የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 11/96 ገጽ 3-4
  • ይሖዋን የሚያስከብር ሠርግ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋን የሚያስከብር ሠርግ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመንግሥቱ ሥራዎች ወጪ የሚሸፈንበት መንገድ
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • የሁሉም ነገር ባለቤት ለሆነው አምላክ ምን ልንሰጠው እንችላለን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • ለጽሑፎቻችን አድናቆት ይኑራችሁ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
  • በጉባኤም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ
    የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
km 11/96 ገጽ 3-4

ይሖዋን የሚያስከብር ሠርግ

1 መጠበቂያ ግንብ 4-105 “ደስታ የሚያመጣ ክርስቲያናዊ ሠርግ” የሚል ጭብጥ የያዘ ግሩም የሆነ የጥናት ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። በዚህ እትም ላይ ያለው ቀጣዩ የጥናት ርዕስ ጭብጥ “የጋብቻን ሥነ ሥርዓት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተደሰቱበት” የሚል ነው። (ለማግባት የሚያስብ ማንኛውም ግለሰብ የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው [ምዕራፍ 2] እና ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት [ምዕራፍ 19 እና 20] ከተሰኙት መጽሐፎች ጥበብ ያለበት ተጨማሪ ምክር ማግኘት ይችላል።) እነዚህ ትምህርቶች ከወጡ በኋላም ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር ሆነዋል፤ ስለዚህ በተለይ ለእኛ አካባቢ የሚሠሩ አንዳንድ ነጥቦችን ከእነዚህ ጽሑፎች ለማካፈልና እንዲሁም የሠርግ ግብዣዎች የጋብቻ መሥራች የሆነውን ይሖዋን የሚያስከብሩ እንዲሆኑ የሚረዱን ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችንም መጠቆም እንፈልጋለን።

2 በአንደኛ ደረጃ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ:- “ሠርግ መደረግ ያለበት መቼ ነው?” የሚለው ነው። የሠርጉ ዕለት በአካባቢው በተለመዱት “የሠርግ ወራት” መሆን ይኖርበታልን? የአካባቢው እምነት በዓመት ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ የሚደረገው ማንኛውም ሠርግ አይሰምርም የሚል ነው። እንዲህ ዓይነቱ እምነት መሠረተ ቢስ የሆነ አጉል እምነት ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋን በደስታና በአንድነት እያገለገሉ ያሉ ብዙ ባልና ሚስቶች በባህላዊው የሠርግ ወራት አልተጋቡም። እኛ በመልካምም ሆነ በመጥፎ ዕድል አናምንም። (ኢሳ. 65:11፤ ቆላ. 2:8) የሠርግ ቀናትን በእነርሱ አጉል እምነት ላይ ተመርኩዘን የምንወስን ከሆነ የማያምኑ ዘመዶች በእውነትና በሐሰት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲገነዘቡ አንረዳቸውም። ሐቁ ክርስቲያኖች በየትኛውም ወር ማግባት ይችላሉ።

