የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 10/1 ገጽ 24-27
  • ከወርቅ የበለጠ ነገር አገኘሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከወርቅ የበለጠ ነገር አገኘሁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አሜሪካ ከገባሁ በኋላ ሁሉ ነገር ድንግርግር አለኝ
  • ከእህቴና ከወንድሜ ጋር ተገናኘሁ
  • ቤተሰብ መመሥረትና የቀብር ሥነ ሥርዓት
  • እውነትን መማር
  • የትውልድ ቀዬን መፈለግ
  • እውነትን በአንደኛ ደረጃ ማስቀመጥ
  • ከጉብዝናችን ወራት ጀምሮ ፈጣሪያችንን ማሰብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ስምንት ልጆችን በይሖዋ መንገድ ማሳደግ ፈታኝ ሆኖም አስደሳች ነበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ለይሖዋ ምን ልከፍለው እችላለሁ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ዓይኔንና ልቤን በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር አድርጌ ነበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 10/1 ገጽ 24-27

ከወርቅ የበለጠ ነገር አገኘሁ

ቻርልስ ሚልተን እንደተናገረው

አንድ ቀን አባቴ “ቻርልስዬን ገንዘብ በአካፋ ወደሚዛቅበት ወደ አሜሪካ ለምን አንልከውም? እዚያ ሆኖ የተወሰነ ገንዘብ ሊልክልን ይችላል እኮ!” አለ።

ብዙ ሰዎች የአሜሪካ አውራ ጎዳናዎች ወርቅ የተነጠፈባቸው ይመስላቸው ነበር። በዚያን ወቅት በምሥራቅ አውሮፓ የሚኖሩ ሰዎች ኑሮው በጣም ከብዶባቸው ነበር። ወላጆቼ አንድ አነስተኛ የእርሻ መሬትና የሚያረቧቸው ጥቂት ላሞችና ዶሮዎች ነበሯቸው። የኤሌክትሪክ መብራትም ሆነ የቧንቧ ውኃ አልነበረንም። በአካባቢያችን መብራትም ሆነ የቧንቧ ውኃ ያስገባ አንድም ሰው አልነበረም።

የተወለድኩት በሆሶቼክ መንደር የዛሬ 106 ዓመት ገደማ ማለትም ጥር 1, 1893 ነበር። የምንኖርበት መንደር የሚገኘው በዚያን ጊዜ የኦስቶሮ-ሀንጋሪያን መንግሥት በሚያስተዳድረው ጋሊቺያ በሚባል ከፍለ ሃገር ሥር ነበር። በአሁኑ ጊዜ ሆሶቼክ የሚገኘው በምሥራቅ ፖላንድ ከስሎቫኪያና ከዩክሬይን ብዙም ሳይርቅ ነው። የዚህ አካባቢ ክረምት በጣም ኃይለኛና ከፍተኛ የበረዶ ግግር የሚፈጠርበት ነው። የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ግማሽ ኪሎ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ ወደሚገኝ ወደ አንድ ጅረት እወርድና በረዶውን በመጥረቢያ እየፈረከስኩ ውኃ አወጣ ነበር። ቀድቼ ያመጣሁትን ውኃ እናቴ ለምግብ ማብሰያና ለማጠቢያ ትጠቀምበታለች። በአካባቢያችን ወደሚገኘው ጅረት በመሄድ አንድን ትልቅ የበረዶ ግግር እንደ ማጠቢያ ዕቃ በመጠቀም ልብስ ታጥብበታለች።

በሆሶቼክ አንድም ትምህርት ቤት አልነበረም። ሆኖም የፖሊሽ፣ የሩሲያ፣ የስሎቫኪያ እና የዩክሬይን ቋንቋ መናገር ተምሬ ነበር። የግሪክ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ሆኜ ያደግሁ ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዲቁና አገለግል ነበር። ይሁን እንጂ ገና ልጅ እያለሁ እንኳ ዓርብ ዕለት ሥጋ መብላት ክልክል መሆኑን እየተናገሩ ራሳቸው ግን በሚበሉ ቀሳውስት በጣም እበሳጭ ነበር።

