“መሄድ ይኖርብኝ ይሆን?”
1 ራሳቸውን የወሰኑ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ለሚለው የኢየሱስ ትእዛዝ ምላሽ በመስጠት ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ለማገልገል ሄደዋል። (ማቴ. 28:19) እነዚህ ወንድሞች “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” ለሚለው ጥሪ ምላሽ የሰጠውን የጳውሎስን ምሳሌ በመኮረጅ ላይ ናቸው። (ሥራ 16:9) ለዚህ ጥሪ ተግባራዊ በሆነ መንገድ ምላሽ መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው?
2 በአንድ ጊዜ አንድ እርምጃ ውሰድ:- በጉባኤህ ውስጥ አልፎ አልፎ ብቻ የሚሠራበት ክልል አለ? ካለ ይህን ክልል ለመሸፈን ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ ከመወሰንህ በፊት ያደረግከው ዝግጅት በቂ መሆንና አለመሆኑን በተመለከተ የጉባኤህ ሽማግሌዎች ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ አማክራቸው። እንዲሁም አገልግሎትህን ልታሰፋበት የምትችለው በአቅራቢያህ አንድ ጉባኤ ካለ እንዲነግርህ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ማነጋገር ትችላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ወጪውን በጥንቃቄ ካሰላህ በኋላ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሄደህ ለመርዳት ታስብ ይሆናል። ጠቅልሎ ለመሄድ ወይም ላለመሄድ ከመወሰን በፊት አካባቢውን ሄዶ ማየት ጥበብ ሊሆን ይችላል።
3 ስደተኝነት ሊያስከትል የሚችለውን ሁኔታ ማጤን:- ብዙ ወንድሞቻችን የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ወይም ከእንግልት ለመገላገል ሲሉ ወደ ሌሎች አገሮች በመሄድ ላይ ናቸው። በዚህ ጊዜ አንዳንዶች አዲሱን አገር እናላምዳችኋለን በሚል ሰበብ ተጠግተው ገንዘባቸውን ከበሉ በኋላ ዞር ለሚሉ አታላዮች ተዳርገዋል። እንዲያውም አንዳንዴ እነዚህ ግለሰቦች ስደተኞቹ የጾታ ብልግና መገልገያ እንዲሆኑ ለማስገደድ እስከመሞከር ይደርሳሉ። እምቢ ካሉ ወደዱም ጠሉ በስደት ያሉበት አገር በሚጥልላቸው ነገር ብቻ ለመኖር ይገደዳሉ። በዚህ የተነሳ የስደተኞች ኑሮ በአገራቸው ከሚያጋጥማቸው ሁኔታ እጅግ የከፋ ይሆናል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ወንድሞች እንዲያስጠጓቸው አሊያም እንዲረዷቸው መጠየቅ ግድ ይሆንባቸው ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ከራሳቸው ችግሮች ጋር በሚታገሉ ክርስቲያን ቤተሰቦች ላይ ሸክም መጨመር ነው። አንዳንዶች ወደ ውጭ በመሄድ ረገድ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ በማድረጋቸው የቤተሰብ አባላት ከመበታተናቸውም ሌላ ቤተሰቦች በመንፈሳዊ ተዳክመዋል።—1 ጢሞ. 6:8-11
4 ከግል ጥቅም አንጻር ወደ ሌላ አገር ለመሄድ የምትፈልግ ከሆነ የትም ኑር የት የምትጋፈጣቸው ችግሮች እንደሚኖሩ አትዘንጋ። በማታውቀው አገር አዲስ ሕይወት ከመጀመር ቋንቋውንና ባሕሉን በምታውቀው አካባቢ ችግሮችን ተቋቁሞ መኖር ይበልጥ ቀላል ነው።