ክብራቸውን ትጠብቅላቸዋለህን?
የአፍሪካ ተወላጆች እንደ እንስሳት ታጉረው እንዲሁም ለማመን በሚያስቸግርና በሚከረፋ ቆሻሻ ውስጥ ታጭቀው ልክ እንደ ጭነት ዕቃ ወደ አሜሪካ ግዛቶች በመርከብ ይጋዙ ነበር። ከእነዚህ መካከል ቢያንስ ግማሽ የሚያህሉት ወደሚጋዙበት ቦታ ሳይደርሱ ይሞታሉ። ወደፊት ጨርሶ ላይተያዩ የቤተሰብ አባላት ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ ይለያዩ ነበር። የባሪያ ንግድ፣ ሰው መሰሉ የሆነውን ሰው ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ የያዘበትና በታሪክ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ አሳዛኝ ክስተት ነው። ጨካኝ የሆኑ ወራሪዎች ራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን የአንድን አካባቢ ተወላጆች በጭካኔ በገዙበት ጊዜም እንዲህ ያሉ ክብርን የሚገፉ ሁኔታዎች ተከስተዋል።
የአንድን ሰው ክብር መግፈፍ ያንን ሰው ከመደብደብ ይበልጥ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው። የሰውን ልጅ ቅስም የሚሰብር ነው። ባርነት በብዙ አገሮች ውስጥ የቀረ ቢሆንም ሰብዓዊ ክብርን መግፈፍ ግን ምናልባት በረቀቀ ሁኔታ ሊፈጸም ቢችልም፣ እስከ አሁን ድረስ ቀጥሏል።
በሌላ በኩል ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ምክር ለመከተል ይጥራሉ። ስለዚህም ‘የሌሎችን የግል ክብር እጠብቃለሁን?’ ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ።—ሉቃስ 10:27
የክብር ተምሳሌት
አንድ መዝገበ ቃላት ክብር የሚለውን ቃል ዋጋማ፣ ላቅ ያለ ወይም ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ሲል ይፈታዋል። የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ አምላክ ያለውን ደረጃ በትክክል የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው! እርግጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ይሖዋንና ሉዓላዊነቱን ከክብር ጋር ያዛምዳሉ። ሙሴ፣ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል፣ ሐዋርያው ዮሐንስና ሌሎችም ልዑሉን አምላክና በሰማይ ያለውን ቤተ መንግሥቱን በራእይ የመመልከት ልዩ መብት አግኝተው የነበረ ሲሆን የሰጡት መግለጫም አስፈሪ ግርማና ክብር ያለው መሆኑን ነው። (ዘጸአት 24:9-11፤ ኢሳይያስ 6:1፤ ሕዝቅኤል 1:26-28፤ ዳንኤል 7:9፤ ራእይ 4:1-3) ንጉሥ ዳዊት የውዳሴ ጸሎት ሲያቀርብ “አቤቱ፣ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፣ ክብርም፣ ድልና ግርማ ለአንተ ነው” ብሏል። (1 ዜና መዋዕል 29:11) ከራሱ ከይሖዋ አምላክ ይበልጥ ክብርና ከፍ ያለ ግምት ሊሰጠው የሚገባ አካል እንደሌለ የተረጋገጠ ነው።
ይሖዋ ሰውን በመልኩና በምሳሌው ሲፈጥር በሰው ልጆች ውስጥ በሌሎች ዘንድ ዋጋማ ሆኖ የመታየት፣ ለራስ ጥሩ ግምት የማሳደርና የመከበር ፍላጎት እንዲኖር አድርጎል። (ዘፍጥረት 1:26) ስለዚህ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ለእያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ክብር ልንሰጠውና ለእሱ ከፍ ያለ ግምት እንዳለን ልናሳይ ይገባል። ይህን ስናደርግ ይሖዋ አምላክ የሰብዓዊ ክብር ምንጭ መሆኑን አምነን መቀበላችንን እናሳያለን።—መዝሙር 8:4-9
ክብር በቤተሰብ ግንኙነት ውስጥ
ባለ ትዳር የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ባሎች ‘ለተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ሚስቶቻቸውን በክብር እንዲይዟቸው’ መክሯል። (1 ጴጥሮስ 3:7 NW፤ ማቴዎስ 8:14) በሌላ በኩል ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሚስትም ባልዋን በጥልቅ ታክብር’ ሲል መክሯል። (ኤፌሶን 5:33 NW) ስለዚህ በጋብቻ ውስጥ የትዳር ጓደኛን ክብር መጠበቅ መሟላት የሚገባው ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃት ነው። ይህን በምን መንገዶች ልናሳይ እንችላለን?
