1 ይሖዋ የተትረፈረፉ ስጦታዎችን ሰጥቶናል። ጥሩነቱና ፍቅራዊ ደግነቱ ‘የማይነገር ስጦታ’ በሚል በጥሩ መንገድ ጠቅለል ተደርጎ ተገልጿል። አዎን፣ ‘ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት’ እጅግ አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ነው።—2 ቆሮ. 9:14, 15 NW
2 ከሁሉ የላቀ ስጦታው፦ ከሁሉ የላቀው ስጦታ ለሰው ልጆች ቤዛ እንዲሆን የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይሖዋ ለሰው ልጆች ዓለም ያለውን ታላቅ ፍቅር የገለጸው የሚወድደውን አንድያ ልጁን በመስጠት ነው። (ዮሐ. 3:16) ይህ ዓይነቱ ይገባናል የማንለው ስጦታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊከበር ይገባዋል። መቼና እንዴት? ሐሙስ፣ ሚያዝያ 1, 1999 ምሽት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ከመሥዋዕቶች ሁሉ የላቀውን የዚህን መሥዋዕት መታሰቢያ በማስታወስ የጌታ ራትን ያከብራሉ።—1 ቆሮ. 11:20, 23-26
3 ክርስቶስ ለእኛ ሲል የሞተው “ገና ኃጢአተኞች ሳለን” ነው። በመሆኑም የእርሱን ሞት መታሰቢያ በማክበርና ሌሎችም በዚህ ከፍተኛ ትርጉም ባለው ሥነ ሥርዓት ላይ ከእኛ ጋር እንዲገኙ በመጋበዝ በግል አመስጋኝነታችንን ልናሳይ እንችላለን።—ሮሜ 5:8
4 ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ ክንውን፦ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል በአንደኛ ደረጃ ኢየሱስ ያላንዳች እንከን የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፉ ጎላ ብሎ የሚታይበት አጋጣሚ ነው። በተጨማሪም በዓሉ በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደር በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም ሊኖረን እንደሚችል እንዲሁም መዳን እንደምናገኝ እርግጠኛ እንድንሆን ያስችለናል። (ሥራ 4:12) በእርግጥም ይህ እጅግ ከፍተኛ ትርጉም ያለው የዓመቱ ክንውን ነው!
5 ሰዎች ከእኛ ጋር ሆነው የጌታ ራትን እንዲያከብሩ መጋበዛችን ለእነርሱ ያለንን ፍቅር ያሳያል። ቤዛው ስላለው ላቅ ያለ ዋጋ የሚማሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤዛው ጥቅም ተካፋይ መሆን እንዲችሉ አጋጣሚው አሁንም ክፍት ነው። (ፊልጵ. 3:8) በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት የሚያሳድሩ ሰዎች እርግጠኛ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል።—ዮሐ. 17:3
6 የመታሰቢያው በዓል ወቅት አምላክ ላሳየን አቻ የማይገኝለት ይገባናል የማንለው ደግነት አድናቆታችንን ለመግለጽ የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ይሰጠናል። ይህ ወቅት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በቅንዓት ለመስበክ በጣም ግሩም አጋጣሚ ነው። ይሖዋ ስለሰጠን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነፃ ስጦታ ከልብ የሚያስቡና በዚህ ዓመት በሚከበረው የጌታ ራት ላይ የሚገኙ ሁሉ ብዙ ጥቅም ይጠብቃቸዋል!