የላቀውን የፍቅር መንገድ መማር
ኮሶቮ፣ ሊባኖስና አየርላንድ። እነዚህ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ሲጠቀሱ የምንሰማቸው ስሞች ናቸው። ሰዎች እነዚህን ስሞች ሲሰሙ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው ደም መፋሰስ፣ የቦንብ ድብደባና ግድያ ነው። እርግጥ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በጎሳና በሌሎች ልዩነቶች ሳቢያ የሚቆሰቆሱ አደገኛ የሆኑ ግጭቶች አዲስ ክስተቶች አይደሉም። እንዲያውም የታሪክ ገጾች በእንደዚህ ዓይነት ግጭቶች የተሞሉ ሲሆኑ በሰው ዘር ላይ ይህ ነው የማይባል መከራ አስከትለዋል።
ብዙዎች በታሪክ ዘመናት በሙሉ ጦርነት ጠፍቶ ስለማያውቅ ጦርነት ሊቀር የማይችል ነገር እንደሆነ ሲሰማቸው ሰዎች እርስ በርስ መጠላላታቸው ተፈጥሯዊ ነገር ነው ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው ትምህርት ጋር ሙሉ በሙሉ ይቃረናል። ቅዱሳን ጽሑፎች “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” በማለት በማያሻማ መንገድ ይገልጻሉ። (1 ዮሐንስ 4:8) ፈጣሪ፣ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲፋቀሩ እንደሚፈልግ ግልጽ ነው።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሰው በአምላክ መልክ መፈጠሩን ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ይህም ማለት የሰው ዘር የአምላክን ባሕርያት (የላቀ ባሕርይ የሆነውን ፍቅርን ጭምር) ማንጸባረቅ የሚያስችል ችሎታ ተሰጥቶታል ማለት ነው። ታዲያ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሰዎች በታሪክ ዘመናት በሙሉ እርስ በርሳቸው ተፋቅረው መኖር ያቃታቸው ለምንድን ነው? አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል። ይህ የሆነው የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ በማመጻቸውና ኃጢአት ውስጥ በመውደቃቸው ነው። ከዚህ የተነሳ ዘሮቻቸው በአጠቃላይ ኃጢአትና አለፍጽምና ወረሱ። ሮሜ 3:23 “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ሲል ይገልጻል። አምላክ የሰጠን ሌሎችን የማፍቀር ችሎታ በወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና ጎደፈ። ይህ ማለት ታዲያ ከዚህ በኋላ ሰዎች እርስ በርስ ተፋቅረው መኖር አይችሉም ማለት ነው? ከሰዎች ጋር ሰላማዊ የሆነ ፍቅራዊ ዝምድና የምንመሠርትበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚያሳይ ምን ተስፋ አለ?
አምላክን መውደድ መማር አለብን
ይሖዋ አምላክ ሰዎች ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ፍቅር የማሳየት ችሎታ እንዳላቸው ያውቃል። እርሱን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ በተቻለ መጠን ፍቅር ለማሳየት እንዲጥሩ የሚጠብቅባቸው ለዚህ ነው። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእስራኤላውያን ከተሰጠው ሕግ ሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ ይህን ብቃት በግልጽ ተናግሯል። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት” ብሏል። በማከልም እንዲህ አለ:- ‘ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም:- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕግ ሁሉ ተሰቅሏል።’—ማቴዎስ 22:37-40
