ዳርዮስ የፍትሕ ዝንባሌ የነበረው ንጉሥ
አንድ ታዋቂ ንጉሥ ያከናወናቸውን የግንባታ ሥራዎች አስመልክቶ በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት በጉራ ተናግሮ ነበር:- “በምሥራቅ በኩል በሚገኘው የባቢሎን አጥር ዙሪያ ጠንካራ ቅጥር ገነባሁ። በግምቡ ዙሪያ ጠላትን ለመከላከል የሚያገለግል ጥልቅና ሰፊ ጉድጓድ ቆፈርሁ። . . . በቃጥራሜና በሸክላ፣ ልክ እንደ ተራራ ከቦታው የማይነቃነቅ ቅጥር ገንብቻለሁ።” አዎን፣ የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰፊ የሆነ የግንባታ ፕሮግራም በማካሄድ የግዛቱን ዋና ከተማ ለማጎልበት ጠንክሮ ሠርቷል። ሆኖም የባቢሎን ከተማ እሱ እንዳሰበው የማትበገር ሆና አልተገኘችም።
ይህ እውነት መሆኑ ጥቅምት 5 ቀን 539 ከዘአበ በተከሰተው ነገር ተረጋግጧል። የፋርሱ ገዥ ዳግማዊ ቂሮስ በሜዶናውያን ሠራዊት እየታገዘ ባቢሎንን ድል አድርጎ ያዘ፤ ከለዳዊውን ገዥ ብልጣሶርንም ገደለ። ታዲያ በቅርቡ ድል በተደረገችው በዚህች ከተማ ላይ የመጀመሪያው ገዥ የሚሆነው ማን ይሆን? ከተማዋ በጠላት እጅ በወደቀች ጊዜ በዚያ ይገኝ የነበረው የአምላክ ነቢይ ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደ፤ ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረ።”—ዳንኤል 5:30, 31
ዳርዮስ ማን ነበር? ምን ዓይነት ንጉሥ መሆኑን አስመስክሯል? ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት ባቢሎን ውስጥ በግዞት ለሚገኘው ለነቢዩ ዳንኤል ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?
ብዙም የተጻፈ ታሪክ የሌለው ንጉሥ
ስለ ሜዶናዊው ዳርዮስ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪካዊ መረጃ በጣም ጥቂት ነው። ሜዶናውያን ምንም ታሪክ መዝግበው አላስቀሩም ለማለት ይቻላል። ከዚህም በላይ በመካከለኛው ምሥራቅ በቁፋሮ የተገኙ የሽብልቅ ቅርፅ ባላቸው ፊደላት የተጻፈባቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የድንጋይ ጽላቶች የሚያቀርቡት መረጃ ያልተሟላና ቁርጥርጥ ያለ ነው። ከጥፋት የተረፉ ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ ዳርዮስ በነበረበት ጊዜ ከተከናወኑ ነገሮች በመቶ ወይም ከዚያ በሚበልጡ ዓመታት ርቀት የተለያዩ ናቸው።
ያም ሆኖ ግን የፋርሱ ገዥ ዳግማዊ ቂሮስ የሜዶንን ዋና ከተማ አሕምታን ከተቆጣጠረ በኋላ ሜዶናውያን ለእሱ ታማኞች እንዲሆኑ ማድረግ ችሎ እንደነበር ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚያ በኋላ ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በእሱ አገዛዝ ሥር በመሆን ግንባር ፈጥረው ይዋጉ ነበር። ደራሲው ሮበርት ኮሊንስ ዘ ሜድስ ኤንድ ፔርሺያንስ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ግንኙነታቸውን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “በሰላም ጊዜ ሜዶናውያን ከፋርሳውያን ጋር እኩል ደረጃ ነበራቸው። በሲቪል አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ የሥልጣን እርካቦችን ይቆናጠጡ የነበረ ሲሆን በፋርስ ሠራዊትም ውስጥ የአመራር ቦታዎችን ይይዙ ነበር። የውጪ አገር ሰዎች ስለ ሜዶናውያንና ፋርሳውያን ሲናገሩ ድል ነሺና ድል ተነሺ የሚል ልዩነት አያደርጉም ነበር።” በመሆኑም ሜዶን ከፋርስ ጋር በመዋሃድ የሜዶ ፋርስ ግዛት ተቋቋመ።—ዳንኤል 5:28፤ 8:3, 4, 20
ሜዶናውያን ባቢሎንን ገርስሶ በመጣል ረገድ አቢይ ሚና እንደተጫወቱ የተረጋገጠ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘የሜዶን ዘር የነበረው የአሕሻዊሮስ ልጅ ዳርዮስ’ በባቢሎን ላይ የገዛ የመጀመሪያው የሜዶ ፋርስ ግዛት ንጉሥ እንደሆነ ይናገራሉ። (ዳንኤል 9:1) ንጉሣዊ ሥልጣኑ ‘በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት የማይለወጡ’ ደንቦች ማውጣትን የሚጨምር ነበር። (ዳንኤል 6:8) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳርዮስ የሚናገረው ነገር ባሕርዩ ምን ይመስል እንደነበር በአጭሩ የሚነግረን ሲሆን እሱን የሚመለከት ሃይማኖታዊ ያልሆነ መረጃ ያልኖረበትንም አጥጋቢ ምክንያት ይገልጽልናል።
