‘ብርሃን አብሪ መሆን’
1 በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባር ባዘቀጠው በዚህ ሥርዓት ውስጥ በዓለም ዙሪያ በ234 አገሮች ስድስት ሚልዮን የሚያህሉ የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ አምላኪዎች ‘እንደ ብርሃን ይታያሉ።’ (ፊልጵ. 2:15) ይህ በቀላሉ ተለይተን እንድንታወቅ ያደርገናል። ከይሖዋ የሚመነጨውን የከበረ የእውነት ብርሃን ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?—2 ቆሮ. 3:18
2 በምግባራችን:- ሰዎች የምናንጸባርቀውን ባሕርይ በቀላሉ ይመለከታሉ። (1 ጴጥ. 2:12) አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክር የሆነው የሥራ ባልደረባዋ ደግና ተባባሪ እንደሆነ እንዲሁም ጸያፍ ቃላት እንደማይናገርና የብልግና ቀልዶች ሲነገሩ አብሮ እንደማይስቅ አስተዋለች። ሌሎች እሱ ባለበት የብልግና ቃላት እየተናገሩ ሊያናድዱት ሲሞክሩ ታግሦ ቢያልፍም ትክክል ለሆነው ነገር ያለውን አቋም አያላላም ነበር። ይህ ሴትዮዋን ምን እንድታደርግ አነሳሳት? እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ባሕርይው በጣም ስላስገረመኝ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ጠየቅሁት። የአምላክን ቃል ማጥናት ጀመርኩና ከጊዜ በኋላ ተጠመቅሁ።” አክላም እንዲህ ብላለች:- “የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው እንደሚያምኑ እንድመረምር ያነሳሳኝ የእሱ ባሕርይ ነበር።”
3 ለባለ ሥልጣናት ያለን አመለካከት፣ ዓለማዊ ልማዶችን በተመለከተ ያለን አቋምና ጤናማ ንግግራችን የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚመሩ ሕዝቦች መሆናቸውን አጉልቶ ያሳያል። እንዲህ ያለው መልካም ሥራ ይሖዋን የሚያስከብር ከመሆኑም በላይ ሌሎችም እርሱን እንዲያመልኩ ያነሳሳቸዋል።
4 በአንደበታችን:- እርግጥ ነው፣ በመልካም ባሕርያችን የሚያውቁን ሰዎች ስለ እምነታችን ካልነገርናቸው በስተቀር ከሌሎች የተለየነው ለምን እንደሆነ ሊያውቁ አይችሉም። የሥራ ባልደረቦችህ ወይም አብረውህ የሚማሩት ልጆች የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ያውቃሉ? በዕለት ተዕለት ጭውውቶች መሃል ምሥክርነቱን ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ስታገኝ ትጠቀምባቸዋለህ? በማንኛውም ተስማሚ አጋጣሚ ‘ብርሃንህን በሰው ፊት ለማብራት’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?—ማቴ. 5:14-16
5 ብርሃን አብሪዎች እንድንሆን የተሰጠንን ተልዕኮ መፈጸም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስን ይጠይቃል። አምላክን በሙሉ ነፍስ የማገልገል ዝንባሌ ሕይወት አድን በሆነው የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን መተውን ይጠይቃል።—2 ቆሮ. 12:15
6 በምግባራችንና በአንደበታችን ብርሃን ማብራታችንን እንቀጥል። እንዲህ ካደረግን ሌሎችም ከእኛ ጋር ይሖዋን ለማክበር ይነሳሳሉ።