ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱን አሳይቶኛል
ያኒስ አንድሮኒኮስ እንደተናገረው
ዓመቱ 1956 ነበር። ባገባሁ ገና በዘጠኝ ቀኔ በሰሜናዊ ግሪክ በሚገኘው ኮሞቲኒ በሚባል ይግባኝ ሰሚ ችሎት ፊት ቀረብኩ። የአምላክን መንግሥት በመስበኬ ምክንያት ተበይኖብኝ የነበረው የ12 ወር እስር ይነሳልኛል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ይግባኝ ሰሚው ችሎት ያሳለፈብኝ የስድስት ወር እስር የነበረኝን ተስፋ ሁሉ ሙጥጥ ያደረገብኝ ከመሆኑም በላይ ገና ወደፊት ለሚደርስብኝ ተከታታይ የፍርድ ቤት ክስ መቅድም ብቻ ነበር። ሆኖም በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት አልተለየኝም።
ጥቅምት 1, 1931 በተወለድኩበት ወቅት ወላጆቼ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ጎብኝቷት በነበረው በመቄዶንያ ናጱሌ በምትገኘው ካቫላ በምትባል ከተማ ይኖሩ ነበር። አምስት ዓመት ሲሆነኝ እናቴ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። እናቴ ያልተማረች ብትሆንም እንኳ ለአምላክ ልባዊ ፍቅርና ፍርሃት እንዲያድርብኝ የተቻላትን ሁሉ አድርጋለች። አባቴ የግሪክ ኦርቶዶክስ ልማድን ሙጭጭ አድርጎ የያዘ አጥባቂ ሰው ነበር። ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ፍላጎት ያልነበረው ከመሆኑም በላይ እናቴን ይቃወማትና ብዙውን ጊዜም ይደበድባት ነበር።
ከዚህ የተነሳ ያደግሁት በእምነት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ነበር። አባቴም እናቴን እየደበደበ ያሠቃያት የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ትቶን ሄደ። እናቴ ከልጅነታችን ጀምሮ እኔንና ታናሽ እህቴን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ይዛን ትሄድ ነበር። ሆኖም 15 ዓመት ሲሞላኝ የወጣትነት ምኞትና በራስ ፈቃድ የመመራት መንፈስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበረኝን ግንኙነት እንዳቆም አደረገኝ። ሆኖም ታማኟ እናቴ አምርራ እያለቀሰች እኔን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች።
ድህነትና የተከተልኩት መጥፎ አኗኗር ከባድ ህመም ላይ ጣሉኝ። በዚህም የተነሳ ከሦስት ወር ለሚበልጥ ጊዜ የአልጋ ቁራኛ ሆንኩ። እናቴ እውነትን እንድታውቅ የረዳት አንድ ትሁት ወንድም ለአምላክ ልባዊ የሆነ ፍቅር እንዳለኝ ያስተዋለው በዚህ ወቅት ነበር። እርዳታ ባገኝ በመንፈሳዊ ላገግም እንደምችል ተሰማው። ሌሎች ግን “ጆንን እረዳለሁ ብለህ ጊዜህን አታባክን። እርሱ እንደ ሆነ በመንፈሳዊ መልሶ አያንሰራራም” ይሉት ነበር። ሆኖም ይህ ወንድም እኔን ለመርዳት ያሳየው ትዕግሥትና ያልተቆጠበ ጥረት የኋላ ኋላ ፍሬ አስገኘ። በ21 ዓመቴ ነሐሴ 15, 1952 ለይሖዋ አምላክ ራሴን መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።
አዲስ ባለትዳርና እስረኛ
ከሦስት ዓመት በኋላ መንፈሳዊ አስተሳሰብና ግሩም ባሕርያት ከነበሯት ከማርታ ጋር ተዋወቅሁ። ወዲያው ተጫጨን። አንድ ቀን ማርታ “ዛሬ ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ አስቤአለሁ። ከእኔ ጋር ለመምጣት ትፈልጋለህ?” ብላ ስትጠይቀኝ ያልጠበቅሁት ነገር ሆነብኝ። ብዙውን ጊዜ የምሰብከው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስለነበረ እስከዚህ ቀን ድረስ በዚህ የስብከት ዘርፍ ተካፍዬ አላውቅም ነበር። በዚያን ወቅት በግሪክ የነበረው የስብከት ሥራ ታግዶ የነበረ ሲሆን የስብከቱን እንቅስቃሴ የምናከናውነው በድብቅ ነበር። የሚያዙ፣ ፍርድ ቤት የሚቀርቡና ከባድ እስር የሚበየንባቸው በርካታ ወንድሞች ነበሩ። እንዲህም ሆኖ እጮኛዬን እምቢ ልላት አልደፈርኩም!
