አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ምሥራቹን ማቅረብ
1 ሁላችንም ከምናከናውነው ተግባር በተለይም ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ደስታና እርካታ ማግኘት እንፈልጋለን። እንደዚህ ያለውን እርካታ እንድናገኝ የሚረዳን ምንድን ነው? አንዱ ነገር ምንም በማያስቆጨው ሌሎችን የመርዳቱ ሥራ ራሳችንን ስናስጠምድ አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን ነው። (ምሳሌ 11:25 አዓት) አቀራረባችን በምንናገረው ነገር ላይ ከልብ እንደምናምን የሚያሳይ መሆን አለበት። ከልባችን አውጥተን የምንናገር ከሆነ በነገሩ ላይ የጸና እምነት ያለን መሆኑ ጉልህ ሆኖ ይታያል። (ሉቃስ 6:45) አቀራረባችንን ቀደም ብለን መለማመዳችን በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ስንነጋገር የበለጠ የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል። ይህም የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው ወይም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተሰኙትን መጽሐፎች በመስከረም ወር በምናበረክትበት ጊዜ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ምሥራቹን በማቅረብ ረገድ ጠቃሚ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ።
2 “ለዘላለም መኖር” የተሰኘውን መጽሐፍ ስታበረክት በመጀመሪያው ውይይታችሁ ወቅት እንደሚከተለው ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ከጎረቤቶቻችን ጋር ባደረግነው ውይይት አንዳንዶቹ በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው መረዳት ችለናል። ሌሎች ደግሞ በእርሱ ማመን አዳጋች ሆኖባቸዋል። እርስዎ እንዴት ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ። [ሮሜ 1:20ን አንብብ።] አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች በመመልከት የእርሱን ‘ዘላለማዊ ኃይልና አምላክነት’ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማስተዋል እንችላለን።” በመጽሐፉ ገጽ 35 ላይ የሚገኘውን አንቀጽ 3 ወይም ገጽ 36 ላይ የሚገኘውን አንቀጽ 5 ካነበብክለት በኋላ በሥዕላዊ መግለጫዎቹ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ከዚያም መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።
3 ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራ ካወያየኸው ሰው ጋር ለመነጋገር ተመልሰህ ስትሄድ እንዲህ ለማለት ትፈልግ ይሆናል:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ባደረግነው ውይይት አምላክ እንዳለ ስለሚያረጋግጡት ድንቅ የፍጥረት ሥራዎቹ ተነጋግረን ነበር። አጽናፈ ዓለምን የፈጠረው አምላክ የእኛም የወደፊት ዕጣ ያሳስበዋል ብሎ ማመኑን አስቸጋሪ ሆኖ ያገኙታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ፈጣሪ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ የወሰነ መሆኑን ማወቁ ትኩረታችንን የሚስብ ነገር ሆኖ እናገኘዋለን።” ኢሳይያስ 46:9, 10ን አንብብ። ሰውዬው ፍላጎት ካሳየ ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 11-13 ላይ የሚገኙትን ሥዕሎች በማሳየት አምላክ የሰጠው የተስፋ ቃል ሲፈጸም ምን ዓይነት አስደሳች ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ጎላ አድርገህ ግለጽ። የምዕራፍ 1ን አሥራ ዘጠነኛ አንቀጽ ካነበብክ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ጋብዘው።
4 ሌላው አማራጭ አቀራረብ ደግሞ የሚከተለው ሊሆን ይችላል:-
◼ “ዛሬ በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ልዩ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነን። ሁላችንም በአካባቢያችን እየጨመረ የመጣው ወንጀልና ዓመፅ ያሳስበናል። ለዚህ ችግር ተጨባጭ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ይኖራል ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ ግን መፍትሔ አለው።” ለዘላለም መኖር የተሰኘውን መጽሐፍ ገጽ 157 ገልጠህ የምሳሌ 2:22ን ጥቅስ ካነበብክ በኋላ ሐሳብ ስጥበት። የመጽሐፉን ርዕስ አሳየውና መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።
5 “የቤተሰብ ኑሮ” በተባለው መጽሐፍ የምትጠቀም ከሆነ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በጊዜያችን ቤተሰብን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች ባለፉት ትውልዶች አይታወቁም ነበር ቢባል አይስማሙም? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ የሆነው ለምን ይመስልዎታል? [ለማለት የፈለገው ነገር እንደገባህ ግለጽ። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3ን አውጥተህ አንብብ።] ‘ለወላጆቻቸው የማይታዘዙና ፍቅር የሌላቸው’ የሚሉት ሐረጎች በጊዜያችን ያሉትን ብዙ ሰዎች ሁኔታ በትክክል ይገልጻሉ። ሆኖም እነዚህ ችግሮች እንደሚከሰቱ የተናገረው አምላክ ራሱ ቤተሰብን ይበልጥ ለማቀራረብ የሚያስችል አስተማማኝ ምክር ጭምር ሰጥቶናል።” በገጽ 2 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፉ አዘጋጂዎች” የሚለውን አንቀጽ አንብብ።
6 ‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ’ እንደመሆናችን መጠን አዎንታዊ አመለካከት ይዘን ምሥራቹን የምናቀርብበት በቂ ምክንያት አለን። (1 ቆሮ. 3:9) እንዲህ ያለውን አመለካከት ይዘን መቀጠላችን የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል።