ትሑት የሆኑ ሰዎች በአምላክ መንገድ እንዲሄዱ አስተምሯቸው
1. ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ ምን ማድረግን ይጨምራል?
1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ‘መንገዱን’ እንደሚከተሉ ተደርገው ተገልጸዋል። (ሥራ 9:2) እውነተኛ ክርስትና የአንድን ግለሰብ መላ ሕይወት ይነካል። (ምሳሌ 3:5, 6) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶችን ከማሳወቅ የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በይሖዋ መንገድ እንዲሄዱ ልንረዳቸው ይገባል።—መዝ. 25:8, 9
2. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የአምላክን መመሪያዎች እንዲታዘዝ ምን ሊያነሳሳው ይችላል?
2 ለይሖዋና ለኢየሱስ ፍቅር እንዲያዳብሩ እርዷቸው:- ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች አስተሳሰባቸውን፣ አመለካከታቸውን፣ ንግግራቸውንና አኗኗራቸውን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ማስማማት እጅግ ፈታኝ ይሆንባቸዋል! (ሮሜ 7:21-23፤ ኤፌ. 4:22-24) ይሁንና ትሑት የሆኑ ሰዎች ለአምላክና ለልጁ ፍቅር ካላቸው እንዲህ የመሰለውን ፈታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል። (ዮሐ. 14:15፤ 1 ዮሐ. 5:3) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር እንዲያዳብሩ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
3. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ለይሖዋና ለኢየሱስ ፍቅር እንዲያዳብሩ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ የይሖዋን ማንነት እንዲያውቁ እርዷቸው። አንድ ወንድም እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “ሰዎች የማያውቁትን ሰው ሊወዱት አይችሉም። ስለሆነም ገና ማጥናት ስንጀምር የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስተምራቸዋለሁ፤ እንዲሁም የይሖዋን ባሕርያት ጎላ አድርጌ ለመግለጽ የሚያስችሉኝን አጋጣሚዎች እፈልጋለሁ።” የኢየሱስን ምሳሌነት ጎላ አድርጎ መግለጽ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው። (ዮሐ. 1:14፤ 14:9) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የክለሳ ሣጥን በመጠቀም ተማሪው በይሖዋና በልጁ ግሩም ባሕርያት ላይ እንዲያሰላስል መርዳት ይቻላል።
4. (ሀ) ለብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለሌሎች ሰዎች መመሥከር ፈታኝ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ጥናቶቻችን በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል ሲጀምሩ ምን ዓይነት ድጋፍ ልንሰጣቸው እንችላለን?
4 ምሳሌ በመሆን አስተምሯቸው:- ሰዎችን የምናስተምርና የምንመራ በመሆኑ በአምላክ መንገድ መሄድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በድርጊታችን ልናሳያቸው ይገባል። (1 ቆሮ. 11:1) ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለማያውቁት ሰው ቀርበው እምነታቸውን ማካፈል ያልተለመደ ነገር ይሆንባቸዋል። በመሆኑም በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ለመካፈል የሚያስፈልጋቸውን ፍቅር፣ እምነትና ድፍረት ማዳበር እንዲችሉ ለመርዳት ትዕግሥተኞችና ጥበበኞች መሆን ይጠይቅብን ይሆናል። (2 ቆሮ. 4:13፤ 1 ተሰ. 2:2) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በተገቢው መንገድ እንዲሄዱ ለመምራት ያለን ልባዊ ፍላጎት በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል በሚጀምሩበት ጊዜ አብረናቸው እንድንሆን ያነሳሳናል።
5. መልካም ምሳሌ መሆናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን የአምላክን ትእዛዛት ማክበር ምን ነገሮችን እንደሚጨምር እንዲያስተውሉ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
5 ምሳሌነታችሁ በሌሎች የክርስቲያናዊ ሕይወት ዋና ዋና ገጽታዎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ መመሪያ እንዲያገኙ ሊረዳቸው ይችላል። የታመሙትን ስትጠይቁ አሊያም በጉባኤያችሁ ውስጥ ላሉት ሰዎች ሞቅ ያለ ሰላምታ ስትሰጡ ፍቅራችሁን በተግባር እንደምትገልጹ ይመለከታሉ። (ዮሐ. 15:12) የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳቱ ሥራ ላይ ስትሳተፉ ወይም ሌሎችን የሚጠቅሙ ተግባራትን ስታከናውኑ ደግሞ ሌሎችን ማገልገል እንደሚገባ እያስተማራችኋቸው ነው። (ዮሐ. 13:12-15) አኗኗራችሁ ቀላል መሆኑን ሲመለከቱ ‘አስቀድሞ መንግሥቱን መፈለግ’ ምን ማለት እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ማቴ. 6:33
6. ሌሎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ መርዳት ምን ያስገኛል?
6 የአምላክን ቃል ለሌሎች የማስተማሩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ብርቱ ጥረት ይጠይቃል። ይሁንና ትሑት የሆኑ ሰዎች ‘በእውነት ሲመላለሱ’ ማየት ምንኛ ያስደስታል!—3 ዮሐ. 4