ይሖዋ የሚፈልግብን ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ነውን?
“እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:8
1. አንዳንዶች ይሖዋን የማያገለግሉት ለምን ሊሆን ይችላል?
ይሖዋ ከሕዝቡ የሚፈልገው ነገር አለ። ይሁን እንጂ ከሚክያስ ትንቢት የተወሰዱትን ከላይ ያሉትን ቃላት ካነበብክ በኋላ አምላክ የሚፈልግብን ብቃቶች ምክንያታዊ መሆናቸውን ትገነዘብ ይሆናል። ያም ሆኖ ብዙ ሰዎች ታላቁ ፈጣሪያችንን የማያገለግሉት ሲሆን በአንድ ወቅት ያገለግሉት የነበሩት አንዳንዶችም እንዲህ ማድረጋቸውን አቁመዋል። ለምን? ምክንያቱም አምላክ ከአቅማችን በላይ እንደሚፈልግብን ስለተሰማቸው ነው። በእርግጥ አምላክ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ይጠብቅብናልን? ወይስ አንድ ሰው ይሖዋ የሚፈልግበትን ብቃት በተመለከተ የተዛባ አመለካከት ይኖረው ይሆን? አንድ ታሪካዊ ዘገባ ይህን ጉዳይ ለማስተዋል ይረዳል።
2. ንዕማን ማን ነበር? የይሖዋ ነቢይስ ምን እንዲያደርግ ጠየቀው?
2 የሶሪያው ሠራዊት አለቃ ንዕማን በሥጋ ደዌ በሽታ ተይዞ ነበር፤ ይሁንና በእስራኤል የሚገኝ አንድ የይሖዋ ነቢይ ሊፈውሰው እንደሚችል ተነገረው። ስለዚህ ንዕማንና አገልጋዮቹ ወደ እስራኤል ተጉዘው የአምላክ ነቢይ ወደሆነው ወደ ኤልሳዕ ቤት መጡ። ኤልሳዕ ሊጎበኘው የመጣውን ያንን ታዋቂ ሰው ከቤቱ ወጥቶ ከመቀበል ይልቅ አገልጋዩን ልኮ እንዲህ አለው:- “በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፣ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ።”—2 ነገሥት 5:10
3. ንዕማን ይሖዋ የሚፈልግበትን ለማድረግ መጀመሪያ ላይ እምቢተኛ የሆነው ለምን ነበር?
3 ንዕማን የአምላክ ነቢይ የነገረውን የሚያደርግ ከሆነ ከዚህ አስቀያሚ በሽታ ሊፈወስ ይችላል። ታዲያ አምላክ እንዲያደርግ የፈለገው ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር ነበርን? በእርግጥ አልነበረም። ይሁንና ንዕማን፣ ይሖዋ የሚፈልግበትን ነገር ለማድረግ እምቢተኛ ሆነ። በጣም ተበሳጭቶ “የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን?” በማለት ተቆጥቶ ሄደ።—2 ነገሥት 5:12
4, 5. (ሀ) ንዕማን ታዛዥነቱ ያስገኘለት ጥቅም ምን ነበር? ከዚያ በኋላስ ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምንን እንመረምራለን?
4 በእርግጥ የንዕማን ችግር ምን ነበር? እንዲያደርግ የተጠየቀው ነገር በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ አልነበረም። የንዕማን አገልጋዮች በዘዴ እንዲህ አሉ:- “ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ:- ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ!” (2 ነገሥት 5:13) ችግሩ የንዕማን አመለካከት ነበር። ተገቢው አክብሮት እንዳልተሰጠው እንዲሁም የማይጠቅምና ክብሩን የሚቀንስ ነው ብሎ የገመተውን ነገር እንዲያደርግ እንደተጠየቀ ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ ንዕማን አገልጋዮቹ በዘዴ የሰጡትን ምክር ተቀበለና በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ። ‘ሥጋው እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ሲመለስና ንጹሕ’ ሲሆን ምን ያህል እንደፈነደቀ ልትገምት ትችላለህ! ልቡ በአመስጋኝነት ተሞልቶ ነበር። ከዚህም በላይ ንዕማን ከእንግዲህ ወዲህ ከይሖዋ በቀር ሌላ አምላክ እንደማያመልክ ተናገረ።—2 ነገሥት 5:14-17
5 በሰው ዘር ታሪክ በሙሉ ይሖዋ የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት ሰዎች እንዲጠብቋቸው ያደርግ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። በምትመረምርበት ጊዜ ይሖዋ ይህን የመሰለውን ነገር እንድታደርግ ቢጠይቅህ ኖሮ ምን ምላሽ ትሰጥ እንደነበር ራስህን ጠይቅ። ወደ ኋላ ላይ ደግሞ በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ እንመረምራለን።
ይሖዋ ከሰዎች የጠየቃቸው ነገሮች ምን ነበሩ?
6. የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ምን እንዲያደርጉ ታዝዘው ነበር? አንተ ብትሆን ኖሮ እንዲህ ላለው መመሪያ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር?
6 ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት አዳምንና ሔዋንን ልጆች እንዲወልዱ፣ ምድርን እንዲያለሙና እንስሳትን እንዲገዙ አዝዟቸው ነበር። በተጨማሪም ባልና ሚስቱ መናፈሻ መሰል ሰፊ መኖሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:9-15) ሆኖም አንድ ገደብ ተጥሎባቸው ነበር። በኤደን የአትክልት ሥፍራ ከሚገኙት ፍሬ የሚሰጡ በርካታ ዛፎች መካከል ከአንደኛው መብላት አልነበረባቸውም። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይህ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ መጠየቁ አልነበረም፤ ነበር እንዴ? ፍጹም በሆነ ጤንነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ቢኖርህ ኖሮ ይህን የመሰለውን የሥራ ኃላፊነት በደስታ ትቀበለው አልነበረምን? በአትክልት ስፍራው ውስጥ አሳሳች ቢመጣ እንኳ የሚያቀርበውን የመከራከሪያ ነጥብ ውድቅ ታደርግበት አልነበረምን? እንዲሁም ይሖዋ ይህን አንድ ቀላል መመሪያ የማውጣት መብት ያለው በመሆኑ ትስማማ አልነበረምን?—ዘፍጥረት 3:1-5
7. (ሀ) ኖኅ ምን ሥራ ተሰጥቶት ነበር? ምንስ ተቃውሞ አጋጠመው? (ለ) ይሖዋ ኖኅን ስላዘዘው ነገር ምን ይሰማሃል?
7 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ከሆነ የጥፋት ውኃ ለመትረፍ የሚያስችል መርከብ እንዲሠራ ኖኅን አዝዞት ነበር። ከመርከቡ ግዝፈት አንጻር ስንመለከተው ሥራው ቀላል አልነበረም፤ ደግሞም ሥራው የሚከናወነው ምናልባትም ብዙ ዘባቾችና ተቃዋሚዎች ባሉበት ነው። ይሁንና ኖኅ ቤተሰቡን ከማዳንም አልፎ ብዙ እንስሳትን ለማዳን መቻሉ እንዴት ያለ መብት ነበር! (ዘፍጥረት 6:1-8, 14-16፤ ዕብራውያን 11:7፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) ይህን የመሰለው ሥራ ቢሰጥህ ኖሮ ሥራውን ከዳር ለማድረስ ጠንክረህ ትሠራ ነበርን? ወይስ ይሖዋ እንዳደርግ የሚፈልገው ከአቅሜ በላይ የሆነ ነገር ነው ብለህ ትደመድም ነበር?
8. አብርሃም ምን እንዲያደርግ ታዝዞ ነበር? የተባለውን ነገር መፈጸሙስ የምን ነገር ምሳሌ ነው?