3 የጋብቻ ንግግር እንዲቀርብ የተወሰነው አስፈላጊ የሆነው የማዘጋጃ ቤት ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ከሆነ በሁለቱ ሥርዓቶች መካከል የብዙ ቀን ልዩነት አለማድረግ ጥበብ ነው። ተጋቢዎቹ የጋብቻ ንግግር በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ከሆነ አዳራሹን ለመጠቀም እንዲችሉ ቀደም ብለው የጉባኤ ሽማግሌዎችን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ለሠርጉ የሚደረጉት ዝግጅቶች ለጉባኤው ሽማግሌዎች ንጹሕ ሕሊና የሚተውላቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ። ከማንኛውም የጉባኤ እንቅስቃሴ ጋር በማይጋጭ መንገድ የሠርጉ ንግግር የሚሰጥበት ሰዓት መወሰን ይኖርበታል። የጋብቻውን ንግግር እንዲያቀርብ የተመረጠው ወንድም ጠቃሚ የሆኑ ምክሮችን ለመለገስና ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ርኩሰት አለመፈጸማቸውን ወይም ለማግባት በሕግ ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሙሽራውንና ሙሽራይቱን ቀደም ብሎ ማነጋገር ይኖርበታል። በተጨማሪም ቀጥሎ እንዲከናወን የታቀደው ማኅበራዊ ግብዣ ምን መልክ እንደሚኖረው የእርሱ ስምምነት መኖሩ አስፈላጊ ነው። የጋብቻ ንግግራችን ግማሽ ሰዓት ያህል ርዝመት ያለው ሲሆን ጨዋነት በተላበሰና መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ባተኮረ መንገድ ይቀርባል። የጋብቻ ንግግሩ ከማንኛውም ድግስ የበለጠ ዋጋ እንዳለው መገንዘብ ይገባል።

4 የክርስቲያን ሠርግ ‘የዓለም ክፍል አለመሆናችንን’ የምናሳይበት ጥሩ አጋጣሚ ነው። (ዮሐ. 17:14፤ ያዕ. 1:27) ሥርዓታማነታችን ጉልህ ሆኖ መታየት ይኖርበታል። ይህም ሰዓት በማሳለፍ ተጋባዦችን ከማስጠበቅና ምናልባትም የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ላይ ችግር ከመፍጠር ይልቅ ሰዓት አክባሪዎች መሆን አለብን ማለት ነው። ይህን ጉዳይ በተለይ ሙሽራዋ የበለጠ ልታስብበት ይገባል፤ ምክንያቱም ዓለማዊ ዘመዶቿ ሙሽራዋ ተፈላጊ መሆኗን ለማሳየት እንድትዘገይ ሊጎተጉቷት ይችላሉ። አንዲት የጎለመሰች ክርስቲያን ሴት ሰዓት አክባሪ በመሆን ትህትናና አሳቢነትን የመሳሰሉ መንፈሳዊ ባሕርያትን ከፍ አድርጋ እንደምትመለከታቸው ልታሳይ ትችላለች! በተጨማሪም ሥነ ሥርዓቱን እንዲቀርጽ ፎቶ አንሺ በሚጋበዝበት ጊዜ ሥርዓታማነት አስፈላጊ ነው። ፎቶ አንሺው ኮት፣ ከረቫትና ተገቢ የሆነ ሱሪ ለብሶ እንዲመጣ ማሳሰባችን ተገቢ ነው። በተጨማሪም ፎቶ በሚያነሳበት ጊዜ ንግግሩን ማወክ አይኖርበትም። ጸሎት በሚደረግበት ጊዜ ፎቶ ማንሳት የተከለከለ ነው። ሥርዓታማ መሆናችን ይሖዋን ያስከብራል፤ እንዲሁም ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል። የሥነ ሥርዓቱን ትክክለኛ ትርጉም የሚያዛባ ማኅበራዊ ሥርዓት ለመከተል መሞከር አስፈላጊ አይደለም።

5 ድግስ የተሳካ ጋብቻ ለመመሥረት የሚያበቃ መሥፈርት አይደለም። እርግጥ ነው ቅዱስ ጽሑፉ እንዲህ ዓይነቱን አስደሳች ወቅት አይከለክልም። ያም ሆኖ ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያዘጋጁት ግብዣ በአባካኝነት፣ አለ ልክ በመጠጣትና በመብላት፣ መረን በለቀቀ ሙዚቃ፣ የጾታ ስሜት በሚያነሳሳ ዳንስና በጠበኝነት ከሚታወቀው ዓለማዊ ግብዣ የተለየ መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ፈንጠዝያን” የሚመድበው ከሥጋ ሥራዎች ጋር ነው። (ገላ. 5:21 አዓት) ተጋባዦቹ በጣም ብዙ በማይሆኑበት ጊዜ ተገቢ የሆነ ቁጥጥር ለማድረግ ቀላል ይሆናል። የአካባቢውን ባህል ለመከተል ሲባል ብቻ ድንኳን መትከል አስፈላጊ አይደለም። አንዳንዶች በቦታ ጥበትና በአየሩ ጠባይ ምክንያት ድንኳን መትከል አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት ይህ በግላቸው የሚወስኑት ጉዳይ ነው።

