ይሖዋ ተራ ለሆኑ ሰዎች ያስባል
የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከሌሎች ለየት ያልክ ወይም አንድ ዓይነት የላቀ ችሎታ ያለህ ሰው መሆን ይኖርብሃልን? አሥራ ስድስተኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን “ጌታ ተራ ሰዎችን አብልጦ ይወድዳል፤ ብዙ አድርጎ የፈጠራቸውም ለዚህ ነው” በማለት ተናግረው ነበር። ብዙዎች ለየት ብለው የሚታወቁበት ምንም ነገር የሌላቸው ተራ ሰዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ተራ የሚለው ቃል “ድሃ፣” “ሹመት፣ ማዕረግ የሌለው፣” “ደረጃው ዝቅ ያለ፣” ወይም “መናኛ” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። ምን ዓይነት ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር መዋል ያስደስትሃል? ትዕቢተኛ፣ አትንኩኝ ባይ ወይም ጉረኛ ከሆኑ ሰዎች ይልቅ አፍቃሪና ትሑት ከሆኑ፣ ልካቸውን ከሚያውቁ እንዲሁም ለሌሎች ከልብ የመነጨ አሳቢነት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር መሆን አያስደስትህም?
ዛሬ በዓለም ላይ ቅስም የሚሰብሩ ቃላት መሰንዘርና በሌሎች ላይ ማፌዝ የተለመደ ነገር በመሆኑ አንዳንዶች አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው ለመቀበል ይከብዳቸዋል። የዚህ መጽሔት አንባቢ የሆነ አንድ ሰው “ያደግሁት ፍቅር በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። የቤተሰቤ አባላት ያንኳስሱኝ፣ ያሾፉብኝና ይሳለቁብኝ ነበር። በመሆኑም ገና ከልጅነቴ የከንቱነት ስሜት አደረብኝ። አሁንም ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙኝ ተስፋ እንድቆርጥ የሚያደርገኝ ሥር የሰደደ የስሜት ጠባሳ አለብኝ።” ሆኖም አምላክ ለተራ ሰዎች ያስባል ብለን እንድናምን የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉ።
አምላክ ለተራ ሰዎች ያስባል
ንጉሥ ዳዊት “እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 145:3) ይሁን እንጂ ይሖዋ ታላቅ መሆኑ ፍቅርና ርኅራኄ እንዳያሳየን አያግደውም። (1 ጴጥሮስ 5:7) እንዲያውም መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 34:18
አምላክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደ አካላዊ ውበት፣ ክብር ወይም ሃብት ላሉት በዓለም ዘንድ ከፍ ተደርገው ለሚታዩ ነገሮች አይደለም። ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ለድሆች፣ ወላጆች ለሌሏቸው ልጆች፣ ለመበለቶችና ለመጻተኞች ርኅራኄ እንዳለው ያሳያል። በግብጽ በጭቆና ቀንበር ሥር ለነበሩት እስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ስደተኛውን አትበድለው፣ ግፍም አታድርግበት። መበለቲቱንና ድሀ አደጎቹን አታስጨንቁአቸው። ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸታቸውን ፈጽሞ እሰማለሁ።” (ዘጸአት 22:21-24) በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው በማለት አምላክ ለድሆች እንደሚያስብላቸው ያለውን እምነት ገልጿል:- “የጨካኞችም ቁጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፣ ለድሀው መጠጊያ፣ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ፣ ከውሽንፍር መሸሸጊያ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል።”—ኢሳይያስ 25:4
የአምላክ “የባሕርዩ ምሳሌ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎቱ ወቅት ለተራ ሰዎች ከልብ የመነጨ አሳቢነት በማሳየት ለደቀ መዛሙርቱ ምሳሌ ትቶላቸዋል። (ዕብራውያን 1:3) ሕዝቡ “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” በተመለከተ ጊዜ “አዘነላቸው።”—ማቴዎስ 9:36
