የተሻለ ነገር እንደሚመጣ የሚያበስረውን ምሥራች ማወጅ
1 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ለ117 ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጠበቃ ሆኖ አገልግሏል። በአሁኑ ወቅት ከእያንዳንዱ እትም በ125 ቋንቋዎች 18,950,000 ቅጂ ይታተማል። ንቁ! መጽሔትም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ለአምላክ ቃል ጥብቅና የቆመ መጽሔት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በ80 ቋንቋዎች 15,730,000 ቅጂዎች በመሠራጨት ላይ ናቸው።— ከቆላስይስ 1:23 ጋር አወዳድር።
2 መጽሔቶች የሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ያረካሉ፦ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት አርክተዋል። እምነት የሚገነቡ ርዕሶችን ለንባብ አብቅተዋል። ለምሳሌ ያህል በየካቲት 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ላይ በይሖዋና በቃሉ ላይ የመታመንን አስፈላጊነት የሚገልጽ ርዕስ አጥንተናል። የመጋቢት 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ በይሖዋ አገልግሎት ሥራ የበዛልን እንድንሆንና እርሱን መጠባበቃችንን እንድንቀጥል አበረታቶናል። ስለ ሶፎንያስ ትንቢት ያጠናነው ዝርዝር ማብራሪያ እንዴት የሚያነቃቃ ነበር! ከዚያ ቀጥሎ በመጋቢት 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ላይ ስለ ክርስቲያናዊ ታማኝነት እምነት የሚያጠነክር ትምህርት ነበር። የግንቦት 15, 1996 እትም የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብና ማጥናት ያለውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ነበር። እነዚህ ርዕሶች ስለ አምላክ ቃል ያለን ግንዛቤ እንዲሰፋና ለአምላክ መንግሥት ያለን አድናቆት እንዲጨምር አድርገዋል።
3 በተጨማሪ እነዚህ መጽሔቶች ስለ አምላካዊ ባሕርያት፣ ስለ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እንዲሁም ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላላቸው ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ወቅታዊና ተግባራዊ ትምህርቶች ይዘው ወጥተዋል። መጽሔቶቹ ሕይወታችንን የሚነኩ አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ። በዚህም ምክንያት የተሻለ ነገር እንደሚመጣ አምላክ የገባው ቃል እስከሚፈጸምም ድረስ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት አግኝተን በመደሰት ላይ ነን።— ኢሳ. 48:17፤ 1 ጢሞ. 6:19
4 በእያንዳንዱ ንቁ! መጽሔት እትም 4ኛ ገጽ ላይ የተገለጸውን ሐሳብ ባጭሩ መመልከታችን ይህ መጽሔት ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሊያነቡት የሚገባ ግሩም መጽሔት ነው ለማለት የሚያስችል ጥሩ ምክንያት ይሰጠናል። እንዲህ ይላል:- “ንቁ! ለመላው ቤተሰብ የሚጠቅም እውቀት ይገኝበታል። የዘመናችንን ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ያመለክታል። የዜና ዘገባዎችን ያቀርባል፣ በተለያዩ አገሮች ስለሚኖሩ ሕዝቦች ይናገራል፣ ሃይማኖትንና ሳይንስን ይመረምራል። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አይወሰንም። ከወቅታዊ ሁኔታዎች በስተጀርባ ያለውን እውነተኛ ሁኔታ ያስረዳል። ምንጊዜም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ነው። አንዱን ዘር ከሌላው አያስበልጥም። ከሁሉም በላይ ይህ መጽሔት አሁን ያለውን ክፉና ዓመፀኛ ሥርዓት የሚተካ ሰላም የሰፈነበት አስተማማኝ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ፈጣሪ በሰጠው ተስፋ ላይ ሰዎች ያላቸውን እምነት እንዲያሳድጉ ያደርጋል።”
5 መጽሔቶችን ለሌሎች አዳርሱ፦ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በማሠራጨት ረገድ ለጋስ ሁን። (ከ1 ጢሞቴዎስ 6:18 ጋር አወዳድር።) ለምታገኛቸው ሰዎች መጽሔቶቹን እንዲወስዱ መጋበዝ እንድትችል መጽሔቶቹ ከእጅህ አይለዩ። (መክ. 11:6) በዚህ ወር ወጣቶችንና አዳዲስ አስፋፊዎችን ጨምሮ ሁላችንም በቅርቡ በወጡት እትሞች ላይ የሚገኙትን ወቅታዊ ርዕሶች የተመረኮዙ አጠር ያሉ አቀራረቦችን ተጠቅመን መጽሔቶችን በማሠራጨት በኩል ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ እንችላለን። ከመጽሔቶቹ ይዘት ጋር በሚገባ ተዋወቅ፤ በተጨማሪም በነገሩ ላይ ጽኑ እምነት እንዳለህ በሚያሳይ መንገድ መጽሔቱን እንዲወስዱ ልባዊ ግብዣ አቅርብላቸው።
6 ማንኛውንም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ሁሉም ሰው የሚያስፈልገውን ትምህርት ይዘው ይወጣሉ። እነዚህን መጽሔቶች ማሠራጨት በቅርቡ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ስለሚገልጸው ምሥራች ሌሎች ሰዎች እንዲያውቁ መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለ ዘዴ ነው!