የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 4/1 ገጽ 23-27
  • ገነትን ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ገነትን ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወደ ግብርና መመለስ
  • እንደገና በአምላክ ማመን ጀመርኩ
  • የጸሎቴ መልስ
  • በጭንቀት ጊዜ የሚገኝ እርዳታ
  • የተሻለ ነገር ለማከናወን መጣጣር
  • ቤቴል​—⁠አስደሳች የሆነ መንፈሳዊ ገነት
  • ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • መማሬን አቁሜ አላውቅም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ይምጡና ይጎብኙ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 4/1 ገጽ 23-27

ገነትን ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ

ፓስካል ስቲዚ እንደተናገረው

ሌሊቱ ተጋምሷል፤ በደቡብ ፈረንሳይ የምትገኘው የቤዚዬ መንደር መንገዶችም ጭር ብለዋል። እኔና ጓደኛዬ ገና አዲስ ቀለም በተቀባ በአንድ የሃይማኖታዊ መጻሕፍት መደብር ግድግዳ ላይ ‘አማልክት ሞተዋል። ኃያል ሰው ለዘላለም ይኑር!’ የሚሉትን የጀርመኑን ፈላስፋ የኒትሽን ቃላት በጥቁር ቀለም በትላልቅ ፊደላት ጻፍን። ይሁንና ወደዚህ ሁሉ የመራኝ ምን ነበር?

በ1951 በፈረንሳይ ውስጥ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ከሆነ የኢጣሊያ ዝርያ ካለው ቤተሰብ ተወለድኩ። ትንሽ ልጅ እያለሁ ለእረፍት ወደ ደቡብ ኢጣሊያ እንሄድ ነበር። በዚያም እያንዳንዱ መንደር የራሱ የሆነ የድንግል ማርያም ምስል ነበረው። ከወንድ አያቴ ጋር በመሆን እነዚህን ልብስ የለበሱ ግዙፍ ሐውልቶች ተሸክሞ በተራራዎች ሥር የሚያልፈውን ማለቂያ የሌለው ሰልፍ ተከትዬ እሄድ ነበር። ይሁንና ይህን አደርግ የነበረው ምንም ሳላምንበት ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የጨረስኩት በአንድ የኢየሱሳውያን ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ ያለኝን እምነት የሚገነባ ነገር ሲነገር የሰማሁበት ጊዜ ትዝ አይለኝም።

ስለ ሕይወት ዓላማ ማሰላሰል የጀመርኩት ሕክምና ለማጥናት ሞንፔሊዬ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በገባሁበት ጊዜ ነበር። አባቴ በጦርነቱ ወቅት ቆስሎ ስለነበር ሐኪሞች ዘወትር ከአልጋው አጠገብ አይለዩም ነበር። ሰዎች በጦርነት የደረሰባቸውን ጉዳት ለመጠገን ብዙ ጊዜና ጉልበት ከማጥፋት ይልቅ ጦርነትን ማስቀረት አይሻልም ነበር? ይሁን እንጂ በቪየትናም የተጧጧፈ ጦርነት በመካሄድ ላይ ነበር። በእኔ አመለካከት ለምሳሌ የሳንባ ካንሰርን ለማከም የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ የበሽታው ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ትምባሆን ማጥፋት ነበር። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በተመጣጠነ ምግብ እጦት፣ ሀብታም በሆኑ አገሮች ደግሞ ከመጠን በላይ በመመገብ ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችስ? በሽታዎቹ የሚያስከትሉትን አሳዛኝ መዘዝ ለመፈወስ ከመሞከር ይልቅ መንስኤያቸውን ማስወገድ አይቀልም ነበር? በምድር ላይ መከራ የበዛው ለምንድን ነው? ይህ ራሱን በራሱ ለማጥፋት ቆርጦ የተነሣ ማኅበረሰብ አንድ የሆነ ከባድ ችግር እንዳለበት ይሰማኝ ነበር፤ ለዚህም ተጠያቂ የማደርገው መንግሥታትን ነበር።