በመጨረሻ በ1956 ከማርታ ጋር ተጋባን። በዚህ ወቅት ማለትም በተጋባን በዘጠኝ ቀናችን ነበር ኮሞቲኒ የሚገኘው ይግባኝ ሰሚ ችሎት የስድስት ወር እስር የበየነብኝ። ከትንሽ ጊዜያት በፊት የእናቴ ጓደኛ ለነበረችው ለአንዲት ክርስቲያን እህት ያቀረብኩላት አንድ ጥያቄ ልክ በዚህ ወቅት ትዝ አለኝ። “እኔ በእርግጥ የይሖዋ እውነተኛ ምሥክር መሆኔን ማሳየት የምችለው እንዴት ነው? እምነቴን ማረጋገጥ የምችልበት አጋጣሚ አላገኘሁም” ብያት ነበር። ይህች እህት ልትጠይቀኝ ወደ እስር ቤት በመጣች ጊዜ ያንን ጥያቄ አስታወሰችኝና “ይሖዋን ምን ያክል እንደምትወደው አሁን ማሳየት ትችላለህ። እንግዲህ ሥራህ ይኸው ነው” አለችኝ።
የሕግ ጠበቃዬ ገንዘብ ከፍሎ እኔን ከእስር ለማስፈታት ሙከራ እንዳደረገ ስሰማ የተፈረደብኝን የእስር ጊዜዬን ጨርሼ መውጣት እንደምፈልግ ነገርኩት። በእስር ቤት ውስጥ ያሳለፍኩትን ስድስት ወር ጨርሼ ስወጣ አብረውኝ ታስረው የነበሩ ሁለት እስረኞች እውነትን ሲቀበሉ በመመልከቴ የተሰማኝን ደስታ ልትገምቱ ትችላላችሁ! በቀጣዮቹ ዓመታት ለምሥራቹ ስል በተደጋጋሚ ጊዜያት ፍርድ ቤት ቀርቤአለሁ።
ፈጽሞ የማንጸጸትባቸው ምርጫዎች
ከእስር ቤት ከተፈታሁ ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ1959 የጉባኤው አገልጋይ ወይም ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ እያገለገልሁ ሳለሁ ለጉባኤ ሽማግሌዎች በሚሰጥ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ኮርስ ላይ እንድገኝ ግብዣ ቀረበልኝ። ሆኖም በዚያው ወቅት ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ለማሟላት የሚያስችል ገንዘብ የሚያስገኝ በአንድ የመንግሥት ሐኪም ቤት ውስጥ ቋሚ ሠራተኛ ሆኜ እንድሠራ ግብዣ ቀረበልኝ። የትኛውን ልምረጥ? በሐኪም ቤቱ ውስጥ ጊዜያዊ ሠራተኛ ሆኜ ለሦስት ወራት ሠርቻለሁ። የመሥሪያ ቤቱም ዲሬክተር ሥራዬ በጣም አርክቶታል። ሆኖም በትምህርት ቤቱ እንድካፈል ግብዣ በቀረበልኝ ጊዜ ሌላው ቀርቶ ደሞዝ ሳይከፈለኝ እንኳ ፈቃድ እንድወጣ ያቀረብኩትን ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ። ጉዳዩን በጸሎት ካሰብኩበት በኋላ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስቀደምና የቀረበልኝን ሥራ ለመተው ወሰንኩ።—ማቴዎስ 6:33
በዚሁ ጊዜ አካባቢ የአውራጃና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በጉባኤያችን ለማገልገል መጡ። ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስትና ከባለ ሥልጣናት ከፍተኛ ተቃውሞ ይደርስብን ስለነበር ስብሰባዎቻችንን በግል መኖሪያ ቤት ውስጥ በድብቅ ማከናወን ነበረብን። አንደኛውን ስብሰባ አድርገን እንደጨረስን የአውራጃ የበላይ ተመልካቹ ወደ እኔ መጣና የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመጀመር አሳብ ያለኝ እንደሆነና እንዳልሆነ ጠየቀኝ። ከተጠመቅሁ ጊዜ ጀምሮ ምኞቴ ይኸው ስለነበር ያቀረበልኝ ሐሳብ ልቤን ነካው። “በጣም እፈልጋለሁ” ብዬ መለስኩለት። ሆኖም በዚህ ወቅት አንዲት ሴት ልጅ የማሳደግ ተጨማሪ ኃላፊነት ነበረብኝ። ወንድምም “በይሖዋ ታመን። እርሱም ግብህን ለማሳካት ይረዳሃል” አለኝ። በዚህም የተነሳ ያለብኝን የቤተሰብ ኃላፊነት ችላ ሳልል ባለቤቴና እኔ ሁኔታዎቻችንን አስተካከልንና በታኅሣሥ 1960 ልዩ አቅኚ ሆኜ በምሥራቅ መቄዶንያ ማገልገል ጀመርኩ። በዚያን ወቅት በአገሪቱ የምንገኘው ልዩ አቅኚዎች አምስት ብቻ ነበርን።