8 አምላክ እንደሚከተለው በማለት አብርሃምን አንድ ከባድ ነገር እንዲያደርግ አዝዞት ነበር:- “የምትወድደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው።” (ዘፍጥረት 22:2) ይሖዋ በወቅቱ ልጅ ያልነበረው ይስሐቅ ዘር እንደሚተካ ለአብርሃም ተስፋ ሰጥቶት ስለነበር አምላክ ይስሐቅን ወደ ሕይወት መልሶ ለማምጣት ባለው ችሎታ ላይ የነበረው የአብርሃም እምነት ተፈትኖ ነበር። አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ሲል አምላክ ጣልቃ በመግባት የወጣቱን ሕይወት ታደገ። ይህ ሁኔታ አምላክ ልጁን ለሰው ልጆች እንደሚሠዋና ከጊዜ በኋላ ከሞት እንደሚያስነሳው የሚያሳይ ምሳሌ ነበር።—ዘፍጥረት 17:19፤ 22:9-18፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሥራ 2:23, 24, 29-32፤ ዕብራውያን 11:17-19
9. ይሖዋ አብርሃምን ያዘዘው ነገር ከአቅሙ በላይ ያልነበረው ለምንድን ነው?
9 አንዳንዶች ይሖዋ አምላክ አብርሃምን ያዘዘው ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። ግን ነበርን? ሙታንን ማስነሳት የሚችለው ፈጣሪያችን ሌላው ቀርቶ ለጥቂት ጊዜ በሞት ማንቀላፋት የሚያስከትልብን እንኳ ቢሆን እሱን እንድንታዘዘው መፈለጉ በእርግጥ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ የጥንት ተከታዮቹ እንደዚያ ብለው አላሰቡም። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሲሉ ሥቃይ ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመሞት እንኳ ሳይቀር ፈቃደኞች ነበሩ። (ዮሐንስ 10:11, 17, 18፤ ሥራ 5:40-42፤ 21:13) አንተስ እንዲህ ዓይነት እምነት የሚጠይቅ ሁኔታ ቢገጥምህ ለመቀበል ፈቃደኛ ነህን? ይሖዋ ሕዝቡ ለመሆን የተስማሙ ሰዎች እንዲያሟሉ የጠበቀባቸውን አንዳንድ ነገሮች ቀጥሎ ተመልከት።
ይሖዋ ለእስራኤል የሰጠው ሕግ
10. ይሖዋ ያዘዘውን በሙሉ ለመፈጸም ቃል የገቡት እነማን ነበሩ? እሱስ ምን ሰጣቸው?
10 በአብርሃም ልጅ በይስሐቅና በልጅ ልጁ በያዕቆብ አማካኝነት የተገኙት ዘሮች በዝተው የእስራኤልን ብሔር አስገኙ። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ አወጣቸው። (ዘፍጥረት 32:28፤ 46:1-3፤ 2 ሳሙኤል 7:23, 24) ከዚያም ወዲያው አምላክ የሚፈልግባቸውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ቃል ገቡ። “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” አሉ። (ዘጸአት 19:8) እስራኤላውያን በእሱ ለመገዛት ያላቸውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይሖዋ ለብሔሩ አሥሩን ትእዛዛት ጨምሮ 600 ሕጎችን ሰጠ። በሙሴ መካከለኛነት የተሰጡ እነዚህ የአምላክ ሕግጋት ከጊዜ በኋላ ሕጉ በመባል መጠራት ጀመሩ።—ዕዝራ 7:6፤ ሉቃስ 10:25-27፤ ዮሐንስ 1:17
11. አንደኛው የሕጉ ዓላማ ምን ነበር? ይህን ለማከናወን የረዱ አንዳንድ ደንቦችስ የትኞቹ ናቸው?
11 አንደኛው የሕጉ ዓላማ የጾታ ሥነ ምግባርን፣ የንግድ ልውውጥንና የልጅ አስተዳደግን የመሳሰሉ ጉዳዮችን በሚመለከቱ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ደንቦች አማካኝነት የእስራኤላውያንን ደህንነት መጠበቅ ነበር። (ዘጸአት 20:14፤ ዘሌዋውያን 18:6-18, 22-24፤ 19:35, 36፤ ዘዳግም 6:6-9) ሌሎች ሰዎችንና እንስሳትን በተገቢው መንገድ ስለ መያዝ የተሰጡ ደንቦችም ነበሩ። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ዘዳግም 22:4, 10) ዓመታዊ በዓላትንና ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብን የሚመለከቱ መመሪያዎች የሕዝቡን መንፈሳዊነት ለመጠበቅ ረድተዋል።—ዘሌዋውያን 23:1-43፤ ዘዳግም 31:10-13
12. የሕጉ ዋነኛ ዓላማ ምን ነበር?