አንድ አናርኪስት የጻፈው በጣም የምወደው አንድ መጽሐፍ ነበር፤ ከዚህ መጽሐፍ የተለያዩ አባባሎችን እየወሰድኩ በግድግዳዎች ላይ እጽፍ ነበር። ቀስ በቀስ እኔ ራሴ አምላክ ወይም ጌታ የሚባል ነገር የማልፈልግ እምነትም ሆነ ግብረ ገብነት የሌለኝ አናርኪስት ሆንኩ። በእኔ አመለካከት አምላክ ወይም ሃይማኖት የሚባለው ነገር ሀብታምና አምባገነን የሆኑ ሰዎች የተቀረውን የሰው ዘር ለመግዛትና ለመበዝበዝ ሲሉ የፈጠሯቸው ነገሮች ነበሩ። ‘በዚህ በምድር ላይ ለእኛ ጠንክራችሁ ከሠራችሁ በሰማይ ባለችው ገነት ውስጥ ትልቅ ሽልማት ታገኛላችሁ’ እንደሚሉ አድርጌ አስብ ነበር። ይሁን እንጂ አማልክት የሚገዙበት ጊዜ አክትሟል። ሰዎች ይህን ማወቅ አለባቸው። ይህን ለሰዎች ማሳወቅ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ደግሞ የተለያዩ መፈክሮችን በግድግዳዎች ላይ በመጻፍ ነበር።

በዚህ ምክንያት ለትምህርቴ ሁለተኛ ቦታ ሰጠሁት። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጂኦግራፊና ሥነ ምህዳር ለማጥናት ሁከት በነገሠበት በአንድ ሌላ የሞንፔሊዬ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገባሁ። ስለ ሥነ ምህዳር ብዙ ባጠናሁ ቁጥር ውቧ ፕላኔታችን ምን ያህል እየተበላሸች እንደሆነ ይበልጥ ስገነዘብ በጣም አዘንኩ።

በየዓመቱ በበጋ የእረፍት ጊዜ ሰዎች በመኪና እንዲወስዱኝ እየለመንኩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በመሸፈን አውሮፓን እዞር ነበር። ከብዙ ሹፌሮች ጋር ካደረግሁት ጉዞና ውይይት ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ እያሰቃዩ ያሉትን መጥፎና ብልሹ ነገሮች በዓይኔ በብረቱ ለመመልከት ችያለሁ። አንድ ጊዜ ገነትን ለማግኘት ፍለጋ ላይ እያለሁ በውቧ የክሬት ደሴት ላይ ወደሚገኙት ዕጹብ ድንቅ የባሕር ዳርቻዎች ደረስኩ። ይሁንና የባሕር ዳርቻዎቹ በነዳጅ ዘይት ተሸፍነው ሳገኛቸው እጅግ አዘንኩ። በአንድ በሆነ የምድር ጥግ ላይ የሚገኝ ገነት ይኖር ይሆን?

ወደ ግብርና መመለስ

በፈረንሳይ የሚገኙ የሥነ ምህዳር አጥኚዎች ለኅብረተሰቡ ችግሮች መፍትሔው ወደ ግብርና መመለስ ነው ብለው ይከራከሩ ነበር። እኔም በእጆቼ ለመሥራት ፈልጌ ነበር። ስለዚህ በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኙት የሴቬን ተራራዎች ሥር ባለች አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ አንድ ያረጀ የድንጋይ ቤት ገዛሁ። በበሩ ላይ የአሜሪካውያን ሂፒዎች መፈክር የሆነውን “ዘመናዊ ገነት” የሚሉትን ቃላት ጻፍኩ። በአካባቢያችን ታልፍ የነበረች አንዲት ጀርመናዊት ሴት ጓደኛዬ ሆነች። መንግሥት በወከለው የማዘጋጃ ቤት ሹም ፊት ቀርቦ ሕጋዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት መፈጸም በእኔ ዘንድ የማይታሰብ ነገር ነበር። በቤተ ክርስቲያን መጋባትስ? እሱንማ ጨርሶ አታንሱት!

