመሙ ተፈወሰ። ከዚህም በላይ ንዕማን ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ለመሆን በቅቷል! ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ተሞክሮ የተፈጸመው በአሥረኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነበር። (2 ነገሥት 5:4-15) በዘመናችንም ብዙ ወጣቶች ስለ መንግሥቱ ለመናገር ተመሳሳይ ድፍረት ያሳያሉ። ከሞዛምቢክ የተገኘው የሚከተለው ተሞክሮ ይህንን ያሳየናል።
የስድስት ዓመቱ ኑኑ ያልተጠመቀ የምስራቹ አስፋፊ ነው። ኑኑ ያልተጠመቀ አስፋፊ ከመሆኑ በፊት እንኳ የሰፈሩን ልጆች ሰብስቦ ከጸለየ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ በተባለው መጽሐፍ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራቸው ነበር።
ኑኑ ብዙውን ጊዜ ቅዳሜ በማለዳ ተነስቶ “ዛሬ ወደ መስክ አገልገሎት እንሄዳለን” በማለት ቤተሰቦቹን ያስታውሳቸው ነበር። ለአገልግሎት ያለው ቅንዓት በሌላም መንገድ ታይቷል። ኑኑ ወላጆቹ በማፑቶ ከተማ ከመንገድ ወደ መንገድ በሚያደርጉት ምስክርነት አብሯቸው ሲያገለግል አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን ለብቻው ቀርቦ ያነጋግራል። አንድ ቀን በተመሳሳይ መንገድ ሲያገለግል አንድ ነጋዴ ጠጋ ብሎ “እነዚህን መጽሔቶቸ የምትሸጠው ለምንድን ነው?” ሲል ጥያቄ አቀረበለት። ኑኑም “መጽሔቶቹን እየሸጥኩ አይደለም፤ ይሁን እንጂ የስብከቱን ሥራ ለመደገፍ የገንዘብ አስተዋጽኦ እቀበላለሁ” ሲል መለሰለት። ነጋዴውም “ፍላጎት ባይኖረኝም እንኳ በአንተ ጠባይና ችሎታ ተደንቄያለሁ። ለዚህ ሥራ አስተዋጽኦ ማድረግ እፈልጋለሁ” በማለት መለሰለት።
በሌላ ጊዜ ኑኑ በመንገድ ላይ ያገኘውን አንድ ሰው ቀረብ ብሎ ካነጋገረው በኋላ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው? የተባለውን መጽሐፍ እንዲወስድ ጋበዘው። ሰውየውም “እዚያ ትምህርት ቤት የምትማረው ነህ አይደል?” በማለት ጠየቀው። ኑኑም እንዲህ በማለት መለሰለት:- “አዎን፣ እዚያ ትምህርት ቤት ነው የምማረው፤ ይሁን እንጂ ዛሬ ከዚህ መጽሐፍ አስፈላጊ የሆነ መልእክት ለሰዎች እየነገርኩ ነው። በዚህ መጽሐፍ ሥዕል ላይ እንደሚታየው አምላክ ወደ ፊት ለሰው ልጆች በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ እርስዎም መኖር እንደሚችሉ ይገልጽልዎታል።” ኑኑ እያነጋገረው ያለው ሰው እሱ በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያለ አስተማሪ እንደሆነ አላወቀም ነበር። አስተማሪው መጽሐፉን ወሰደ፤ በዚህ አላበቃም አሁን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ቋሚ ደንበኛ ሆኗል።
ኑኑ በስብከቱ ሥራ መካፈል ለምን እንደሚያስደስተው ሲጠየቅ እንዲህ ብሏል:- “ለሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መናገርና ማስተማር እፈልጋለሁ።” አክሎም “ሰዎች አልሰማም ቢሉ የማዝንበት ምንም ምክንያት የለም” ሲል ተናግሯል።
በዓለም ዙሪያ እንደ ኑኑ ያሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶቸ ስለ አምላክ መንግሥት ለማስተማርና ለመስበክ “በፈቃዳቸው ራሳቸውን ያቀርባሉ።” (መዝሙር 110:3 NW) ይሁን እንጂ ይህ በአጋጣሚ የሚሆን ነገር አይደለም። ወላጆች ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው ጀምረው በማሰልጠናቸው፣ በአገልግሎት ጥሩ አርአያ በመሆናቸውና በቅንዓት የመንግሥቱን ፍላጎት በማስቀደማቸው የሚያገኙት ትልቅ ወሮታ ነው።