የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ለአምላክ አገልግሎት መወሰኑ—የይሖዋ በዓል
ከጥንት ጊዜያት ጀምሮ ደስታ የሞላባቸው በዓላት የእውነተኛ አምልኮ ክፍል ሆነው ቆይተዋል። በጥንቷ እስራኤል ይከበሩ የነበሩ አንዳንድ በዓላት ከአንድ ቀን በላይ ይቆዩ የነበረ ሲሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ አምላኪዎችም በበዓሉ ላይ ይገኛሉ። ሰሎሞን የገነባው ቤተ መቅደስ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ሰባት ቀን የፈጀ ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ ለአንድ ሳምንት የቆየ የዳስ በዓል ተከብሯል። ይህ በዓል እስራኤላውያን ይሖዋ እነርሱን ለመንከባከብ የተጠቀመበትን አስደናቂ መንገድ እንዲያስቡ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። “እግዚአብሔርም . . . ስላደረገው ቸርነት ሁሉ በልባቸው ተደስተው ሐሤትም አድርገው ወደ ስፍራቸው ሄዱ።”—1 ነገሥት 8:66
ከግንቦት 17-22, 1999 ዩ ኤስ ኤ፣ ኒው ዮርክ፣ ፓተርሰን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከል በተከናወነው በዓል ላይ የተገኙ ጎብኚዎች ጥንት ይከናወኑ የነበሩ አስደሳች በዓላትን እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል። ዓለም አቀፉን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለማራመድ ታቅደው የተገነቡትን 28 ሕንፃዎች ለአምላክ አገልግሎት ለመወሰን በዚህ ሳምንት አንድ ልዩ እንቅስቃሴ ተደርጓል። በብሩክሊን፣ ዎልኪል እና ፓተርሰን የሚኖሩ 5,400 የሚሆኑት የዋናው መሥሪያ ቤት አባላት በዚያ በማይረሳ ሳምንት መላውን የፓተርሰን ሕንፃ እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ከእነዚህ እንግዶች መካከል የትምህርት ማዕከሉ በተገነባበት ወቅት በሥራ ተካፍለው የነበሩ ከ500 የሚበልጡ ሠራተኞች፣ ከ23 የተለያዩ የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የመጡ ተወካዮችና በአቅራቢያ ከሚገኙ ጉባኤዎች የመጡ ሌሎች ሰዎችን ጨምሮ በጠቅላላው 8,100 የሚሆኑ ጎብኚዎች በቦታው ተገኝተው ነበር።
ለጎብኚዎች ትምህርት ሰጪ የሆኑ የፎቶ ግራፍ መግለጫዎች
የትምህርት ማዕከሉን ለጎብኚዎቹ በሚገባ ለማስተዋወቅ እንዲቻል ልዩ የሆኑ የፎቶ ግራፍ መግለጫዎች፣ ትምህርት ሰጪ የቪዲዮ ፊልሞችና ጎብኚዎችን የሚመሩ ምልክቶች ተዘጋጁ። በዋናው የእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ የሚያሳይ አንድ ምስል የጎብኚዎቹን ትኩረት የሳበው ወዲያው ነበር። የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ጊልያድ የቀድሞ ታሪክ፣ ታሪካዊ ትላልቅ ስብሰባዎች፣ የጉባኤ ስብሰባዎች፣ በየሳምንቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች የሚመሩበት በየሳምንቱ የሚደረገውን ዘመናዊ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ እንዳይገታ የሕግ ክፍሉ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ያደረገውን እንቅስቃሴ ጎላ አድርገው የሚያሳዩ ሌሎች መግለጫዎችም ነበሩ።—ማቴዎስ 28:19, 20