አንዳንድ ወዳጆቻችን ከዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ ይዘው ይመጡና ቤታቸውን ያድሱ እንዲሁም ለእርሻ ሥራ የሚሆኑ ማሽኖችን ይገዙ ነበር። አባባ በድጋሚ ወደዚያ ለመሄድ ከሚያስቡ ጎረቤቶቻችን ጋር እኔን ወደ አሜሪካ ስለመላክ እንዲናገር ያነሳሳው ይህ ነበር። ይህ የሆነው በ1907 ሲሆን በዚያን ጊዜ የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ።

አሜሪካ ከገባሁ በኋላ ሁሉ ነገር ድንግርግር አለኝ

ወዲያው በመርከብ ተሳፈርኩና በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የአትላንቲክን ውቅያኖስ አቋረጥን። በዚያ ጊዜ አንድ ሰው 20 የአሜሪካ ዶላር ከሌለው ወደ ትውልድ አገሩ ይመለስ ነበር። እኔ 20 ዶላር ስለነበረኝ ወደ አሜሪካ የሚያስገባውን የኤሊስን ደሴት አልፈው ወደ ኒው ዮርክ ከገቡት በሚልዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቃሁ። አሜሪካ ገንዘብ የሚታፈስበትና ጎዳናው ሁሉ ወርቅ የተነጠፈበት አገር ሆኖ አላገኘሁትም። እንዲያውም አብዛኞቹ ጎዳናዎች እንኳን ወርቅ አስፋልትም የተነጠፈባቸው አልነበሩም!

ባቡር ተሳፈርንና ወደ ጆንስታውን፣ ፔንሲልቫኒያ ተጓዝን። አብረውኝ የነበሩት ሰዎች ቀደም ሲል ከተማውን ያውቁት ስለነበር ላርፍ የምችልበትን አልቤርጎ አሳዩኝ። እዚያ ለመቆየት የፈለኩት በጀሮም፣ ፔንሲልቫንያ የምትኖረውን ታላቅ እህቴን ለማግኘት ነበር። በኋላ ግን እህቴ የምትኖረው 25 ኪሎ ሜትር ርቃ እንደሆነ ተረዳሁ። በቋንቋዬ “ጄ” የሚነበበው እንደ “ዋይ” ተደርጎ ስለሆነ ጀሮም ከማለት ይልቅ ያሮም እያልኩ እጠይቅ ነበር። ያሮም የሚባል ቃል ሰምቶ የሚያውቅ ማንም የለም፤ እንግሊዝኛ መናገር ሳልችልና በቂ ገንዘብ ሳይኖረኝ በዚህ በባዕድ አገር ምን እንደማደርግ አላውቅም ነበር።

በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ሥራ ፍለጋ እውል ነበር። ሥራ ለመቀጠር ከተሰለፍነው መካከል የሚቀጠሩት ሁለት ወይም ሦስት ብቻ ነበሩ። ስለዚህ በየቀኑ ወደ ተከራየሁት አልቤርጎ እመለስና በራስ አገዝ መጻሕፍት እየተረዳሁ እንግሊዝኛ አጠና ነበር። አልፎ አልፎ ዕለታዊ ሥራ አገኝ ነበር። ሆኖም ወራት እያለፉ ሄዱ፣ የነበረኝም ገንዘብ እያለቀ ሄደ።

ከእህቴና ከወንድሜ ጋር ተገናኘሁ

አንድ ቀን በባቡር ጣቢያው አካባቢ በሚገኝ አንድ ቡና ቤት አጠገብ አለፍኩ። የምግቡ ሽታ ምራቅ ያስውጥ ነበር! አንድ ሰው አምስት ሳንቲም የሚያወጣ አንድ ትልቅ ጠርሙስ ቢራ ከገዛ ሳንድዊችና ሌሎች ምግቦች በነጻ መመገብ ይችል ነበር። ምንም እንኳ ዕድሜዬ የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ባይፈቅድልኝም መጠጥ ሻጩ አዘነልኝና ቢራ ሸጠልኝ።

እየተመገብኩ ሳለሁ ጥቂት ሰዎች ገቡና “ቶሎ ቶሎ ጠጡ! ወደ ጀሮም የሚሄደው ባቡር እየመጣ ነው” በማለት ተናገሩ።

“ያሮም ማለታችሁ ነው?” ብዬ ጠየቅኩ።

“አይደለም፣ ጀሮም ነው” በማለት መለሱልኝ። እህቴ የት እንደምትኖር ያወቅኩት በዚህ ጊዜ ነበር። እንዲያውም እዚያው ቡና ቤቱ ውስጥ እህቴ በምትኖርበት ቤት መደዳ የሚኖር አንድ ሰው አገኘሁ! ከዚያም የባቡር ትኬት ቆረጥኩና ተሳፍሬ ሄድኩ፤ በመጨረሻም እህቴን አገኘኋት።

እህቴና ባለቤቷ ለከሰል ማዕድን ሠራተኞች አልቤርጎ ያከራዩ ነበር። እኔም ከእነርሱ ጋር መኖር ጀመርኩ። እነርሱም ከማዕድን ጉድጓድ ውስጥ ውኃ እየሳበ የሚያወጣ ፓምፕ የመጠበቅ ሥራ አገኙልኝ። ፓምፑ መሥራቱን ካቆመ ቶሎ ብዬ መካኒክ መጥራት አለብኝ። ለዚህ ሥራ በቀን 15 ሳንቲም ይከፈለኝ ነበር። ከዚያም በባቡር ላይ፣ በብሎኬት ማምረቻ ድርጅትና በኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ሳይቀር ሠርቻለሁ። ከጊዜ በኋላ ወንድሜ ስቲቭ ወደሚኖርበት ወደ ፒትስበርግ ሄድኩ። እዚያም በብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ እንሠራ ነበር። ወደ ቤተሰቦቼ ልልክ የምችለው ምንም ገንዘብ አላገኘሁም።

ቤተሰብ መመሥረትና የቀብር ሥነ ሥርዓት

አንድ ቀን ወደ ሥራ እየሄድኩ ሳለሁ አንዲት የቤት ሠራተኛ በምትሠራበት ቤት ደጃፍ ላይ ቆማ አየሁ። ‘አቤት፣ እንዴት ያለች ቆንጆ ናት!’ ብዬ አሰብኩኝ። ከሦስት ሳምንት በኋላ በ1917 ሄለን እና እኔ ተጋባን። በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ስድስት ልጆች ወለድን። አንደኛው ግን ገና ሕፃን እያለ ሞተ።

በ1918 በፒትስበርግ ሬልዌይስ በተባለ ኩባንያ ውስጥ የሠራተኞች ሰርቪስ ሾፌር ሆኜ ተቀጠርኩ። ሰርቪሱን በማሳድርበት ቦታ አቅራቢያ ጎራ እያልኩ ቡና የምጠጣበት አንድ ሻይ ቤት ነበር። የሻይ ቤቱ ባለቤት የሆኑት ሁለቱ ግሪካውያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲሰብኩ ለመስማት ፈቃደኛ እስከሆንክ ድረስ ምንም ነገር ብታዝ ጉዳያቸው አይደለም። “መላው ዓለም የተሳሳተ መሆኑንና እናንተ ሁለታችሁ ብቻ ትክክል እንደሆናችሁ ነው ልትነግሩኝ የፈለጋችሁት?” አልኳቸው።

“መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ተመልከት!” ብለው መለሱልኝ። ሆኖም በዚያን ወቅት ሊያሳምኑኝ አልቻሉም።

የሚያሳዝነው በ1928 ውዷ ሄለን በጠና ታመመች። ከእኔ ጋ ከመሆን ይልቅ እዚያ ይሻላቸዋል ብዬ ልጆቼን ወደ እህቴ ሰደድኳቸው። በዚያ ወቅት አንድ የእርሻ መሬት ገዝተው ነበር። ልጆቹን ዘወትር እጠይቃቸው የነበረ ሲሆን ለምግባቸው የሚሆን ገንዘብ በየወሩ እልክ ነበር። ልብስም እልክላቸው ነበር። የሚያሳዝነው ሄለን በሽታዋ እየጠናባት ሄደና ነሐሴ 27, 1930 ሞተች።