ውኃ ለአንድ ተክል እድገት አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ባልና ሚስትም ለብቻቸው ሲሆኑም ሆነ በሌሎች ፊት የትሕትና አነጋገርና ደግነት የሞላባቸው አካላዊ መግለጫዎች መለዋወጣቸው በመካከላቸው ያለውን ዝምድና ሊያጎለብትላቸው ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ አስቂኝ በሆኑ ተከታታይ የቴሌቪዥን ታሪኮች ላይ በብዛት እንደሚሰሙት ባሉ ቃላት በመጠቀም ሌላውን በነገር መውጋት፣ መሳደብ ወይም ሸካራ የሆኑ የዘለፋ ቃላት መጠቀም አፍራሽ ነው። እነዚህ ቃላት እንደ ዋጋ ቢስነት፣ የመንፈስ ጭንቀትና ጥላቻ አልፎ ተርፎም በቀላሉ ሊፈወስ የማይችል የስሜት ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
በተጨማሪም የሌሎችን የግል ክብር መጠበቅ ማለት እነርሱን በሚመለከት አስቀድመን በአእምሯችን ከያዝነው ሁኔታ ጋር እንዲስማሙ ከመፈለግ ወይም አግባብነት በሌለው መንገድ ከሌሎች ጋር ለማወዳደር ከመሞከር ይልቅ የግል ሁኔታዎቻቸውን እንዳለ መቀበል ማለት ነው። ይህ በተለይ በባልና ሚስት መካከል አስፈላጊ ነው። ሐሳብ ለሐሳብ መግባባትና በነፃነት ስሜትን መገላለጽ ከተቻለ እንዲሁም ማንም እነቀፋለሁ ወይም እገሰጻለሁ ብሎ የማያስብ ከሆነ ቅርርባቸው ይዳብራል። ባልና ሚስት ተፈጥሯዊ ባህርያቸውን ቢያንጸባርቁ ቤት ከዚህ ጨካኝና ሸካራ ዓለም የሚከልል ማረፊያ ይሆናል።
ልጆች ወላጆቻቸውን የማክበርና የመታዘዝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አለባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ጥበበኛና አፍቃሪ ወላጆች የልጆቻቸውን ክብር ይጠብቃሉ። ለመልካም ባህርያቸው ሞቅ ያለ ምስጋናና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በትዕግሥት የሚሰጥ ተግሣጽ ልጆችን “በጌታ ምክር” ለማሳደግ ያስችላል። የማያቋርጥ ነቀፋ፣ ጩኸትና “ደደብ” ወይም “የማትረባ” በሚሉ አዋራጅ ቃላት መጠቀም እነሱን ከማስቆጣት ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም።—ኤፌሶን 6:4
ሦስት ወንዶችንና ሦስት ሴቶች ልጆችን የሚያሳድግ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ስንሆን ተግሣጽ የምንሰጣቸው በተቻለን መጠን ምንም ድምፅ ሳናሰማ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጎንተል ማድረግ ወይም ፊትን ኮስተር አድርጎ መመልከት በቂ ነው። ከበድ ያለ ተግሣጽ የሚያስፈልግ ከሆነ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ልጆች በማያዩበት ሁኔታ እንዲሁም በቤታችን ውስጥ በግል እናደርገዋለን። አሁን ልጆቹ ስላደጉ ለእነሱ ተግሣጽ መስጠት ለእያንዳንዳቸው በግል በሚያስፈልጋቸው መሠረት ከአምላክ ቃል ፍቅራዊና ጥበብ ያለበት ምክር መስጠትን ይጨምራል። እነዚህን የግል ጉዳዮች በምስጢር በመያዝ እያንዳንዱ ልጅ ያለውን ነፃነትና ክብር የማግኘት መብት እንደምናከብር እናሳያለን።”