ሆኖም ብዙ ሰዎች አይተው የማያውቁትን ግለሰብ መውደድ በጣም እንደሚከብድ ይሰማቸዋል። ይሖዋ አምላክ ደግሞ መንፈስ ስለሆነ እኛ እርሱን ማየት አንችልም። (ዮሐንስ 4:24) ይሁን እንጂ ሕይወታችን አምላክ ለእኛ ሲል በፈጠራቸው ብዙ መልካም ነገሮች ላይ የተመካ በመሆኑ በየቀኑ እርሱ የሚያደርጋቸው ነገሮች ይነኩናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይህን ሐቅ ጠቅሷል:- “[አምላክ] መልካም ሥራ እየሠራ፣ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።”—ሥራ 14:17
ምንም እንኳ ሁሉም ሰው ፈጣሪ ካደረጋቸው ዝግጅቶች በዚያም ሆነ በዚህ መጠቀሙ የማይቀር ቢሆንም ለእርሱ ያላቸውን አድናቆት የሚገልጹት ወይም እርሱን ለማመስገን የሚነሳሱት ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂቶች ናቸው። በመሆኑም አምላክ ለእኛ ያደረገልንን መልካም ነገሮች በሙሉ መለስ ብለን ማየትና በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በሚንጸባረቁት አስደናቂ ባሕርያቱ ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን የታላቁ ፈጣሪያችንን አስደናቂ ጥበብና ኃይል ማስተዋል እንድንችል ሊያደርገን ይገባል። (ኢሳይያስ 45:18) ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕይወትን መስጠት ብቻ ሳይሆን መኖር የሚያስገኘውን ደስታ እንድናገኝም ስላስቻለን እጅግ አፍቃሪ አምላክ መሆኑን እንድንገነዘብ ሊረዳን ይገባል።
ለምሳሌ ያህል አምላክ በምድር ላይ ስለፈጠራቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሚያማምሩ የአበባ ዓይነቶች እስቲ አስብ። እንዲሁም እነዚህን ውበት የተላበሱ ነገሮች በማየት ከፍተኛ ደስታ ማግኘት የሚያስችለንን ተሰጥኦ መስጠቱ ምንኛ ያስደንቃል! በተመሳሳይም አምላክ በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልጉንን ሁሉንም ዓይነት ገንቢ ምግቦች ሰጥቶናል። በተጨማሪም ከመብላት ደስታ ማግኘት እንድንችል በውስጣችን የመቅመስ ችሎታ መፍጠሩ ምንኛ አሳቢ ቢሆን ነው! እነዚህ ነገሮች አምላክ በእርግጥ እንደሚወድደንና ለእኛ የሚበጀውን እንደሚያስብ የሚያሳዩ አሳማኝ ማስረጃዎች አይደሉምን?—መዝሙር 145:16, 17፤ ኢሳይያስ 42:5, 8
ፈጣሪ “በፍጥረት መጽሐፍ” አማካኝነት ራሱን ከማሳወቁም በተጨማሪ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ገልጾልናል። ይህ የሆነበት ምክንያት ይሖዋ አምላክ ከዚህ ቀደም ያደረጋቸው በርካታ ፍቅራዊ ነገሮችና በቅርቡ ደግሞ ለሰው ልጆች ለማምጣት ቃል የገባቸው ልዩ ልዩ በረከቶች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው ስለሚገኙ ነው። (ዘፍጥረት 22:17, 18፤ ዘጸአት 3:17፤ መዝሙር 72:6-16፤ ራእይ 21:4, 5) ከሁሉ ይበልጥ ከኃጢአትና ከሞት እስራት ነፃ መሆን እንድንችል አንድያ ልጁን አዳኝ አድርጎ መስጠቱ አምላክ ለሰው ልጆች ላለው ፍቅር ከሁሉ የላቀው መግለጫ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። (ሮሜ 5:8) በእርግጥም አፍቃሪ ስለሆነው ፈጣሪያችን ብዙ ባወቅን መጠን እርሱን ይበልጥ ከልብ ለመውደድ እንነሳሳለን።
ሰዎችን መውደድ መማር
ኢየሱስ እንደተናገረው አምላክን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችንና ሐሳባችን ከመውደዳችን በተጨማሪ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ አለብን። እንዲያውም የአምላክ ፍቅር ሰዎችን እንድንወድ ግድ ይለናል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ወዳጆች ሆይ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።” ነጥቡን ይበልጥ ሲያጎላም እንዲህ ብሏል:- “ማንም:- እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።”—1 ዮሐንስ 4:11, 20, 21