በአብዛኛው የምንሄደው በባዶ እግራችን ሲሆን ረዥም ፀጉርና ድብልብል ያለ ጢም ነበረኝ። ፍራፍሬና አታክልት ማብቀል ያስደስተኝ ነበር። በበጋ ሰማዩ ጥርት ያለ ሲሆን ትናንሽ ነፍሳት ሲጮኹ ይሰማል። መሬቱን የሸፈኑት አበቦች ጣፋጭ መዓዛ ያላቸው ሲሆኑ እናበቅላቸው የነበሩት የሜዲትራንያን ፍሬዎች ማለትም ወይንና በለስ ብዙ ውኃ ያላቸው ነበሩ! ለእኛ የምትስማማ ገነት ያገኘን ይመስል ነበር።

እንደገና በአምላክ ማመን ጀመርኩ

ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ጊዜ ሴሉላር ባዮሎጂ፣ ስነ ፅንስና አናቶሚ አጥንቼ የነበረ ሲሆን ውስብስብነታቸውና ስምም የሆነው የአሠራር ሂደታቸው በጣም ነካኝ። በየቀኑ ተፈጥሮን በቅርበት ለመመልከትና በዚያም ላይ ለማሰላሰል መቻሌ የተፈጥሮ ውበትና ያላት ከፍተኛ አቅም በአድናቆት እንድሞላ አድርጎኛል። የተፈጥሮ መጽሐፍ በየዕለቱ ገጽ በገጽ በፊቴ እንደሚገለጥ ያህል ነበር። አንድ ቀን በኮረብታዎች ላይ ረዥም የእግር ጉዞ ካደረግሁና ስለ ሕይወት በጥልቅ ካሰላሰልኩ በኋላ አንድ ፈጣሪ መኖር አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። በልቤ በአምላክ ማመን አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ከዚህ ቀደም በውስጤ የባዶነትና የብቸኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ልክ በአምላክ ማመን በጀመርኩበት ቀን ለራሴ እንዲህ አልኩ:- ‘ፓስካል፣ ከአሁን በኋላ በፍጹም ብቸኛ አትሆንም።’ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነበር።

ብዙም ሳይቆይ እኔና ጓደኛዬ አማንዲን የምትባል ትንሽ ሴት ልጅ ወለድን። ልጃችንን እንደ ዓይኔ ብሌን ነበር የምመለከታት። አሁን በአምላክ ማመን ስለጀመርኩ የማውቃቸውን ጥቂት የሥነ ምግባር ሕጎች አከብር ጀመር። መስረቅና መዋሸት አቆምኩ፤ ይህም በአካባቢዬ ከነበሩ ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረኝ እንደረዳኝ ወዲያው ተገነዘብኩ። አዎን፣ የራሳችን የሆኑ ችግሮች ነበሩን፤ የእኔም ገነት ሙሉ በሙሉ እንደ ተመኘሁት ሊሆን አልቻለም። በአካባቢው የሚገኙ የወይን ገበሬዎች የሚጠቀሙባቸው የተባይና የአረም ማጥፊያ መድኃኒቶች የእኔንም ሰብል አበላሹት። ስለ ክፋት ምንጭ የነበረኝ ጥያቄ አሁንም መልስ አላገኘም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ስለ ቤተሰብ ሕይወት ብዙ ባነብም ከጓደኛዬ ጋር ከመነታረክ እንድቆጠብ ሊያደርገኝ አልቻለም። ጥቂት ጓደኞች ቢኖሩንም እነሱም ቢሆኑ እውነተኛ ጓደኞች አልነበሩም፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም ጓደኛዬ በእኔ ላይ እንድትወሰልት ሊያደርጉ ሞክረው ነበር። ከዚህ የተሻለ ገነት መኖር ነበረበት።

የጸሎቴ መልስ

አምላክ ሕይወቴን እንዲመራልኝ ትክክል ነው ብዬ በማስበው መንገድ ደጋግሜ ወደ እሱ እጸልይ ነበር። አንድ እሁድ ጧት ኢሬን ሎፔስ የምትባል ወዳጃዊ የሆነ ስሜት ያላት ሴት ከትንሽ ወንድ ልጅዋ ጋር ወደ ቤታችን መጣች። የይሖዋ ምሥክር ነች። የምትናገረውን አዳመጥኳትና ሌላ ጊዜ መጥተው እንዲያነጋግሩኝ ያቀረበችልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። ሁለት ወንዶች ሊያነጋግሩኝ መጡ። ካደረግነው ውይይት ገነትና የአምላክ መንግሥት የሚሉትን ሁለት ነገሮች በአእምሮዬ ያዝኩ። እነዚህን ሐሳቦች በሚገባ በልቤ ውስጥ አስቀመጥኳቸው። ወራት እያለፉ በሄዱ ቁጥር ደግሞ ንጹሕ ሕሊናና እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ከፈለግሁ አንድ ቀን ከአምላክ የአቋም መስፈርቶች ጋር ራሴን ማስማማት እንደሚኖርብኝ ተገነዘብሁ።

