የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 2/15 ገጽ 13-18
  • የክርስቶስ ቤዛ የአምላክ የመዳን መንገድ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የክርስቶስ ቤዛ የአምላክ የመዳን መንገድ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኃጢአትንና ሞትን ማስወገድ
  • ኃጢአት የሚጠይቀውን ዋጋ መሸፈን
  • “ተመጣጣኝ ቤዛ”
  • ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ያለው ዋጋ 
  • ከክርስቶስ ቤዛ ጥቅም ማግኘት
  • ቤዛው የፍቅር መግለጫ ነው
  • ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ . . . ቤዛ” አዘጋጀ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ለሁሉ የሚሆን ተመጣጣኝ ቤዛ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 2/15 ገጽ 13-18

የክርስቶስ ቤዛ የአምላክ የመዳን መንገድ

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”—⁠ዮሐንስ 3:​16

1, 2. የሰው ዘር የሚገኝበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ግለጽ።

ቀዶ ሕክምና ካልተደረገልህ በስተቀር ሕይወትህን የሚያሳጣህ በሽታ ይዞሃል እንበል። ለቀዶ ሕክምናው የሚያስፈልገው ወጪ አቅምህ ከሚችለው በላይ ቢሆን ምን ይሰማሃል? ሌላው ቀርቶ የቤተሰብህና የወዳጆችህ ገቢ ተሰባስቦ እንኳ ወጪውን ለመሸፈን ባይበቃስ? እንዲህ ባለ የሕይወትና የሞት አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ምንኛ ተስፋ አስቆራጭ ነው!

2 ይህ ምሳሌ የሰው ዘር የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያስረዳ ነው። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት ፍጹም ሆነው ነበር። (ዘዳግም 32:​4) ለዘላለም የመኖርና “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም” የሚለውን የአምላክ ዓላማ የመፈጸም ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:​28) ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን በፈጣሪያቸው ላይ ዓመፁ። (ዘፍጥረት 3:​1-6) የአዳምና የሔዋን አለመታዘዝ በእነሱ ላይ ብቻ ሳይሆን ከአብራካቸው በሚወጡ ልጆቻቸውም ላይ ኃጢአት አምጥቷል። ታማኙ ኢዮብ ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው “ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም።”​—⁠ኢዮብ 14:​4

3. ሞት ለሰዎች ሁሉ የተዳረሰው እንዴት ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና” ብሎ ስለሚናገር ኃጢአት ሁሉንም ሰው እንደያዘ አንድ በሽታ ሊቆጠር ይችላል። ይህ ሁኔታ ለሕይወት አስጊ የሆኑ መዘዞች አሉት። አዎን፣ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት [ነው]።” (ሮሜ 3:​23 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ 6:​23) ማንኛችንም ልናመልጥ አንችልም። የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ሁሉም ይሞታሉ። የአዳም ዝርያዎች በመሆናችን የተወለድነው በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው። (መዝሙር 51:​5) ጳውሎስ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 5:​12) ይህ ማለት ግን ምንም የመዳን ተስፋ የለንም ማለት አይደለም።

ኃጢአትንና ሞትን ማስወገድ

4. የሰው ልጆች በራሳቸው ጥረት በሽታንና ሞትን ሊያስወግዱ የማይችሉት ለምንድን ነው?

4 ኃጢአትንና የእሱ ውጤት የሆነውን ሞትን ለማስወገድ ምን ያስፈልጋል? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይህ ከማንኛውም ሰው አቅም በላይ የሆነ ነገር ነው። መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ሐዘኑን ገልጿል:- “ለሰው ሕይወት የሚከፈለው ዋጋ እጅግ ብዙ ነው፤ . . . እንዳይሞትና ወደ መቃብር እንዳይወርድ፣ ለዘላለም እንዲኖር ለማድረግ፣ የቱንም ያህል ቢከፈል በቂ አይሆንም።” (መዝሙር 49:​8, 9 የ1980 ትርጉም) እርግጥ ነው፣ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ በማዳበርና የሕክምና ክትትል በማድረግ ሕይወታችንን ለጥቂት ዓመታት ለማስረዘም እንችል ይሆናል፤ ሆኖም ማናችንም ብንሆን በራሳችን ጥረት ከወረስነው ኃጢአት መፈወስ አንችልም። ማናችንም ብንሆን በእርጅና ምክንያት የሚመጣውን የአካል መሽመድመድ ልንቀለብስና አምላክ መጀመሪያ አስቦት ወደነበረው የአካል ፍጽምና ልንመልሰው አንችልም። በእርግጥም ጳውሎስ በአዳም ኃጢአት ምክንያት ሰብዓዊው ፍጥረት “ለከንቱነት ተገዝቶአልና” ወይም ዘ ጀሩሳሌም ባይብል እንደሚለው “እንደታለመለት መሆን አልቻለም” ብሎ ሲናገር ማጋነኑ አልነበረም። (ሮሜ 8:​20) ደስ የሚለው ግን ፈጣሪ እርግፍ አድርጎ አልተወንም። ኃጢአትንና ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ዝግጅት አድርጓል። እንዴት?