12 የሕጉን ዋነኛ ዓላማ አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ተስፋው የተሰጠው ዘር [ክርስቶስ] እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ።” (ገላትያ 3:19) ሕጉ እስራኤላውያን ፍጹም አለመሆናቸውን ያስታውሳቸው ነበር። ስለሆነም ኃጢአታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድላቸው ፍጹም መሥዋዕት ያስፈልጋቸው ነበር። (ዕብራውያን 10:1-4) ስለዚህ ሕጉ መሲሕ ወይም ክርስቶስ የነበረውን ኢየሱስን እንዲቀበሉ ሕዝቡን ለማዘጋጀት ታስቦ የተሰጠ ነበር። ጳውሎስ “እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል” ሲል ጽፏል።—ገላትያ 3:24
የይሖዋ ሕግ ሸክም ነበርን?
13. (ሀ) ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሕጉን እንዴት አድርገው ተመልክተውታል? ለምንስ? (ለ) ሕጉ በእርግጥ ሸክም ነበርን?
13 ምንም እንኳ ሕጉ ‘ቅዱስ፣ ጻድቅና በጎ’ ቢሆንም ብዙዎች እንደ ሸክም አድርገው ይመለከቱት ነበር። (ሮሜ 7:12) ሕጉ ፍጹም ስለነበረ እስራኤላውያን ከፍተኛ የአቋም ደረጃውን ሊያሟሉ አልቻሉም። (መዝሙር 19:7) ለዚህም ነው ሐዋርያው ጴጥሮስ “አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው [ያልቻልነው] ቀንበር” ብሎ የጠራው። (ሥራ 15:10) እርግጥ ሕጉ በራሱ ሸክም አልነበረም፤ እሱን መታዘዝም ለሕዝቡ ጥቅም አምጥቷል።
14. ሕጉ እስራኤላውያንን በእጅጉ ለሚጠቅም ዓላማ ማገልገሉን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
14 ለምሳሌ ያህል ሕጉ አንድ ሌባ እንዲታሰር ሳይሆን የሰረቀውን እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ እንዲከፍል ሲል እንዲሠራ ያዝዝ ነበር። ይህ አሠራር በተሰረቀው ሰው ላይ ምንም ዓይነት ኪሳራ እንዳይደርስ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የእስር ቤት አገልግሎት የሚጠይቀውን ሸክም ያስቀራል። (ዘጸአት 22:1, 3, 4, 7) ለጤና አስጊ የሆኑ ምግቦች የተከለከሉ ነበሩ። የአሣማ ሥጋ በደንብ ካልበሰለ ትራይክኖሰስ የሚባል በሽታ የሚያስይዝ ሲሆን የጥንቸል ሥጋ ደግሞ ቱለርሚያ የሚባል በሽታ ሊያስተላልፍ ይችላል። (ዘሌዋውያን 11:4-12) በተመሳሳይም ሕጉ በድን መንካትን በመከልከል ጥበቃ ያደርግ ነበር። በድን የነካ ሰው ሰውነቱን መታጠብና ልብሱን ማጠብ ይጠበቅበት ነበር። (ዘሌዋውያን 11:31-36፤ ዘኁልቁ 19:11-22) ዓይነ ምድር መቀበር የነበረበት ሲሆን ይህም በጀርሞች ስርጭት ከሚመጣው ጉዳት ሕዝቡን ይጠብቅ ነበር። ይሁንና ሳይንቲስቶች የእነዚህን ጀርሞች መኖር ያወቁት ከቅርብ ምዕተ ዓመታት ወዲህ ነው።—ዘዳግም 23:13
15. ለእስራኤላውያን ሸክም የሆነባቸው ነገር ምን ነበር?