ዳንኤል ሞገስ አገኘ
ዳርዮስ ወዲያው በባቢሎን ሥልጣን እንደጨበጠ ‘በመንግሥቱ ላይ መቶ ሀያ መሳፍንት እንደ ሾመና ሦስት አለቆች በላያቸው እንዳደረገ፣ ከእነርሱም አንደኛው ዳንኤል እንደነበረ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዳንኤል 6:1, 2) ይሁን እንጂ ሌሎች ባለ ሥልጣኖች ዳንኤል ባገኘው ከፍተኛ ሥልጣን አልተደሰቱም ነበር። ንጹህ አቋሙ ምግባረ ብልሹነት እንዲገታ እንዳደረገ አያጠራጥርም፤ ይህ ደግሞ በሌሎች ዘንድ እንዲጠላ ሳያደርገው አይቀርም። በተጨማሪም ከፍተኛ ባለ ሥልጣናቱ ዳንኤል ሞገስ በማግኘቱና ንጉሡ ጠቅላይ ሚንስትር ሊያደርገው በማሰቡ ቅናት ሳያድርባቸው አልቀረም።
ለዚህ ሁኔታ መቋጫ ለማበጀት በማሰብ ሁለቱ አለቆችና መሳፍንቱ አንድ የሕግ ተንኮል ሸረቡ። ወደ ንጉሡ ሄዱና ለዳርዮስ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ለ30 ቀናት ያህል ‘ለአምላክ ወይም ለሰው ልመና እንዳያቀርብ’ የሚከለክል ድንጋጌ ካረቀቁ በኋላ በፊርማው እንዲያጸድቅላቸው ጠየቁ። ድንጋጌውን የሚጥስ ማንኛውም ሰው አንበሶች ጉድጓድ መጣል አለበት የሚል ሐሳብ አቀረቡ። ዳርዮስ ድንጋጌው በሁሉም ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል የሚል እምነት አደረበት፤ እንዲሁም ባለ ሥልጣናቱ ለንጉሡ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳይ ይመስል ነበር።—ዳንኤል 6:1–3, 6–8
ዳርዮስ ድንጋጌውን ፈረመ፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ድንጋጌው ካስከተለው ነገር ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጠ። ዳንኤል ለይሖዋ አምላክ ጸሎት ማቅረቡን በመቀጠሉ ድንጋጌውን ለመጣስ የመጀመሪያው ሰው ሆነ። (ከሥራ 5:29 ጋር አወዳድር።) ምንም እንኳ ንጉሡ ከማይለወጠው ድንጋጌ የሚያመልጥበትን ዘዴ ለመፈለግ ልባዊ ጥረት ቢያደርግም የታመነ የነበረው ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ። ዳርዮስ የዳንኤል አምላክ ነቢዩን በሕይወት ሊጠብቀው እንደሚችል ትምክህት እንዳለው አሳይቷል።—ዳንኤል 6:9–17
ዳርዮስ ምግብ ሳይበላና እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ካደረ በኋላ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ በፍጥነት ሄደ። ዳንኤልን ምንም ጉዳት ሳይደርስበት በሕይወት በማግኘቱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ንጉሡ የዳንኤልን ከሳሾችና ቤተሰቦቻቸውን ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ እንዲጣሉ በማድረግ ፍትሐዊ የሆነ የአጸፋ እርምጃ ወሰደ። በተጨማሪም ‘በመንግሥቱ ግዛት ሥር ያሉ ሰዎች ሁሉ በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ’ የሚያዝ ደንብ አወጣ።—ዳንኤል 6:18–27
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዳርዮስ የዳንኤልን አምላክና ሃይማኖት የሚያከብር መሆኑን ከማሳየቱም በላይ ፍትሐዊ እርምጃ በመውሰድ ስህተትን ለማረም ፈጣን ነበረ። ይሁንና የዳንኤልን ከሳሾች መቅጣቱ የተቀሩት ባለ ሥልጣናት በጠላትነት እንዲመለከቱት ሳያደርገው አልቀረም። ከዚህም በላይ በመንግሥቱ ግዛት ውስጥ ያሉ በሙሉ ‘የዳንኤልን አምላክ እንዲፈሩ’ የሚያዘው የዳርዮስ አዋጅ ኃያል በሆኑት ባቢሎናዊ ቀሳውስት ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ አይቀርም። እነዚህ ነገሮች በጻፎች ላይ ተጽእኖ ማሳደራቸው ስለማይቀር ዳርዮስን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለማጥፋት ሲሉ ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ዘገባዎችን ቢበርዙ ምንም አያስገርምም። ቢሆንም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው አጭር ታሪክ ዳርዮስ አድልዎ የማያደርግና የፍትሕ ዝንባሌ የነበረው ገዥ መሆኑን ያሳያል።