5. ለእስራኤል የተሰጠው ሕግ ለፍትሕ የላቀ ግምት የሚሰጠው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ “ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል።” (መዝሙር 33:​5) ለእስራኤል የሰጠው ሕግ ሚዛናዊ ለሆነ ፍርድና አድሏዊነት ለሌለበት ፍትሕ የሚሰጠውን የላቀ ግምት ያንጸባርቃል። ለምሳሌ ያህል በዚህ የሕጎች አካል ውስጥ ‘ሕይወት ስለ ሕይወት’ መከፈል እንዳለበት የሚናገር ቃል እናነባለን። በሌላ አነጋገር አንድ እስራኤላዊ አንድ ሰው ቢገድል ባጠፋው ሕይወት ምትክ የራሱን ሕይወት ማጣት ነበረበት። (ዘጸአት 21:​23፤ ዘኁልቁ 35:​21) በዚህ መንገድ የመለኮታዊው ፍትሕ ሚዛን ትክክል ይሆናል።​—⁠ከዘጸአት 21:​30 ጋር አወዳድር።

6. (ሀ) አዳም ነፍሰ ገዳይ ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው? (ለ) አዳም ያጣው ምን ዓይነት ሕይወት ነው? የፍትሕ ሚዛን ትክክል እንዲሆንስ ምን ዓይነት መሥዋዕት ያስፈልጋል?

6 አዳም ኃጢአት ሲሠራ ነፍሰ ገዳይ ሆነ። እንዴት? ለዘሮቹ በሙሉ ኃጢአትንና ሞትን በማውረሱ ነው። ዛሬ አካላችን ከዕለት ወደ ዕለት እየደከመ ወደ መቃብር በማዝገም ላይ የሚገኘው በአዳም ኃጢአት ምክንያት ነው። (መዝሙር 90:​10) የአዳም ኃጢአት ሌላም የከፋ ነገር አስከትሏል። አዳም ራሱንም ሆነ ልጆቹን ያሳጣው 70 ወይም 80 ዓመት የሚቆይ ተራ ሕይወት አይደለም። አዳም ያጣው ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት ነው። ስለዚህ ‘ሕይወት ለሕይወት’ መከፈል ካለበት በዚህ ረገድ ፍትሕን ለማሟላት ምን ዓይነት ሕይወት መሰጠት አለበት? ፍጹም ሰብዓዊ ፍጡሮችን ማስገኘት የሚችል እንደ አዳም ያለ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ማስፈለጉ ምክንያታዊ ነው። ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡ የፍትሕ ሚዛን ትክክል እንዲሆን ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ኃጢአትንና የእሱ ውጤት የሆነውን ሞትን ጠራርጎ ለማጥፋት ያስችላል።

ኃጢአት የሚጠይቀውን ዋጋ መሸፈን

7. “ቤዛ” የሚለውን ቃል ትርጉም ግለጽ።

7 እኛን ከኃጢአት ለማዳን የሚያስፈልገው ዋጋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ቤዛ’ ተብሎ ተገልጿል። (መዝሙር 49:​7) ቤዛ ተብሎ የተተረጎመው ራንሰም የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አንድ አጋች አግቶ በያዘው ሰው ፈንታ የሚጠይቀውን ክፍያ ሊያመለክት ይችላል። እርግጥ ይሖዋ ያዘጋጀው ቤዛ ከማገት ጋር የተያያዘ አይደለም። ክፍያን ግን የሚጠይቅ ነው። እንዲያውም “ቤዛ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል ግሥ ቀጥታ ሲተረጎም “መሸፈን” የሚል ትርጉም አለው። ኃጢአት እንዲሠረይ ቤዛው መሸፈን ካለበት ማለትም ከአዳም ፍጹም ሕይወት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመጣጠን መሆን አለበት።

8. (ሀ) የመቤዠትን መሠረታዊ ሥርዓት ግለጽ። (ለ) የመቤዠት መሠረታዊ ሥርዓት ኃጢአተኞች ከሆንነው ከእኛ ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት ነው?