ለአንድ ዓመት ያህል ልዩ አቅኚ ሆኜ ካገለገልኩ በኋላ በአቴንስ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ግብዣ አቀረበልኝ። ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት የአንድ ወር ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ ወደ ቤት ተመልሼ ለማርታ ተሞክሮ እየነገርኳት ሳለ የአንድ ትልቅ የማንጋኒዝ ማዕድን ማውጫ ኩባንያ ዲሬክተር ወደ ቤታችን መጣና የአንድ ማጣሪያ ክፍል ዲሬክተር እንድሆን ጠየቀኝና አምስት ዓመት የሚቆይ ኮንትራት፣ አንድ ቤትና አንድ መኪና እንደሚሰጠኝ ገለጸልኝ። በሁለት ቀን ውስጥ መልሱን እንዳሳውቀው ነግሮኝ ሄደ። አሁንም ምንም ሳላመነታ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ብዬ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። (ኢሳይያስ 6:8) ባለቤቴም ሙሉ በሙሉ በውሳኔዬ ተስማማች። በይሖዋ ታምነን የተጓዥ የበላይ ተመልካችነትን ሥራ ጀመርን። ይሖዋም በፍቅራዊ ደግነቱ አሳፍሮን አያውቅም።
የተለያዩ እንቅፋቶች እያሉ ማገልገል
የኢኮኖሚ ችግር የነበረብን ቢሆንም ወደፊት ከመግፋት ወደኋላ አላልንም። ይሖዋም የሚያስፈልገንን አላሳጣንም። መጀመሪያ ላይ ጉባኤዎችን እጎበኝ የነበረው በአንዲት ትንሽ ሞተር ብስክሌት ሲሆን እስከ 500 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት እሸፍን ነበር። ብዙ ጊዜ ችግር ያጋጥመኝ የነበረ ሲሆን አንዳንድ አደጋዎችም ደርሰውብኛል። በአንድ የክረምት ወቅት አንድ ጉባኤ ጎብኝቼ ወደ ቤት ስመለስ የሞላ ጅረት ለማቋረጥ ስሞክር የሞተር ብስክሌቱ ሞተር ጠፋና እስከ ጉልበቴ ድረስ በውኃ ራስኩ። ከዚያም የሞተር ብስክሌቱ ጎማ ተነፈሰ። በዚያ አካባቢ ያልፍ የነበረ አንድ ጎማ መንፊያ የያዘ ሰው ረዳኝና በቅርብ ወደምትገኝ አንዲት መንደር ደርሼ ጎማውን አሠራሁ። በመጨረሻም በብርድ ተቆራምጄና ደክሞኝ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት እቤት ደረስኩ።
በሌላ ወቅት ደግሞ ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ እየሄድኩ ሳለሁ ሞተር ብስክሌቱ ተንሸራተተና ጉልበቴ ላይ ወደቀ። በዚህም የተነሳ ሱሪዬ ተቀዶ በደም ራስኩ። ቅያሪ ሱሪ ስላልነበረኝ ቁመቱ ቢረዝምብኝና ወገቡ ቢሰፋኝም ከአንድ ወንድም ሱሪ ተውሼ የዚያን ምሽት ንግግር ለመስጠት ቻልኩ። ያም ሆኖ ግን የትኛውም ዓይነት ችግር ይሖዋንና ወንድሞችን ለማገልገል ያለኝን ምኞት ሊያቀዘቅዝብኝ አልቻለም።
በሌላ ወቅት ባጋጠመኝ አደጋ እግሬ ላይ ስብራት ደረሰብኝ እንዲሁም የፊት ጥርሶቼ ተሰበሩ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ አሜሪካ ትኖር የነበረች እህቴ (ምሥክር አይደለችም) በዚህ ወቅት ልትጠይቀኝ መጣች። መኪና እንድገዛ ረዳችኝ። ይህ ትልቅ ግልግል ነበር በአቴንስ ቅርንጫፍ ቢሮ ያሉ ወንድሞች የደረሰብኝን አደጋ ሲሰሙ አንድ አበረታች ደብዳቤ ላኩልኝ። በደብዳቤው ላይ ከሰፈሩት ማበረታቻዎች መካከል “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” የሚሉት ሮሜ 8:28 ላይ የሚገኙት ቃላት ይገኙበታል። ይህ አባባል በተደጋጋሚ ጊዜያት እውነት ሆኖ አግኝቼዋለሁ!