ቀጥሎም 1,700 ሰዎችን ሊያስቀምጡ የሚችሉ ወንበሮች ባሉት በአንድ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ በዚህ ለአምላክ አገልግሎት ለመወሰን በተደረገው በዓል ላይ የተገኙ ጎብኚዎች “በመንፈሴ እንጂ በጉልበት አይደለም!” የሚል ርዕስ ያለው 33 ደቂቃ የሚፈጅ የቪዲዮ ፊልም እንዲመለከቱ ተጋበዙ። ቪዲዮው የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከል እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያሳያል። ይሖዋ ነገሮችን ይመራ እንደነበረና በእርሱም በረከት 15 ዓመት የፈጀው ይህ የግንባታ ሥራ በተሳካ ሁኔታ ወደ ፍጻሜው እንደደረሰ በፊልሙ ላይ የታዩት ቃለ መጠይቆች ግልጽ አድርገው አሳይተዋል። በሺህ የሚቆጠሩ በግንባታው ሥራ በቀጥታ ተካፍለዋል። በ1994 በአንድ ወቅት 350 የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኞች፣ 113 ጊዜያዊ ሠራተኞችና 63 ተመላላሽ ሠራተኞች በጠቅላላው 526 ሠራተኞች በሥራው ላይ ተካፍለዋል። በጣም ብዙዎች ደግሞ የገንዘብ እርዳታ በማድረግ ሥራውን ደግፈዋል። ሆኖም የይሖዋ መንፈስ ባይታከልበት ኖሮ ሁሉም ነገር እንደዚህ ሊሰምር እንደማይችል ሁሉም ያውቃሉ።—ዘካርያስ 4:6
በትምህርት ማዕከሉ ውስጥ የሚከናወነው ሥራ ዋነኛ ዓላማ መለኮታዊውን ትምህርት ማራመድ እንደሆነ ጎብኚዎቹ ሊገነዘቡ ችለዋል። በትምህርት ቤቱ ሕንፃ አንደኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው በጊልያድ ትምህርት ቤት መግቢያ ላይ ያለው የፎቶ ግራፍ መግለጫ ትምህርት ቤቱ ያስገኘውን መንፈሳዊ ብልጥግናና የትምህርት ቤቱን ታሪክ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነበር። የጊልያድ ትምህርት ቤት በ1943 በሳውዝ ላንሲግ፣ ኒው ዮርክ ከተቋቋመበት ከመጀመሪያው ክፍል አንስቶ ከ7,000 የሚበልጡ ተማሪዎችን ለሚስዮናዊ አገልግሎት አሠልጥኗል። በትምህርት ቤቱ ሕንፃ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው የፎቶ ግራፍ መግለጫ ደግሞ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ትምህርት ቤትንና የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ትምህርት ቤት የሚያሳዩ ናቸው። ሁለቱም ትምህርት ቤቶች የሚካሄዱት በዚሁ ፎቅ ላይ ነው። በኅዳር 1995 ሥራውን የጀመረው የቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ከ106 አገሮች ለመጡ 360 የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ መመሪያ ሰጥቷል።