ኢየሱስ ሐዋርያቱ እንዲሆኑ የመረጣቸው ሰዎች “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” መባላቸውንም ልብ በል። (ሥራ 4:13 አ.መ.ት) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ተከታዮቹ የአምላክን ቃል ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መናገር ጀመሩ። ሐዋርያው ጳውሎስ ማንኛውም “የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው” ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሊመጣና አማኝ ሊሆን እንደሚችል ጽፎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:24, 25) አምላክ ለአገልግሎቱ የመረጠው ከዓለማዊ መሥፈርቶች አንጻር ተደናቂነት ያተረፉትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ተራ ሰዎችንም ጭምር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “ወንድሞች ሆይ፣ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፣ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፣ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ።”—1 ቆሮንቶስ 1:26-29
ዛሬም ቢሆን አምላክ ስለ እኛ በጥልቅ ያስባል። እርሱ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) አምላክ ለሰው ዘር ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ ልጁ እንዲሞት ወደ ምድር ከላከው እንደማይወደን ወይም ዋጋ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ መካከል ከሁሉ የሚያንሰውን ልክ እንደ ራሱ አድርገው መንከባከባቸው አስፈላጊ መሆኑን ለተከታዮቹ ሲገልጽ “ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 25:40) ዓለም ለእኛ ያለው አመለካከት ምንም ይሁን ምን ለእውነት ፍቅር እስካለን ድረስ በአምላክ ፊት ውድ ነን።
ፍራንሲስኮa የተባለ አንድ በብራዚል የሚኖር አባት የሌለው ልጅ ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና ከመሠረተ በኋላ የተሰማውን እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ይሖዋንና ድርጅቱን ማወቄ የነበረብኝን በራስ ያለመተማመንና የባይተዋርነት ስሜት እንዳሸንፍ ረድቶኛል። ይሖዋ ለእያንዳንዳችን በግል እንደሚያስብልን ተገንዝቤአለሁ።” ለፍራንሲስኮ ይሖዋ በእውን እንዳለ አባት ሆኖለት ነበር።
ይሖዋ ለወጣቶች ያስባል
ይሖዋ በቡድን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም ለወጣቶች ከልብ ያስባል። እርግጥ ነው፣ ወጣቶችም ሆንን በዕድሜ የገፋን ራሳችንን ከልክ በላይ ከፍ አድርገን መመልከት የለብንም። ያም ሆኖ አምላክ ወደፊት ሊጠቀምበት የሚችል ተሰጥኦ ወይም ባሕርይ ይኖረን ይሆናል። ይሖዋ ይህንን ተሰጥኦዋችንን ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል ምን ማስተካከያዎችና ሥልጠናዎች እንደሚያስፈልጉን ያውቃል። በ1 ሳሙኤል ምዕራፍ 16 ላይ ያለውን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ነቢዩ ሳሙኤል የእስራኤል ንጉሥ ለመሆን ከዳዊት የተሻለ ብቃት ያላቸው ዕጩዎች እንዳሉ ተሰምቶት ነበር፤ ይሖዋ ግን የእሴይ የመጨረሻ ልጅ የሆነውን ዳዊትን የመረጠበትን ምክንያት እንዲህ በማለት አስረዳው:- “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና [የዳዊትን ታላቅ ወንድም] ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።”—1 ሳሙኤል 16:7
ዛሬ ያሉ ወጣቶች ይሖዋ ከልብ እንደሚያስብላቸው እምነት ሊያሳድሩ ይችላሉ? አና የተባለችውን ብራዚላዊት ወጣት ሁኔታ ተመልከት። እንደ ብዙዎቹ ወጣቶች ሁሉ እሷም ምግባረ ብልሹነትና የፍትሕ መጓደል እየተስፋፋ መሄዱ ያሳስባት ነበር። በዚህ መሃል አባቷ እሷንና እህቶቿን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይወስዳቸው ጀመር። አና ስለ አምላክ ቃል ለምትማረው ነገር ፍቅር አደረባት። መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ማንበብና ወደ ይሖዋ አምላክ መጸለይ ጀመረች። ቀስ በቀስ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መሠረተች። እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “በቤቴ አቅራቢያ ወደሚገኝ ኮረብታማ ቦታ በብስክሌት ሄጄ ፀሐይ ስትጠልቅ መመልከት ያስደስተኛል። ይሖዋ ላሳየን ደግነትና ልግስና በጸሎት አመሰግነዋለሁ፤ እንዲሁም ለእርሱ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር እገልጽለታለሁ። ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ማወቄ የአእምሮ ሰላምና የመረጋጋት መንፈስ እንዲኖረኝ አድርጓል።” አንተስ ይሖዋ ስላሳየን ፍቅራዊ አሳቢነት የምታሰላስልበት ጊዜ ማመቻቸት ትችላለህ?