ያልተጠበቀ አስደሳች አጋጣሚ
በ1963 ከአንድ ልዩ አቅኚ ጋር በምናገለግልበት መንደር የሚኖሩ ሰዎች ጥሩ ምላሽ ሳይሰጡን ቀሩ። የመንገዱን ግራና ቀኝ ይዘን ለየብቻ ለማገልገል ወሰንን። ወደ አንድ ቤት ሄጄ ገና ማንኳኳት ስጀምር አንዲት ሴት ጎትታ ወደ ውስጥ አስገባችኝና በሩን ቀረቀረችው። በጣም ግራ ተጋብቼ የሚሆነውን ነገር መመልከት ጀመርኩ። ከዚያም ብዙም ሳትቆይ ልዩ አቅኚውንም እያቻኮለች ወደ ቤት አስገባችው። ከዚያም “እሽ! ዝም በሉ!” አለችን። ከዚያም ትንሽ እንደቆየን ከውጭ ጫጫታ ሰማን። እኛን የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ። ሰፈሩ ሁሉ ረጭ ሲል ሴትዬዋ እንዲህ አለችን:- “ይህን ሁሉ ያደረግኩት ለእናንተ ስል ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች አንደሆናችሁ ስለማምን አከብራችኋለሁ።” ከልባችን ካመሰገንናትና በርካታ ጽሑፎችን ከሰጠናት በኋላ ወጥተን ሄድን።
ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ግሪክ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሳለሁ አንዲት ሴት ወደ እኔ ቀረብ አለችና “ወንድም፣ ታስታውሰኛለህ? በምኖርበት መንደር ምሥክርነቱን ለመስጠት በመጣህ ጊዜ ከተቃዋሚዎች እጅ ያዳነችህ ያቺ ሴት እኔ ነኝ” አለችኝ። ወደ ጀርመን ተሰድዳ በነበረችበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መተባበር ጀምራ ነበር። በዚህ ጊዜ መላው ቤተሰቧ በእውነት ውስጥ ነበር።
በእርግጥም በእነዚህ ዓመታት ሁሉ በርካታ “የማመስገኛ መልእክት” በማግኘት ተባርከናል። (2 ቆሮንቶስ 3:1) የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት እውቀት እንዲቀስሙ የረዳናቸው በርካታ ሰዎች አሁን ሽማግሌ፣ የጉባኤ አገልጋይና አቅኚ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በ1960ዎቹ አገለግልበት በነበረው ወረዳ የነበሩት ጥቂት ሰዎች አሁን ከ10,000 የሚበልጡ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ሲሆኑ መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ነው! ለዚህ ሁሉ መመስገን የሚኖርበት በራሱ መንገድ የተጠቀመብን ፍቅራዊ ደግነቱ የማያልቀው አምላካችን ነው።
‘በደዌ አልጋ’
ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነን ባገለገልንባቸው ዓመታት ማርታ ሁልጊዜ ደስተኛ ዝንባሌ ያላት አጋር ሆናልኛለች። ይሁን እንጂ በጥቅምት 1976 በጠና ታመመችና በጣም ከባድ ቀዶ ሕክምና ተደረገላት። በመጨረሻም ከወገቧ በታች ሽባ ሆነችና ያለ ጋሪ መንቀሳቀስ የማትችልበት ደረጃ ላይ ደረሰች። ወጪውንና የደረሰብንን የስሜት ሥቃይ መቋቋም የቻልነው እንዴት ነበር? አሁንም በይሖዋ ላይ መታመናችን የእርሱን ፍቅርና ልግስና እንድንቀምስ አድርጎናል። በመቄዶንያ ለማገልገል በምሄድበት ጊዜ ማርታ ሕክምና እየተደረገላት በአቴንስ ከሚኖሩ ወንድሞች ጋር