8 ይህም በሙሴ ሕግ ውስጥ ከሚገኘው ስለ መቤዠት ከሚናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል። አንድ እስራኤላዊ ቢደኸይና እስራኤላዊ ላልሆነ ሰው ራሱን ባሪያ አድርጎ ቢሸጥ ዘመዱ የሆነ ሰው ከባሪያው ዋጋ ጋር እኩል ይሆናል ተብሎ የሚገመተውን ክፍያ በመክፈል ሊቤዠው (ወይም ቤዛ ሊሰጥለት) ይችል ነበር። (ዘሌዋውያን 25:​47-49) መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ፍጽምና የሌለን “የኃጢአት ባሪያዎች” እንደሆንን ይናገራል። (ሮሜ 6:​6 የ1980 ትርጉም፤ 7:​14, 25) እኛን ለመቤዠት ምን ያስፈልጋል? ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የጠፋው ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ምንም ሳይጨምርም ሆነ ምንም ሳይቀንስ ሌላ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት እንዲከፈል ይጠይቃል።

9. ይሖዋ ኃጢአትን ለመሸፈን ምን ዝግጅት አድርጓል?

9 እኛ ሰዎች የተወለድነው ከአለፍጽምና ጋር ነው። አንዳችንም ብንሆን ከአዳም ጋር እኩል አይደለንም፤ ማናችንም ብንሆን ፍትሕ የሚጠይቀውን የቤዛ ዋጋ ልንከፍል አንችልም። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ለሕይወታችን አስጊ የሆነ በሽታ ይዞን ከበሽታው መገላገል የሚያስችለውን የቀዶ ሕክምና ለማድረግ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የመክፈል አቅም የሌለን ያክል ነው። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ እያለን አንድ ሰው ጣልቃ ገብቶ ወጪውን ቢሸፍንልን በጣም ከፍተኛ ውለታ እንደዋለልን አይሰማንምን? ይሖዋም ያደረገው ይህንኑ ነው! ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እኛን ከኃጢአት ለመቤዠት ዝግጅት አድርጓል። አዎን፣ አቅማችን ፈጽሞ የማይፈቅደውን ነገር ይሖዋ ሊሰጠን ፈቃደኛ ሆነ። እንዴት? ጳውሎስ “የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ . . . በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 6:​23) ዮሐንስ ኢየሱስን “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት ገልጾታል። (ዮሐንስ 1:​29) ይሖዋ የሚወደውን ልጁን የቤዛውን ዋጋ እንዲከፍል እንዴት እንደተጠቀመበት ቀጥለን እንመልከት።

“ተመጣጣኝ ቤዛ”

10. አንድን “ዘር” የሚመለከቱ ትንቢቶች በዮሴፍና በማርያም ላይ ያተኮሩት እንዴት ነበር?

10 ከኤደን ዓመፅ በኋላ ይሖዋ የሰው ልጆችን ከኃጢአት የሚቤዥ “ዘር” ወይም ልጅ ለማስገኘት ያለውን ዓላማ ወዲያውኑ አስታወቀ። (ዘፍጥረት 3:​15) ተከታታይ በሆኑ መለኮታዊ ራእዮች አማካኝነት ይህ ዘር የሚገኝበትን የቤተሰብ መስመር ይሖዋ ለይቶ አሳውቋል። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ራእዮች በፍልስጥኤም ምድር ይኖሩ በነበሩ እጮኛሞች ማለትም በዮሴፍና በማርያም ላይ አነጣጠሩ። ዮሴፍ በሕልም አማካኝነት ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ እንደ ፀነሰች ተነግሮታል። መልአኩ “ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 1:​20, 21