በቤተሰብ ውስጥ በቃልና በድርጊት ጨዋነት የማሳየትን አስፈላጊነትም ቢሆን ችላ ልንለው አይገባም። ቤተሰባዊ ቅርርባችን “እባክህ፣” “አመሰግናለሁ፣” “ይቅርታ” እና “አዝናለሁ” የሚሉትን ቃላት ከመጠቀም ወደ ኋላ እንድንል ሊያደርገን አይገባም። የጨዋነት ምግባር የራስንም ሆነ የሌሎችን ክብር ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው።
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ
ኢየሱስ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 11:28) የተጨቆኑ፣ የተጨነቁና ትንንሽ ልጆች እንኳን ሳይቀር በኢየሱስ ስብዕና ተማርከው ይቀርቡት ነበር። እነዚህ ሰዎች በጊዜው በነበሩት እብሪተኛ እንዲሁም ተመጻዳቂ ቀሳውስትና መሪዎች ዘንድ የተናቁ ነበሩ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚገባቸውን ክብር ሰጥቷቸዋል።
ኢየሱስን በመኮረጅ ለእምነት አጋሮቻችን የእረፍት ምንጭ ልንሆን እንፈልጋለን። ይህ ማለት ደግሞ በአነጋገራችንና በድርጊቶቻችን እነሱን ለመገንባት አጋጣሚዎችን እንፈልጋለን ማለት ነው። በንግግራችን ውስጥ ደግነት የሞላባቸው ገንቢ አስተያየቶች መሰንዘራችን ምንጊዜም ተገቢ ነው። (ሮሜ 1:11, 12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:11) ምን ብለን እንደምንናገርና እንዴት እንደምንናገር ጥንቃቄ በማድረግ ለሌሎች ስሜት እንደምናስብ እናሳያለን። (ቆላስይስ 4:6) በተጨማሪም በክርስቲያን ስብሰባዎች ወቅት ተገቢ የሆነ ልብስ መልበሳችንና ልከኛ ጌጣጌጦችን መጠቀማችን ለአምላካችን፣ ለአምልኮቱና ለእምነት አጋሮቻችን ያለንን ጥልቅ አክብሮት ያንጸባርቃል።
ኢየሱስ ሲያገለግላቸውም እንኳ የሰዎችን ክብር ይጠብቅ ነበር። ልቆ ለመታየት ሲል የሌሎችን ስሜት አልጎዳም ወይም ደግሞ አላዋረዳቸውም። አንድ ለምጻም ፈውስ ለማግኘት ወደ እሱ በመጣ ጊዜ ኢየሱስ ሰውየውን ንጹህ አይደለህም ወይም የማትረባ ነህ ብሎ አላባረረውም፤ ወይም ይታይልኝ በሚል ስሜት የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ አልሳበም። ከዚህ ይልቅ “ጌታ ሆይ፣ ብትወድስ፣ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለምጻሙ በለመነው ጊዜ ኢየሱስ “እወዳለሁ” በማለት የዚያን ለምጻም ክብር ጠብቋል። (ሉቃስ 5:12, 13) በችግር ላይ የሚገኙትን መርዳት ብቻ ሳይሆን ሸክም ሳይሆኑ ተፈላጊና ተወዳጅ መሆናቸውን ብናረጋግጥላቸው ምንኛ ተገቢ ነው! በዓለም ዙሪያ ዓይን አፋር የሆኑ ሰዎች፣ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸውና የአካል ጉዳተኞች ችላ ይባላሉ፣ ሰዎች ያገሏቸዋል ወይም ያዋርዷቸዋል። እነዚህ ሰዎች በክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መካከል በሚሆኑበት ጊዜ ግን እውነተኛ ጓደኝነትና ተቀባይነት ሊያገኙ ይገባል። ይህ ዓይነቱ መንፈስ እንዲኖር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርብናል።