ጎብኚዎቹ ጉብኝታቸውን እየቀጠሉ ሲሄዱ ብዙዎቹን አካባቢዎች የሚጎበኙት በፎቶ ግራፍ መግለጫዎች ብቻ እንዳልሆነ ወዲያው ተገነዘቡ። ወደ ተለያዩ የሥራ ክፍሎች በመሄድ ቢሮዎችንና ሌሎች የሥራ ቦታዎችን በቀጥታ መጎብኘትና በዚያ ስለሚካሄዱ ሥራዎች ጥልቀት ያለው ግንዛቤ ለማግኘት ችለዋል። ጉብኝቱን ልዩ ካደረገው ነገር መካከል አንዱ የድምፅና የምስል ቀረጻ የሚካሄድበት ሕንፃ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለማራመድ እገዛ የሚያደርጉ የተሟሉ መሣሪያዎች በዚህ ሕንፃ ውስጥ ይገኛሉ! ጎብኚዎቹ እውቀት በሚጨምሩ ተከታታይ የፎቶ ግራፍ መግለጫዎችና አጠር አጠር ባሉ የቪዲዮ ፊልሞች አማካኝነት የድምፅ ቀረጻ እንዴት እንደሚከናወንና የቪዲዮ ክሮች እንዴት እንደሚዘጋጁ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል። ለድራማ የሚሆን ቁሳቁሶችና አልባሳት በማዘጋጀት ረገድ ምን ያክል ከፍተኛ ጥናት እንደሚደረግ ትምህርት አግኝተዋል። በአነስተኛ ወጪ እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ሳይቀር ያካተተ የመድረክ ዝግጅት እንዴት እንደሚከናወን ተመልክተዋል። አንድን ትእይንት በመመልከት ላይ የሚገኙ ሰዎች በትዕይንቱ ውስጥ እንዳሉ ሆኖ እንዲሰማቸው ለማድረግ ሙዚቃ የሚጫወተውን ሚና ተመልክተዋል። ከ1990 ጀምሮ ማኅበሩ በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ለሚጠቀሙ ካዘጋጃቸው የቪዲዮ ክሮች በተጨማሪ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦችን የሚያጎሉ አሥር የቪዲዮ ክሮችን በ41 ቋንቋዎች አዘጋጅቶ አውጥቷል።
በጉብኝቱ የተካፈሉ ብዙዎች የፎቶ ግራፍ ሥራ የሚከናወንበትን፣ የሥዕል ክፍሉን፣ የኮምፒዩተር ሥልጠናና ድጋፍ የሚሰጠውን የመረጃ አገልግሎት ክፍሉን፣ 11,242 ጉባኤዎችንና 572 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠረውን የአገልግሎት ክፍሉን እንዲሁም በየዓመቱ 14,000 የሚሆኑ ጥያቄዎችን የሚያስተናግደውን የደብዳቤ ልውውጥ ክፍሉን ጎብኝተዋል። ለአንድ ደብዳቤ መልስ ከመሰጠቱ በፊት በሚደረገው ምርምርና ከባድ ከሆኑ ችግሮች ጋር እየታገሉ እንዳሉ የሚጠቁም ደብዳቤ ለጻፉ ሰዎች በሚሰጠው ልዩ ትኩረት ተደንቀዋል።
እንደ ጉንዳን የሚተሙት ጎብኚዎች የትርጉም አገልግሎትንም ጎብኝተዋል። ማኅበሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያዘጋጅ በነበረባቸው ቋንቋዎች ላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ሌሎች 102 ቋንቋዎች የታከሉ መሆናቸው ሲነገራቸው በጣም ተገረሙ። በዓለም ዙሪያ 80 በመቶ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበሩ የሚያወጣቸውን ጽሑፎች የሚያነቡት በእንግሊዝኛ ሳይሆን በሌሎች ቋንቋዎች ነው። ይህንንም ፍላጎት ለማሟላት ከ1,700 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች በ100 አገሮች በትርጉም ሥራ ይካፈላሉ። በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ ተደርድሮ ይታይ ነበር። ጎብኚዎች በ31 ቋንቋዎች ተተርጉሞ የሚገኘውን የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ መመልከት ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች በ332 ቋንቋዎች እንደሚገኙና አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር ከእነዚህ ቋንቋዎች ውስጥ በ219ኙ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንደሚገኝ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ጎብኚዎቹ የሕግ ክፍሉ በዓለም ዙሪያ ትኩረት የሚሹ በርካታ ሕግ ነክ ጉዳዮችን እንደሚከታተል ለመመልከት ችለዋል። አንድ የይሖዋ ምሥክር የሕግ ጠበቃ ደምን በሚመለከት ፍርድ ቤት ሲሟገት የሚያሳይ የቪዲዮ ፊልም ተመልክተዋል። ለሕዝብ የሚደረገው የምስራቹ ስብከት ሥራ እንዳይታገድ ምን እየተከናወነ እንዳለም ለመገንዘብ ችለዋል። (ፊልጵስዩስ 1:7) በዚህ በያዝነው ዓመት የመጋቢት ወር የፌደራሉ አውራጃ ፍርድ ቤት ስላሳለፈው ውሳኔም ገለጻ ተደርጎላቸዋል። ይኸው የአውራጃ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኒው ጄርሲ ዩ ኤስ ኤ የኦረዴል ማዘጋጃ ቤት ያወጣውን፣ የይሖዋ ምሥክሮች በማኀበረሰቡ ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ ፈቃድና ደረት ላይ የሚለጠፍ ካርድ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ውሳኔውን እንዲያነሳ የሚጠይቅ ነበር።
ጎብኚዎቹ እየተዘዋወሩ የተመለከቱት ይህን ብቻ አይደለም። በኮንክሪት መጋገሪያ ክፍል ውስጥ የሚገኘውን በፎቶ ግራፍ የተደገፈ መግለጫ በደንብ የተመለከቱ ሲሆን የፍሳሽ ውኃ ማጣሪያውን፣ የኃይል ማመንጫ ጣቢያን፣ ከውኃ ውስጥ አስፈላጊ ያልሆኑ ማዕድናት የሚወገዱበትን ዘዴና በርካታ የጥገና ክፍሎችን እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል። በእርግጥም ይህ ፈጽሞ የማይረሳ ወቅት ነበር።
የውሰናው ፕሮግራም መለኮታዊ ትምህርትን አጉልቶ አሳይቷል
ለአምላክ አገልግሎት የመወሰኑ ፕሮግራም የተከናወነው ረቡዕ ግንቦት 19 ከሰዓት በኋላ በ10 ሰዓት ላይ ነበር። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚገኙ ሠራተኞችን፣ በማኅበሩ የተጋበዙ እንግዶችንና በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ የተገናኙ በካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኙ 372 ተሰብሳቢዎችን ጨምሮ በጠቅላላው 6,929 በደስታ የፈነደቁ እንግዶች የፕሮግራሙ ታዳሚዎች ነበሩ።
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ሚልተን ጂ ሄንሼል ከልብ በመነጨ ስሜት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክቱን ሲያስተላልፍ በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል። የአስተዳደር አካል አባልና የሥነ ሥርዓቱ ሊቀ መንበር የነበረው ቲኦዶር ጃራዝ ቀጣዩን ተናጋሪ ዊልያም ሜለንፋንትን ጋበዘ። “የግንባታው ፕሮግራም ጎላ ያሉ ክንውኖች” በሚለው ንግግሩ በመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከል እድገት፣ ንድፍና ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ሦስት ወንድሞች ቃለ ምልልስ አደረገ። ሕንፃው እየተገነባ በነበረባቸው ዓመታት ከ8,700 የሚበልጡ ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኞች በራሳቸው ወጪ በሥራው ላይ መካፈላቸውን በቃለ መጠይቁ ውስጥ ተገልጿል። መለኮታዊ ትምህርት ላስገኘው አንድነትና የለጋስነት መንፈስ ይህ እንዴት ያለ ጥሩ ምሥክር ነው!