11. (ሀ) ይሖዋ ልጁ ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ ዝግጅት ያደረገው እንዴት ነበር? (ለ) ኢየሱስ “ተመጣጣኝ ቤዛ” ሊያቀርብ የቻለው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ይኖር ስለነበር ይህ እርግዝና እንደ ማንኛውም ሌላ ተራ እርግዝና አልነበረም። (ምሳሌ 8:​22-31፤ ቆላስይስ 1:​15) ሕይወቱ በይሖዋ ተአምራዊ ኃይል አማካኝነት ወደ ማርያም ማህፀን በመዛወሩ በአምላክ ዘንድ ተወዳጅ የነበረው ይህ ልጅ ሰው ሆኖ ሊወለድ ችሏል። (ዮሐንስ 1:​1-3, 14፤ ፊልጵስዩስ 2:​6, 7) ኢየሱስ በአዳም ኃጢአት እንዳይበከል ይሖዋ አስፈላጊውን ጥበቃ አድርጓል። በመሆኑም ኢየሱስ ፍጹም ሆኖ ተወለደ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ አዳም ያጣውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ሊያገኝ ቻለ። በመጨረሻ የኃጢአትን ዋጋ ሊሸፍን የሚችል ሰው ተገኘ! ኢየሱስም በኒሳን 14 ቀን 33 እዘአ ያደረገው ይህንኑ ነበር። በዚያ ታሪካዊ ቀን ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ እንዲገድሉት በመፍቀድ ራሱን “ተመጣጣኝ ቤዛ” አድርጎ አቅርቧል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​6 NW

ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ያለው ዋጋ 

12. (ሀ) በኢየሱስ ሞትና በአዳም ሞት መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት ግለጽ። (ለ) ኢየሱስ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች “የዘላለም አባት” የሆነው እንዴት ነው?

12 በኢየሱስ ሞትና በአዳም ሞት መካከል ልዩነት ያለ ሲሆን ልዩነቱ የቤዛውን ዋጋማነት የሚያጎላ ነው። አዳም በፈጣሪው ላይ ያመፀው ሆን ብሎ ስለሆነ ሞቱ የሚገባው ነበር። (ዘፍጥረት 2:​16, 17) በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ‘ምንም ኃጢአት ስላላደረገ’ በፍጹም መሞት አይገባውም ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:​22) ስለዚህ ኢየሱስ ሲሞት ኃጢአተኛው አዳም በሞተበት ጊዜ ያልነበረው ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር ማለትም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ይዞ የመቀጠል መብት ነበረው። ይህም በመሆኑ የኢየሱስ ሞት መሥዋዕታዊ ዋጋ አለው። መንፈሳዊ አካል ለብሶ ወደ ሰማይ በማረግ የመሥዋዕቱን ዋጋ ለይሖዋ አቅርቧል። (ዕብራውያን 9:​24) ኢየሱስ እንዲህ በማድረግ ኃጢአተኛውን የሰው ዘር የገዛ ሲሆን በአዳም ምትክም አዲስ አባት ሆኗቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:​45) ስለዚህ ኢየሱስ “የዘላለም አባት” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። (ኢሳይያስ 9:​6) ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስቡ! ኃጢአተኛ አባት የሆነው አዳም ለዘሮቹ በሙሉ ሞትን አዳርሷል። ፍጹም አባት የሆነው ኢየሱስ የመሥዋዕቱን ዋጋ በመጠቀም ታዛዥ የሰው ልጆች ዘላለማዊ ሕይወት እንዲያገኙ ያደርጋል።

13. (ሀ) አዳም ያመጣውን ዕዳ ኢየሱስ እንዴት እንደሰረዘው በምሳሌ አስረዳ። (ለ) የኢየሱስ መሥዋዕት የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ኃጢአት የማይሸፍነው ለምንድን ነው?

13 ይሁንና የአንድ ሰው ሞት የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸፍን የሚችለው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 20:​28) ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በወጣ አንድ ርዕሰ ትምህርት ላይ ቤዛውን በሚከተለው ምሳሌ ገልጸነው ነበር:- “በመቶ የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያሉት አንድ ትልቅ ፋብሪካ አለ እንበል። የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አጭበርባሪ ሰው ሆነና ድርጅቱን አከሰረው። ፋብሪካው ተዘጋ። አሁን እነዚያ ሁሉ በመቶ የሚቆጠሩ ሠራተኞች አለ ሥራ ስለ ቀሩ ለመኖሪያ ወጪያቸው የሚከፍሉት ገንዘብ አጡ። በዚህ አንድ ሰው ምግባረ ብልሹነት ምክንያት የትዳር ጓደኞቻቸው፣ ልጆቻቸውና አበዳሪዎቻቸው ሁሉ ችግር ላይ ወደቁ! በዚህ ጊዜ አንድ ሀብታም የሆነ በጎ አድራጊ ሰው መጣና የኩባንያውን ዕዳ በሙሉ ከፍሎ ፋብሪካው እንዲከፈት ያደርጋል። የዚህ የፋብሪካው ዕዳ መከፈል ሠራተኞቹ ሁሉ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለአበዳሪዎቻቸው ሁሉ ሙሉ እፎይታ አመጣላቸው። ይሁን እንጂ የቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ከዚህ አዲስ ብልጽግና ሊካፈል ይችላልን? አይችልም፤ ምክንያቱም በወንጀሉ ምክንያት በእሥር ቤት የሚገኝ ስለሆነ ወደ ሥራው ሊመለስ አይችልም! በተመሳሳይም የአዳም ዕዳ መሻሩ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ዘሮቹ ጥቅም ያስገኛል፤ ለአዳም ግን ምንም ጥቅም አያመጣለትም።”