6 ሰዎችን በጥሪ ወረቀት አማካኝነት መጋበዝ የእንግዶችን ቁጥር ለመገደብ የሚያስችል ጥሩ መንገድ እንደሆነ ተሞክሮ አሳይቷል። መላውን ጉባኤ በአንድነት ከመጋበዝ ይልቅ እያንዳንዱን ግለሰብ በግል መጋበዝ ጥበብ ነው። እንዲሁም ሥርዓታማ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ያለውን ገደብ ማክበር ይኖርብናል። የጥሪ ወረቀት መጠቀም የተወገደ ግለሰብ በግብዣ ቦታ ላይ ድንገት እንዳይገኝ ለማድረግ ይረዳል። አንድ የተወገደ ግለሰብ በግብዣ ቦታ ላይ ቢገኝ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ግብዣውን አቋርጠው ለመሄድ ሊመርጡ ይችሉ ይሆናል። (1 ቆሮ. 5:9-11) ተጋቢዎቹ የማያምኑ ዘመዶቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን የሚጋብዙ ከሆነ የእምነት ባልደረቦቻቸው የሆኑትን ለማስበለጥ ሲሉ ቁጥራቸውን ውስን እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለውም። (ገላ. 6:10) አንዳንዶች የሚያውቋቸውን ዓለማውያን ወይም የማያምኑ ዘመዶቻቸውን በምግብ ግብዣ ላይ ከመጥራት ይልቅ የጋብቻ ንግግር በሚሰጥበት ቦታ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ መርጠዋል። ለምን? ብዙ ወንድሞችና እህቶች በግብዣው ላይ መቆየት እንደማይችሉ እስኪሰማቸው ድረስ ዓለማዊ ዘመዶች በሠርግ ግብዣ ላይ አሳፋሪ ድርጊቶችን እንደፈጠሩ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። አንዳንድ ሙሽራዎች ለቅርብ ቤተሰቦቻቸው አባላትና ለክርስቲያን ወዳጆቻቸው ቀለል ያለ ራት አዘጋጅተዋል።

7 ከዮሐንስ 2:8, 9 (የ1980 ትርጉም) ጋር በሚስማማ መንገድ “የግብዣ ኃላፊ” መመደብ ተገቢ ነው። ሙሽራው ሥርዓታማነትና ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ መጠበቁን የሚከታተል የታመነ ክርስቲያን ለመምረጥ ይፈልጋል። ወዳጆች ስጦታ ይዘው የሚመጡ ከሆነ ‘የይታይልኝ መንፈስ’ ሊንጸባረቅ አይገባም። አጠያያቂ ግጥም፣ ከፍተኛ ጩኸት ወይም የብልግና ውዝዋዜ የማይፈጥር ሙዚቃ መጠቀም አስደሳች ሊሆን ይችላል። የሚቀርቡት ዘፈኖች ምን ዓይነት እንደሆኑ ለማወቅ አንድ ሽማግሌ ቀደም ብሎ ቢያዳምጣቸው ብዙዎች የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። ብዙ ባሕላዊ ውዝዋዜዎች ከመራባት አምልኮ ጋር የተያያዙና የጾታ ስሜት የሚያነሳሱ በመሆናቸው ውድቀት ሊያስከትሉ ይችላሉ። “ኬክ የሚቆረስበትና ሻምፓኝ የሚከፈትበት” ጊዜያት ዓለማዊ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ልቅ የሆነ ባሕርይ የሚያሳዩበት ወቅት ነው። ብዙ ክርስቲያን ተጋቢዎች በሠርጋቸው ግብዣ ወቅት የአልኮል መጠጥ እንዳይኖር በመወሰናቸው ምክንያት ችግሮች የሚፈጠሩበትን አጋጣሚ አስወግደዋል።