በከፍተኛ የብቸኝነትና የሃዘን ስሜት ተዋጥኩ። የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለማከናወን ወደ ቄሱ ስሄድ “ከአሁን ጀምሮ የዚህ ቤተ ክርስቲያን አባል አይደለህም። ከአንድ ዓመት በላይ ያልከፈልከው ዕዳ አለብህ” አለኝ።

ባለቤቴ ለረዥም ጊዜ ታማ እንደነበርና ልጆቼ ከምልክላቸው ገንዘብ በጀሮም ለሚገኘው ቤተ ክርስቲያን መዋጮ እንደሚያደርጉ ገለጽኩለት። እንዲህም ሆኖ ቄሱ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለማከናወን ፈቃደኛ ከመሆኑ በፊት የነበረብኝን ዕዳ ሁሉ ለመክፈል 50 ዶላር መበደር ነበረብኝ። ቄሱ ወዳጅ ዘመዶች ሄለንን ለመጨረሻ ጊዜ ለመሰናበት ወደተሰበሰቡት የሄለን ታላቅ እህት ቤት ሄዶ ፍትሃት ለማድረግ ተጨማሪ 15 ዶላር እንዲሰጠው ጠየቀ። 15 ዶላሩን ማግኘት አልቻልኩም። ሆኖም ደሞዝ በምቀበልበት ቀን ገንዘቡን የምሰጠው ከሆነ ፍትሃት ለማድረግ ተስማማ።

ደሞዝ ስቀበል ልጆቹ ለትምህርት ቤት የሚያስፈልጋቸውን ጫማና ልብስ መግዛት ነበረብኝ። ከሁለት ሳምንት አካባቢ በኋላ ቄሱ በምነዳው ሰርቪስ ውስጥ ተሳፈረ። “15 ዶላር ተበድረኸኛል” በማለት ተናገረ። የሚወርድበት ቦታ ሲደርስ “ወደ አለቃህ ዘንድ እሄድና ከደሞዝህ ላይ ቆርጦ እንዲሰጠኝ አደርጋለሁ” በማለት በዛቻ ተናገረ።

የቀኑ ሥራ ማገባደጃ ላይ ወደ አለቃዬ ዘንድ ሄድኩና የሆነውን ነገር ሁሉ አጫወትኩት። ምንም እንኳ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ቢሆንም “ያ ቄስ እዚህ መጥቶ ቢሆን ኖሮ ልክ ልኩን ነግሬው አባርረው ነበር!” በማለት ተናገረ። አለቃዬ እንዲህ ብሎ መናገሩ ‘ቀሳውስቱ የሚፈልጉት ገንዘባችንን ብቻ ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ አስተምረውን አያውቁም’ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ።

እውነትን መማር

በሌላ ጊዜ ወደ ሁለቱ ግሪካውያን ቡና ቤት ሄድኩና ቄሱ ያደረገኝን ሁሉ ነገርኳቸው። ከዚያም በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ከሚጠሩት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጥናት ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎች እያነበብኩ ሌሊቱን አነጋ ነበር። ቄሱ እንደተናገረው ሄለን ያለችው በመንጽሔ ሥቃይ ላይ ሳይሆን በሞት ያንቀላፋች መሆኗን አወቅኩ። (ኢዮብ 14:​13, 14፤ ዮሐንስ 11:​11–14) በእርግጥም ከወርቅ የሚበልጥ ነገር አግኝቻለሁ። እርሱም እውነትን ማወቅ ነው!

ከሁለት ሳምንት በኋላ ፒትስበርግ በሚገኘው በጋርደን ቲያትር ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት ወቅት እጄን አወጣሁና “ካቶሊክ በነበርኩባቸው ዓመታት ያልተማርኳቸውን ትምህርቶች በዛሬዋ ምሽት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬአለሁ” ብዬ ተናገርኩ። በኋላም በቀጣዩ ቀን በስብከት ሥራ መካፈል የሚፈልጉ እንዳሉ ጥያቄ በቀረበ ጊዜ እንደገና እጄን አወጣሁ።