14, 15. አዳምና ሔዋን ሆን ብለው ኃጢአት ሠርተዋል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? እኛ ያለንበት ሁኔታ እነሱ ከነበሩበት ሁኔታ የሚለየውስ እንዴት ነው?

14 ይህ ደግሞ አግባብነት ያለው ነገር ነው። አዳምና ሔዋን ሆን ብለው ኃጢአት መሥራታቸውን አስታውሱ። አምላክን ላለመታዘዝ መረጡ። እኛ ግን የተወለድነው በኃጢአት ውስጥ ነው። ምንም ምርጫ የለንም። ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ ኃጢአት ከመሥራት ሙሉ በሙሉ ልንቆጠብ አንችልም። (1 ዮሐንስ 1:​8) አንዳንድ ጊዜ እንደሚከተለው ብሎ እንደጻፈው እንደ ጳውሎስ ይሰማን ይሆናል:- “መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ!”​—⁠ሮሜ 7:​21-24

15 ሆኖም በቤዛው ምክንያት ተስፋ ሊኖረን ችሏል! አምላክ በገባው ቃል መሠረት ‘የምድር አሕዛብ ሁሉ ራሳቸውን የሚባርኩበት’ ዘር ኢየሱስ ነው። (ዘፍጥረት 22:​18፤ ሮሜ 8:​20) የኢየሱስ መሥዋዕት በእሱ ለሚያምኑ ሰዎች አስደናቂ የሆኑ አጋጣሚዎችን ከፍቶላቸዋል። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

ከክርስቶስ ቤዛ ጥቅም ማግኘት

16. ኃጢአተኞች ብንሆንም በኢየሱስ ቤዛ አማካኝነት በአሁኑ ጊዜ ምን ጥቅሞች ልናገኝ እንችላለን?

16 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና” ሲል ተናግሯል። (ያዕቆብ 3:​2) ይሁን እንጂ በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ስህተቶቻችን ይቅር ሊባሉልን ይችላሉ። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው።” (1 ዮሐንስ 2:​1, 2) እርግጥ ነው፣ ኃጢአትን አቃልለን መመልከት የለብንም። (ይሁዳ 4፤ ከ1 ቆሮንቶስ 9:​27 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ስህተት ከሠራን ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ መሆኑን በመተማመን ልባችንን ልናፈስስለት እንችላለን። (መዝሙር 86:​5፤ 130:​3, 4፤ ኢሳይያስ 1:​18፤ 55:​7፤ ሥራ 3:​19) በዚህ መንገድ ቤዛው በንጹህ ሕሊና አምላክን ለማገልገልና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በጸሎት ወደ እርሱ ለመቅረብ ያስችለናል።​—⁠ዮሐንስ 14:​13, 14፤ ዕብራውያን 9:​14

17. ቤዛው ወደፊት ምን በረከቶች እንዲገኙ መንገድ ጠርጓል?

17 ታዛዥ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ አምላክ ያለውን ዓላማ ከግቡ እንዲደርስ የክርስቶስ ቤዛ መንገድ ይከፍታል። (መዝሙር 37:​29) ጳውሎስ “እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፣ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ [በክርስቶስ] ደግሞ ነው” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 1:​20) በእርግጥም ሞት ‘ነግሦአል።’ (ሮሜ 5:​17) አምላክ ይህን ‘የመጨረሻ ጠላት’ ለማስወገድ ቤዛው መሠረት ይሆነዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:​26፤ ራእይ 21:​4) የኢየሱስ ቤዛ የሞቱትን እንኳ ሳይቀር ሊጠቅም ይችላል። ኢየሱስ ‘በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት እንደሚመጣ’ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​20-22

18. ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ምን አሳዛኝ የሆነ ነገር አስከትሏል? ይህስ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚስተካከለው እንዴት ይሆናል?

