ቅራኔዎችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው?
የኃይል እርምጃ ወስዶ ሌላውን ማጥቃት የሰውን ዘር ያህል ረጅም ዘመን የቆየ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የኃይል እርምጃ መውሰድ የተጀመረበትን ጊዜ ሲያመለክት የአቤል ወንድምና የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የበኩር ልጅ ወደነበረው ወደ ቃየን ዘመን ይመልሰናል። አምላክ እሱ ካቀረበው መሥዋዕት ይልቅ የአቤልን ሲቀበል ቃየን “እጅግ ተናደደ።” የተፈጠረውን ሁኔታ የተወጣው እንዴት ነበር? “ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሳበት፣ ገደለውም።” ከዚህ በኋላ ከአምላክ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ገባ። (ዘፍጥረት 4:5, 8-12) ቃየን የኃይል እርምጃ መውሰዱ ከፈጣሪው ጋር ለነበረው ቅራኔ መፍትሄ አላስገኘም።
ቃየን እንዳደረገው ኃይል በመጠቀም ቅራኔዎችን ከመፍታት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ኃይለኛነትን ትቶ ቻይ መሆን
የመጀመሪያው ሰማዕት ክርስቲያን ማለትም እስጢፋኖስ በተገደለበት ጊዜ ድርጊቱን በመደገፍ ይመለከት የነበረውን ሰው ውሰድ። (ሥራ 7:58፤ 8:1) ይህ ሰው ማለትም የጠርሴሱ ሳውል የእስጢፋኖስን ሃይማኖታዊ አቋም ከመቃወሙም በላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መገደሉ የእስጢፋኖስን ሥራ ለማስቆም የተወሰደ ፍትሃዊ እርምጃ አድርጎ በመቁጠር ድርጊቱን ደግፏል። ሳውል በሁሉም የሕይወቱ ዘርፍ ኃይለኛ አልነበረ ይሆናል። ሆኖም ቅራኔዎችን ለመፍታት የኃይል እርምጃን እንደ አማራጭ ለመጠቀም ዝግጁ ነበር። እስጢፋኖስ ከተገደለ በኋላ ወዲያውኑ ሳውል “ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ [“በከፍተኛ ቁጣ ያሳድድ፣” NW] ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር።”—ሥራ 8:3
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አልበርት ባርነስ እንዳሉት ከሆነ እዚህ ላይ “ያፈርስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንበሳና ተኩላ የመሳሰሉት አራዊት ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ያመለክታል። “ሳውል በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ልክ እንደ አውሬ በቁጣ ተነስቷል የሚለው ጠንካራ መግለጫ [ክርስቲያኖችን] ሲያሳድድ የነበረውን ቅንዓትና ንዴት ያሳያል” ሲሉ ባርነስ ገልጸዋል። ሳውል ሌሎች የክርስቶስ ተከታዮችን ለመያዝ ወደ ደማስቆ ሲያመራ “የጌታን [የክርስቶስን] ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ” ይሄድ ነበር። በጉዞ ላይ ሳለ ከሙታን ተነስቶ የነበረው ኢየሱስ አነጋገረው፤ ይህ ክስተት ሳውል ወደ ክርስትና እንዲለወጥ ምክንያት ሆኗል።—ሥራ 9:1-19
ሳውል ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ከሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ተለውጧል። ከ16 ዓመታት በኋላ የተከሰተ አንድ ሁኔታ ያደረገውን ለውጥ በተጨባጭ ያሳያል። አንዳንድ ሰዎች እርሱ አባል በሆነበት በአንጾኪያ ወደሚገኘው ጉባኤ መጡና በዚያ የሚገኙት ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ እንዲፈጽሙ አጥብቀው አሳሰቧቸው። በዚህ ምክንያት “ብዙ ጥልና ክርክር” ተነሳ። በዚህ ወቅት ይበልጥ ጳውሎስ በሚለው መጠሪያ የሚታወቀው ሳውል በክርክሩ ላይ አቋም ወሰደ። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው የጦፈ ክርክር አድርገዋል። ሆኖም ጳውሎስ የኃይል እርምጃ አልወሰደም። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩ በኢየሩሳሌም ጉባኤ ወደሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲላክ ጉባኤው ሲወስን እርሱም እሺ ብሏል።—ሥራ 15:1, 2
በኢየሩሳሌም ሽማግሌዎቹ ባደረጉት ስብሰባ ላይ እንደገና ‘ብዙ ክርክር’ ተነሳ። ጳውሎስ ‘ሕዝቡም ሁሉ ዝም እስኪሉ’ ድረስ ጠበቀና የአምላክ መንፈስ ባልተገረዙት አማኞች መካከል ያከናወነውን አስደናቂ ሥራ ተረከላቸው። ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የነበሩ ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ‘በአንድ ልብ ሆነው’ ባልተገረዙት አማኞች ላይ የማያስፈልግ ሸክም ላለመጫን ከዚህ ይልቅ ‘ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም እንዲርቁ’ ለመምከር ተስማሙ። (ሥራ 15:3-29) በእርግጥም ጳውሎስ ለውጥ አድርጎ ነበር። አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ተምሮ ነበር።
የኃይለኝነትን አዝማሚያ መቆጣጠር
ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። . . . በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፣ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25) ጳውሎስ ወጣት የበላይ ተመልካች የሆነው ጢሞቴዎስ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በሰከነ መንፈስ እንዲይዝ መክሮታል። ጳውሎስ እውነታውን አልካደም። በክርስቲያኖች መካከል እንኳ ሳይቀር የስሜት መገንፈል ሊከሰት እንደሚችል ያውቅ ነበር። (ሥራ 15:37-41) “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” ብሎ ለመምከር ጥሩ ምክንያት ነበረው። (ኤፌሶን 4:26) እንደነዚህ ዓይነት ስሜቶችን መወጣት የሚቻልበት ተገቢው መንገድ ከቁጥጥር ውጭ በሆኑ ቁጣ ሳይገነፍሉ ንዴትን በመቆጣጠር ነው። ሆኖም ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
በዛሬው ጊዜ ቁጣን መግታት ቀላል አይደለም። በሃርቫርድ የሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት ረዳት ዲን የሆኑት ዶክተር ዴብራ ፕሮትሮውስቲት “ብዙ ሰው ክፉ መሆን ይቀናዋል” ሲሉ ተናግረዋል። “እንዲያውም እንደ መደራደር፣ ለሰላም ሲባል አንዳንድ ነገርን መተው፣ ችግሩን በሌላው ቦታ ሆኖ ማየትና ይቅር ባይነት የመሳሰሉት ከሌሎች ጋር ተቻችሎ ለመኖር የሚያስችሉት ባሕርያት አብዛኛውን ጊዜ እንደ ደካማነት የሚቆጠሩ ሆነዋል።” ይሁን እንጂ እነዚህ ባሕርያት ብርቱ የሆነ ሰው የሚያሳያቸው ሲሆኑ የታመቀን የኃይለኝነት አዝማሚያ ለማርገብ አስፈላጊ ናቸው።
ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ የአስተሳሰብ ልዩነቶችን መያዝ የሚችልበትን የተሻለ መንገድ ተምሯል። ይህ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተ ነው። ጳውሎስ የአይሁድን እምነት ጠንቅቆ የተማረ ሊቅ እንደመሆኑ መጠን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ትውውቅ ነበረው። ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የመሳሰሉ ጥቅሶች ያውቅ ነበር:- “በግፈኛ ሰው አትቅና፣ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ።” “ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፣ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል።” “ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፣ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።” (ምሳሌ 3:31፤ 16:32፤ 25:28) ሆኖም ይህ እውቀት ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በክርስቲያኖች ላይ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ አልገታውም ነበር። (ገላትያ 1:13, 14) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ የጦፈ ክርክር የሚያስነሱ ጉዳዮችን ለመፍታት ኃይል ከመጠቀም ይልቅ ምክንያት እያቀረበና ሰዎችን እያግባባ ለማነጋገር የረዳው ምንድን ነው?
ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ብሎ በተናገረበት ጊዜ ፍንጭ ሰጥቶናል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገለት ነገር ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። (1 ጢሞቴዎስ 1:13, 14) ክርስቶስ ሊከተለው የሚገባ አርአያ ሆኖለት ነበር። ኢየሱስ ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ሲል ከፍተኛ መከራ እንደደረሰበት አወቀ። (ዕብራውያን 2:18፤ 5:8-10) ጳውሎስ ስለ መሲሑ የሚናገረው ከዚህ ቀጥሎ ያለው የኢሳይያስ ትንቢት በኢየሱስ ላይ መፈጸሙን ማረጋገጥ ችሏል:- “ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።” (ኢሳይያስ 53:7) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ኢየሱስ] ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።”—1 ጴጥሮስ 2:23, 24
ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለተቋቋመበት መንገድ ያደረበት አድናቆት እንዲለወጥ አድርጎታል። የእምነት አጋሮቹን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላስይስ 3:13) የኃይለኝነትን ባሕርይ ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን መቀበሉ ብቻ አይበቃም። ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረጉልን ነገር ያለን አድናቆት የኃይለኝነት ዝንባሌዎችን ታግለን እንድናሸንፍ ሊገፋፋን ይገባል።
የሚቻል ነገር ነው?