ዛሬ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው አብዛኞቹ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” በመሆን እኔ ልቅደም የሚል ዝንባሌ በሚያሳዩበት ዓለም ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2) ስለዚህ የላቀውን የፍቅር መንገድ መማር ከፈለግን ሰዎች ባጠቃላይ የሚከተሉትን የራስ ወዳድነት መንገድ ከመከተል ይልቅ አስተሳሰባችንን ለማስተካከልና አፍቃሪ የሆነውን ፈጣሪያችንን ለመምሰል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ሮሜ 12:2፤ ኤፌሶን 5:1) ሌላው ቀርቶ አምላክ ‘ለማያመሰግኑና ለክፉዎች እንኳ ቸር ነው፤’ ‘በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል።’ ሰማያዊ አባታችን እንዲህ ዓይነት ግሩም ምሳሌ ስለተወልን እኛም ለሰዎች ሁሉ ደግነት ለማሳየትና እነርሱን ለመርዳት መጣር አለብን። እንዲህ በማድረግ ‘የአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ልጆች’ መሆናችንን ማስመስከር እንችላለን።—ሉቃስ 6:35፤ ማቴዎስ 5:45
አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ፍቅራዊ ድርጊቶች ሰዎች የእውነተኛው አምላክ አምላኪዎች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ የቤት እመቤት የሆነች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለጎረቤቷ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማካፈል ጥረት ስታደርግ ሴትዬዋ አምርራ ተቃወመቻት። ሆኖም እህት ይህን ዓይነት ምላሽ በማግኘቷ ተስፋ አልቆረጠችም። ከዚህ ይልቅ ለጎረቤቷ ደግነት ማሳየቷንና በአንዳንድ ነገር ድጋፍ ማድረጓን ቀጠለች። አንድ ወቅት ላይ ጎረቤቷ ቤት በምትቀይርበት ጊዜ እህት አገዘቻት። በሌላ ጊዜ ደግሞ ጎረቤቷ ዘመዶቿን ለመቀበል ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ስትሄድ እህት አንዲት ሴት አብራት እንድትሄድ ዝግጅት አደረገች። ከጊዜ በኋላ ጎረቤቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር የተስማማች ሲሆን በመጨረሻም ባለቤቷ ከፍተኛ ስደት ቢያደርስባትም እንኳ ቀናተኛ ክርስቲያን ሆነች። አዎን፣ እነዚያ የፍቅር መግለጫዎች ዘላለማዊ በረከት የሚያስገኝ መሠረት ጥለዋል።
በጉዳዩ ላይ ሐቀኞች ከሆንን አምላክ እኛን የወደደን ብዙ የሚደነቁ ባሕርያት ስላሉን እንዳልሆነ አምነን እንቀበላለን። ከዚህ በተቃራኒ ብዙ ጥፋትና ጉድለት ቢኖርብንም እንኳ ይወደናል። ነገሩ እንዲህ በመሆኑ እኛም በተመሳሳይ ሰዎች ብዙ እንከኖች ቢኖሩባቸውም እነርሱን መውደድ መማር አለብን። የሌሎችን ጉድለት ከመመልከት ይልቅ ያሏቸውን መልካም ባሕርያት ማስተዋልና ማድነቅ እንድንችል ራሳችንን ካሰለጠንን ለእነርሱ ፍቅር ማሳየት በጣም ቀላል ይሆንልናል። ለእነርሱ ያለን ስሜት በመሠረታዊ ሥርዓት ከሚመራው ፍቅር ልቆ ሊሄድና በቅርብ ጓደኛሞች መካከል ያለውን የሞቀ ፍቅርና መዋደድ ሊያካትት ይችላል።
ፍቅራችሁን አሳድጉ
ፍቅርና ጓደኝነት መኮትኮት ይፈልጋሉ፤ ቅንነትና ሐቀኝነት ደግሞ አስፈላጊ ከሆኑት ማዳበሪያዎች መካከል ናቸው። አንዳንዶች ጓደኛቸው እንዲሆን በሚፈልጉት ሰው ዘንድ በጎ ስሜት ለማሳደር ሲሉ ድክመቶቻቸውን ለመደባበቅ ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ሰዎች እውነታውን አውቀው በእንዲህ ዓይነት ማታለያ መጎዳታቸው ስለማይቀር ውጤቱ የከፋ ይሆናል። ስለዚህ ለማሸነፍ የምንጥራቸው ድክመቶች ቢኖሩብንም እንኳ ሌሎች በትክክል የእኛን ማንነት እንዲያውቁ ማድረጉ ሊከብደን አይገባም። እንዲህ ማድረጋችን ከእነርሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ሊረዳን ይችላል።