ቀጥሎ “ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው መለኮታዊ ትምህርት” በሚል ርዕስ አንድ ሲምፖዚየም ቀረበ። ንግግሩን ያቀረቡት አራት የአስተዳደር አካል አባላት ነበሩ። ጆን ኢ ባር የመለኮታዊ ትምህርት መሠረቱ ክርስቲያኖች ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈሩና በአምላክ እውቀት እያደጉ’ እንዲሄዱ የሚያበረታታው የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገለጸ። (ቆላስይስ 1:10-12) ዳንኤል ሲድሊክ መለኮታዊ ትምህርት የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ አንስቶ እስከ እያንዳንዱ የዓለም አቀፉ የወንድማማች ኅብረት አባል ድረስ በቲኦክራሲያዊ መንገድ ምን ያክል የተደራጀ እንደሆነ አብራራ። (1 ቆሮንቶስ 12:12-27) የሲምፖዚየሙን የመጨረሻ ሁለት ንግግር ያቀረቡት ጌሪ ሎሽ እና ኬሪ ባርበር መለኮታዊ ትምህርት በሁሉም ቦታ ሰዎችን አግኝተው የሚያነጋግሩና ያነጋገሯቸውንም ሰዎች በአምላክ መንገድ መጓዝ ይችሉ ዘንድ መመሪያ እንዲሰጧቸው አገልጋዮችን እንዴት አድርጎ ብቁ እንደሚያደርግ አመለከቱ።—ኢሳይያስ 2:1-4፤ 2 ቆሮንቶስ 3:5
በዚህ የትምህርት ማዕከል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ጋር አድማጮችን ለማስተዋወቅ ከአስተማሪዎችና በተለያዩ ዘርፎች ተሳትፎ ካደረጉ ከሌሎች ሰዎች ጋር ቃለ ምልልስና ውይይት ተደርጓል። የመለኮታዊውን ትምህርት ፕሮግራም በማስፈጸም ረገድ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የሚጫወተው ሚና ግልጽ ሆኖ ተብራርቷል። የጊልያድ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርገው እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በማጥናት፣ በዘመናዊዎቹ የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክና ለሚስዮናዊ አገልግሎት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገለጸ። የቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ደግሞ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትን የሚመለከቱ የተለያዩ መስኮችን የሚዳስሱ ትምህርቶች የሚሰጡበት ትምህርት ቤት ነው። ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የተዘጋጀው ትምህርት ቤት የተጓዥ ወንድሞችን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ የተቋቋመ ሳይሆን በተለይ ጉባኤዎች መጠቀም ይችሉ ዘንድ መንፈሳዊ እርዳታ መስጠት እንዲችሉ ለማስታጠቅ እንደሆነ ተገለጸ።
ይህን ልዩ ዝግጅት ለመደምደም የአስተዳደር አካል አባል የነበረው ሎይድ ባሪ “ከታላቁ ፈጣሪያችን ጋር ተባብሮ መገንባት” በሚል ርዕስ የውሰናውን ንግግር አቀረበ። ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ በፍጥረት ሥራዎቹ እንደሚደሰትና እኛም ከእርሱ ጋር ደስ እንዲለን እንደሚጋብዘን ገለጸ። (ኢሳይያስ 65:18) ‘ሁሉን ያዘጋጀው አምላክ’ እንደመሆኑ መጠን ለዚህ ሁሉ የግንባታ ሥራ ምሥጋና ሊሰጠው የሚገባው ይሖዋ አምላክ ነው። (ዕብራውያን 3:4) ተናጋሪው እነዚህን የመሰሉ ነጥቦች ከገለጸ በኋላ የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከልን ለታላቁ ፈጣሪያችን ለይሖዋ ለመወሰን ልባዊ ጸሎት አቀረበ።a
በጉብኝቱ የተካፈሉ ሁሉ በዚያ ሳምንት የተደረገውን በዓል ፈጽሞ ሊዘነጉት እንደማይችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከልን ለመጎብኘት ለምን ዝግጅት አታደርግም? የምታደርገው ጉብኝት ስለ አፍቃሪው ፈጣሪያችን ይበልጥ ለማወቅና እርሱ ያወጣቸውን የጽድቅ አቋም ደረጃዎች ጠብቀህ ለመኖር በምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ማበረታቻ እንደሚያስገኝልህ እርግጠኞች ነን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ወንድም ባሪ ሐምሌ 2, 1999 ምድራዊ ሕይወቱን በታማኝነት ጨርሷል። ጥቅምት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16ን ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከአፍ እስከ ገደፉ የተሞላው አዳራሽና በተሰብሰቢዎች የተጥለቀለቀው የመመገቢያ ክፍል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጉብኝቱ ለየት ያለ የደስታ ጊዜ ነበር