‘ሁልጊዜ መልካም ለማድረግ ትጉ’
1 ክርስቲያናዊ ሕይወት ለሰው ‘ሁሉ መልካም ለማድረግ መትጋትን’ የሚጠይቅ ነው። (1 ተሰ. 5:15) በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለሌሎች መልካም ማድረግ የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እናገኛለን። እንዲህ ባሉት ጊዜያት ሰዎች ስለ እኛ ብዙ ነገሮችን ማስተዋል እንዲሁም እነርሱን ከምንይዝበት መንገድ በመነሳት ስለ እኛ አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆናችን መጠን መልካም ስማችንን ጠብቀን ለመኖር ‘ሁሉን ሰው እንደምናከብር’ በድርጊታችን ማሳየት ያስፈልገናል። (1 ጴጥ. 2:17) ይህም ‘ለራሳችን የሚጠቅመንን ሳይሆን የሌሎችን ጥቅም መመልከትን’ ይጨምራል። (ፊልጵ. 2:4) ይህ የልጆቻችንን ጠባይ በተመለከተ እንዴት እንደሚሠራ እንመልከት።
2 ልጆቻችን መልካም እንዲያደርጉ ማስተማር፦ ወላጆቻቸው በቅርብ የማይከታተሏቸው አንዳንድ ልጆች ችግሮች ሲፈጥሩ ይታያሉ። (ምሳሌ 29:15) አንዳንድ ጊዜ ይህ የሚሆነው ወላጆች በሌሎች ጉዳዮች ተጠምደው ልጆቻቸውን ሳይቆጣጠሩ ስለሚቀሩ ነው። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ልጆች በጣም የሚረብሹ ከመሆናቸው የተነሳ ምሥክሮችንም ሆነ ምሥክር ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችን ያስቸግራሉ።
3 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ምን ዓይነት ክርስቲያናዊ ባሕርይ ሊያሳዩ እንደሚገባ ከአውራጃ ስብሰባው በፊት ጊዜ ወስዳችሁ ብታነጋግሯቸው ጥሩ ይሆናል። (ኤፌ. 6:4) ለምሳሌ ያህል፣ እውነተኛ የሆነ ክርስቲያናዊ ፍቅር ‘የማይገባውን እንደማያደርግ፣ የራሱን ጥቅም እንደማይፈልግ፣ እንደማይበሳጭ’ አሳዩአቸው። (1 ቆሮ. 13:5) አዋቂዎች ለሁሉም መልካም አርዓያ በመሆን ለእነዚህ ቃላት አጽንዖት ሊሰጡ ይችላሉ። ልጆች፣ ወላጆቻችሁን በመታዘዝ፣ የሌሎችን ንብረት ላለማበላሸት ጥንቃቄ በማድረግና አብረዋችሁ ላሉት አሳቢነት በማሳየት መልካም ማድረግ ትችላላችሁ። (ቆላ. 3:20) በአንድነት ለሰዎች ሁሉ መልካም ለማድረግ ስንጥር ‘ስለ አዳኛችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር እናስመሰግናለን።’—ቲቶ 2:9-10