በጃፓን የሚኖር አንድ ሰው ይህ ዓይነቱ ጠንካራ ግፊት የሚያሳድር ነገር አስፈልጎታል። ወታደር የነበረው ግልፍተኛ አባቱ ቤተሰቡን የሚገዛው በኃይል ነበር። ይህ ሰው የኃይል ድርጊት ተጠቂ ስለሆነና እናቱም ተመሳሳይ ጥቃት ሲደርስባት ይመለከት ስለነበረ የኃይለኝነት ባሕርይ ተጠናውቶት አደገ። የተለያየ ርዝመት ያላቸውን ሁለት ጎራዴዎች በመያዝ ቅራኔዎችን ለመፍታትና ሰዎችን ለማስፈራራት ይጠቀምባቸው ነበር።
ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመረችበት ጊዜ ነገሩን ከቁምነገር ሳይቆጥር እንዲሁ በጥናቱ ላይ ይገኝ ነበር። ሆኖም ይህ የመንግሥት ምሥራችa የሚል ርዕስ ያለውን ቡክሌት ካነበበ በኋላ ለውጥ አደረገ። ለምን? “‘ኢየሱስ ክርስቶስ’ እና ‘የቤዛው ዋጋ’ በሚሉት ንዑስ ርዕሶች ሥር ያሉትን ሐሳቦች ሳነብ የጸጸት ስሜት አደረብኝ” ሲል ገልጿል። “ምንም እንኳ ጋጠወጥ ሕይወት ብመራም አብሬአቸው ለምኖረው ሰዎች ደግ መሆን ያስደስተኝ ነበር። ጎደኞቼን ማስደሰት እርካታ ይሰጠኝ ነበር፤ ሆኖም ይህን የማደርገው የራሴን ሕይወት የማይጎዳ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ እንደ እኔ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ሕይወቱን ለሰው ዘር ለመስጠት ፈቃደኛ ነበር። ይህን ስገነዘብ አናቴን በመዶሻ የተመታሁ ያህል ክው ብዬ ቀረሁ።”
ከቀድሞ ጎደኞቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት ካቋረጠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በሚካሄደው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመሳተፍ ተመዘገበ። ይህ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለሌሎች ሰዎች የማስተማር ችሎታ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ሥልጠናው ለዚህ ሰው ተጨማሪ ጥቅም አስገኝቶለታል። እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “ወጣት ሳለሁ ስሜቶቼን ለሰዎች በቃላት መግለጽ ስለሚያቅተኝ ዛቻና ኃይል ወደመጠቀም አመራ ነበር። ለሰዎች ሐሳቤን የመግለጽ ችሎታ እየተማርኩ ስሄድ ግን ኃይል ከመጠቀም ይልቅ ከሌሎች ጋር ምክንያቴን እያስረዳሁ መወያየት ጀመርኩ።”
ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ ይህ ሰው የክርስቶስን አካሄድ ተከትሏልን? በወንድማማችነት ቃል ኪዳን የተሳሰረው የቀድሞ ጓደኛው ክርስቲያን እንዳይሆን ለመከልከል በሞከረበት ጊዜ እምነቱ ተፈተነ። “ጓደኛው” እሱን ከመምታቱም በላይ የአምላኩን የይሖዋን ስም ሰደበበት። ቀድሞ ኃይለኛ የነበረው ይህ ሰው ራሱን ተቆጣጥሮ መሐላውን መጠበቅ ባለመቻሉ ይቅርታ ጠየቀው። “ወንድሙ” ያሰበውን ሳያሳካ በመቅረቱ ተናድዶ ጥሎት ሄደ።
በፊት ቁጡ የነበረው ይህ ሰው የኃይለኝነት ጠባዩን በማሸነፍ አምላክንና ሰዎችን በማፍቀር ኅብረት ያላቸው ብዙ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች አፍርቷል። (ቆላስይስ 3:14) እንዲያውም ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን ከሆነ ከ20 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ አሁን የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። እሱ እንደተማረው ሁሉ አውሬ መሰል ባሕርያት ያሏቸው ሰዎች ኃይል ሳይጠቀሙ ቅራኔዎቻቸውን መፍታት መማር እንደሚችሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማሳየቱ ምንኛ ያስደስተዋል። እንዲሁም ቀጥሎ ያሉት ትንቢታዊ ቃላት ወደፊት ታላቅ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ማሳወቅ መቻሉ እንዴት ያለ መብት ነው:- “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና”!—ኢሳይያስ 11:9
እንደ ሐዋርያው ጳውሎስና ቀድሞ የኃይል እርምጃ መውሰድ ያስደስተው እንደነበረው እንደዚህ ሰው ሁሉ አንተም ቅራኔዎችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ወደ ጠብ የሚያመሩ ሁኔታዎችን በአግባቡ መያዝን መማር ትችላለህ። በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በደስታ ይረዱሃል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ጳውሎስ እውነታውን አልካደም። በክርስቲያኖች መካከል እንኳ ሳይቀር የስሜት መገንፈል ሊከሰት እንደሚችል አውቋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ ስላደረገልን ነገር ያለን አድናቶት ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን አስተዋጽኦ ያደርጋል