ጥሩ አዳማጭ ሁኑ
1 በጥሞና ለማዳመጥ ራስን መገሠጽ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም አዳማጩ ከሚነገረው ነገር ትምህርትና ጥቅም ለማግኘት ፍላጎት ሊያድርበት ይገባል። ከዚህ የተነሳ ኢየሱስ “እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ” በማለት አስፈላጊነቱን ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል።—ሉቃስ 8:18፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
2 በተለይ በጉባኤ፣ በወረዳና በልዩ እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በጥሞና ማዳመጣችን በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህ በጥሞና ልናዳምጥባቸው የሚገቡ ወቅቶች ናቸው። (ዕብ. 2:1) በእነዚህ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስትገኙ ጥሩ አዳማጮች ለመሆን የሚረዷችሁ አንዳንድ ነጥቦች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።
◼ የስብሰባዎቹን አስፈላጊነት ተገንዘቡ። ‘በታማኙ መጋቢ’ አማካኝነት ‘ከይሖዋ የምንማርባቸው’ ዋነኛ መንገዶች ናቸው።—ኢሳ. 54:13፤ ሉቃስ 12:42
◼ አስቀድማችሁ ተዘጋጁ። ውይይት የሚደረግበትን ትምህርት ቀደም ብላችሁ አንብቡ። እንዲሁም ወደ ስብሰባ ስትመጡ መጽሐፍ ቅዱስንና የሚጠኑትን ጽሑፎች መያዝ አትርሱ።
◼ ስብሰባው በሚካሄድበት ጊዜ ሐሳባችሁን ሰብስባችሁ ለማዳመጥ ልዩ ጥረት አድርጉ። አጠገባችሁ ከተቀመጠ ሰው ጋር ማውራትም ሆነ አንዳንዶች በሚያደርጉት ነገር ሐሳባችሁ እንዲከፈል መፍቀድ የለባችሁም። ከስብሰባው በኋላ ስለምታደርጉት ነገር ወይም ስለ ሌሎች ጉዳዮቻችሁ በማሰብ ትኩረታችሁ እንዲከፋፈል አትፍቀዱ።
◼ እየቀረበ ባለው ትምህርት ላይ በጥሞና ለማሰብ ሞክሩ። ‘ትምህርቱ እኔን የሚነካኝ እንዴት ነው? ተግባራዊ የማደርገው መቼ ነው?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።
◼ ዋና ዋና ነጥቦቹንና ጥቅሶችን በአጭሩ በማስታወሻችሁ ላይ ጻፉ። እንዲህ ማድረጋችሁ ሐሳባችሁ በትምህርቱ ላይ እንዲያተኩርና ቁልፍ ነጥቦችን በሥራ ላይ ማዋል ስትፈልጉ ማስታወስ እንድትችሉ ይረዳችኋል።
3 ልጆቻችሁን እንዲያዳምጡ አስተምሯቸው:- ልጆች መንፈሳዊ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። (ዘዳ. 31:12) ጥንት ሕጉ ለአምላክ ሕዝቦች ሲነበብ ‘አስተውለው የሚሰሙ ሁሉ’ በጥሞና ማዳመጥ ይጠበቅባቸው ነበር። (ነህ. 8:1-3) ወላጆች በስብሰባው የሚመሰጡና በጥሞና የሚያዳምጡ ከሆነ ልጆቻቸውም እንዲሁ ያደርጋሉ። ልጆች እንዳይረብሹ በማሰብ መጫወቻዎችንና የሥዕል መጽሐፎች መስጠት ትክክል አይደለም። ሳያስፈልግ ቶሎ ቶሎ ወደ መጸዳጃ ቤት የሚሄዱ ከሆነም ሳያዳምጡ ይቀራሉ። ‘ስንፍና በሕፃን ልብ ስለታሰረ’ ወላጆች ልጆቻቸው በስብሰባ ላይ አርፈው እንዲቀመጡና በጥሞና እንዲያዳምጡ ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል።—ምሳሌ 22:15
4 ጥሩ አዳማጭ በመሆን በእርግጥም ጠቢባን መሆናችንንና ‘ተጨማሪ ጥበብ’ ማግኘት እንደምንፈልግ እናሳያለን።—ምሳሌ 1:5