አቀራረብን በመለዋወጥ ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን በሚሰብክበት ወቅት እንደ አድማጮቹ አስተዳደግና አስተሳሰብ አቀራረቡን በመለዋወጥ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (1 ቆሮ. 9:19-23) እኛም እንደ እርሱ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል። በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ በሚወጡ የናሙና መግቢያዎች ላይ ቀደም ብለን ጥቂት ካሰብን በኋላ በክልላችን ከሚገኙት ሰዎች ሁኔታ ጋር እንደሚስማማ አድርገን አቀራረባችንን መለዋወጥ እንችላለን። ወደምናንኳኳው ቤት እየተጠጋን ሳለን የቤቱን ባለቤት ስሜት የሚጠቁሙ ነገሮችን ካስተዋልን አቀራረባችንን እንደሁኔታው ልንለዋውጥ እንችላለን። ይሁን እንጂ በአገልግሎታችን ላይ አቀራረባችንን ለመለዋወጥ የሚያስችለን ሌላም መንገድ አለ።
2 ሰዎች በሚሰጡት ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ ውይይት ማድረግ:- ምሥራቹን ለሰዎች ስንሰብክ አብዛኛውን ጊዜ ጥያቄ እንጠይቃለን፤ ከዚያም የቤቱ ባለቤት መልስ እስኪሰጠን እንጠብቃለን። ሰውየው የሚሰጠውን መልስ እንዴት ታየዋለህ? ለደንቡ ያህል አመስግነኸው ቀደም ሲል ወደተዘጋጀህበት መግቢያ ዘወር ትላለህ? ወይስ የቤቱ ባለቤት የሰጠህን አስተያየት ከግምት ውስጥ በማስገባት ውይይቱን ትቀጥላለህ? ሌሎች የሚሰጡትን ሐሳብ ለመስማት ከልብ የምትፈልግ ከሆነ ሰዎቹ ምን እንደሚያስቡ በትክክል ለማወቅ የሚያስችሉህን ጥያቄዎች በዘዴ መጠየቅ ትችላለህ። (ምሳሌ 20:5) በዚህ መንገድ አድማጮችህን ከሚያሳስቧቸው ነገሮች ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ያላቸውን የመንግሥቱን መልእክት ገጽታዎች አንስተህ ልታወያያቸው ትችላለህ።
3 ይህም በቅድሚያ የተዘጋጀነውን የውይይት ሐሳብ ትተን በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ፈቃደኞች መሆንን የሚጠይቅ ነው። በዜና ላይ የሰማነውን አንድ ችግር ተመርኩዘን ውይይት ከጀመርን በኋላ የቤቱ ባለቤት የአካባቢውን አሊያም የራሱን ችግር ሊነግረን ይችላል፤ የሰውየውን ስሜት ለመማረክ ያለን ልባዊ ፍላጎት እርሱን ይበልጥ ባሳሰበው ጉዳይ ላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት እንድናደርግ ይገፋፋናል።—ፊልጵ. 2:4
4 አቀራረባችንን መለዋወጥ:- የቤቱ ባለቤት ጥያቄ ሲጠይቀን በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርምር አድርገን ውይይታችንን እንድንቀጥል ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ መያዙ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ጉዳዩን አንድ በአንድ የሚያብራሩ ጽሑፎችን ማበርከት እንችላለን። ይህን ሁሉ ጥረት ማድረጋችን ሰዎች ይሖዋን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ለመርዳት ያለንን ልባዊ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።—2 ቆሮ. 2:17