ከዚያም ጥቅምት 4, 1931 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። በዚህ ወቅት ቤት ተከራየሁና ከእኔ ጋር እንዲኖሩ ልጆቼን አመጣሁ። እነርሱን የምትንከባከብ ሠራተኛም ቀጠርኩ። የቤተሰብ ኃላፊነት ቢኖርብኝም ከጥር 1932 እስከ ሰኔ 1933 ረዳት ተብሎ በሚታወቅ በዓይነቱ ልዩ በሆነ አገልግሎት ተካፈልኩ። በየወሩ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች በመንገር ከ50 እስከ 60 ሰዓት አሳልፍ ነበር።

በዚህ ጊዜ ከሥራ ወደ ቤት፣ ከቤት ወደ ሥራ ከማመላልሳቸው ሠራተኞች መካከል በአንዲት ቆንጆ ሴት ላይ ዓይኔ አረፈ። በውስጠኛው መስተዋት ድንገት ዓይን ለዓይን እንተያይ ነበር። ማሪ እና እኔ የተገናኘው በዚህ መንገድ ነበር። ከተጠናናን በኋላ ነሐሴ 1936 ተጋባን።

በ1949 በምሠራበት መሥሪያ ቤት ረዥም ዘመን በማገልገሌ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተብሎ በሚጠራው በአቅኚነት ለመካፈል የሚያስችለኝን የሥራ ሰዓት እንድመርጥ ተፈቀደልኝ። የሁሉም ታናሽ የነበረችው ሴት ልጄ ጅን በ1945 የአቅኚነት አገልግሎት ጀመረችና አብረን ማገልገል ጀመርን። ከጊዜ በኋላ ጅን ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና ጽሕፈት ቤት በቤቴል ያገለግል ከነበረው ከሳም ፍሬንድ ጋር ተዋወቀች።a በ1952 ተጋቡ። እኔም አቅኚነቴን በፒትስበርግ ቀጠልኩና በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ቻልኩ። በአንድ ወቅት በየሳምንቱ የማስጠናቸው 14 ቤተሰቦች ነበሩ። በ1958 ከምሠራበት መሥሪያ ቤት ጡረታ ወጣሁ። ከዚያ በኋላ በየቀኑ ለስምንት ሰዓት ያክል የምሠራው ሰብዓዊ ሥራ ስላልነበረኝ አቅኚነት ቀላል ሆነልኝ።

በ1983 ማሪ ታመመች። ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት ጥሩ አድርጋ እንደተንከባከበችኝ እኔም በተራዬ እርሷን መንከባከብ ጀመርኩ። በመጨረሻ ማሪ መስከረም 14, 1986 አረፈች።

የትውልድ ቀዬን መፈለግ

በ1989 ጅን እና ሳም ፖላንድ በሚደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አብሬአቸው እንድሄድ ጋበዙኝ። እዚያም ያደኩበትን አካባቢ ጎበኘን። ሩስያውያን ያንን የዓለም ክፍል በወረሩበት ወቅት የከተማውን ስም ቀይረው የአካባቢውን ነዋሪዎች ወደ ሌሎች ቦታዎች አግዘዋቸው ነበር። አንደኛው ወንድሜ ወደ ኢስታንቡል ሌላዋ እህቴ ደግሞ ወደ ሩስያ ተግዘው ነበር። የመንደሩ ስም ለጠየቅናቸው ሰዎች ሁሉ እንግዳ ነበር።

በርቀት የሚታዩት ተራራዎች የማውቃቸው ነበሩ። ወደ መንደሩ እየቀረብን ስንሄድ እንደ ኮረብታ፣ መንታ መንገድ፣ አንድ ቤተ ክርስቲያን፣ የወንዝ ድልድይ የመሰሉ ሌሎች የማውቃቸውን ነገሮች አገኘን። ድንገት “ሆሶቼክ” የሚል ስም የተለጠፈበት አንድ ምልክት ተመለከትን! በቅርቡ ኮሚንስቶች ከስልጣናቸው ሲወርዱ መንደሩ በቀድሞው ስሙ ተመልሶ ተሰየመ።