ሕይወታችንን በአምላክ ቃል ከተገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ለማስማማት ስንል ጓደኛዬ መጀመሪያ ላይ ልታገባኝ ተስማምታ ነበር። ሆኖም በአምላክና በሕጎቹ ከሚያሾፉ መጥፎ ሰዎች ጋር ገጠመች። በአንድ የጸደይ ምሽት ወደ ቤት ስመለስ አንድ አስደንጋጭ ነገር ጠበቀኝ። ቤታችን ባዶ ነበር። ጓደኛዬ የሦስት ዓመት ልጃችንን ይዛ ቤቱን ጥላ ጠፋች። ተመልሰው ይመጣሉ በሚል ተስፋ ለብዙ ቀናት ብጠብቅም የውኃ ሽታ ሆነው ቀሩ። አምላክን ከመውቀስ ይልቅ እንዲረዳኝ ወደ እሱ ጸለይኩ።

ከዚያም ወዲያው በተከልኩት የበለስ ዛፍ ስር ቁጭ ብዬ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩ። እንዲያውም ቃሎቹን እንደ ውኃ ጥጥት አደረግኳቸው ማለት ይቻላል። ከዚህ ቀደም በሳይኮአናሊስቶችና በሥነ ልቡና ጠበብቶች የተጻፉ በጣም ብዙ ዓይነት መጽሐፎችን ባነብም ይህን የመሰለ ጥበብ ያዘለ መጽሐፍ ግን አጋጥሞኝ አያውቅም። ይህ መጽሐፍ በመለኮታዊ ኃይል የተጻፈ መሆን አለበት። የኢየሱስ ትምህርቶችና እሱ ስለ ሰው ተፈጥሮ የነበረው ማስተዋል እጅግ አስገረመኝ። መዝሙራት ያጽናኑኝ የነበረ ሲሆን በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ተግባራዊ ጥበብ ደግሞ ያስደንቀኝ ነበር። ተፈጥሮን ማጥናት አንድ ሰው ይበልጥ ወደ አምላክ እንዲጠጋ በመርዳት ረገድ በጣም ጥሩ ቢሆንም ሊያሳውቀው የሚችለው ‘የመንገዱን ዳርቻ ብቻ’ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም።​—⁠ኢዮብ 26:​14

የይሖዋ ምሥክሮቹ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት እና የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች አድርገው የተባሉትን መጻሕፍት ጭምር ትተውልኝ ሄደው ነበር።a እነዚህን መጻሕፍት ማንበቤ ዓይኖቼ እንዲገለጡ አድርጓል። የእውነት መጽሐፍ መጠነ ሰፊ የሆነ ብክለት፣ ጦርነት፣ እየጨመረ የሚሄድ ዓመፅና በኑክሌር የመጥፋት ስጋት በሰው ልጅ ላይ የተጋረጠው ለምን እንደሆነ እንዳስተውል ረድቶኛል። ከአትክልት ቦታዬ ሆኜ አየው የነበረው ቀይ ሰማይ የሚቀጥለው ቀን ጥሩ አየር እንደሚኖረው እንደሚያሳውቅ ሁሉ እነዚህም ክንውኖች የአምላክ መንግሥት መምጫ መቅረቡን የሚያረጋግጡ ናቸው። የቤተሰብ ኑሮ የተባለውን መጽሐፍ ባየሁ ቁጥር ጓደኛዬ ትዝ ትለኝ ነበር፤ መጽሐፉን ላሳያትና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ደስተኞች መሆን እንደምንችል ልነግራት እመኝ ነበር። ሆኖም ይህ የማይቻል ነገር ነበር።

መንፈሳዊ እድገት ማድረግ

የበለጠ ለማወቅ ስለፈለግሁ ሮቤር የሚባል የይሖዋ ምሥክር እንዲረዳኝ ጠየቅሁት። መጠመቅ እንደምፈልግ ስነግረው በጣም ተገረመ፤ ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረልኝ። ስለምማረው ነገር ለሌሎች መናገርና በመንግሥት አዳራሹ የማገኛቸውን ጽሑፎች ማሰራጨት የጀመርኩት ወዲያውኑ ነበር።