15 ሕጉ ከሕዝቡ አቅም በላይ የሆነ ነገር የሚጠይቅ አልነበረም። ሕጉን ይተረጉሙ ስለነበሩ ሰዎች ግን እንዲህ ብሎ ለመናገር አይቻልም። እነዚህ ሰዎች ያወጧቸውን ደንቦች በሚመለከት በጄምስ ሃስቲንግስ የተዘጋጀው ኤ ዲክሺነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ እርስ በርሳቸው በተቆላለፉ ጥቃቅን መመሪያዎች የታጠረ ነበር። . . . በመሆኑም እያንዳንዱን ጉዳይ በሕጉ ሥር ለማካተትና የሰዎችን አኗኗር በአጠቃላይ ርኅራሄ የለሽ በሆነ የአስተሳሰብ ሥርዓት ለመምራት ጥረት ተደርጎ ነበር። . . . የሕሊና ድምፅ ታፍኖ ነበር፤ መለኮታዊው ቃል ያለው ሕያው ኃይል ተዳክሞና ባዕድ በሆኑ ደንቦች ተዳፍኖ ነበር።”
16. ኢየሱስ ሃይማኖታዊ መሪዎቹ ስላወጧቸው ሸክም የሆኑ ደንቦችና ወጎች ምን ብሎ ነበር?
16 ኢየሱስ ክርስቶስ በርካታ ደንቦችን በሰዎች ላይ የሚጭኑ የሃይማኖት መሪዎችን እንዲህ በማለት አውግዟል:- “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።” (ማቴዎስ 23:2, 4) የተንዛዛ የመንጻት ሥርዓትን ጨምሮ እንደ ሸክም በሚከብዱ ሰው ሠራሽ ደንቦቻቸውና ወጎቻቸው አማካኝነት ‘የአምላክን ቃል አቃልለው’ ነበር። (ማርቆስ 7:1-13፤ ማቴዎስ 23:13, 24-26) ይሁንና ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት እንኳ በእስራኤል የሚገኙ ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች ይሖዋ ከሕዝቡ የሚፈልገውን ነገር አዛብተው ያቀርቡ ነበር።
ይሖዋ በእርግጥ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው?
17. ይሖዋ እምነት የለሽ በሆኑት እስራኤላውያን በሚቀርቡት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ያልተደሰተው ለምን ነበር?
17 ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ ብሎ ነበር:- “የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።” (ኢሳይያስ 1:10, 11) አምላክ እንዲቀርቡለት ሲል ራሱ በሕጉ ላይ እንዲሰፍሩ ባደረጋቸው መሥዋዕቶች ያልተደሰተው ለምን ነበር? (ዘሌዋውያን 1:1–4:35) ምክንያቱም ሕዝቡ መሥዋዕቱን ስላቃለለው ነበር። ስለዚህ እንዲህ ተብለው በጥብቅ ተመክረው ነበር:- “ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፣ መልካም መሥራትን ተማሩ፣ ፍርድን ፈልጉ፣ የተገፋውን አድኑ፣ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።” (ኢሳይያስ 1:16, 17) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ስለሚፈልገው ነገር ግንዛቤ እንድናገኝ ይህ አይረዳንምን?
18. ይሖዋ በእርግጥ ከእስራኤላውያን የሚፈልገው ነገር ምን ነበር?
18 አምላክ በእርግጥ ምን እንደሚፈልግ ኢየሱስ ገልጿል። ይህን ያደረገበት አንደኛው አጋጣሚ “ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ተብሎ በተጠየቀበት ወቅት ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰ:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም:- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” (ማቴዎስ 22:36-40፤ ዘሌዋውያን 19:18፤ ዘዳግም 6:4-6) ነቢዩ ሙሴ እንደሚከተለው ብሎ በጠየቀ ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ ነጥብ ጠቅሷል:- “አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ፣ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፣ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፣ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ፣ መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?”—ዘዳግም 10:12, 13፤ 15:7, 8
19. እስራኤላውያን ቅዱስ ሆነው ለመታየት የሞከሩት እንዴት ነበር? ሆኖም ይሖዋ ምን አላቸው?
