የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w05 7/15 ገጽ 14-16
  • ‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጠንቃቃ ገበሬ ወይስ “ኀያል ጦረኛ”?
  • “ራሱ በኣል ይሟገተው”
  • እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት
  • የውጊያ ስልት
  • ምን ትምህርት እናገኛለን?
  • ጌድዮን ምድያማውያንን አሸነፈ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ጌዴዎንና 300 ተዋጊዎቹ
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • ሽማግሌዎች—ከጌድዮን ምሳሌ ተማሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • የቅርብ ወዳጃችን የሆነው ይሖዋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
w05 7/15 ገጽ 14-16

‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ’

አንድን የእርሻ ቦታ ድምጥማጡን እንደሚያጠፋ የአንበጣ መንጋ በጣም ብዙ ናቸው። ወቅቱ መሳፍንት በእስራኤል የሚገዙበት፣ እስራኤላውያን ደግሞ ተስፋ ቆርጠው የነበረበት ጊዜ ነው። ለሰባት ዓመታት ያህል፣ የዘሩት እህል ገና ማሸት ሲጀምር ግመል ጋላቢዎቹ ምድያማውያንና አማሌቃውያን እንዲሁም የምሥራቅ ሕዝቦች መጥተው ምድሪቱን ይወሩ ነበር። ዘራፊዎቹ የሚያግዷቸው መንጋዎች በግጦሽ መሬት ላይ ተሰማርተው ሣር ቅጠሉን እንክት አድርገው ይበላሉ። በሌላ በኩል እስራኤላውያን አህያ፣ በሬ ወይም በግ አልነበራቸውም። አስፈሪ የነበረው የምድያማውያን አገዛዝ ያስጨነቃቸውና ድህነት ያቆራመዳቸው እስራኤላውያን የሰበሰቡትን አዝመራ በየተራራው ጥግ፣ በዋሻዎችና በቀላሉ በማይደረስባቸው ቦታዎች ለመሸሸግ ተገደዱ።

ይህን የመሰለ አስከፊ ችግር የደረሰባቸው ለምንድን ነው? ከዳተኞቹ እስራኤላውያን የሐሰት አማልክት ያመልኩ ስለነበር ነው። በአጸፋው ይሖዋ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጣቸው። የእስራኤል ልጆች ችግሩን መቋቋም ባለመቻላቸው ይሖዋ እንዲረዳቸው ለመኑ። እርሱስ ይሰማቸው ይሆን? የእስራኤላውያን ተሞክሮ ምን ያስተምረናል?—መሳፍንት 6:1-6

ጠንቃቃ ገበሬ ወይስ “ኀያል ጦረኛ”?

አብዛኛውን ጊዜ እስራኤላውያን ገበሬዎች ስንዴ የሚወቁት በበሬ የሚጎተት ጠፍጣፋ ብረት በላዩ በማስኬድ እህሉ ከገለባው እንዲላቀቅ ካደረጉ በኋላ ለነፋስ የተጋለጠ ቦታ ላይ ሆነው በመንሽ ወደ ላይ በመበተን ፍሬውን ከእብቁ በመለየት ነው። ይሁን እንጂ ምድሪቱን ለማራቆት ታጥቀው የተነሱ ወንበዴዎች በሚያዩት ቦታ እህል መውቃት ራስን ለችግር ማጋለጥ ነው። ጌዴዎን ከምድያማውያን ተደብቆ በወይን መጭመቂያ ሥፍራ (ከድንጋይ ተጠርቦ የተሠራ አንድ ትልቅ ገንዳ ሊሆን ይችላል) ስንዴ ይወቃ ነበር። (መሳፍንት 6:11) በዚህ ቦታ መጠኑ አነስተኛ የሆነ የስንዴ ነዶ በዱላ እየመታ የሚወቃ ይመስላል። ከሁኔታው አንጻር ጌዴዎን ማድረግ የሚችለው ይህንኑ ነው።

የይሖዋ መልአክ ወደ እርሱ ቀርቦ “አንተ ኀያል ጦረኛ! እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” ሲለው ጌዴዎን ምን ያህል ተደንቆ እንደሚሆን ገምት። (መሳፍንት 6:12) ጌዴዎን በወይን መጭመቂያ ውስጥ ተደብቆ ስንዴ ለመውቃት የተገደደ ሰው ሆኖ ሳለ ጀግና ነኝ ብሎ እንደማያስብ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ቃል ጌዴዎን በእስራኤል ላይ ኀያል ገዥ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም መለኮታዊ ማረጋገጫ ነው። ሆኖም ይህንን ጉዳይ እርሱ ራሱ አምኖ እንዲቀበል ማድረግ ያስፈልግ ነበር።