ቤታችን ቦታው ላይ የለም። ይሁን እንጂ ምግብ እናበስልበት የነበረው ከቤት ውጪ የሚገኘው ምድጃ ግማሽ አካሉ መሬት ውስጥ ተቀብሮ እዛው እንዳለ ቀርቷል። ከዚያም ወደ አንድ ዛፍ እያመለከትኩ “ያንን ዛፍ ተመልከቱት። ወደ አሜሪካ ከመሄዴ በፊት የተከልኩት ነው። ምን እንደሚያክል ተመልከቱት!” በማለት ተናገርኩ። ከዚያም የቤተሰቦቼን ስሞች ለማግኘት ስንል ወደ መካነ መቃብር ሄድን። ሆኖም የማንንም መቃብር አላገኘንም።

እውነትን በአንደኛ ደረጃ ማስቀመጥ

ጅን በ1993 ባለቤቷ ከሞተ በኋላ የቤቴል አገልግሎቷን ትታ እኔን ለመንከባከብ የእርሷን እርዳታ እፈልግ እንደሆነ ጠየቀችኝ። እንዲህ ብታደርግ ከሁሉ የከፋ አሳዛኝ እንደሚሆን ነገርኳት። አሁንም ቢሆን ያለኝ አመለካከት እንደዚያው ነው። 102 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ ለብቻዬ ከኖርኩ በኋላ ለአረጋውያን እንክብካቤ ወደሚሰጥበት ተቋም መግባቴ ግድ ሆነ። ፒትስበርግ በሚገኘው ቤሌቩ ጉባኤ አሁንም ሽማግሌ ሆኜ እያገለገልኩ ነው። በየሳምንቱ እሁድ ወንድሞች ለስብሰባ ወደ መንግሥት አዳራሽ ይወስዱኛል። ምንም እንኳ በስብከቱ እንቅስቃሴ ያለኝ ተሳትፎ የተገደበ ቢሆንም ከአቅኚዎች ዝርዝር ውስጥ ግን አልወጣሁም።

ለበርካታ ዓመታት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የበላይ ተመልካቾችን ለማሰልጠን በሚያዘጋጃቸው ልዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመካፈል መብት አግኝቼአለሁ። ባለፈው ታኅሣሥ ለጉባኤ ሽማግሌዎች በተዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ከፊሉን ተካፍያለሁ። እንዲሁም ባለፈው ሚያዝያ 11 ዕለት በተከበረው በክርስቶስ የሞቱ መታሰቢያ በዓል ላይ ጅን ወስዳኝ ተገኝቻለሁ። ከ1931 ጀምሮ በየዓመቱ በዚህ በዓል ላይ ስገኝ ቆይቻለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ ካስጠናኋቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፤ ሌሎቹ በደቡብ አሜሪካ ሚስዮናዊ ናቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ አያቶች ሆነው ከልጆቻቸው ጋር አምላክን ያገለግላሉ። ሦስቱ ልጆቼ ማሬ ጃን እና ጅን እንዲሁም የእነርሱ ልጆችና የልጅ ልጆች ይሖዋ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ላይ ናቸው። ሌላዋ ሴት ልጄና የተቀሩት የልጅ ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ልጆች በተመሳሳይ መንገድ ይሖዋን እንዲያገለግሉ የዘወትር ጸሎቴ ነው።

አሁን 105 ዓመቴ ሲሆን ሁሉም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠናና የተማራቸውን ነገሮች ለሌሎች እንዲናገር አበረታታለሁ። አዎን፣ ይሖዋን የሙጥኝ ብላችሁ ከኖራችሁ የጠበቃችሁት ነገር ሳይፈጸም በመቅረቱ እንደማትቆጩ ከራሴ ተሞክሮ ተገንዝቤአለሁ። እናንተም ከሚጠፋ ወርቅ ይልቅ ሕይወት ከሰጠን ከይሖዋ አምላክ ጋር ውድ ዝምድና እንድትመሠርቱ የሚያስችላችሁን እውነት በማግኘት ልትደሰቱ ትችላላችሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሳም ፍሬንድ የሕይወት ታሪክ ነሐሴ 1, 1986 የመጠበቂያ ግንብ እትም (እንግሊዝኛ) ገጽ 22–26 ላይ ይገኛል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሠራተኞችን ሰርቪስ ስነዳ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ለአረጋውያን እንክብካቤ በሚሰጥበት ተቋም ውስጥ ሆኜ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1989 ያገኘነው የመንገድ ምልክት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