ደስተኛ አድራጊዎች ሁኑ
1 በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ አብዛኞቹ ሰዎች መገኘቱን ‘እንደማያስተውሉ’ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴ. 24:37-39) በመሆኑም ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች መስማት አለመፈለጋቸው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። ታዲያ አገልግሎታችንን በምንፈጽምበት ጊዜ የደስተኝነት ስሜታችንን ጠብቀን እንድንኖር ምን ሊረዳን ይችላል?—መዝ. 100:2
2 በመጀመሪያ ደረጃ፣ መልእክታችንም ሆነ የስብከት ተልዕኳችን ከአምላክ የተሰጠን መሆኑን መገንዘብ ይገባናል። አቅማችን የፈቀደውን ያህል ጥረን በአገልግሎቱ ምላሽ ቢጠፋ ምላሽ የተነፈገው ይሖዋ ነው። በስብከቱ ሥራ በታማኝነት መካፈላችን ሞገሱን እንደሚያስገኝልን ማሰባችን የአምላክ ቃል አድራጊዎች በመሆን ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል።—ያዕ. 1:25
3 በሁለተኛ ደረጃ፣ አሁንም ቢሆን የይሖዋን የመዳን ዝግጅት የሚቀበሉ ሰዎች አሉ። አብዛኞቹ ሰዎች ግድ የለሽ ቢሆኑም ወደ መጨረሻው ዘመን ዘልቀን በገባንበት በዚህ ጊዜ በግ መሰል ሰዎች ገና በመሰብሰብ ላይ ናቸው። “በዚያ የሚገባው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ” ለመመርመር ወደ “ማናቸውም ከተማ ወይም መንደር” እየገባን መስበካችንን መቀጠል ያስፈልገናል።—ማቴ. 10:11-13
4 አዎንታዊ አመለካከት ያዙ:- የሐሰት ሃይማኖት ያስመዘገበው አሳዛኝ ታሪክ አንዳንዶችን ግራ አጋብቷል። ይህ የነገሮች ሥርዓት አንዳንዶችን ‘የተጨነቁና የተጣሉ’ አድርጓቸዋል። (ማቴ. 9:36) ብዙዎች ሥራ፣ ሕክምናና ዋስትና በማጣታቸው ተስፋ ቆርጠው ሊሆን ይችላል። ይህን ማወቃችን ሳንታክት እንድንሠራ ይረዳናል። በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በጣም ስለሚያሳስባቸው ጉዳዮች አንስተን ውይይት ለማስጀመር ጥረት እናድርግ። የአምላክ መንግሥት ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዳቸው። ምሥራቹ ልባቸውን እንዲነካ ለማድረግ በጥቅሶችና ከጽሑፎች ላይ በተመረጡ ነጥቦች ተጠቀም።—ዕብ. 4:12
5 ደስተኛ የቃሉ አድራጊዎች ‘የይሖዋ ደስታ ኃይላቸው’ እንደሆነ ፈጽሞ አይዘነጉም። (ነህ. 8:10) ደስታ የምናጣበት ምንም ምክንያት የለም። “ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ።” (ማቴ. 10:13) ቅዱስ በሆነው አገልግሎቱ በትዕግሥት ከጸናን ይሖዋ ደስታችንንና ኃይላችንን ያድስልናል እንዲሁም ታማኝ ሆነን በመገኘታችን ይባርከናል።