አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ
ዲያብሎስ በእርግጥ አለ?
አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ እውን አካል ያለው ፍጡር እንደሆነ ያስተምራል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን የሚተቹ ሰዎች፣ ‘ዲያብሎስ አለ’ በሚለው ትምህርት ያፌዛሉ። እነዚህ ሰዎች ሰይጣን በሰዎች ልብ ውስጥ የሚገኝን የክፋት ሐሳብ የሚያመለክት እንደሆነ ይናገራሉ።
የሰይጣንን እውነተኛ ማንነት በተመለከተ ግራ መጋባት መኖሩ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ አንድ ወንጀለኛ ማንነቱን የሚጠቁም ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይገኝ ለማድረግና ሳይታወቅበት በሕገወጥ ድርጊቱ ለመቀጠል ሲል ወንጀሉን ከፈጸመበት ቦታ የጣት አሻራውን ያጠፋ ይሆናል። በተመሳሳይም ሰይጣን ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶችን በድብቅ የሚያስፋፋ ወንጀለኛ ነው። ኢየሱስ፣ ዛሬ በሰው ልጆች ዘንድ ለሚታየው ክፋት ተጠያቂው ሰይጣን መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። በተጨማሪም ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል።—ዮሐንስ 12:31
ዲያብሎስ የመጣው ከየት ነው? መጀመሪያ ላይ ፍጹም መንፈሳዊ አካል ኖሮት በሰማይ የተፈጠረ መልአክ ነበር፤ ይህ ዓመፀኛ መልአክ፣ ሰዎች ከአምላክ ይልቅ እሱን እንዲያመልኩት ከፍተኛ ምኞት ባደረበት ጊዜ ራሱን ዲያብሎስ አደረገ። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከሰይጣን ጋር እንደተነጋገረ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የዲያብሎስን የራስ ወዳድነት ምኞት አጋልጧል። ሰይጣን፣ ኢየሱስ ‘አንድ ጊዜ ተደፍቶ እንዲያመልከው’ ለማድረግ ሞክሮ ነበር።—ማቴዎስ 4:8, 9
በተመሳሳይም በኢዮብ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ሰይጣን ከአምላክ ጋር በተነጋገረባቸው ጊዜያት የልቡ ዝንባሌ በግልጽ ታይቷል። ሰይጣን ሰዎች አምላክን ማምለካቸውን እንዲተዉ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።—ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7, 8
እስቲ አስበው፦ ሰይጣን ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተነጋግሮ ከነበረ በሌሎች ልብ ውስጥ ያለ የክፋት ሐሳብ እንዴት ሊሆን ይችላል? በአምላክም ሆነ በልጁ ልብ ውስጥ ምንም ዓይነት ክፋት የለም! ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሰይጣን እውን አካል አለው፤ ይህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ለይሖዋም ሆነ ለኢየሱስ ምንም አክብሮት የለውም።
ዛሬ በሰው ልጆች ላይ የሚታየው ክፋት ዲያብሎስ በእርግጥ መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የዚህ ዓለም መንግሥታት በአገራቸው የሚኖሩ ሰዎች እየተራቡ ከመጠን ያለፈ እህል በመጋዘን እንዲበሰብስ ያደርጋሉ። መንግሥታት፣ እርስ በርስ እንዲተላለቁ የሚያደርጓቸውን ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ያከማቻሉ፤ እንዲሁም ምድርን ይበክላሉ። ያም ሆኖ አብዛኞቹ ሰዎች፣ መንግሥታት እንዲህ ያለውን አጥፊና ራስን የሚጎዳ ባሕርይ እንዲያሳዩ የሚገፋፋቸው ማን እንደሆነ አያውቁም። ለምን?
መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ‘የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ እንዳሳወረ’ በግልጽ ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰዎችን በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል በዓይን የማይታይ ድርጅት ይጠቀማል። ሰይጣን ‘የአጋንንት አለቃ’ ተብሏል። (ማቴዎስ 12:24) አንድ የተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን መሪ በድርጅቱ ውስጥ ላሉት ሠራተኞች ሁሉ ራሱን መግለጥ ሳያስፈልገው ድርጅቱን ማንቀሳቀስ እንደሚችል ሁሉ ሰይጣንም እሱ የሚሠራውን ሥራም ሆነ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የማይገነዘቡትን በርካታ ሰዎች ለመቆጣጠር ክፉ መላእክቱን ባቀፈውና አደገኛ በሆነው ሕቡዕ ድርጅቱ ይጠቀማል።
መጽሐፍ ቅዱስ የዲያብሎስንና የድርጅቱን ማንነት በግልጽ እንድናውቅ ስላደረገን ምንኛ አመስጋኞች ነን! እንግዲያው የዲያብሎስን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችለንን እርምጃ አሁኑኑ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ጥብቅ ምክር ይሰጠናል፦ “ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።”—ያዕቆብ 4:7