19 እስራኤላውያን መጥፎ ነገር ቢሠሩም ቅዱስ መስለው ለመታየት ፈልገው ነበር። ሕጉ ጾምን የሚያዝዘው በዓመታዊው የሥርየት ቀን ላይ ብቻ ቢሆንም እነሱ ግን አዘውትረው መጾም ጀመሩ። (ዘሌዋውያን 16:30, 31) ሆኖም ይሖዋ እንዲህ ሲል ገሠጻቸው:- “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፣ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፣ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቆተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፣ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?”—ኢሳይያስ 58:3-7
20. ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ግብዞቹን የነቀፋቸው ለምን ነበር?
20 እነዚህ ተመጻዳቂ እስራኤላውያን ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ ከተናገራቸው ሃይማኖታዊ ግብዞች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ችግር ነበረባቸው:- “ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፣ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።” (ማቴዎስ 23:23፤ ዘሌዋውያን 27:30) የኢየሱስ ቃላት ይሖዋ በእርግጥ ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር ግንዛቤ እንድናገኝ አይረዱንምን?
21. ነቢዩ ሚክያስ ይሖዋ እንድናደርገው የሚፈልገውንና የማይፈልገውን ነገር ጠቅለል አድርጎ የገለጸው ምን በማለት ነበር?
21 ይሖዋ እንድናደርገው የሚፈልገውንና የማይፈልገውን ነገር ግልጽ ለማድረግ ሲል የአምላክ ነቢይ የነበረው ሚክያስ እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኩር ልጄን ስለ በደሌ፣ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን? ሰው ሆይ፣ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:6-8
22. ይሖዋ በተለይ በሕጉ ሥር ከነበሩት ሰዎች የሚፈልገው ነገር ምን ነበር?
22 ስለዚህ ይሖዋ በሕጉ ሥር ከነበሩ ሰዎች በተለይ የሚፈልገው ነገር ምን ነበር? እርግጥ ይሖዋ አምላክን መውደድ ነበረባቸው። ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፣ እርሱም:- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው” ብሏል። (ገላትያ 5:14) በተመሳሳይም ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች “ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። . . . ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው” ብሏቸዋል።—ሮሜ 13:8-10
ከአቅም በላይ አይደለም
23, 24. (ሀ) ይሖዋ የሚፈልግብንን ማድረጉ በፍጹም ከአቅማችን በላይ ሊሆንብን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ቀጥሎ የምንመረምረው ምንን ይሆናል?
23 ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪ፣ አሳቢና ሩኅሩኅ አምላክ መሆኑን በማወቃችን ስሜታችን አልተነካም? አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው የአምላክን ፍቅር በማጉላት ሰዎች በይሖዋ ፊት ውድ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነበር። የአምላክን ፍቅር ለመግለጽ ሲል ኢየሱስ እዚህ ግቡ የማይባሉትን ድንቢጦች ጠቅሶ “ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም” በማለት ተናግሯል። ከዚያም “አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ” ሲል ደምድሟል። (ማቴዎስ 10:29-31) በእርግጥም እንዲህ ያለው አፍቃሪ አምላክ የሚፈልግብንን ማንኛውንም ነገር ማድረግ ከአቅማችን በላይ ሊሆንብን አይገባም!
24 ይሁን እንጂ ዛሬ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶችስ አምላክ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር የሚጠብቅባቸው የሚመስላቸው ለምንድን ነው? እነዚህን ጥያቄዎች መመርመሩ ይሖዋ የሚጠብቅብንን ማንኛውንም ነገር ማድረጉ አስደናቂ መብት የሆነው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል።
ልትመልስ ትችላለህ?
◻ አንዳንዶች ይሖዋን ከማገልገል ወደ ኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?
◻ ባለፉት ዓመታት በሙሉ የይሖዋ መሥፈርቶች የተለያዩ የሆኑት እንዴት ነበር?
◻ ሕጉ የትኞቹን ዓላማዎች ለማሳካት አገልግሏል?
◻ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ከአቅማችን በላይ የማይሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጽሕናን የሚመለከቱ ዝርዝሮችን የመሳሰሉ ሰው ሠራሽ ደንቦች አምልኮን ሸክም እንዲሆን አድርገውታል