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳንመሠርት አስተዳደጋችን እንቅፋት ሊሆንብን እንደሚችል አይካድም። የሊዲያን ሁኔታ ተመልከት። በጣም የሚያሳስባትን ጉዳይ ለአባቷ ስትነግረው “ይኼ እኮ ተራ ነገር ነው” በማለት ያጣጥልባት ነበር። አባቷ እንዲህ የሚያደርገው ችግሩን እንድትረሳው በማሰብ እንደሆነ ይገባታል። ሊዲያ እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናቴ የምፈልገውን ሁሉና ከዚያም በላይ ለማግኘት ችያለሁ። ይሖዋ ማራኪ ባሕርያት ያሉት መሆኑ ከማንም አብልጬ እንድቀርበው አድርጎኛል። አሁን ስሜቴንና ውስጣዊ ጭንቀቴን ግልጥልጥ አድርጌ ልነግረው የምችለውና ችግሬን የሚረዳልኝ አፍቃሪ አባት አግኝቻለሁ። ጆሮውን ሰጥቶ እንደሚያዳምጠኝ ቅንጣት ታህል ሳልጠራጠር የጽንፈ ዓለሙን የበላይ አካል ለሰዓታት ማነጋገር እችላለሁ።” እንደ ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ እንድትመለከት ረድተዋታል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”
የሚያስፈልጉህን ነገሮች ለማግኘት እርዳታ መጠየቅ
ይሖዋ ለዓለም አቀፉ ጉባኤና በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ለአገልጋዮቹ አሳቢነቱን ያሳያል። እኛም ከእርሱ ጋር የምንነጋገርበት ጊዜ በመመደብ ለሰማያዊው አባታችን ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና ፈጽሞ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ዳዊት ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና ከፍ ያለ ቦታ ይሰጥ ስለነበር እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።”—መዝሙር 25:4, 5
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና የመመሥረቱ ጉዳይ ከዚህ በፊት ሰምተኸው የማታውቀው ሊሆንብህ ይችላል። ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥምህ የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ አካል ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ እርዳታ እንደሚያደርግልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (1 ዮሐንስ 5:14, 15) ስለዚህ ያለህበትን ሁኔታና የሚያስፈልጉህን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት በምታቀርበው ጸሎት ላይ ጉዳዩን በቀጥታ ጥቀስ።
ጸሎት ስናቀርብ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለይቶ የመጥቀሱ አስፈላጊነት ቤተ መቅደሱ ሲመረቅ ሰሎሞን ባቀረበው ጸሎት ላይ በጉልህ ታይቷል:- “በምድር ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፣ ጠላቶቻቸውም የአገሩን ከተሞች ከብበው ቢያስጨንቁአቸው፣ ማናቸውም መቅሠፍትና ደዌ ቢሆን፣ ማንም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ፣ ማናቸውም ሰው ሕመሙንና ኀዘኑን አውቆ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ . . . በማደሪያህ በሰማይ ስማ፣ ይቅርም በል፤ . . . [ለ]ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው።” (2 ዜና መዋዕል 6:28-31) ‘ሕመምህንና ሐዘንህን የምታውቀው’ አንተ ብቻ እንደሆንክ የታወቀ ነው። እንግዲያው ትክክለኛ ፍላጎትህንና ምኞትህን ለይተህ መጥቀስህ በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ካደረግህ ‘ይሖዋ የልብህን መሻት ይሰጥሃል።’—መዝሙር 37:4
ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
ይሖዋ ተራ ሰዎች ከእርሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲመሠርቱ ይፈልጋል። የአምላክ ቃል “ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- . . . ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 6:17, 18) በእርግጥም ይሖዋና ልጁ ስኬታማ እንድንሆንና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ይፈልጋሉ። በቤተሰብ፣ በሥራ ቦታና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉብንን ኃላፊነቶች እንድንወጣ ይሖዋ እንደሚረዳን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው!
ያም ሆኖ ሁላችንም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። የጤና እክል፣ የቤተሰብ ችግሮች፣ የገንዘብ እጥረት ወይም ሌሎች ነገሮች ያስጨንቁን ይሆናል። አንድ ፈተና ወይም መከራ ሲያጋጥመን እንዴት እንደምንወጣው ግራ ይገባን ይሆናል። እነዚህን ከቀን ወደ ቀን እየጨመሩ የሚሄዱ ጫናዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያመጣብን በአምላክ ሕዝቦች ላይ መንፈሳዊ ጦርነት የከፈተው ክፉው ከሳሽ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሆኖም ችግራችንን የሚገነዘብልንና ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን እንድንቀጥል የሚረዳን አንድ አካል አለ። እሱም በሰማይ በሥልጣን መንበሩ ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ እንዲህ ይላል:- “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”—ዕብራውያን 4:15, 16
የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ዝነኞች ወይም ባለጸጎች መሆን እንደማያስፈልገን ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ከባድ መከራ ቢያጋጥምህም እንኳን እንዲህ ሲል እንደጸለየው መዝሙራዊ ዓይነት አመለካከት ይኑርህ:- “እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፣ ጌታ ግን ያስብልኛል፤ አንተ ረዳቴና መድኃኒቴ ነህ።” (መዝሙር 31:9-14፤ 40:17) ይሖዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ተራ ሰዎች እንደሚያስብ አትጠራጠር። በእርግጥም፣ ‘ስለ እኛ ስለሚያስብ የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንችላለን።’—1 ጴጥሮስ 5:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል አብዛኞቹ ያልተማሩና ተራ ሰዎች ነበሩ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ጠንካራ እምነት ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ሞገስ ለማግኘት በሰዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለን መሆን አያስፈልገንም