8 ይሖዋን ማስከበር የምንፈልግ እስከሆንን ድረስ ከመጠን ያለፈ ትኩረት ወደ ራሳችን ከመሳብ እንርቃለን። ዓለማዊ ጽሑፎች እንኳን ሳይቀሩ ብዙ ሰዎች የሚያሳዩትን የአባካኝነት መንፈስ ተችተዋል። ቅጥ ያጣ ሠርግ ለማዘጋጀት ሲሉ ለአንድ ቀን ያወጡትን ገንዘብ ለመክፈል ለዓመታት ችግር ላይ ቢወድቁ እንዴት ያለ ጥበብ የጎደለው ድርጊት ነው። በሠርጉ ቀን የሚለበሰው ልብስም ቢሆን አምላክን እናከብራለን ለሚሉ ሰዎች የተገባና ሥርዓታማ መሆን አለበት። (1 ጢሞ. 2:9, 10) “የክርስቲያን ሠርግ ምክንያታዊነትን ማንጸባረቅ ይኖርበታል” በሚል ርዕስ (ጥር 15, 1969 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ) ልብስን አስመልክቶ የወጣው ትምህርት የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ አስፍሮ ነበር:-

9 “አንድ ሰው የሠርግ ቀኑ ልዩ የሆነ ወቅት ስለሆነ አስደሳችና ማራኪ ሆኖ ለመታየት ጥረት ያደርጋል። ይህ ማለት ግን አንድ ሰው በሚለብሰው ልብስ አንድ ዓይነት ደንብ መከተል አለበት ማለት አይደለም። አንድ ሰው በአካባቢው ተቀባይነት ያለው የአለባበስ ልማድ፣ ወጪውንና የግል ምርጫውን በጉዳዩ ውስጥ ያስገባል። . . . ይሁን እንጂ በጣም ውድ የሆነ ልብስ ለመግዛት ሲባል ራሳቸውንና ሌሎች ሰዎችን ዕዳ ውስጥ መጨመር ምክንያታዊነት ነው? . . . አንዳንድ የሴት ሙሽሮች የቅርብ ወዳጃቸውን ወይም የዘመዳቸውን የሙሽራ ልብስ ተውሰው ለብሰዋል። ሌሎች ደግሞ በሌላ ጊዜም ሊለበስ የሚችል የራሳቸውን የሙሽራ ልብስ በማዘጋጀታቸው ተደስተዋል። ሙሽሮቹ በሠርጋቸው ወቅት የክት ልብሳቸውን ለብሰው ቢጋቡ ምንም ስህተት የለውም። . . . ሌሎች ደግሞ ትልቅ የሠርግ ድግስ የማዘጋጀት አቅም እያላቸው የጊዜውን አስጨናቂነት ግምት ውስጥ በማስገባት ‘ቀለል ያለ የሠርግ ዝግጅት’ ለማድረግ በግላቸው ሊመርጡ ይችላሉ። . . .— 2 ጴጥ. 3:12”

10 በተመሳሳይም የሙሽራውና የሙሽራይቱ ሚዜዎች ብዙ መሆን አያስፈልጋቸውም። እነርሱም ቢሆኑ በአለባበሳቸውና በድርጊታቸው የማያስፈልግ ትኩረት ወደ ራሳቸው ለመሳብ መሞከር አይኖርባቸውም። የተወገደ ግለሰብ በመንግሥት አዳራሹ በሚሰጠው ንግግር ላይ እንዲገኝ ሊፈቀድለት ቢችልም መጠበቂያ ግንብ 4-105 እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የተወገዱ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በከፍተኛ ሁኔታ የሚቃረን አኗኗር ያላቸውን ግለሰቦች ሚዜ ማድረግ ፍጹም የተገባ አይደለም።”

11 ኢየሱስ ሠርግ ላይ የተገኘ ቢሆንም እንኳን ዛሬ ቢኖር ኖሮ የአካባቢውን ልማድ በመከተል ሙሽሮችን አጅበው ከፍተኛ ድምፅ እያሰሙ ከተማ በመኪና ከሚዞሩና በሚያሰሙት የጥሩንባ ድምፅ የተነሳ ትራፊክ ከሚቀጣቸው ሹፌሮች ጋር አብሮ ይጓዝ ነበር ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው። (ማቴ. 22:21) ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያኖች አሕዛብ የሚያሳዩትን የይታይልኝ መንፈስና አድራጎታቸውን ከመቅዳት ይልቅ በትሑታን ዘንድ ያለውን ጥበብ ያንጸባርቃሉ።— ምሳሌ 11:2

12 በጎረቤቶች፣ በዓለማዊ የሥራ ባልደረቦች ወይም በሩቅ ጓደኞች ሠርግ ላይ ስለ መገኘትስ ምን ለማለት ይቻላል? በዚህ ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን የራሱን ውሳኔ ያደርጋል። ለአገልግሎት፣ ለግል ጥናት፣ ለቤተሰብና ለጉባኤ ሥራዎች ጊዜ ስለሚያስፈልገን ጊዜያችን ውድ መሆኑን ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ኤፌ. 5:15, 16) ስብሰባዎች እንዲሁም ልንሰርዘው የማንፈልገው የመስክ አገልግሎት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ላይ ይደረጋሉ። (ዕብ. 10:24, 25) ብዙ ሠርጎች ትልልቅ ስብሰባዎች በሚደረጉበት ወቅት ወይም ለአገልግሎት ትልቅ ትኩረት በሚሰጥበት የጌታ ራት ሰሞን ይከናወናሉ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞቻችን እንደሚያደርጉት ተመሳሳይ የሆነ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ትኩረታችን ወደ ሌላ ዞር እንዲል መፍቀድ አይኖርብንም። እውነትን ከማወቃችን በፊት አምላክን በማያስከብር ተግባር በመሳተፍ ከዓለማዊ ሰዎች ጋር ብዙ ሰዓት አጥፍተን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3, 4) አሁን ግን ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ተለውጧል። አዲስ ለተጋቡ ዓለማዊ ባልና ሚስት ካርድ በመላክ ወይም በሌላ ጊዜ እቤታቸው ጎራ በማለት መልካም ምኞት መግለጽ ይቻላል። እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ምሥክርነት ለመስጠትና አዲስ ለተጋቡ ሰዎች የሚስማማ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶችን ለማካፈል ተጠቅመውበታል።

13 ከዓለማዊ ልማዶች ይልቅ መንፈሳዊ ይዘት ያለው ሠርግ በእርግጥም ይሖዋን ያስከብራል። ክርስቲያኖች አጉል ልማድና አባካኝነት ከሞላበት ዓለም ሙሉ በሙሉ በመለየት፣ ዕለታዊ እንቅስቃሴያችንን እንዲያደናቅፍብን ባለመፍቀድ፣ ይታይልኝ ከሚል መንፈስ ይልቅ ልከኝነትን በማንጸባረቅ ከሠርግ ግብዣዎች ደስታ ያገኛሉ። እንዲሁም ወቅቱን በጥሩ ሕሊናና አስደሳች በሆነ ትዝታ ወደ ኋላ ተመልሰው ማስታወስ ይችላሉ። ሁሉም የክርስቲያን ሠርጎች ልበ ቅን ለሆኑ ተመልካቾች ምሥክርነት የሚሰጡና ጥበበኞችና ምክንያታዊ መሆናችንን የሚያሳዩ ይሁኑ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