የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት
1 ውጤታማ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራው እንዴት ነው? ለዚህስ ምን ዋና ምሳሌ አለን? በምናስጠናበት ጽሑፍ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች እንዴት ልንወያይባቸው እንችላለን? አንቀጾቹን ማንበብ ያለበት ማን ነው? ተማሪው እውነትን የራሱ እንዲያደርግ ለመርዳት መሠረታዊ ከሆነው የማስጠናት ዘዴ በተጨማሪ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ልናስወግዳቸው የሚገቡን ምን ዕንቅፋቶች አሉ?
2 ጥናት የሚመራው እንዴት ነው? ጠቅለል አድርጎ ለመናገር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናትን የአጠናን ዘዴ የተከተለ ነው። በመጀመሪያ የምንወያይበት አንቀጽ ይነበባል። ከዚያም ጥናቱን የሚመራው ሰው ለዚያ አንቀጽ የተዘጋጀውን በጽሑፉ ላይ ያለውን ጥያቄ ይጠይቅና ተማሪው እንዲመልስ ያደርጋል። ተማሪው ቶሎ ለመመለስ ከተቸገረ አስጠኚው ወደ መልሱ የሚመሩ ሌሎች ጥያቄዎችን ለመጠየቅ የተዘጋጀ መሆን ይኖርበታል። እነዚህም ጥያቄዎች ተማሪው በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበትና ትክክለኛ የሆነ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ያደርጉታል።
3 ጥቅሱ በአንቀጹ ውስጥ ላለው ሐሳብ እንዴት እንደሚሠራ ተወያዩበት። ተማሪው የተጠቀሱትን ጥቅሶች እንዴት መለየት እንደሚችል አሳየው፤ እንዲሁም ጥቅሶቹ ከሐሳቡ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ እንዲገነዘብ እርዳው። የጥቅሶቹ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ ተጠቅሶ የያዙት ሐሳብ ግን ካልተጻፈ በጣም ረጃጅም ያልሆኑትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥታችሁ ብትመለከቷቸው ጥሩ ነው። ከዚያ ተማሪው ጥቅሶቹን እንዲያነብና ጥቅሶቹ አንቀጹ ውስጥ ያለውን ሐሳብ እንዴት እንደሚደግፉ ወይም ግልጽ እንደሚያደርጉ እንዲናገር አድርግ።
4 ተማሪው እውነትን የራሱ እንዲያደርግ እርዳው፦ ተማሪዎቹ ለጥናታቸው በደንብ እንዲዘጋጁ አበረታታቸው። ለመማር ማንበብ እጅግ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አበክረህ ግለጽላቸው። ተማሪው የሚያጠናውን ጽሑፍ ይበልጥ ባነበበና ባሰላሰለበት መጠን የበለጠ እየገባው ይሄዳል። አንዳንድ አስጠኚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ወቅት አንቀጾቹን ሁሉ ተማሪው እንዲያነብ ሲያደርጉ ሌሎቹ ደግሞ ከተማሪው ጋር ተራ በተራ በመፈራረቅ አንቀጾቹን ያነባሉ። የተማሪውን መንፈሳዊ ዕድገት በአእምሮ በመያዝ አመዛዝኖ የሚሻለውን መወሰን ያስፈልጋል።
5 ጥናቱን እንደ ትምህርት አድርጎ ማጥናቱ ተማሪው እውቀት እንዲያካብት ሊረዳው ይችል ይሆናል። ነገር ግን የሚማረውን ነገር ያምንበታልን? እውነትን የራሱ ለማድረግ ከፈለገ ትምህርቱ እሱን በግሉ እንዴት እንደሚነካው መረዳት አለበት። ስለሚማረው ነገር ምን ይሰማዋል? የተማረውን ነገር እንዴት ሊጠቀምበት ይችላል? የተማሪውን ልብ ለመንካት እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ተጠቀም።
6 ዕንቅፋቶችን አስወግድ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ልናስወግዳቸው የሚገቡን ዕንቅፋቶች አሉ። ብዙውን ጊዜ እየተጠና ካለው ሐሳብ ጋር የማይዛመዱ ጉዳዮች ከተነሱ ጥናቱ ካበቃ በኋላ ወይም በሌላ ጊዜ ብትነጋገሩባቸው የተሻለ ነው። በተጨማሪም ተማሪው ከመጽሐፉ እያነበበ ከሚመልስ ይልቅ በራሱ አነጋገር መመለሱ አስፈላጊ ነው። ይህም አስጠኚው ተማሪው ሐሳቡን እንደተረዳውና እንዳልተረዳው ለማወቅ ይረዳዋል።
7 ቢያንስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖርህ ለምን ግብ አታወጣም? በይሖዋ ላይ የምትተማመንና የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናትን መሠረታዊ የአጠናን ሂደት የምትከተል ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ከባድ ሥራ አይሆንብህም። ሌሎችን ለማስተማርና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ ውጤታማ መንገድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ነው። ይህን በማድረግ አንተም በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ያለውን የኢየሱስ ትዕዛዝ ለመፈጸም ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ከሚገኘው ደስታ ተካፋይ ትሆናለህ።