ምንም እንኳ ስህተቶች የሚሠሩና ልዩ ልዩ ባሕርያት የነበራቸው ቢሆንም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ‘ወገኖቹ’ አድርጎ ‘እስከ መጨረሻ ወዷቸዋል።’ (ዮሐንስ 13:1) ንጹህ ልብ እንዳላቸውና ለአባቱ በሙሉ ነፍስ እንዳደሩ ተመልክቶ ነበር። በተመሳሳይም የእምነት አጋሮቻችን አንዳንድ ነገሮችን እኛ በምንፈልገው መንገድ ባለማድረጋቸው ወይም ልማዳቸው ወይም ባሕርያቸው ስለሚያናድደን ብቻ በክፉ ዓይን ልንመለከታቸው አይገባም። የወንድሞቻችንን ክብር መጠበቃችን ይሖዋን እንደሚወዱና ከንጹህ ልብ ተነሣስተው እሱን እንደሚያገለግሉት በማመን እንድንወዳቸውና የግል ሁኔታቸውን እንዳለ እንድንቀበል ይገፋፋናል።—1 ጴጥሮስ 4:8-10
በተለይ ሽማግሌዎች በጥበቃቸው ሥር በሚገኙት ሰዎች ላይ አላስፈላጊ ጭንቀቶች እንዳይጨምሩ ሊጠነቀቁ ይገባል። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ሽማግሌዎች ኃጢአት ከፈጸመ አንድ የጉባኤ አባል ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ ደግነትና አሳቢነት የተላበሱ ቃላትን መጠቀም ይገባቸዋል፤ እንዲሁም አላስፈላጊ የሆኑ አሳፋሪ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ መቆጠብ አለባቸው። (ገላትያ 6:1) ሌላው ቀርቶ ከባድ ወቀሳ ወይም ተግሣጽ መስጠት በሚያስፈልግበት ጊዜ እንኳ የበደለኛውን ክብርና ለራሱ ያለውን ጥሩ ግምት ማክበራቸውን ይቀጥላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2
የራስን ክብር መጠበቅ
በአምላክ መልክና ምሳሌ በመፈጠራችን በተቻለን አቅም ክብሩን ጨምሮ የእርሱን ዕጹብ ድንቅ ባሕርያት በዕለት ተለት ሕይወታችን ማንጸባረቅ ይገባናል። (ዘፍጥረት 1:26) በተመሳሳይም “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” በሚለው ትእዛዝ ውስጥ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የግል ክብራችንን ልንጠብቅና ስለ ራሳችን ጥሩ ግምት ልናሳድር እንደሚገባ የሚገልጽ ሐሳብ በተዘዋዋሪ ተጠቅሷል። (ማቴዎስ 22:39) ሌሎች እንዲያከብሩንና ክብራችንን እንዲጠብቁልን ከፈለግን መከበር የሚገባን ሰዎች ሆነን መገኘት አለብን።
ለራሳችን ጥሩ ግምት ለማሳደርና የግል ክብራችንን ለመጠበቅ የሚያስችለን አንዱ አስፈላጊ ነገር ንጹሕ ሕሊና ይዘን መኖራችን ነው። የረከሰ ሕሊናና የጥፋተኝነት ስሜት በቀላሉ ዋጋ እንደሌለን እንዲሰማን፣ በሐዘን እንድንዋጥና የመንፈስ ጭንቀት እንዲያድርብን ሊያደርገን ይችላል። በመሆኑም አንድ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ንስሐ ለመግባት አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንዲሁም ‘ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንዲመጣለት’ የሽማግሌዎችን መንፈሳዊ እርዳታ ሊጠይቅ ይገባል። ንስሐ የገባ ሰው ከሚመጣለት መጽናናት መካከል ቀደም ሲል የነበረውን የግል ክብርና ለራሱ ያለውን ጥሩ ግምት መልሶ ማግኘትን ያካትታል።—ሥራ 3:19
ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናችንን ለመከላከል የማያቋርጥ ጥረት በማድረግ ምንም ነገር እንዲያቆሽሸው ወይም እንዲያዳክመው አለመፍቀድ የተሻለ ነው። በዕለት ተለት የሕይወት መስኮቻችን በሙሉ ማለትም በምንመገብበት፣ በምንጠጣበት፣ በምንሠራበት፣ በምንዝናናበትና ከተቃራኒ ፆታ ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ራሳችንን መግዛታችን ንጹሕ ሕሊና ይዘን ለመቆየትና በሕይወታችን ላይ የአምላክን ክብር ሙሉ በሙሉ ለማንጸባረቅ ይረዳናል።—1 ቆሮንቶስ 10:31
በሠራናቸው ስህተቶች ምክንያት የሚሰማን የጥፋተኝነት ስሜት ከአእምሯችን አልጠፋ ካለስ? ወይም የደረሰብን በደል ትቶ ያለፈው ጠባሳ አሁንም የሚያሰቃየን ከሆነስ? ይህ የግል ክብራችንን ሊነካብንና ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ሊጥለን ይችላል። “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸውም የተሰበረውን ያድናቸዋል” የሚሉት በመዝሙር 34:18 ላይ የሚገኙት የንጉሥ ዳዊት ቃላት እንዴት የሚያጽናኑ ናቸው! ይሖዋ የመንፈስ ጭንቀትና የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማቸውን አገልጋዮቹን ለመደገፍ ዝግጁና ፈቃደኛ ነው። እሱን በመለመንና በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸውን ክርስቲያን ወላጆች፣ ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች የጎለመሱ ወንድሞችን እርዳታ መጠየቅ ለራሳችን ጥሩ ግምትና የግል ክብር እንዲኖረን የሚረዱን ነገሮች ናቸው።—ያዕቆብ 5:13-15
በሌላ በኩል ደግሞ በግል ክብርና በትዕቢት መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ይኖርብናል። ቅዱስ ጽሑፋዊው ምክር “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፣ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ” ይላል። (ሮሜ 12:3) ለራሳችን ጥሩ ግምት ማሳደር ተገቢ ቢሆንም ከእኔ በቀር ሌላ ሰው የለም የሚል የተጋነነ አመለካከት እንዲኖረን አንፈልግም ወይም ደግሞ በሰብዓዊ ክብር ምንነትና በሌሎች ዘንድ ክብር ለማግኘት ሲሉ አንዳንዶች በሚያደርጉት የራስ ወዳድነት ሩጫ መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሊሆንልን ይገባል።
አዎን፣ የሌሎችን ክብር መጠበቅ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው። የቤተሰብ አባሎቻችንና የእምነት አጋሮቻችንን ክብር ልንጠብቅና ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባናል። ይሖዋ ሁላችንንም በተወሰነ መጠን ክብር እንዲኖረን አድርጎ ፈጥሮናል። ይህን ሁላችንም ልንገነዘብና እንዳይጠፋ ልንጠብቀው ይገባል። ይሁን እንጂ ሁላችንም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ አምላክ ለተላበሰው ወደር የለሽ ክብርና ግርማ አክብሮታዊ ፍርሃት ልናዳብር ይገባል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶች የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ሰዎች ክብር ሊሰጡ ይችላሉ