ራሴን ለማስተዳደር ስል የግንበኝነት ሥራ ሥልጠና ወሰድኩ። የአምላክ ቃል ለአንድ ሰው ሕይወት ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን ስለተገነዘብኩ አብረውኝ ለሚማሩ ተማሪዎችና ለአስተማሪዎቼ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመስከር የሚያስችለኝን እያንዳንዱን አጋጣሚ እጠቀም ነበር። አንድ ቀን ምሽት በአንድ መተላለፊያ ላይ ከሰርዥ ጋር ተገናኘን። ጥቂት መጽሔቶችን በእጆቹ ይዞ ነበር። “ማንበብ የምትወድ ይመስለኛል” አልኩት። “አዎን፣ ግን እነዚህ ሰልችተውኛል።” “ጥሩ ይዘት ያለው ጽሑፍ ለማንበብ በእርግጥ ትፈልጋለህ?” ብዬ ጠየቅሁት። ስለ አምላክ መንግሥት ጥሩ ውይይት ካደረግን በኋላ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወሰደ። በቀጣዩ ሳምንት አብሮኝ ወደ መንግሥት አዳራሹ መጣ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት።

አንድ ቀን፣ ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ መስበክ እችል እንደሆነ ሮቤርን ጠየቅሁት። ወደ ቁም ሳጥኑ ሄደና ሙሉ ልብስ አውጥቶ ሰጠኝ። በሚቀጥለው እሁድ ከእሱ ጋር በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገልግሎት ሄድኩ። በመጨረሻም መጋቢት 7, 1981 ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን በመጠመቅ ይፋ አደረግሁ።

በጭንቀት ጊዜ የሚገኝ እርዳታ

ይህ በእንዲህ እንዳለ አማንዲንና እናቷ በውጪ አገር እንደሚኖሩ ሰማሁ። የሚያሳዝነው ነገር እናቷ የምትኖርበትን አገር ሕግ በመጠቀም ሴት ልጄን እንዳላይ በሕግ ከለከለችኝ። ይህ ለእኔ አስደንጋጭ ነገር ነበር። የአማንዲን እናት ሌላ ሰው ስታገባና ባሏ ያለ እኔ ስምምነት ሴት ልጄን በጉዲፈቻነት መቀበሉን የሚገልጽ ሕጋዊ ደብዳቤ ሲደርሰኝ ከምንጊዜውም ይበልጥ ተስፋዬ ሁሉ ጨለመ። ከአሁን በኋላ በልጄ ላይ ምንም መብት የለኝም። ሕጋዊ ሙከራ ባደርግም ልጄን የማየት መብት ለማግኘት አልቻልኩም። ከባድ ሸክም የተሸከምኩ ያህል ከፍተኛ ስቃይ ይሰማኝ ነበር።

ይሁን እንጂ የይሖዋ ቃል በብዙ መንገዶች ድጋፍ ሰጥቶኛል። አንድ ቀን በከፍተኛ ኃዘን ተውጬ እያለሁ በምሳሌ 24:​10 ላይ የሚገኙትን “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው” የሚሉትን ቃላት ደጋግሜ አነበብኩ። ይህ ጥቅስ ተስፋ ቆርጬ እንዳልወድቅ ረድቶኛል። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ልጄን ለማየት ያደረግሁት ሙከራ ሳይሳካልኝ ሲቀር የመጻሕፍት ቦርሳዬን ብድግ አድርጌ ወደ አገልግሎት ወጣሁ። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት “በሄዱ ጊዜ፣ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ” የሚሉትን በመዝሙር 126:​6 ላይ የሚገኙትን ቃላት እውነትነት ለመገንዘብ ችያለሁ። አንድ የተማርኩት ጠቃሚ ትምህርት ቢኖር ከባድ ችግሮች ሲገጥሟችሁ እነሱን ለመፍታት የምትችሉትን ሁሉ አድርጋችሁ ሳይሳካ ሲቀር እነሱን ወደ ኋላ ትታችሁ በይሖዋ አገልግሎት በቆራጥነት ወደፊት መግፋት እንደሚኖርባችሁ ነው። ደስታችሁን ጠብቃችሁ ለመኖር የምትችሉበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው።

የተሻለ ነገር ለማከናወን መጣጣር

ውድ ወላጆቼ ያደረግሁትን ለውጥ በመመልከት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እንድቀጥል ሊረዱኝ ፈቃደኞች መሆናቸውን ገለጹልኝ። ወላጆቼን አመሰገንኳቸው፤ ሆኖም አሁን ሌላ ግብ አውጥቻለሁ። እውነት ከሰብዓዊ ፍልስፍና፣ ከልብ ወለድ ታሪክና ከኮከብ ቆጠራ ነፃ አውጥቶኛል። አሁን እርስ በርስ በጦርነት የማይገዳደሉ እውነተኛ ጓደኞች አሉኝ። እንዲሁም በምድር ላይ መከራ የበዛው ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄዬ መልስ አግኝቻለሁ። ለዚህ አመስጋኝነቴን ለማሳየት ስል በሙሉ ኃይሌ አምላክን ለማገልገል ፈለግሁ። ኢየሱስ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎቱ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን እኔም የእሱን ምሳሌ ለመከተል ፈለግሁ።

የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን በ1983 የግንባታ ሥራዬን አቆምኩ። በአንድ መናፈሻ ውስጥ ራሴን የማስተዳድርበት የግማሽ ቀን ሥራ በማግኘቴ ጸሎቴ ተመለሰልኝ። በግንባታ ሥራ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ውስጥ አግኝቼው ከመሰከርኩለት ወጣት ማለትም ከሰርዥ ጋር በአቅኚዎች ትምህርት ቤት መካፈላችን እንዴት የሚያስደስት ነበር! የዘወትር አቅኚ ሆኜ ለሦስት ዓመት ካገለገልሁ በኋላ በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ለመሥራት ፍላጎት አደረብኝ። ስለዚህ በ1986 በፓሪስ አቅራቢያ በምትገኘው ውብና ማራኪ በሆነችው የፕሮቨ መንደር ውስጥ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንድሠራ ተመደብኩ። አብዛኛውን ጊዜ ማታ ቤቴ ስገባ ስለ እሱ ለሌሎች በመናገር ስላሳለፍኩት አስደሳች ቀን ይሖዋን ተንበርክኬ አመሰግነዋለሁ። እንዲያውም በሕይወቴ ውስጥ የሚያስደስቱኝ ሁለቱ ትላልቅ ነገሮች አምላክን ማነጋገርና ስለ አምላክ መናገር ናቸው።

በደቡብ ፈረንሳይ በምትገኝ ሴባሳ በምትባለው አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ትኖር የነበረችው የ68 ዓመት ዕድሜ የነበራት እናቴ ስትጠመቅ ማየቴ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አደረገው። እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ስትጀምር የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ኮንትራት ገባሁላት። ነገሮችን የምታመዛዝን ሰው በመሆኗ እውነትን ለማስተዋል ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም።

ቤቴል​—⁠አስደሳች የሆነ መንፈሳዊ ገነት

የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የልዩ አቅኚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ሲወስን በአገልጋዮች የማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል አሊያም በፈረንሳይ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ማለትም በቤቴል ውስጥ ለማገልገል አመለከትሁ። ይሖዋ፣ እሱን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል በምችልበት ቦታ ራሱ እንዲመድበኝ ውሳኔውን ለእሱ ትቼው ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ በታኅሣሥ 1989 በሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ፣ በሉቪዬ በሚገኘው ቤቴል ገብቼ እንዳገለግል ተጠራሁ። ቤቴል የሚገኝበት ቦታ ወላጆቻችን በጠና በታመሙ ጊዜ ይንከባከቧቸው የነበሩትን ወንድሜንና የወንድሜን ሚስት ለማገዝ የሚያስችለኝ ስለነበረ አጋጣሚው በጣም ጥሩ ነበር። በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ በሚስዮናዊነት እያገለገልሁ ቢሆን ኖሮ ይህን ለማድረግ አልችልም ነበር።

እናቴ ብዙ ጊዜ ቤቴል እየመጣች ትጠይቀኝ ነበር። ከእኔ ተለይታ መኖሯ መሥዋዕትነትን የሚጠይቅባት ቢሆንም ብዙ ጊዜ እንዲህ ትለኝ ነበር:- “የእኔ ልጅ፣ በቤቴል ማገልገልህን ቀጥል። በዚህ መንገድ ይሖዋን እያገለገልህ በመሆንህ ደስተኛ ነኝ።” የሚያሳዝነው ነገር ሁለቱም ወላጆቼ በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሉም። ቃል በቃል ወደ ገነትነት በተለወጠች ምድር ላይ እንደገና ላያቸው እናፍቃለሁ!

በዛሬው ጊዜ አንድ ቤት “ዘመናዊ ገነት” የሚለውን መጠሪያ ማግኘት አለበት ከተባለ “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም ካለው ከቤቴል የተሻለ ቦታ የለም። ምክንያቱም እውነተኛው ገነት ከምንም ነገር በላይ መንፈሳዊ ነው፤ ቤቴል ደግሞ መንፈሳዊነት ሰፍኖ የሚገኝበት ቦታ ነው። የመንፈስ ፍሬዎችን ለማፍራት የሚያስችል አጋጣሚ አለን። (ገላትያ 5:​22, 23) በየቀኑ ከሚካሄደው የዕለቱ ጥቅስ ውይይትና በቤተሰብ ከምናደርገው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የምናገኘው የበለጸገ መንፈሳዊ ምግብ በቤቴል አገልግሎት የሚያስፈልገኝን ጥንካሬ እንዳገኝ ይረዳኛል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋን ለአሥርተ ዓመታት ሲያገለግሉ ከኖሩ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሮ መሥራት መቻል ቤቴልን በመንፈሳዊ ለማደግ የሚቻልበት ልዩ ቦታ ያደርገዋል። ከሴት ልጄ ከተለያየሁ 17 ዓመት ቢሆነኝም በቤቴል ውስጥ እንደ ልጆቼ የማያቸው በቅንዓት የተሞሉ ብዙ ወጣቶች ያገኘሁ ሲሆን የሚያደርጉት መንፈሳዊ እድገትም ያስደስተኛል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ሰባት የተለያዩ የሥራ ምድቦች ተቀብያለሁ። እነዚህን የሥራ ለውጦች ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም ለዘለቄታው የሚጠቅመኝ ስልጠና አግኝቼበታለሁ።

በሚያፈራበት ጊዜ መቶ እጥፍ ምርት የሚሰጥ አንድ የባቄላ ዘር እዘራ ነበር። በተመሳሳይም መጥፎ ነገር በምትዘሩበት ጊዜ መቶ ጊዜ የሚብስ መጥፎ ነገር ከአንድ ጊዜ በላይ እንደምታጭዱ ከተሞክሮዬ ተገንዝቤአለሁ። ከራስ ተሞክሮ መማር ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ትምህርት ቤት ነው። በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብቼ ከምማር ይልቅ በይሖዋ መንገዶች ተመርቼ ባድግ እመርጥ ነበር። በክርስቲያን ወላጆች ሥር ያደጉ ልጆች እንዴት ታድለዋል! በይሖዋ አገልግሎት ጥሩ የሆነውን ነገር ዘርቶ መቶ እጥፍ ሰላምና እርካታ ማጨድ የተሻለ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም!​—⁠ገላትያ 6:​7, 8

አቅኚ በነበርኩበት ጊዜ በግድግዳው ላይ የአናርኪስቶች መፈክር በጻፍንበት የመጻሕፍት መደብር አጠገብ አንዳንድ ጊዜ አልፍ ነበር። ወደ ውስጥ ገብቼም ለባለቤቱ ሕያው ስለሆነው አምላክና ስለ ዓላማው አነጋግሬዋለሁ። አዎን፣ አምላክ ሕያው ነው! ከዚህም በላይ እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆነው ይሖዋ ልጆቹን በፍጹም የማይተው የታመነ አባት ነው። (ራእይ 15:​4) ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ብዙ ሰዎች ሕያው የሆነውን አምላክ ይሖዋን በማገልገልና በማወደስ በአሁኑ ጊዜ ያለውን መንፈሳዊ ገነትና ወደፊት ተመልሶ የሚቋቋመውን ገነት እንዲያገኙ ምኞቴ ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አስደናቂ በሆኑ ተፈጥሯዊ ነገሮች በጥልቅ በመነካት በአምላክ ለማመን በልቤ ወሰንኩ። (በስተቀኝ) ዛሬ በቤቴል አገልግሎት ላይ እያለሁ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