ለምሳሌ ያህል በሩቅ ምሥራቅ በሚገኝ ጉባኤ ያለች አንዲት በዕድሜ የገፋች የይሖዋ ምሥክር የትምህርት ደረጃዋ በጣም ዝቅተኛ ነበር። ሆኖም ይህን ጉዳይ ሌሎች እንዳያውቁ ለመሸፋፈን አትሞክርም። ለምሳሌ ያህል የአሕዛብ ዘመን ያበቃው በ1914 መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችና ትንቢቶች ላይ ተመሥርታ ለሌሎች ማስረዳት እንደማትችል ሳትሸሽግ ትናገራለች።a ሆኖም ለአገልግሎት ባላት ቅንዓት እንዲሁም ለወንድሞች በምታሳየው ፍቅርና ልግስና ጥሩ ምሳሌ ስለሆነች በጉባኤው ውስጥ እንደ ዕንቁ ትታያለች።
በአንዳንድ ባሕሎች በይፋ ፍቅርን መግለጽ ተቀባይነት የለውም። ሰዎች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ግብረገብነት እንዲኖራቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል። ምንም እንኳ ግብረገብነትና አሳቢነት ማሳየት ምንጊዜም መልካም ቢሆንም ይህ ለሌሎች ያለንን ስሜት ከመግለጽ እንዲገታን ወይም እንዲያግደን መፍቀድ የለብንም። ይሖዋ የተመረጠ ሕዝቡ ለነበረው ለጥንቱ እስራኤል ያለውን ፍቅር ሲገልጽ “በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ” ብሎ መናገር አላሳፈረውም። (ኤርምያስ 31:3) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚኖሩ መሰል አማኞች እንዲህ ብሏቸዋል:- “እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።” (1 ተሰሎንቄ 2:8) ስለዚህ ለሰዎች እውነተኛ ፍቅር ለማዳበር በጣርን መጠን እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር አምቀን ከመያዝ ይልቅ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ መግለጻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይስማማል።
የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል
ሌሎችን ማፍቀርና ፍቅራችንን መግለጽ መማር ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው። የራሳችንን አለፍጽምናም ሆነ ይህ ፍቅር የለሽ ዓለም የሚያሳድርብንን ከባድ ተጽእኖ ለመቋቋም በእኛ በኩል ትጋት ማሳየት ስላለብን ይህን ማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቅብናል። ይሁን እንጂ ይህ የሚያስገኘው የተትረፈረፈ በረከት በእርግጥ ጥረት ሊደረግለት የሚገባ ያደርገዋል።—ማቴዎስ 24:12
በዚህ ከፍጽምና በራቀ ዓለም ውስጥ እንኳ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ከፍተኛ ደስታ፣ ሰላምና እርካታ በማስገኘት ከሰዎች ጋር የተሻለ ዝምድና መመሥረት እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱን ጥረት በማድረግ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አስደናቂ የሆነውን ለዘላለም የመኖር ተስፋ ለማግኘት ብቁ እንደሆንን ማሳየት እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ የላቀውን የፍቅር መንገድ በመማር አሁንም ሆነ ለዘላለም የአፍቃሪው ፈጣሪያችንን ሞገስና በረከት ማግኘት እንችላለን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ከገጽ 132-5 ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የደግነት ድርጊቶች በመፈጸም ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየት ይቻላል
[ምንጭ]
UN PHOTO 186226/M. Grafman