ይሖዋ፣ “እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ” እንዲያወጣ ተልእኮ በሰጠው ወቅት ጌዴዎን በትሕትና “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለው። ጠንቃቃ የሆነው ጌዴዎን ከምድያማውያን ጋር በሚዋጋበት ጊዜ አምላክ ከእርሱ ጋር እንደሚሆን ለማረጋገጥ ምልክት እንዲያሳየው ጠየቀ። ይሖዋም ጌዴዎን እርግጠኛ ለመሆን ሲል ያቀረበውን ተገቢ ጥያቄ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሆኗል። ከዚያም ጌዴዎን ሊያነጋግረው ለመጣው መልአክ ምግብ ያቀረበ ሲሆን ከአለት ውስጥ እሳት በመውጣት መሥዋዕቱን በላው። ይሖዋ፣ ጌዴዎን የነበረበት ፍርሃት እንዲወገድለት ካደረገ በኋላ ጌዴዎን በዚያ ቦታ ላይ መሠዊያ ሠራ።—መሳፍንት 6:12-24

“ራሱ በኣል ይሟገተው”

የእስራኤላውያን ዋነኛ ችግር የምድያማውያን ጭቆና ሳይሆን ከበዓል አምልኮ ጋር ያላቸው ቁርኝት ነበር። ይሖዋ “ቀናተኛ አምላክ” ስለሆነ አንድ ሰው ሌሎች አማልክትን እያመለከ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አይችልም። (ዘፀአት 34:14) ስለዚህም ይሖዋ ጌዴዎንን፣ አባቱ ለበዓል የገነባውን መሠዊያ እንዲያፈርስ እንዲሁም የአሼራን ዐምድ እንዲሰብር አዘዘው። ጌዴዎን የታዘዘውን በቀን ቢፈጽም ከአባቱም ሆነ ከሌሎች ሊገጥመው የሚችለውን ተቃውሞ በመፍራት አሥር አገልጋዮቹን አስከትሎ በሌሊት እርምጃ ወሰደ።

በአካባቢው ያሉት የበዓል አምላኪዎች በዓልን “አራክሷል” ብለው ሊገድሉት መነሳታቸው ጌዴዎን ያደረገው ጥንቃቄ ተገቢ እንደነበር ያሳያል። የጌዴዎን አባት ኢዮአስ ለሕዝቡ የማያሻማ ማስረጃ በማቅረብ በዓል አምላክ ከሆነ ራሱን ሊከላከል ይችላል አላቸው። ከዚያም ኢዮአስ ልጁን ይሩበኣል ብሎ የጠራው ሲሆን ትርጉሙም “በኣል ይጋፈጠው” ማለት ነው።—መሳፍንት 6:25-32 የግርጌ ማስታወሻ።

አምላክ እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍ የድፍረት እርምጃ የሚወስዱትን አገልጋዮቹን ምንጊዜም ይባርካቸዋል። ምድያማውያንና የእነርሱ ተባባሪዎች የእስራኤላውያንን ክልል በድጋሚ በወረሩ ጊዜ “የእግዚአብሔር መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ።” (መሳፍንት 6:34) በአምላክ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል መሪነት ጌዴዎን ከምናሴ፣ ከአሴር፣ ከዛብሎን እና ከንፍታሌም ነገድ ወታደሮችን አሰባሰበ።—መሳፍንት 6:35

እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት

ምንም እንኳ ጌዴዎን 32,000 ተዋጊ ያገኘ ቢሆንም አምላክ ምልክት እንዲያሳየው ጠየቀ። ይሖዋ አምላክ በእርሱ ተጠቅሞ እስራኤልን የሚያድን መሆኑን ለማረጋገጥ በአውድማው ላይ ያስቀመጠው የበግ ጠጉር ባዘቶ ጤዛ ይዞ መሬቱ ግን ደረቅ እንዲሆን ጠየቀ። ይሖዋም ይህን ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው ማለትም ምድሩን በጤዛ እንዲሸፍን ባዘቶውን ደግሞ ደረቅ እንዲያደርግ የጠየቀውን ተአምር ጭምር ፈጽሞለታል። የጌዴዎን ጥንቃቄ ከልክ ያለፈ ነበር? እንዳልነበረ ግልጽ ነው፣ ምክንያቱም ይሖዋ ልመናውን ሰምቶ ማረጋገጫ ሰጥቶታል። (መሳፍንት 6:36-40) ዛሬ እንዲህ ያለ ተአምር አንጠብቅም። ሆኖም የይሖዋን መመሪያና ማበረታቻ ከቃሉ ማግኘት እንችላለን።

