የአገልግሎት ክልልህን አጣርተህ ሸፍን
1 አልፎ አልፎ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንደ ኪዎስክ፣ ምግብ ቤት ወይም የችርቻሮ ሱቅ የመሳሰሉ አነስተኛ የንግድ ቤቶች ያጋጥሙናል። እነዚህ ቤቶች ከቀረው የአገልግሎት ክልል ጋር አብረው የሚሸፈኑ ከሆነ በመኖሪያ ቤቶቹ ውስጥ ያገኘሃቸውን ሰዎች ባነጋገርክበት መንገድ ልታነጋግራቸው ይገባል።
2 ቀላልና አጭር አቀራረብ በመጠቀም እንደሚከተለው ልትል ትችላለህ:- “አንድ ነገር ላሳይዎት ይዤ መጥቻለሁ።” በወቅቱ ባለቤቱ ሥራ የበዛበት የሚመስል ከሆነ ትራክት ካበረከትክለት በኋላ “እንደዛሬው ሥራ በማይበዛብዎት ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ። ስለዚህ ትራክት ምን አስተያየት እንዳለዎት ለማወቅ እፈልጋለሁ” ልትለው ትችላለህ።
3 ለሱቅ ሻጮች መመስከር ሊያስፈራን አይገባም። አንድ አስፋፊ እንዲህ ብሏል:- “የሰዎቹ ምላሽ አሉታዊ ይሆናል ብዬ ጠብቄ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎቹ ለመንግሥቱ መልእክት የሰጡት ምላሽ ካሰብኩት ፍጹም ተቃራኒ መሆኑ አስገርሞኛል። ትሑትና የወዳጅነት ስሜት የሚያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ ሁልጊዜ ማለት እችላለሁ መጽሔት ይወስዳሉ።”
4 በአንድ የሽያጭ ኩባንያ ውስጥ የምትሠራ ሴት የይሖዋ ምሥክሮችን ወደ ቢሮዋ እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። መጽሔቶቹን ከመቀበሏም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች። እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አሳዩአት፤ ወዲያው እዚያው ቢሮዋ ውስጥ ጥናት ተጀመረላት!
5 የአገልግሎት ክልልህን አጣርተህ እንድትሸፍን የተሰጠህ ኃላፊነት በአካባቢው በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ግለሰቦችን ማነጋገርንም ይጨምራል። (ሥራ 10:42 አዓት) ወደ ግል መኖሪያ ቤቶች ሄደህ ሰዎችን እንደምታነጋግር ሁሉ ወደ እነዚህም ቦታዎች ሄደህ ሰዎችን ለማነጋገር ዕቅድ አውጣ። እንዲህ ካደረግህ የአገልግሎት ክልልህን በተሻለ መንገድ ለመሸፈን ከመቻልህም በላይ አስደሳች ተሞክሮዎችን በማግኘት ልትባረክ ትችላለህ!