‘በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል’
1 የክርስቲያን ጉባኤ ተቀዳሚ ሥራ የመንግሥቱን መልእክት በመላው ዓለም መስበክ ነው። (ማቴ. 24:14) ይህ በጣም ሰፊ ሥራ ነው። ከዳር ሆነው ለሚመለከቱን ሥራው አሁን እኛ ካለን የበለጠ ጥሪት እንደሚጠይቅ ሆኖ ይታያቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሰዎች ስለሚያፌዙብን፣ ተቃውሞና ስደት ስለሚያጋጥመን ተልእኮውን መወጣት የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ማቴ. 24:9፤ 2 ጢሞ. 3:12) ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች ሥራው ፈጽሞ ዳር ሊደርስ እንደማይችል ያምናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል” ብሏል።—ማቴ. 19:26
2 ልንመስላቸው የሚገቡ በጎ ምሳሌዎች:- ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር በወቅቱ በነበረው የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ምንም ደጋፊ አልነበረውም። ተልእኮው እንዳይሳካለት ለማድረግ ተቃዋሚዎች እርሱን ለማዋረድ የቻሉትን ያህል ከመጣርም አልፈው በመጨረሻ በአሠቃቂ ሁኔታ እንዲሞት አድርገዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በስተ መጨረሻ “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ሲል በትምክህት ተናግሯል። (ዮሐ. 16:33) ይህ በእውነትም ድንቅ ስኬት ነው!
3 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ከእሱ ጋር የሚመሳሰል ድፍረትና ቅንዓት አሳይተዋል። ብዙዎቹ ተገርፈዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል ሌላው ቀርቶ ተገድለዋል። ይሁን እንጂ “ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ” ተደስተዋል። (ሥራ 5:41) ብዙ እንቅፋቶች ቢገጥሟቸውም ከላይ ሲታይ የማይቻል የሚመስለውን ምሥራቹን ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ የመስበክ ሥራ በተሳካ ሁኔታ አከናውነዋል።—ሥራ 1:8፤ ቆላ. 1:23
4 በዘመናችን ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው? እኛም የተለያዩ እንቅፋቶች ቢገጥሙንም ስለ መንግሥቱ በመስበኩ ሥራ በቅንዓት እየተካፈልን ነው። ሥራችንን እንድናቆም ለማድረግ እገዳ ቢጣልብንም፣ ስደት ቢደርስብንም፣ እስራትና ሌሎች የኃይል እርምጃዎች ቢወሰዱብንም ስኬት እያገኘን ነው። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” (ዘካ. 4:6) ይሖዋ ከጎናችን ሆኖ ስለሚደግፈን ሥራችንን ምንም ነገር ሊያስቆመው አይችልም!—ሮሜ 8:31
5 በምንሰብክበት ጊዜ የምንፈራበት ወይም ብቃቱ አይኖረን ይሆናል ብለን የምንሸማቀቅበት ምንም ምክንያት የለም። (2 ቆሮ. 2:16, 17) የመንግሥቱን ምሥራች እያስፋፋን ወደፊት ለመገስገስ የሚያስችል ትልቅ ምክንያት አለን። በይሖዋ እርዳታ ‘የማይቻለውን’ ነገር እናደርጋለን!—ሉቃስ 18:27