የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራችሁን ቀጥሉ
1 ክርስቲያን አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በምንሰብክበት ጊዜ ሁሉም ሰው እንደማይሰማን እናውቃለን። (ማቴ. 10:14) ሆኖም አንዳንዶች የሚሰጡን መጥፎ ምላሽ ምሥራቹን ከመናገር ወደኋላ እንዲያደርገን መፍቀድ አይኖርብንም። (ምሳሌ 29:25) የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራችንን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ክርስቶስ ኢየሱስን የማወቅን ታላቅነት’ መገንዘቡ ‘ስለ ወንጌል እውነት እርግጠኛ በመሆን’ እንዲሰብክ ገፋፍቶታል። (ፊልጵ. 3:8፤ 1 ተሰ. 1:5 የ1980 ትርጉም) አንዳንዶች የሚሰብከው መልእክት የማይረባ እንዲሁም ሞኝነት እንደሆነ አድርገው ቢያዩትም፣ እርሱ ግን ምሥራቹ “ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል” እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ሮሜ 1:16) ስለዚህ ተቃውሞ ባጋጠመው ጊዜም እንኳ “ስለ ጌታ በድፍረት” መናገሩን ቀጥሏል።—ሥራ 14:1-7፤ 20:18-21, 24
3 የብርታታችን ምንጭ:- ጳውሎስ ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነት መስጠት የቻለው በራሱ ኃይል አልነበረም። ጳውሎስ ስለ ራሱና ስለ ሲላስ ሲናገር “ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን” በማለት ጽፏል። (1 ተሰ. 2:2፤ ሥራ 16:12, 37) በተጨማሪም ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ጊዜ “መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ” በማለት ሌሎች ክርስቲያኖችን ጠይቋል። (ኤፌ. 6:18-20) ጳውሎስ ከራሱ ይልቅ በይሖዋ በመታመኑ የአምላክን ቃል በድፍረት መናገሩን ሊቀጥል ችሏል።—2 ቆሮ. 4:7፤ ፊልጵ. 4:13
4 ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ወንድም በሚሠራበት ቦታ የይሖዋ ምሥክር መሆኑን መናገርና አብረውት ለሚሠሩት መመሥከር በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ስላገኘው ስለ ጉዳዩ ከጸለየ በኋላ መመሥከር ጀመረ። አንድ አብሮት የሚሠራ ሰው መጀመሪያ ላይ ጥረቱን ቢያጣጥልበትም ስለ ትንሣኤ ተስፋ ሲሰማ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ወንድም እያንዳንዱን አጋጣሚ ለመመሥከር ይጠቀምበት ጀመር። ሌላ ሥራ ከያዘም በኋላ በ14 ዓመት ውስጥ አብረውት ከሚሠሩት መካከል 34 የሚያህሉትን እንዲጠመቁ ረድቷቸዋል። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ ‘ቃሉን በፍጹም ድፍረት መናገር እንድንችል’ እንደሚያበረታን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሥራ 4:29