መለኮታዊ ድጋፍ ያለው ሥራ
1 በዛሬው ጊዜ ካሉት የአምላክ አገልጋዮች መካከል ከፍተኛ ትምህርት፣ ሃብት ወይም ሥልጣን ያላቸው በጣም ጥቂት ናቸው። ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች የስብከቱ ሥራችን ምንም ፋይዳ እንደሌለው በማሰብ መልእክቱን ለመስማት እንቢተኞች ይሆናሉ። (ኢሳ. 53:3) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ተልእኳችን በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መጽናኛና ተስፋ አስገኝቶላቸዋል። ተራ የሆኑ ሰዎች ይህን የመሰለ አስደናቂ ውጤት ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነው? መለኮታዊ ድጋፍ ስላላቸው ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር ብርቱዎችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ” ብሏል።—1 ቆሮ. 1:26-29
2 ሐዋርያትም ሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች በአመዛኙ “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” ነበሩ። (ሥራ 4:13) ሆኖም ምሥራቹን እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ በድፍረት ተወጥተዋል፤ ይሖዋም ጥረታቸውን ባርኮላቸዋል። የተለያየ ችግርና ተቃውሞ ቢኖርም ‘የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄዷል።’ ሥራው መለኮታዊ ድጋፍ ስለነበረው ምንም ነገር ሊያስቆመው አልቻለም። (ሥራ 5:38, 39፤ 19:20) በዚህ ዘመንም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ኃይለኛ ገዥዎች ሥራውን ለማስቆም ቆርጠው ቢነሱም እንኳ ምሥራቹ እንዳይስፋፋና እንዳያድግ ማገድ አልቻሉም።—ኢሳ. 54:17
3 መመስገን ያለበት አምላክ ነው:- የአምላክ አገልጋዮች የመሆን ልዩ መብት ማግኘታችን ራሳችንን ከፍ ከፍ እንድናደርግ ምክንያት ይሆነናል? በፍጹም። ጳውሎስ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን አገልግሎት በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።” (2 ቆሮ. 4:7) ጳውሎስ አገልግሎቱን ማከናወን የቻለው አምላክ ኃይል ስለሰጠው እንደሆነ ተገንዝቧል።—ኤፌ. 6:19, 20፤ ፊልጵ. 4:13
4 እኛም ብንሆን የስብከቱ ሥራ በመከናወን ላይ ያለው ‘የአምላክ ርዳታ ስላልተለየን’ እንደሆነ እንገነዘባለን። (ሥራ 26:22) በዚህ ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ አማካኝነት ይሖዋ ብሔራትን ለማናወጥ አስደናቂ በሆነ መንገድ በእኛ እየተጠቀመ ሲሆን ይህም በቅርቡ ለሚመጣው ከባድ ጥፋት መቅድም ነው። (ሐጌ 2:7) በታላቁ መንፈሳዊ የመከር ወቅት “ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ” በመሆናችን ምንኛ ታድለናል!—1 ቆሮ. 3:6-9