ትቆያለች። ስልክ እየደወለች በሚከተሉት ቃላት ታበረታታኛለች:- “እኔ ደህና ነኝ። አንተ ቀጥል። ሕመሜ ሲሻለኝ በጋሪዬ ላይ ተቀምጬ አብሬህ እሠራለሁ።” ያደረገችውም ልክ ይህንኑ ነበር። በቤቴል የሚኖሩ ወድ ወንድሞቻችን የሚያበረታቱ በርካታ ደብዳቤዎችን ልከውልናል። ማርታ “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል” የሚሉትን የመዝሙር 41:3 ቃላት የያዙ ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ ይደርሷት ነበር።
በ1986 በእነዚህ ሥር የሰደዱ የጤና እክሎች የተነሳ የውዷ ልጃችን ቤተሰብ በሚኖርበት አካባቢ በካቫላ ልዩ አቅኚ ሆኜ ባገለግል የተሻለ እንደሚሆን ተነገረኝ። ባለፈው መጋቢት ውዷ ማርታ እስከ መጨረሻው እንደ ጸናች አረፈች። ከመሞቷ በፊት ወንድሞች ማርታን “እንደ ምን ነሽ” ብለው ሲጠይቋት ሁልጊዜ ትሰጥ የነበረው የተለመደው መልሷ “ከይሖዋ ጋር እስካለሁ ድረስ ደህና ነኝ!” የሚል ነበር። ወደ ስብሰባ ለመሄድ በምንዘጋጅበት ወይም ብዙ ሥራ ወዳለበት አካባቢ ሄደን እንድናገለግል በምንጠየቅበት ጊዜ ማርታ “ጆን፣ እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ለማገልገል እንሂድ” ትለኝ ነበር። መንፈሳዊ ቅንዓቷ ፈጽሞ አልጠፋም ነበር።
ከጥቂት ዓመታት በፊት እኔም ከባድ የጤና እክል መቋቋም አስፈልጎኛል። መጋቢት 1994 ለሕይወቴ አደገኛ የሆነ የልብ ህመም እንዳለብኝ በሕክምና ስለተረጋገጠ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ግዴታ ሆነ። በዚህ በጣም አስጊ በሆነ ወቅትም ቢሆን የይሖዋ ፍቅራዊ እርዳታ እንዳልተለየኝ ይሰማኛል። ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ከሚደረግበት ክፍል እንደወጣሁ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች አልጋዬ አጠገብ ሆኖ የጸለየውን ጸሎትም ሆነ ለእውነት ፍላጎት ካሳዩ ከአራት ሕሙማን ጋር እዛው በተኛሁበት ክፍል ውስጥ የመራሁትን የመታሰቢያ በዓል ፈጽሞ አልረሳቸውም።
ይሖዋ ረዳታችን ሆኖልናል
ጊዜው ይነጉዳል አካላችንም ይደክማል፤ መንፈሳችን ግን በጥናትና በአገልግሎት ይታደሳል። (2 ቆሮንቶስ 4:16) “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ካልሁ እነሆ አሁን 39 ዓመት ሆኖአል። ደስታ የሞላበትና አርኪ ሕይወት ነበር። አዎን፣ አንዳንድ ጊዜ “ችግረኛና ምስኪን” እንደሆንኩ ሆኖ ቢሰማኝም በልበ ሙሉነት “አንተ ረዳቴና መድኃኒቴ ነህ” ብዬ ለመናገር እችላለሁ። (መዝሙር 40:17) በእርግጥም፣ ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱን አሳይቶኛል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከማርታ ጋር በ1956
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካቫላ የሚገኘው ወደብ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከማርታ ጋር በ1997