ወደ አምላክ ቅረብ
‘ከአምላክ ፍቅር ሊለየን’ የሚችል ነገር ይኖራል?
መወደድ የማይፈልግ ማን አለ? እንዲያውም ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን እንደሚወዱን ሲሰማን እንደሰታለን። በሰዎች መካከል ያለው ፍቅር በቀላሉ ሊጠፋ ወይም ደግሞ በጊዜ ሂደት አሊያም በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀዘቅዝ የሚችል መሆኑ ያሳዝናል። የምንወዳቸው ሰዎች ሊያስቀይሙን፣ ሊያገሉን አልፎ ተርፎም ሊጠሉን ይችላሉ። ይሁን እንጂ ፍቅሩ ምንጊዜም የማይቀዘቅዝ አንድ አካል አለ። ይሖዋ አምላክ ለአገልጋዮቹ ያለው ፍቅር በሮሜ 8:38, 39 ላይ ማራኪ በሆነ መንገድ ተገልጿል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከአምላክ ፍቅር ሊለየን የሚችል’ ምንም ነገር እንደሌለ ‘መረዳቱን’ ተናግሯል። “ሊለየን” የሚለውን ቃል፣ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ስለ ራሱ ብቻ ሳይሆን አምላክን በታማኝነት ስለሚያገለግሉ ሰዎች እንደሆነ ያሳያል። ጳውሎስ ይህን ሐሳብ ለማጠናከር፣ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ፍቅር ከማሳየት ሊያግዱት የማይችሉ በርካታ ነገሮችን ዘርዝሯል።
“ሞትም ይሁን ሕይወት።” ይሖዋ አገልጋዮቹ ቢሞቱ እንኳ ለእነሱ ያለው ፍቅር አይጠፋም። አምላክ የሞቱ አገልጋዮቹን የሚያስታውሳቸውና በቅርቡ በሚመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ በትንሣኤ የሚያስነሳቸው መሆኑ ለእነሱ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:3, 4) በተጨማሪም አምላክ፣ በሕይወት ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር ቢደርስባቸውም ለእነሱ ያለው ፍቅር አይቀዘቅዝም።
‘መላእክትም ይሁኑ ባለሥልጣናት።’ (የ1980 ትርጉም) የሰው ልጆች፣ ተደማጭነት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ባለሥልጣናት በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ሊሸነፉ ይችላሉ፤ ይሖዋ ግን እንዲህ አይደለም። ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ተብሎ የተጠራውን መልአክ ጨምሮ ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታት አምላክ ሕዝቦቹን እንዳይወድ ሊያደርጉት አይችሉም። (ራእይ 12:10) እውነተኛ ክርስቲያኖችን የሚቃወሙ መንግሥታትም ቢሆኑ አምላክ ለአገልጋዮቹ ያለውን አመለካከት እንዲለውጥ ሊያደርጉት አይችሉም።—1 ቆሮንቶስ 4:13
“ያለውም ይሁን የሚመጣው።” የአምላክ ፍቅር መቼም ቢሆን አይቀዘቅዝም። የአምላክ አገልጋዮች አሁን እየደረሱባቸው ያሉትም ሆኑ ወደፊት የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ይሖዋን ፍቅሩን ከማሳየት ሊያግዱት አይችሉም።
“ወይም ማንኛውም ኀይል።” እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ኀይል” የሚለው የግሪክኛ ቃል ሰፊ ትርጉም አለው። የቃሉ ትክክለኛ ትርጉም ምንም ይሁን ምን በአንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን:- በሰማይም ሆነ በምድር የሚገኝ ማንኛውም ኃይል ይሖዋ ለሕዝቦቹ ፍቅር እንዳያሳይ ሊያደርገው አይችልም።
“ከፍታም ይሁን ጥልቀት።” ይሖዋ ሕዝቦቹ በየትኛውም ሁኔታ ሥር ቢገኙ ማለትም ያሉበት አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይወዳቸዋል።
“ወይም የትኛውም ፍጥረት።” ጳውሎስ በእነዚህ ቃላት አማካኝነት የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች ከእሱ ፍቅር ሊለያቸው የሚችል አንድም ነገር እንደሌለ ገልጿል።
የሰዎች ፍቅር እያደር ሊጠፋ አሊያም ሊቀዘቅዝ የሚችል ቢሆንም አምላክ በእሱ ለሚያምኑ ሰዎች ያለው ፍቅር ግን ምንጊዜም የማይለወጥና ዘላለማዊ ነው። ይህን ማወቃችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብና ለእሱ ያለንን ፍቅር ለማሳየት የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ እንደሚያነሳሳን ጥርጥር የለውም።