ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ያሳዩትን ፍላጎት ለመኮትኮት ተመልሰህ ሂድ
1 በነሐሴና በመስከረም በምናደርገው የመቄዶንያ ዘመቻችን ራቅ ወዳሉ የአገልግሎት ክልሎች ለመሄድ አቅደናል። የመንግሥቱ መልእክት እምብዛም ወዳልደረሳቸው አካባቢዎች ሄደን የመንግሥቱን ዘር መዝራት ተቀዳሚው ፍላጎታችን ቢሆንም ሰዎች ያሳዩትን ፍላጎት የተቻለንን ያህል ለመኮትኮትም እንፈልጋለን።
2 ጉባኤው በመቄዶንያ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እንዳደረገ አያጠራጥርም። ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤታቸው ስትሄድ ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ወረቀትህ ላይ ጥሩ ማስታወሻ መውሰድ አትዘንጋ። ምስክርነት ለመስጠት ስትሄድ የምትይዘውን ቦርሳ ስታዘጋጅ ባለፈው ጊዜ ያበረከትከውን ጽሑፍ ይዘህ ሂድ። ይህን ካደረግህ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግላቸው ጽሑፉን እያሳየሃቸው ልታወያያቸው ትችላለህ።
“እነሆ!” የተባለውን ብሮሹር አበርክተህ ከነበረ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “እንደገና ለመገናኘት በመቻላችን ደስ ብሎኛል። ባለፈው ጊዜ ስንነጋገር የዚህን ብሮሹር ሽፋን አሳይቼዎት ነበር። እንዲሁም አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ለእያንዳንዱ ሰው ቤትም ሆነ ሥራ እንደሚሰጥ የሚያረጋግጡ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብበን ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በሽታንና እርጅናን ሞትንም ጭምር እንደሚያስቀር ቃል ገብቷል። የማይታመን ነገር ይሆንብዎታልን? [የቤቱ ባለቤት መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ባለፈው ጊዜ በሰጠሁዎት ብሮሹር አንቀጽ 4 ላይ ያለውን ይህንን ሐሳብ እስቲ ይመልከቱት።” አንቀጹን አንብበውና በገጹ ግርጌ ላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መሃል አንድ ሁለቱን አንብብለት። ይህንን ስታደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርክለት ማለት ነው!
3 አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? በተባለው ብሮሹር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደማስጠናት የሚመሩ ጥሩ ተመላልሶ መጠየቆች ለማድረግ በብሮሹሩ ውስጥ በክፍል 10 ሥር የሚገኘውን ሐሳብና ከገጽ 25 እስከ 27 ላይ በሚገኙት ሥዕሎች አማካኝነት መዘጋጀት ይቻላል።
4 ትራክት የሰጠናቸውን ሰዎች ተመልሰን በመሄድ ማነጋገር፦ ምናልባት ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም የተባለውን ትራክት ለቤቱ ባለቤት ሰጥተነው ሊሆን ይችላል። ተመልሰን ሄደን በምናነጋግረው ጊዜ በትራክቱ መግቢያ ላይ ያሉትን አንቀጾች ልናወያየው እንችላለን። በገጽ 3 ላይ ያለው መዝሙር 37:29 የተጠቀሰበት የመጀመሪያ አንቀጽ መደምደሚያ ላይ ስንደርስ እንዲህ ልንለው እንችላለን:-
◼ “እነዚህ ቃላት አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? በተባለው በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ጎላ ተደርገው ተገልጸዋል። በገጽ 27 አንቀጽ 22 ላይ ያለውን ሐሳብ ይመልከቱ።” ከዚያም አንቀጹን ልናነብለትና በጽሑፉ ላይ ያለውን ጥያቄ ልንጠይቀው እንችላለን። ቀጥለን “አምላክ እነዚህን ተስፋዎች የሚፈጽምልን እንዴት ነው?” ልንለው እንችላለን። “የደረሰውን ጉዳት መጠገን” በሚለው ርዕስ ሥር የሚገኙት ቀጥሎ ያሉት ጥቂት አንቀጾች ይህንን ያብራራሉ። ከዚያም አንቀጹን አንብብለትና በጽሑፉ ላይ ያለውን ጥያቄ ጠይቀው። ንዑስ ርዕሱን በሙሉ ልታወያየው ትችል ይሆናል። ከዚያም ወደፊት መጥተህ እንድታነጋግረው ቀጠሮ ለመያዝ ወይም በሚቻለው መንገድ ሁሉ ውይይቱን ለመጠቀል ሞክር።
5 ራቅ ባሉ የአገልግሎት ክልሎችም ውስጥ ሳይቀር ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ያላቸውን ፍላጎት መኮትኮት በጣም አስፈላጊ ሥራ ነው። ኢየሱስ የተማሩትን ነገር ለሌሎች እንዲያስተምሩ ተከታዮቹን አዝዟቸዋል። ይሖዋ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክልን እንጸልያለን። እንግዲያው ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ፈልገን በማግኘትና እነዚህ ሰዎች በመከሩ ሥራ የሚካፈሉ የሥራ ባልደረቦቻችን እንዲሆኑ በማስተማር የበኩላችንን እናድርግ። — ማቴ. 9:37፤ 28:19, 20