ይሖዋ የጌዴዎን ወታደሮች ብዙ መሆናቸውን ነገረው። እስራኤላውያን ይህንን ሁሉ ጦር ይዘው ጠላቶቻቸውን ድል ቢነሱ ያሸነፉት በራሳቸው ኃይል እንደሆነ አድርገው በማሰብ ሊኩራሩ ይችላሉ። ይሁንና ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ድል ክብር ማግኘት ያለበት ይሖዋ ነው። ታዲያ መፍትሔው ምን ይሆን? ጌዴዎን የፈሩ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በሚያዘው የሙሴ ሕግ መሠረት አሰናበታቸው። በዚህ ጊዜ 22,000 የሚያክሉት ሲመለሱ 10,000 ብቻ ቀሩ።—ዘዳግም 20:8፤ መሳፍንት 7:2, 3

በአምላክ ዓይን ሲታይ አሁንም ቢሆን ቁጥራቸው ብዙ ነው። ጌዴዎን ሰዎቹን ወደ ወንዝ እንዲወስዳቸው ተነገረው። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንዳለው አምላክ ጌዴዎንን የቀኑ ሙቀት በሚያይልበት ሰዓት ወታደሮቹን ወደ ወንዝ እንዲወስዳቸው አዘዘው። የወሰዳቸው መቼም ይሁን መቼ ጌዴዎን ውኃውን እንዴት እንደሚጠጡ ተመለከተ። የጠላት ድንገተኛ ጥቃት እንዳይደርስባቸው አካባቢውን በመቃኘት በአንድ እጃቸው ውኃ እየጨለፉ የጠጡት 300 ብቻ ነበሩ። ከጌዴዎን ጋር አብረው የሚሄዱት እነዚህ ጠንቃቃ የሆኑ 300 ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። (መሳፍንት 7:4-8) እስቲ ራሳችሁን በእነርሱ ቦታ አድርጋችሁ አስቡ። የጠላቶቻችሁ ቁጥር 135,000 ሆኖ እያለ ድል ማድረግ የምትችሉት በይሖዋ ኃይል እንጂ በራሳችሁ እንዳልሆነ አምናችሁ እንደምትቀበሉ የታወቀ ነው።

ይሖዋ ለጌዴዎን አንድ አገልጋይ ይዞ ሄዶ የምድያማውያንን ሰፈር እንዲቃኝ ነገረው። እዚያ እንደ ደረሱ ጌዴዎን አንድ ሰው ስላየው ሕልም ለጓደኛው ሲያወራለትና እርሱ ደግሞ ፍቺው አምላክ ምድያማውያንን በጌዴዎን እጅ አሳልፎ ለመስጠት መወሰኑን እንደሚያመለክት በእርግጠኝነት ሲነግረው ሰማ። ጌዴዎንም ይህን ቃል መስማቱ አበረታታው። ይሖዋ ለእርሱና አብረውት ላሉት 300 ሰዎች በምድያማውያን ላይ ድል እንደሚያቀዳጃቸው እርግጠኛ ሆነ።—መሳፍንት 7:9-15

የውጊያ ስልት

እነዚህ 300 ሰዎች እያንዳንዳቸው 100 ሰዎች በያዙ ሦስት ቡድኖች ተከፈሉ። ለእያንዳንዱ ሰው ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ ተሰጠው። እንዲሁም በማሰሮ ውስጥ ችቦ ደብቀው ይዘው ነበር። ጌዴዎን የሰጣቸው የመጀመሪያ ትእዛዝ ይህ ነበር:- ‘እኔን ተመልከቱ፤ የማደርገውንም አድርጉ፤ እኔ ቀንደ መለከቱን ስነፋ እናንተም ቀንደ መለከቶቹን እየነፋችሁ “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” በማለት ጩኹ።’—መሳፍንት 7:16-18, 20

ሦስት መቶ የሚያክሉት እስራኤላውያን ተዋጊዎች በዝግታ ወደ ጠላት ጦር ሰፈር ደረሱ። ጊዜው ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ማለትም ልክ ዘቦቹ እንደተቀየሩ ነበር። ይህም አዲሶቹ ተረኞች ዓይናቸው ጨለማውን እስኪላመድ ድረስ ያለው ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ አመቺ እንደሚሆን ታስቦ ሊሆን ይችላል።

በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ከፍተኛ ሽብር ውስጥ የሚከት ሁኔታ ገጠማቸው! በድንገት 300 ማሰሮዎች ሲሰባበሩ የሚያሰሙት ድምፅ፣ ከ300 ቀንደ መለከቶች የሚወጣው ጩኸት እንዲሁም የ300 ሰዎች ሁካታ ሰፍኖ የነበረውን ፀጥታ ሰበረው። በተለይ ምድያማውያን ‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ’ በሚለው ድምፅ በመደናገጣቸው ያሰሙት ጩኸት ሁካታውን አባባሰው። የተፈጠረው ትርምስ ጠላትን ከወዳጅ መለየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። አምላክ የጠላት ሠራዊት በሰይፍ እርስ በርሱ እንዲጨራረስ ሲያደርግ እነዚህ 300 ሰዎች ከተመደቡበት ቦታ ንቅንቅ አላሉም። ከዚያም ሠራዊቱ ደንግጦ እንዲሸሽ በማድረግ፣ ማምለጫ ቀዳዳ በማሳጣት እንዲሁም ያመለጡትን አሳድዶ በመማረክና በመግደል የምድያማውያንን ጥቃት ለዘለቄታው አስወገዱ። ለረጅም ጊዜ የቆየው የጭቆና አገዛዝ በዚህ ሁኔታ ተደመደመ።—መሳፍንት 7:19-25፤ 8:10-12, 28

ጌዴዎን ከዚህ ድል በኋላም ቢሆን በትሕትና መመላለሱን ቀጥሏል። ኤፍሬማውያን ለውጊያው ያልጠራቸው ንቋቸው እንደሆነ አድርገው በማሰብ ከእርሱ ጋር ጠብ ለመፍጠር በፈለጉበት ወቅት ምላሽ የሰጣቸው ረጋ ባለ መንፈስ ነበር። የእርሱ የለዘበ መልስ ቁጣቸውን አርግቧል።—መሳፍንት 8:1-3፤ ምሳሌ 15:1

እስራኤላውያን አሁን ይናፍቁት የነበረውን ሰላም ስላገኙ ጌዴዎን ንጉሣቸው እንዲሆን ለመኑት። ይህ ከባድ ፈተና ነበር! ይሁን እንጂ ጌዴዎን ሐሳባቸውን አልተቀበለውም። በምድያማውያን ላይ ድል የተቀዳጀው ማን መሆኑን አልዘነጋም። ስለዚህም እንዲህ አላቸው:- “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ እግዚአብሔር ነው።”—መሳፍንት 8:23

ይሁን እንጂ ጌዴዎን ፍጽምና የሚጎድለው ስለሆነ ሁልጊዜ ጥሩ ውሳኔ ያደርጋል ማለት አይቻልም። ምክንያቱ ይህ ነው ተብሎ ባይጠቀስም ከምርኮ በተገኘ ወርቅ ኤፉድ ሠርቶ በትውልድ ከተማው አስቀመጠው። ዘገባው እንደሚያሳየው እስራኤላውያን ሁሉ ኤፉዱን በማምለክ ‘አመነዘሩ’። በመሆኑም ለጌዴዎንና ለቤተሰቡ ወጥመድ ሆነባቸው። ይሁን እንጂ ጌዴዎን ሙሉ በሙሉ ጣዖት አምላኪ አልሆነም። እንደውም መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ላይ እምነት የነበረው ሰው እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል።—መሳፍንት 8:27፤ ዕብራውያን 11:32-34

ምን ትምህርት እናገኛለን?

የጌዴዎን ታሪክ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ማበረታቻ ይዞልናል። ይሖዋ ሥነ ምግባር በጎደለው አኗኗራችን ምክንያት መንፈሱንም ሆነ ሞገሱን ከእኛ ቢያርቅ መንፈሳዊ ሁኔታችን የአንበጣ መንጋ ባወደመው ምድር በድህነት ተቆራምደው ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ይሆናል። የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ቢሆንም የይሖዋ በረከት ‘ብልጽግናን እንደምታመጣና፤ መከራም እንደማይታከልባት’ ፈጽሞ ልንዘነጋው አይገባንም። (ምሳሌ 10:22) ይሖዋን “በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ” ስለምናገለግለው የእርሱን በረከት እናገኛለን። ያለበለዚያ ግን ይተወናል።—1 ዜና መዋዕል 28:9

ይሖዋ ደካማ ወይም አቅመ ቢስ መስለው በሚታዩ ሰዎች ተጠቅሞ ሕዝቦቹን ከማንኛውም ዓይነት መከራ ሊታደግ እንደሚችል ስለሚገልጽ ስለ ጌዴዎን ከሚናገረው ዘገባ ማበረታቻም ማግኘት እንችላለን። ጌዴዎንና አብረውት የነበሩት 300 ሰዎች 135,000 ምድያማውያንን ማሸነፋቸው ለአምላክ ገደብ የለሽ ኃይል ማስረጃ ነው። እኛም ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ልንገኝና ጠላቶቻችን እጅግ ብዙ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው የጌዴዎን ታሪክ በእርሱ የሚታመኑትን በሚባርከውና ነጻ በሚያወጣው በይሖዋ እንድንታመን ያደርገናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