18 ዛሬ ከተጫኑን ጭንቀቶች ሁሉ ተገላግለን ሕይወትን መጀመሪያ ታቅዶ በነበረው ሁኔታ ማጣጣም ስንችል ምን ያህል እንደምንደሰት እስቲ አስቡት! ኃጢአት ከአምላክ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳችን አእምሮ፣ ልብና አካል ጋር ስምምነት እንዳይኖረን አድርጓል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ “ታምሜአለሁ” የሚል እንደማይኖር ያረጋግጥልናል። አዎን፣ አካላዊና ስሜታዊ ሕመሞች የሰውን ልጅ መቅሰፋቸውን ያቆማሉ። ለምን? ኢሳይያስ “በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል” በማለት ይመልሳል።​—⁠ኢሳይያስ 33:​24

ቤዛው የፍቅር መግለጫ ነው

19. በግለሰብ ደረጃ ለክርስቶስ ቤዛ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው?

19 ይሖዋ የሚወደውን ልጁን እንዲልክ ያነሳሳው ፍቅር ነው። (ሮሜ 5:​8፤ 1 ዮሐንስ 4:​9) ኢየሱስም ‘ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን እንዲቀምስ’ የገፋፋው ፍቅር ነው። (ዕብራውያን 2:​9፤ ዮሐንስ 15:​13) ጳውሎስ “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ . . . በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ” ሲል የጻፈው አለምክንያት አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 5:​14, 15) ኢየሱስ ላደረገልን ነገር አድናቆት ካለን አዎንታዊ ምላሽ እንሰጣለን። ደግሞም ከሞት እጅ ማምለጥ የሚያስችለን ቤዛው ነው! የኢየሱስን መሥዋዕት ዋጋ እንደ ርካሽ ነገር አድርገን እንደምንመለከተው በተግባራችን ለማሳየት እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው።​—⁠ዕብራውያን 10:​29

20. የኢየሱስን ‘ቃል’ ልንጠብቅ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

20 ለቤዛው ልባዊ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከመያዙ ጥቂት ቀደም ብሎ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 14:​23) የኢየሱስ ‘ቃል’ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን ተልእኮ ከዳር ለማድረስ በቅንዓት መካፈልን ያካትታል። (ማቴዎስ 28:​19) በተጨማሪም ለኢየሱስ ታዛዥ መሆን ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ፍቅር ማሳየትን ይጠይቃል።​—⁠ዮሐንስ 13:​34, 35

21. ሚያዝያ 1 በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ መገኘት ያለብን ለምንድን ነው?

21 ለቤዛው ያለንን አድናቆት የምናሳይበት አንድ ጥሩ መንገድ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ መገኘት ሲሆን በዚህ ዓመት በዓሉ ሚያዝያ 1 ላይ ይከበራል።a ኢየሱስ በዓሉን ባቋቋመ ጊዜ ተከታዮቹን “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት አዝዟቸው ስለነበር ይህም ትእዛዝ በኢየሱስ ‘ቃል’ ውስጥ የሚካተት ነው። (ሉቃስ 22:​19) በዚህ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ክንውን ላይ በመገኘትና ክርስቶስ ያዘዘውን ሁሉ በጥሞና በመከተል የኢየሱስ ቤዛ የአምላክ የሕይወት መንገድ መሆኑን ከልብ እንደምናምን እናሳያለን። በእርግጥም “መዳንም በሌላ በማንም የለም።”​—⁠ሥራ 4:​12

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒሳን 14 ቀን 33 እዘአ ክርስቶስ የሞተበት ዕለት በዚህ ዓመት የሚውለው ሚያዝያ 1 ቀን ላይ ነው። የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበትን ጊዜና ቦታ በአካባቢህ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጠይቀህ ተረዳ።

[ልታስታውስ ትችላለህ?]

◻ ሰዎች ለኃጢአተኝነታቸው ማካካሻ መስጠት የማይችሉት ለምንድን ነው?

◻ ኢየሱስ “ተመጣጣኝ ቤዛ” የሆነው በምን መንገድ ነው?

◻ ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ይዞ የመቀጠል መብቱን ለእኛ ጥቅም ያዋለው እንዴት ነው?

◻ በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ለሰው ልጆች ምን በረከቶች ተዘርግተውላቸዋል?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፍትሕን ሚዛን እንዲስተካከል የሚያደርገው ከአዳም ጋር የሚመጣጠን ፍጹም ሕይወት ያለው ሰው ብቻ ነው

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ይዞ የመቀጠል መብት ስለነበረው ሞቱ መሥዋዕታዊ ዋጋ አለው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